Saturday, 26 March 2016 11:17

ሃጢያት ከተደጋገመ ፅድቅ ይመስላል

Written by 
Rate this item
(36 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ አዕምሮውን ነካ ያደርገዋል የሚባል ሰው ቀን በጠራራ ፀሐይ ወደ አንድ የስልክ እንጨት (ምሰሶ) ይሄዳል፡፡ ከዚያም እንደ ስልከኛ ምሰሶው ላይ እግሩን አጠላልፎ መውጣት ይጀምራል፡፡
ሰው ምን ሊያደርግ ነው እያለ ዙሪያውን መክበብ ጀመረ፡፡ ዙሪያውን የከበበውን ሰው ያየ መንገደኛ ሁሉ ወደ ስብስቡ ተቀላቀለ፡፡ የሁሉም ሰው ጥያቄ፤
“ምን ሊያደርግ ይሆን?” የሚል ሆነ፡፡
ሰውየው መውጣቱን ቀጠለ፡፡ ህዝቡም መሰብሰቡን ቀጠለ፡፡
ከፊሉ - “ይሄ ሰውዬ ጫፍ ከደረሰ በኋላ ሊወረወር ነው፡፡ በጊዜ እናስወርደው” አለ፡፡
ከፊሉ - “ለማንኛውም ፖሊስ ብንጠራ ይሻላል”
ሌላው - “ፖሊስ ቢመጣ ምን ሊያደርግ ይችላል፡፡ በገመድ አይጠልፈው”
ሌላው - “ግዴላችሁም አንድ ሰው ተከትሎት ይውጣ”
“ተከትሎት ወጥቶ በእርግጫ ቢለውስ ዕብድ አይደለ እንዴ?”
“እባችሁ ምንም አይሆን፤ ዝም ብለን የሚያደርገውን እንይ”
“ለምን አንጠይቀውም?”
“ምን ብለን ልንጠይቀው ነው፤ እኛ ቴሌ ኮሙኒኬሽን አደለን”
“ለምን ለሚመለከተው መስሪያ ቤት አንነግርም”
“መሥሪያ ቤቱ ንብረቴ ነው ካለ እራሱ ይምጣ እንጂ እኛ ምን ቤት ነን?”
ዕብዱ ሰው መውጣቱን ቀጠለና ጫፍ ደረሰ፡፡
ቀጠለና ከኪሱ እስክሪቢቶና ወረቀት አወጣ፡፡
ታች ያለው ሰው ግምቱን አወጋ-
“ይሄዋ ኑዛዜውን እየፃፈ ነው”
“ዕብድ ደሞ ምን ኑዛዜ ይኖረዋል?”
“ምን ይታወቃል? ሰውኮ ሊሞት ሲል የሚናገረው ነገር ይበዛል”
“እባክህ፤ መንግሥትን ሊሳደብ ይሆናል”
“መንግሥት ለመሳደብ ምሰሶ ጫፍ ላይ መውጣት አለብህ እንዴ?”
ዕብዱ ሰው ጽሑፉን ጨረሰ፡፡ በፕላስተር ምሰሶው ጫፍ ላይ ለጠፈው፡፡
እየተንሸራተተ ወደ መሬት ወረደ፡፡
ታች ከተሰበሰበው ህዝብ አንዱ፤
“ምን ብለህ ጽፈህ ነው የለጠፍከው?” አለና ጠየቀው፡፡
ዕብዱ ሰውም
“ወጥቶ ማየት ነዋ!” ብሎ ሄደ፡፡
ከህዝቡ ማህል አንደኛው፤
“ወጥተን እንየው እንጂ” አለ፡፡
ሁሉም “አንድ ሰው ይውጣ” አለ፡፡
አንድ ጐበዝ ከማህል ወደ ስልክ እንጨቱ ሄደ፡፡
ሁሉ ሰው አበረታታው፡፡ “ጐበዝ ውጣ!” “ቀጥል ጀግናው!” “ይሄ ነው ወንድ!” “ግፋ!”
ሰውየው እግሩን እየሳበ ወጣ ወጣና ጫፍ ደረሰ፡፡ ወረቀቱ ላይ የተፃፈውን አየ፡፡
ታች የለው ህዝብ “አንብብልን!” ብሎ ጮኸ፡፡
ጐበዙ ሰው ጮክ ብሎ አንበበው፤
“የምሰሶው ጫፍ እዚህ ጋ ነው!”
*   *   *
ማንኛውም ሰው ህዝብን እንዳሻው ለመንዳት ከቻለ ሀገር ላይ ችግር አለ፡፡ ያ ሰው ዕብድ ከሆነ ደግሞ የባሰ ችግር አለ፡፡ አሳሳቢ ሆነ ማለት ነው፡፡ ጥርጣሬ ላይ የወደቀ ህዝብ ይዋልላል፡፡ በመንግሥት፣ በተቋማትና በማህበራት ላይ ዕምነት አይኖረውም፡፡ ዕምነት ያጣ ህዝብ ከመምራት ዕምነት የለው የልቡን የሚናገር ተቃዋሚ ህዝብ መምራት ይሻላል ይላሉ ፀሐፍት፡፡
ኢትዮጵያን በተለየ መንገድ ለማሳደግ ህዝብ በአጭበርባሪዎች እንዳይታለል ተቆጣጥሮ ህጋዊነትን ማስከበር ያሻል፡፡ ህዝብ ሙሉ ዕምነት ሊኖረው ያስፈልጋል፡፡
ተቋማቱን አስተማማኝና እርግጠኛ ፍቃደ ልቡና ይለግሳቸው ዘንድ እንዳይመዘበር፣ እንዳይበዘበዝ ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል፡፡ ለዚህም የአስተሳሰብ ብልጽግና፣ የግንዛቤ ጥራት፣ የልብ ለልብ መግባባትና የመቻቻል ምንነት በግልጽ የገባው ሊሆን ያሻል፡፡ ከጦርነት ይልቅ ሰላምን የሚመርጥበት ምክንያት ከልምድ ከተማረው በተጨማሪ ወቅታዊ ንቃት እንዲኖረው ያስፈልጋል፡፡
ሙስናን ለመቋቋም እየሰጋን መሆን የለበትም፡፡ መታሠር ያለበት ህገ ወጥ ሰው ከሆነ የፍርድ ቤት ጉዳይ እንጂ የእከሌ ከእከሌ አማራጭ መፍጠር ወይም “አጥፊው ስለበዛ እንተወው” መፍትሔ አይሆንም፡፡ ሁሉም የየድርሻውን ማግኘቱ የፍትሕን መጉላትና መጠንከርን እንደሚያሳይ አለመዘንጋት ነው፡፡ በተለይ በህዝብ ላብ የሚቀልድ ማንም ይሁን ማን ሊተው አይገባም፡፡ በተለይም በልዩ መዋቅር ተሳስሮ ጀርባው ደንደን ያለውን መተው፣ ኮሳሳውን ማጥቃት ለፍትሕ ጐጂ ባህል ነወ፡፡ ይህን የሚያስከብሩ ተቋማት መጠንከር አለባቸው። ይህም ሲባል ተቋማቱ ግዑዝ አይደሉምና የሚመሯቸው ሰዎች በሚሠሩት አምነውና ጠንክረው ይጓዙ ማለታችን ነው፡፡
አበሻ አደባባይ ያምናል፡፡ ለአበሻ ሚዲያ መንግሥት ነው፡፡ ስለሆነም ለማናቸውም ሚዲያ ተጠቃሚ ተአማኒ ነው፡፡ ሚዲያ ላይ የቀረበ፤ አንድም መንግሥታዊ ነው፣ አንድም የታመነ ነው!  ቴሌቪዥን አይቶ፣ ሬዲዮ ሰምቶ የማያውቅ ሰው እንኳ ቢሆን በቴሌቪዥን ታየ፣ በሬዲዮ ተነገረ ካሉት የዕምነቱን ዣንጥላ ይዘረጋል፡፡ በአደባባይ የታየው፣ የተሰማው ነገር ህጋዊ ነው እንደማለት ነው! የዛሬ ዘመን የ “ቢዝነስ” ሁኔታ የደራሲ አቤ ጉበኛን “ጐብላንድ አጭበርባሪው ጦጣን” የሚያስታውሰን ነው፡፡ ለነገሩ የተመዘበረው ብር ብዛት ሲታይ እሰው እጅ ያለው ገንዘብ ኤሎሄ ያሰኛል፣ እንደ ልብ ደረቅ ቼክ መፃፍ፣ ባንክ ውስጥ በቂ ገንዘብ የለውም መባል፤ የወትሮ ነገር ሆኗል፡፡ ዲቪ የደረሰው ቀርቶ ያልደረሰው ይሄዳል በሚባልበት፣ ኮንዶምኒየም የደረሰው ቀርቶ ያልደረሰው ይኖርበታል በሚባልበት፣ ፖለቲካው ግራ ሲያጋባንና የምሁርነት ጥልቀት እያደር እንደ ውሃችን ቱቦ ሲደፈን
“እንተኛም ካላችሁ፣ እንገንደሰው
መኝታ እንደሆነ ቀርቷል ካንድ ሰው”
የሚል ዘፈን በምናቀነቅንበት ሀገር፤ ፖለቲካ ሁሉ የመሬት ጉዳይ ቢሆን ብዙ የሚያስደምም ሁኔታ አይሆንም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ለምሁራን ታዳሚዎች እንዳሉት፤ “እኛም እናንተም ችግር አለብን፡፡…ህብረተሰቡም እልከኛ ነው”…ይህንን የችግር ሶስት ማዕዘን (Triangular problem) መቼ እንደምንገላገለው ማሰብ ይጠበቅብናል፡፡
ችግሩ ባለቤት እንጂ ሁልቆ መሣፍርት የለውም፡፡ ዘርዝሮ ማየት እንጂ ችግር አለብን ብቻ መፍትሔ አይሆነንም፡፡ “የኤሊት ግሩፕ ቱጃር እየፈጠርን መጓዝ አንችልም” ያሉት ግን ሊሰመርበት የሚገባ ሀቅ ነው፡፡ “የመላዕክት ስብስብ አይደለንም” ያሉትም ሌላው ሀቅ ነው፡፡
በተደጋጋሚ የምናሰማው እሮሮ መጠነ ሰፊ ሆኗል፡፡ ሙስና አጠጠ፣ ት/ቤቶች ጥራት የላቸውም፡፡ መሠረተ - ጤና እንደምንፈልገው አልተስፋፋም፡፡ ተቋማት ይቋቋማሉ እንጂ አፈፃፀም የላቸውም፡፡ ባንኮች ንፅህናቸው አልተፈተሸም የከፍተኛ አመራሩ ችግር አለበት፡፡ ከፖለቲካ ልዩነት፤ ከሃይማኖት ልዩነት፣ ከዘር ልዩነት ነፃ ነን እንበል እንጂ ጣጣው አልለቀቀንም፡፡ “ሃጢያቱ ከተደጋጋመ ፅድቅ ይመስላል” ይሏልና፣ ቆም ብለን ተግባር ላይ እናተኩር!!
Read 12690 times