Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 25 February 2012 12:49

ከመሠረት ጋር አትጣላ ለሁልጊዜ ይሆንሃል፡፡

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ካብ ጋ አትጠጋ እላይህ ላይ ይፈርሳል!

ከዕለታት አንድ ቀን ቁራዎችና አሞራዎች የሰማይን ግዛትና የመሬትን ስፋት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለመጠቀም ይችሉ ዘንድ ለመወያየትና ስምምነት ላይ ለመድረስ ስብሰባ ይቀመጣሉ፡፡ ከሁለቱም ወገን አንጋፋ የሚባሉት ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡ በመጀመሪያ “ስብሰባው በእኩልነት እንዲመራ ከአንደኛው ወገን ሊቀመንበር፣ ከሌላኛው ወገን ደግሞ ፀሀፊ ቢደረግ በመተማመን ሰብሰባውን ለመቀጠል ይቻላል” የሚል ሃሳብ ቀረበ፡፡ በዚህ ተስማሙ፡፡ ሊቀመንበሩ ከቁራዎች፣ ፀሐፊ ከአሞራዎች ወገን እንዲሆን በተወሰነው መሰረት ምርጫ ተካሄደ፡፡ ሊቀመንበሩ ቁራ ስብሰባውን ለማስጀመር፤

“በስብሰባችን ላይ ብዙ ውዝግብና ንትርክ እንዳይኖር አስቀድመን ለሁላችንም የጋራ የሆነ አጀንዳ እንምረጥ” አለ፡፡

አንድ ቁራ ተነስቶ፤

“ሰማይንም መሬትንም እኩል የምንካፈልበት ዘዴ እንፍጠር፡፡ ለምሳሌ ሰሜኑን ለአሞራዎች ከሰጠን ደቡብን ለቁራዎች እንስጥ፡፡ እንደዚሁ ምሥራቁን ለቁራዎች ከሰጠን ምዕራቡን ለአሞራዎች እናድርግ” አለ፡፡

አንድ አሞራ ተነሰቶ ደግሞ፤

“ይሄ አያስኬደንም፡፡ ምክንያቱም የትኛው የሰማይ ክፍል ደመናማ እንደሆነ አናውቅም፡፡ እንደዚሁም ደግሞ የትኛው መሬት ለም፣ የትኛው ጠፍ እንደሆነም አልተጠናም፡፡ ስለዚህ ያጣላናል” አለ፡፡

ብዙ ሀሳብ ከቀረበ በኋላ በመጨረሻ አንድ አንጋፋ ቁራ ተነሱና፤

“ወገኖቼ፤ የምትሰጡት ሀሳብ ለሁላችንም ጥቅም እሰከሆነ ድረስ መወያየቱ አይከፋም፡፡ ነገር ግን ዋናውን የችግራችንን ቁልፍ ነገር ሳናነሳ ስለሰማይና መሬት ብናወጋ ብዙም የሚፈይደን ነገር አይኖርም፡፡ ስለዚህ እኔ የቁራዎች ወገን ወክዬ ቁልፍ ችግራችንን ላነሳ እፈልጋለሁ፡፡ ይኸውም አበው በተረትና ምሳሌ ስለሚጠቅሱት ጉዳይ ነው፡፡ “ጩኸትን ለቁራ፣ መብልን ለአሞራ” ስለሚለው፡፡ ይህ ተረት እንዲስተካከል፣ ከተፈለገ እኩል መጮህ አለብን፡፡ እኩል መብላት አለብን፡፡ አለበለዛ መቼም ተስማምተን በእኩልነት ልንኖር አንችልም” አሉ፡፡

የእኒህን አዛውንት ቁራ ሀሳብ ሁሉም ደገፉና “እኩል እንጩህ! እኩል እንብላ!” የሚል መፈክር ወጣ፡፡ በየቦታው ተፃፈና ተለጠፈ፡፡ ይህ በሆነ በጥቂት ቀናት ውስጥ አንድ የቆሰለ ቀበሮ ጫካ ውስጥ ወድቆ ተገኘ፡፡ ቁራዎች እየጮሁ ተጣሩ፡፡ አሞራዎችም ጩኸታቸውን አስተጋቡ፡፡ ሁሉም ተሰበሰቡ፡፡ ቀበሮው ወደ ወደቀበት ደረሱ፡፡

“እንግዲህ በስምምነታችን መሠረት ይሄንን ቁራ እኩል እኩል መካፈል አለብን” አሉ ቁራዎች፡፡

“በትክክል ይከፈል፡፡ ጥሩ ሃሳብ ነው” አሉ አሞራዎች፡፡

ቁራዎችም፤

“እንግዲያው እኛ የላይኛውን ግማሽ እንውሰድ እናንተ የታችኛውን ግማሸ ውሰዱ” አሉ፡፡

አሞራዎችም፤

“ጥሩ ሀሳብ ነው እኛ የታችኛውን ወገን እንወስዳለን” አሉ፡፡

ይሄኔ ቀበሮው ከት ብሎ ሳቀና፤

“ይገርማል! እኔኮ ሁልጊዜ በአፈጣጠር ታላቆቹ አሞራዎች ይመስሉኝ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት የእኔን የላይኛውን ክፍል ማለትም አንጐሌንና ሌሎች ለስላሳና ጣፋጭ ነገሮች ያሉበትን ወገን፤ መብላት ያለባቸው አሞራዎች ናቸው እል ነበር፡፡ አሁን ግን ሲገባኝ ለካ ቁራዎች ይበልጣሉ፡፡ እነሱ አንጐሌን ሊበሉ ነው!” አለ፡፡

ይሄን ሲሰሙ አሞራዎች፤

“አሃ! ቀበሮ ውነቱን ነው የላይኛው ክፍል ለእኛ ነው የሚገባን” አሉ፡፡

ቁራዎችም፤

“የለም! አንዴ ተስማምተናል የላይኛው ወገን የእኛ ነው” አሉ፡፡ ግብ ግብ ተፈጠረ፡፡ መደባደብ ጀመሩ፡፡ ከሁለቱም ወገን በርካቶች መሬት ላይ ተዘረሩ፡፡ የቀሩት በየአቅጣጫው ክንፌ-አውጪኝ እያሉ በረሩ፡፡ አጅሬ ቀበሮ ሆዬም መሬት ላይ የተዘረሩትን አሞራዎችና ቁራዎች እየበላ መሰንበቻውን አገግሞ ወደ ጫካው ሄደ!

***

የትላልቆችና የኃያላን ፀብ ጥቅሙ ለደካሞች ነው፡፡ ሆኖም ደካሞቹ ብልህ ሲሆኑ ነው፡፡ የኃያላኑን ደካማ ጐን ሲያውቁ ነው፡፡ የሚያውቁትን ደካማ ጐንም በዘዴ ለመናገር ሲችሉ ነው፡፡ ገዢዎች ቦታ ለመከፋፈል ግማሹን ለአንተ ግማሹን ለኔ ማለታቸው ያለ ነገር ነው፡፡ በሙስናም ሆነ በጉልበት የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር ላይ ታች ማለታቸው አይቀሬ ነው፡፡ ይሄንን ማወቅና ማስተዋል ብልህነት ነው፡፡ አንዱ እየጮኸ፣ ሌላው ከሚበላበት ሥርዓት ይሰውረን፡፡ ጉልበተኛ ልቡ እብሪት አያጣም፡፡ ተዓብዮ ያበዛል፡፡ ከሱ ጡንቻ ሌላ ኃይል ያለ አይመስለውም፡፡ በዚህ ምክንያት ጉልበቱን ከማሳየትም ባሻገር አዋቂ እኔ ብቻ ነኝ ይላል፡፡ ከሱ ሀዲድ ሌላ ሀዲድ የሌለ ስለሚመስለውም ሌላ ባቡር አለ ብሎ አያምንም፤ አይቀበልም፡፡ ደራሲ ከበደ ሚካኤል:-

“ኩራትና ትዕቢት የሞሉት አናት

ሠይፍና ጐራዴ የመቱት አንገት

አይገላገሉም እንዲህ በቀላሉ

እመሬት ላይ ወድቀው ሳይንከባለሉ”

ይሉናል፡፡ መልካም ማጠቃለያና መጠቅለያ ይሆነናል፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል መባሉ ለዚህ ነው፡፡

ስለ ዲሞክራሲ እየለፈፍን በወገናዊነት ከታጠርን፣ ስለፍትህ እየደሰኮርን ፍርድ ካዛባን፣ ስለማረሚያ ቤት መልካምነት እያወጋን ብልሹ ባህሪን መከላከል ካልቻልን፣ ስለመልካም አስተዳደር እየፎከርን አመራራችን የተወላገደ ከሆነ፣ በየሴሚናሩና ኮንፈረንሱ ደግ ደግ ነገር እያወጋን ቢሮ ስንገባ የሚጠፋብን ከሆነ… ቢያንስ ተዓማኒነትን እናጣለን፤ ሲከፋ ደግሞ ለክፉ እንዳረጋለን! ካለፈው ተምረናል እያልን እሱኑ እየደገምን ከተገኘን የሥርዓት ለውጥ መኖሩም ደብዛው ይጠፋል፡፡ የኢኮኖሚ ችግራችን ላይ ስናተኩር ፖለቲካው መላው ከጠፋ፣ ፖለቲካውን እያስተካከልን ነን እያልን ኢኮኖሚው ዶግ-አመድ ከሆነ ቅጥ-አምባሩ የጠፋ የዲሞክራሲ ውጣ ውረድ ውስጥ እንደምንወድቅና ከድጡ ወደ ማጡ እንደምንገባ ማስተዋል ይኖርብናል!

ሰውዬው - “እዚህ አገር በሁለት ቢላዋ የሚበሉ ሰዎች አሉኮ!” አለው፡፡

ሌላኛው ሰውዬም - “የሚበላ ተገኝቶ?” አለ አሉ፡፡ ፌዛችን መራራ፣ ህይወታችን መራራ ሆኗል፡፡ ደግ ቀን ያምጣልን!

አንድም የህዝብን ድጋፍ እንዳናጣ ለህዝብ የሚበጅ ተግባር ያስፈልገናል፡፡ አንድም ደግሞ ከሃያላን የማመጣብንን ጫና ለመገደብ የምንችለው ውስጣዊ አሰራራችን ግልፅና የፀዳ፤ መንፈሳችን ቀና ሲሆን ነው፡፡ ይህ ካለን ደግሞ “ከመሰረት ጋር አትጣላ ለሁልጊዜ ይሆንሃል፡፡ ካብ ጋ አትጠጋ እላይህ ላይ ይፈርሳል” የሚለው ተረት በደንብ ይገባናል!!

 

 

Read 3535 times Last modified on Saturday, 25 February 2012 12:51