Saturday, 19 March 2016 11:30

ራዕይ ታየኝ ከሚሉ “ሃሰተኛ ነቢዮች” ይጠብቃችሁ!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(20 votes)

* አንዲት ሴት በፓስተሯ ደረሰብኝ ያለችውን ተናግራለች
* የናይጄሪያው “ፓስተር” ሴቶችን ጡት መያዣ አታድርጉ ይላል
* አየር ባየር ሃይማኖት ሳይጀመር አይቀርም - ጠንቀቅ ነው!

         ናይጄሪያ ውስጥ ነው፡፡ ፓስተሩ የናይጄሪያ ዳያስፖራ ነው፡፡ ሴቶችን ብቻ ነው እፈውሳለሁ የሚለው፡፡ ወደሱ ቸርች የሚሄዱትም ሴቶች ብቻ ናቸው ይላል -ከድረ ገጽ የተገኘው መረጃ፡፡ ደዌው ደግሞ ከፍቅርና ከትዳር ጋር የተገናኘ መሆን አለበት፡፡ የትዳር አጋር አልዋጣልን አለ፣የፍቅር ጓደኛ አይበረክትልንም----ወዘተ ችግሮች ያሉባቸው ወደኔ ይምጡ ይላል፤ ናይጄሪያው ፓስተር። ወደሱ ቸርች ፈውስ ፍለጋ የሚመጡ ሴቶች፣ ጡት መያዣ እንዳያደርጉ ይመክራሉ፡፡ ያለምክንያት አይደለም። ለምሳሌ አንዲት ሴት፣ ከፍቅረኛዋ ጋር ጥሩ ኖራ ኖራ፣ የትዳር ሃሳብ ስታቀርብለት ፊት ቢነሳት ናይጄሪያዊው ፓስተር፣ “z spirit of rejection” ነው ይላል፡፡ (ወግድ የመባል መንፈስ እንደማለት!)
ያ አሉታዊ መንፈስ የሚገኘውም በጡት ላይ ነው የሚለው ፓስተሩ፤ “እኔ መንፈሱን ከጡቷ ውስጥ መጥጬ በማውጣት፣ ከደዌው ነጻ አወጣታለሁ” ባይ ነው፡፡ በእርግጥም በየጊዜው እንስቶች ተታለውም ሆነ ሆን ብለው ጡታቸውን ለሰውየው በማቅረብ ከደዌያቸው ለመፈወስ ሞክረዋል፡፡ (መፈወሳቸው ባይረጋገጥም!)
ከዕለታት አንድ ቀን ግን አንዲት ናይጄሪያዊ ዲጄ ተጫወተችበት፡፡ በናይጄሪያ አንዱ የሬዲዮ ጣቢያ ውስጥ ነው የምትሰራው፡፡ ፓስተሩ ጋ ትደውልና ለትዳር ሳልመው የኖርኩት ፍቅረኛዬ ፊት ነሳኝ ትለዋለች። እሱም ሙያዊ ማብራሪያውን በዝርዝር ሰጣት፡፡ በመካያውም፣ የጡት መያዣ ሳታደርግ ወደ ቸርቹ ብቅ እንድትል ያዛታል፡፡ (በጡት ተለክፎ የለ!)
ነገርየው የገባት ዲጄም፡- “እኔ የምልህ፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የትኛው ክፍል ላይ ነው የሴትን ደዌ ለመፈወስ ጡቷን ጥባ የሚለው?” ስትል ታፋጥጠዋለች፡፡ የሌባ ዓይነ ደረቅ እንዲሉ፣ “የመጽሐፍ ቅዱስን ነገር አሁን አናንሳው፤ አንቺ ብቻ ዝም ብለሽ ነይ” ሲል ተለሳልሶ ይመልስላታል። እሷም በሹፈት ቅላጼ “ስምህን ማን ነበር ያልከኝ?” አለችው፡፡ ሰውየውም እውነተኛ ስሙን ከመንገር ይልቅ፤ “A man of God በይኝ” ይላታል፡፡ (አለማፈሩ?!) እሷም፤ “ለማንኛውም እስካሁን የተናገርከው በሬዲዮ ቀጥታ ስርጭት (ላይቭ) ሲተላለፍ ነበር” ብላ ስልኩን ጠረቀመችው፡፡ (Mission accomplished!)  ሰሞኑን አንድ የልብ ወዳጄ፤ በንዴት እየተንጨረጨረ እንዳነበው የሰጠኝ መንፈሳዊ መጽሄት “ቤቴል” ይሰኛል። በኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስትያን ቤቴል ወንጌል ክፍል የሚዘጋጅ ነው፡፡ ወዳጄ የተንጨረጨረው በመጽሄቱ ሳይሆን ውስጡ በታተመ አንድ ቃለ-ምልልስ ነበር። አንዲት እንግዳ የተባለች የ4 ልጆች እናት፤መንፈሳዊ አባቷ ነኝ በሚል “ፓስተር”፤ (መጽሄቱ ሐሰተኛ ነቢያት ይላቸዋል!) የደረሰባትን ከፍተኛ የገንዘብና እምነት መጭበርበር ትናገራለች - በቃለ ምልልሱ፡፡ (ስምንተኛው ሺ ገባ እንዴ?) በነገራችን ላይ መጽሄቱ በሐሰተኛ ነቢያት ዙሪያ ሰፊ ዘገባና ሃይማኖታዊ ትንተናም አቅርቧል፡፡ ይሄ ደግሞ የወደፊት ተጎጂዎችን ቁጥር ለመቀነስና ግንዛቤ ለመፍጠር እንዲሁም በሃይማኖት ስም የማጭበርበር ወንጀል የሚፈጽሙትን ሃሰተኛ ነቢያት ለማጋለጥ በእጅጉ ይጠቅማል፡፡ (ዝምታው ይሰበር!)
እንግዳ የተባለችው ተጎጂ የሰጠችውን አሳዛኝ ቃለ-ምልልስ አንብቤ ከጨረስኩ በኋላ ዓይኔ ያረፈው ፖሊስ ክስ በመሰረተባቸው መምህር ግርማ ወንድሙ ምስልና ዘገባ ላይ ነው፡፡ ይሄን ዘገባ ለየት የሚያደርገው ወደ 800ሺ ብር ገደማ ተጭበርብሬያለሁ ብለው ለፖሊስ ያመለከቱት የ73 ዓመቱ አቶ በላይ ከበደ፤ የሰጡት ቃለምልልስ መሆኑ ነው፡፡ (From the horse’s mouth - ከባለቤቱ አፍ እንዲሉ!)
እናላችሁ---- የድራማና የህልም ድብልቅ የሚመስለውን የአዛውንቱን ቃለ-ምልልስ አንብቤ ስጨርስ፣አንድ ነገር ተገነዘብኩ፡፡ እንግዳ የተባለችው ሴት፣ በፓስተሩ ተፈጸመብኝ ያለችው ዝርፊያና አዛውንቱ አቶ በላይ ከበደ በተጠርጣሪው መምህር ግርማ ደረሰብኝ ያሉት የማጭበርበር ወንጀል በእጅጉ መቀራረቡ አስደነቀኝ፡፡  እስቲ ጥቂቶቹን እንመልከት፡፡ አቶ በላይ መኖሪያ ቤታቸውን ሸጠው በፍጥነት ከአካባቢው እንዲወጡ ግፊትና ጫና ተደረገብኝ የሚሉት በመምህር ግርማ ነው፡፡ (ቤቱን ካለቀቅህ ትሞታለህ ተብለው) እንግዳ በበኩሏ፤ ከቤተሰቦቿ በውርስ የተሰጣትንና መተዳደሪያዋ የሆነውን ሆቴሏን እንድትሸጠው ፓስተሩ ግፊት እንዳደረገባት ተናግራለች፡፡ (ካልሸጥሽው መጥፊያሽ ነው በሚል ማስፈራሪያ!) ከዚያስ? አቶ በላይ ከቤታቸው ሽያጭ ያገኙትን 800ሺ ብር፣ መምህር ግርማ ልጸልይበት ብለው እንደወሰዱባቸው ለፖሊስ መንገራቸው ይታወቃል፡፡ እንግዳም ሆቴሏ ተሸጦ የተገኘው 500ሺ ብር ገደማ በፓስተሩ እጅ እንደቀረ ነው የምታስረዳው፡፡
በነገራችን ላይ እንግዳም ደረሰብኝ ያለችውን መጭበርበር ለፖሊስ አመልክታለች - ተመሳሳይ በደል በፓስተሩ ተፈጽሞብናል ከሚሉ ከአረብ አገር የመጡ ጥቂት ሴቶች ጋር በመሆን፡፡
የሃሰተኛ ትንቢትና ነቢይ ሰለባ የሆነችው እንግዳ፤ ከ4 ልጆቿ አባትና ከትዳር አጋሯ ጋር ያለያያት “ትንቢት” እንደነበር በቁጭት ትናገራለች፡፡ በውርስ ያገኘችውን ታዋቂውን የአሰበ ተፈሪ ሆቴል ያጣችውም በሃሰት ትንቢት መሆኑን ገልጻለች፡፡ “ቤቴል” መጽሄት ከእንግዳ ጋር ካደረገው ሰፊ ቃለምልልስ ውስጥ ለማሳያ ያህል ጥቂቶቹን መርጬ አቅርቤላችኋለሁ፡፡ በተረፈ ግን የመጽሄቱን የየካቲት 2008 ዕትም ፈልጋችሁ ብታነቡት የበለጠ መረጃ ታገኛላችሁ ብዬ አምናለሁ፡፡ ወደ ቃለ ምልልሱ፡-
ቤቴል፡- አሁን ላለሽ ሕይወት ምክንያት ከሆነሽ አገልጋይ “ፓስተር” አለምሰገድ ዋጅና ጋር ያለሽ እውቅና እንዴት ተጀመረ?
እንግዳ፡- አዲስ አበባ ቦሌ አማኑኤል ተሃድሶ ቤተ ክርስቲያን ከማውቃት ዘማሪት ፀሐይ ዘለቀ ጋር ፕሮግራም ተካፍለን ስንወጣ፣ በቤ/ክ በር ላይ በራሪ ወረቀት ይታደል ነበር፡፡ በራሪ ወረቀቱ የኮንፈረንስ ነበር፡፡ ፀሐይ ዘለቀ ወረቀቱን ካየች በኋላ ፕሮግራሙን ያዘጋጀውን ፓስተር አለምሰገድን እንደምታውቀውና እግዚአብሔር የሚጠቀምበት ሰው እንደሆነ ነግራኝ አብረንም እንሄዳለን አለችኝ፡፡ እሺ ብያት በፕሮግራሙ ወቅት ተያይዘን ሄድን። ፕሮግራሙ በኢትዮጵያ ሆቴል ውስጥ ነበር የተደረገው፡፡ --- በፕሮግራሙ መጨረሻ ፀሐይ ዘለቀ አስተዋወቀችን፡፡ በውርስ ንብረት ምክንያት ችግር ስላለባት ፀልይላት አለችው፡፡ እሺ በማለት ስልክ ቁጥሬን ተቀበለኝ፡፡
ቤቴል፡- እውቅናችሁ እንዲህ ተጀመረ፡፡ ታዲያ ደወለልሽ?
እንግዳ፡- እኔ ወደ ሀገሬ ከተመለስኩ በኋላ በ3ኛው ቀን ረቡዕ ሌሊቱ 5 ሰዓት ላይ ስልኬ ጮኸ፡፡ የደወለው ዓለምሰገድ ዋጀና ነበር፡፡ መልእክት ይነግረኝ ጀመር። “የሚገርምሽ አሁን ስለአንቺ እየፀለይኩ ነበር። እግዚአብሔር የተናገረኝ ነገር አለ፤ጌታ በአንቺ ላይ ታላቅ ዓላማ አለው፡፡” አለኝ፤ አሜን አልኩ፡፡ በመቀጠል ያለሁበት፣ ያለፍኩበትን ሁኔታ በሙሉ ያለ አንዳች ስህተት ነገረኝ፡፡ “ከልጆችሽ መካከል በጣም የምትወጃት ልቧን የሚያማት ልጅ አለሽ?” አለኝ “አዎን” አልኩት። ፍፁም የእግዚአብሔር ሰው ነው ብዬ አመንኩት፡፡ ከዚያ በመቀጠል እግዚአብሔር የሚለኝን ለማድረግ ዝግጁ መሆኔን ጠይቆ፣ ፈቃደኝነቴን ካረጋገጠ በኋላ ወደ ምኖርበት አለም ጤና እንደሚመጣ ነገረኝ። “ሀገሩን ታውቀዋለህ ወይ?” ብዬ ጠየኩት “ችግር የለም፤ የሚያውቀው ሰው ስላለ እመጣለሁ፤ጌታ ሂደህ ቤቱን ርገጠው ብሎኛል” አለኝ፡፡ እንዴት እንደሚመጣ ላስረዳው ስል እንደሚያውቀው ነገሮኝ ስልኩን ዘጋው፡፡
ቤቴል፡- ታዲያ እንዳለው መጣ?
እንግዳ፡- በቀጣዩ ቀን ሀሙስ ከሌሎች 2 አብረውት ከሚያገለግሉ ሰዎች ጋር መጣ፡፡ ከአክስቴ ልጅ ጋር ምግብ አዘጋጅቼ ተቀበልኩት፡፡ ከተመገቡ በኋላ “ወደ ሆቴሉ መሄድ መርገጥ አለብኝ” አለኝ፡፡ ሆቴሉ እንደተከራየ ነገርኩት፡፡ ይሁን ብሎ ተያይዘን ሄድን። ሆቴሉን በሙሉ ተዘዋውሮ ከተመለከተ በኋላ ተከራይታ ለምትሰራበት ሴት፤ “ይህ ሆቴል እግዚአብሔር ለክብሩ የሚፈልገው ሆቴል ስለሆነ ትለቂያለሽ” አላት፡፡ የተከራየችውም ሴት፤ “በገንዘቤ ተከራይቼ እስከሆነ ድረስ የሚያስለቅቀኝን አያለሁ” አለችው፡፡ በቃላት አንድ አንድ ተባባሉ፣ ሊጣሉም ሲሉ ይዘነው ወጣን፡፡ ከዚያም “እኔ በ24 ሰዓት ውስጥ ከእግዚአብሄር ጋር እነጋገራለሁ፤ ምን ማድረግ እንዳለብሽ እነግርሻለሁ፤ ይህቺ ተከራይሽ መንፈስ ያለባት ሴት ናት፤ በአስቸኳይ መልቀቅ አለባት” አለኝ። ግራ ገባኝ፣ በመቀጠል “ሆቴል ውስጥ የተቀበረ ነገር አለ፤ መድኃኒት አሰርታብሻለች” አለኝ፡፡ እሺ ከማለት ውጪ ሌላ አማራጭ አልነበረኝም፡፡ በቀጣዩ አርብ ቀን ሌሊት ደውሎ፤ “እግዚአብሔር ቤቱ ከእጅሽ ይውጣ ብሏል። በምንም ብር ይሁን ከእጅሽ ይውጣ፤ አለበለዚያ መንፈሱ ያቺን በሽተኛ ልጅሽን ሊገድላት ነው፡፡” አለኝ፤ እኔም “ልጄ እኮ ዝም ብላ ልቤን ትላለች እንጂ በሽተኛ አይደለችም” አልኩት፡፡ መልሴን ሳይሰማኝ “ብቻ ልጅሽን ሳይበቀል ቤቱን ቶሎ ከእጅሽ አውጪ” አለኝና ፀለየልኝ። የሞባይል ስልክ ካርድ ሞላልኝ፡፡ ምንድነው? ስለው ይህ ካርድ ከማለቁ በፊት በስልክሽ መልካም መልካም ዜና ትሰሚያለሽ አለኝ፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ ደውሎ ሆቴሉ መሸጥ አለበት የሚል ውሳኔ አስተላለፈ፡፡ “እሺ ና እና እኔም የማውቀው ሰው፣ ከዚህ በፊት መኖሪያ ቤት የሸጥኩለት አለ፤ እርሱን እናናግረዋለን” አልኩት፡፡ ሰውየውም መጣ፤ ሆቴሉን እንዲገዛ አናገረው፡፡ ሰውየው፤ ቤተሰቦቿ ከሌሉበት አልገባበትም አለ፡፡
ቤቴል፡- እዚህ ጋ እናቋርጥሽ፤ ቆይ ከአንቺ ቤተሰብ ማንም የለም?
እንግዳ፡- አባትና እናቴ ሞተዋል፤ እህቴ አግብታ ሌላ ቦታ እየኖረች ነው፡፡ የሆቴሉ ወራሽ ደግሞ እኔ ነኝ፡፡
ቤቴል፡- የተባለው ሰው ሆቴሉን ገዛሽ?
እንግዳ፡- ሰውየው ቤተሰቤን የሚያውቅ ሰው ነው፤ ስለዚህ መጀመሪያ ከእህትሽ ጋር ተነጋገሪ ተስማሚ፤ ከገዛሁሽ በኋላ ሌላ ጭቅጭቅ እንዲመጣብኝ አልፈልግም አለ፡፡ ስለዚህ ከእርሱ ጋር መጨረስ ባለመቻሉ፣ ፓስተሩ፤“እኔ ራሴ ገዥ አመጣለሁ” ብሎ መቂ የሚኖር ሰው ጋር ተነጋግሮ አገናኘኝ፤ “የመሸጫውን ዋጋ 550 ሺህ ብር ተነጋገሬአለሁ” አለኝ፡፡ እኔ ደግሞ “በሚሊዮን ብር የሚሸጥ ቤት እንዴት በዚህ ዋጋ?” አልኩት። “ነግሬሻለሁ ይሄ ቤት መጥፊያሽ ከመሆኑ በፊት ባልኩት ዋጋ ሽጪ” አለኝ፡፡ ለመከራከር ሞከርኩ ግን አልሆነም። በመጨረሻ በተባለው ተስማማሁና ከገዥው ጋር ለመፈራረም ወደ ማዘጋጃ ቤት ስንሄድ፣ ከንቲባው “ይህን የሚያህል ትልቅ ቤት በዚህ ዋጋ መሸጥ የለበትም” ብሎ ተከራከረ፡፡ ፓስተሩ፤ “ምን አገባህ? እሷ ተስማምታለች፤ አይመለከትህም እኔ መንፈሳዊ አባቷ ነኝ፤ አንተ ባሏ ነህ እንዴ? አያገባህም” ሲል ተናገረው፡፡ ከብዙ ሰዓት ጭቅጭቅ በኋላ እሺ ቤተሰብ ይጠራ ተባለና እህቴ ጋር ሲደወል ስልኳ ዝግ ሆነ፡፡ አጎቴ ጋር ደግሞ ሲደወል የሚያሳርሰው እርሻ ስለነበር ወደዚያ ሄዷል ተባ። ሁሉ ነገር ተገጣጠመለት፤ ዛሬ ማለቅ አለበት ብሎ አጣደፈኝ። “ነገ ዱባይ ስለምሄድ መቆየት አልችልም” ብሎ የውሸት ሰበብ አመጣ፤ ከዚያ ከገዢው ጋር እንድፈርምለት ተደረገ፡፡ በመጨረሻ ሽያጩን በ370 ሺህ ብር አድርገው አመጡት፡፡ “ለምን ከተባለው ደግሞ ተቀነሰ?” ስለው “አንቺ የምትባረኪው በዚህ ብር ነው፡፡
ከዚህ በላይ ከሆነ የእርግማን ገንዘብ ስለሆነ መጥፊያዋ ነው ብሎኛል እግዚአብሔር፡፡” አለኝ። ይሄ ሁሉ ሲሆን ብር ስላልተቀበልኩ ብሬን ጠየኩት፤ ገዥው ሰው “ከፓስተርሽ ከአለምሰገድ ጋር ተነጋግረናል፤ መኪና እገዛላታለሁ ብሎ ለእርሱ ሰጥቻለሁ” አለኝ። አሃ! መኪናው 500,000 ብር የሚያወጣ ነው ብዬ ስጠይቀው፣ አይ 350,000 ብር ነው አለኝ፡፡ ቀሪውስ ብር ስለው፣“ስለ እሱ ከፓስተርሽ ጋር ተነጋገሪ” አለኝ። በዚህ መሃል ፓስተር አለምሰገድ በማላውቀው ሁኔታ አንድ ቆማ በነበረችው ዶልፊን መኪና ተሳፍሮ ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ፣ ስልክ ስደውልለት ስልኩ አይሰራም፤ ሰማይ ምድር ዞረብኝ፤ የምይዘው የምጨብጠው ጠፋኝ፡፡ --------

Read 9414 times