Saturday, 19 March 2016 11:04

መብላት ያስለመድከው ሲያይህ ያዛጋል

Written by 
Rate this item
(17 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን የዱር አራዊት ንጉሥ የሆነው አያ አንበሶ በጉልበት፣ በማን አለብኝና በገዢነት ስሜቱ መዋጡን ትቶ፣ ከሁሉም አራዊት ጋር አብሮ መኖርና ተጋግዞ በጋራ ፍሬ ማፍራትን በመፈለጉ፣ የዱሮው አያ አንበሶ መሆኑን ለመተው ማሰቡን ይፋ ለማድረግ አሻ፡፡
ስለሆነም ዋና መርሆው፡-
“ከሌሎች የዱር እንስሳት ጋር ተባብሮ መኖር ነው!” አለ
ይህንኑ በተግባር ለመተርጐም አያ ጅቦ ጋ ሄደና፤
“አያ ጅቦ የወትሮ ጠብና የገዢና ተገዢ ነገር ያብቃና በጋራ ተሳስበን እንኑር ብዬ አስቤያለሁ”፤
“መልካም ሀሳብ ነው፡፡ ደስ ብሎኛል” አለ፡፡
አያ አንበሶ ቀጥሎ ወደ አያ ነብሮ ሄደና፤
“አያ ነብሮ፤ የወትሮ ጠብና የገዢና ተገዢ ነገር ያብቃና በጋራ ተሳስበን የምንኖርበት ሥርዓት እንፍጠር” አለው፡፡
አያ ነብሮ፤
“እጅግ ቀና ሃሳብ ነው - ይህን የተቀደሰ ሃሳብ ማን እምቢ ይላል?” አለና መለሰ፡፡
ቀጥሎ ተኩላ ጋ ሄደ፡፡
ተባብሮ አብሮ የመሥራትን ሥርዓት ጉዳይ አነሳበት፡፡
ተኩላ፤
“ይሄማ እሰየው ነው፡፡ ምን ሆኜ እቃወመዋለሁ?” አለ፡፡
የሦስቱም መልስ እጅግ ያስደስተዋል፡፡
“እንግዲያው የተስማማንበትን በተግባር ማየት አለብን” አለ ተኩላ፡፡
ተስማሙና ታላቁ አደን ላይ ተሰማሩ፡፡
ሄደው ሄደው አርፍደው አንዳች የሚያህል ጐሽ ፊታቸው ድቅን አለ፤ ተረባረቡና ጐሹን መሬት ላይ ጣሉት፡፡ ከዚያ ተካፍለው ድርሻ ድርሻቸውን መውሰድ ነበረባቸው፡፡ አሁን ጉድ ፈላ
አንበሳ ዋና ደልዳይና አከፋፋይ ሆነ፡፡ አራቱም የምግብ አጠቃቀም ዘዬአቸው የተለያየ ነው። አብረው መብላት የማይታሰብ ነው፡፡
አያ አንበሶ፤ “መብላት አለብን፤ ተካፍለን እንመገብ” አለ፡፡
ሌሎቹ ልባቸው ባያምንበትም “በጄ” አሉ፡፡ አንበሳ የጐሹን ሥጋ አራት ላይ ከፈለው፡፡
የመጀመሪያውን የቅርጫ መደብ፤
“ይሄ መደብ የእኔ ነው፡፡ የአራዊት ንጉሥ በመሆኔ የማገኘው ድርሻዬ ነው”
ቀጠለና፤ “ሁለተኛወን መደብ የሚያገኘው
“አደኑ ላይ ትልቅ ሚና የተጫወተው ነው ያ ደግሞ እኔ ራሴ ነኝ፡፡”
“ሦስተኛው መደብ፤ እኔ ራሴ በአንበሳነቴ ልክ እንደናንተው ድርሻዬ ነው” አለ፡፡
አያ አንበሶ፤ አራተኛውን ቅርጫ ወደ ወለሉ ገፋና
“ይሄን የቅርጫ መደብ የሚነካ ወዮለት!” አለ፡፡
*   *   *
“የባህርይ ነገር አይለወጥም፡፡ በበጐ ፈቃድ አይሻርም፡፡ ጅብ ማንከሱን፣ አዞ ማልቀሱን፣ እባብ መላሱን በፍላጐታቸው ሊተውት አይቻላቸውም” ይባላል፡፡
የአንበሳውን ድርሻ አንበሳው ብቻውን እንደሚወስድ በሚታወቅበት አካባቢ፣ ዲሞክራሲያዊነት በዋዛ የሚገኝ ነገር አይሆንም፡፡ “ሞኝ ከልጅህ እኩል አርገኝ ይላል” እንደሚለው ተረት ዓይነት መሆኑ ነው፡፡
በራስ ወዳድነት ላይ ብቃት - አልባነት ሲጨመር ትልቅ እርግማን ነው፡፡ ራዕይ ይደበዝዛል። የታቀደው ነገር ሁሉ የአፈፃፀም፣ ሰለባ ይሆናል፡፡ የበለጠ አሰቃቂው ነገር ደግሞ ስህተትን መድገም እንጂ ከስህተት መማር አይኖርም፡፡ ደጋግመን ስለአንድ ችግር የምናወራው ለዚህ ነው፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ሙስና፣ ኢ - ፍትኃዊነት፣ የደላሎች ስርዓት፣ ኔትዎርክ፣ የመልካም አስተዳደር ጉድለት፣ የአቋም መሸርሸር፣ የአፈፃፀም ችግር፣ የተቋማት አለመጠንከር፣ ብቁ አመራር አለመኖር ወዘተ … እነዚህን ሐረጋት ስንቴ ደገምናቸው? ወይ ማረም አሊያም በተሸናፊነት ከጨዋታው መውጣታችንን ማመን ነው፡፡ ለዚህም ቢሆን ውስጠ - ማንነታችንን መፈተሸ ይበጃል፡፡ ራሳችንን እንጠይቅ፡፡ አብሮ መብላት ለማይችሉ ሰዎች፤ የትብብር ባህል ምን ያህል ዕሙናዊ ነው? ምን ያህልስ ረዥም መንገድ አብሮ መጓዝ ይቻላል? ራሳችንን በራሳችን እንድንሸረሽር የሚያደርጉ ኃይሎች ይኖሩ ይሆን? ለምንድን ነው ጉዟችን ውሃ ወቀጣ የሚመስለው? የመብራት … የውሃ ችግር ነጋ ጠባ የምናነሳው ለምንድነው? የህዝብ ብዛታችን በተለይ በዋና ከተሞች ጭንቅንቅ ደረጃ መድረሱን እያጤንን ነውን? ጥያቄዎች እየበዙ መልሶች እያነሱ መምጣታቸውን ልብ እንበል፡፡ የታክሲን ሰልፍ ርዝመት መጨመር እያስተዋል ነው? በአንድ አገር ላይ ዋና ለውጥ ሊያስከትል የሚችለው የአስተሳሰብ ለውጥ ወይስ የህንፃዎች ብዛትና የዓይነታቸው መበራከት ነው? የህንፃዎች መበራከት፣ የመንገዶች መሰራት በራሱ ይበል የሚያሰኝ ነገር ነው፡፡ ይሄ ግን የብዙሃኑን ተገልጋይ ህዝብ ኑሮ ፈቀቅ የሚያደርግ መሆን አለበት። ህዝባዊ ኑሮ፣ ዕድገትም ሲታይ የዜጎች ተስፋ ይለመልማል፡፡ የበለጠ የህይወት ዕሳቤ ይመጣል፡፡ የሥነ-ልቡናና የአመለካከት ለውጥ ተጨባጭ ይሆናል፡፡ የኢኮኖሚ መደላደሉም አስተማማኝ ይሆናል፡፡
ግምገማዎች ከእከክልኝ ልከክልህ መውጣት አለባቸው፡፡ ይህ ችግር የሚወገደው ድክመቶች እየበዙና እየተሳሰሩ ሲመጡ አይደለም፡፡ የአንዱን ድክመት አንዱ የሚሸፍንለት ራሱን ማዳን ስላለበት ነው፡፡ የነግ - በኔ ሥጋትም ስላለበት ነው፡፡ አብረው የገቡበትን ሌብነት መደበቅ ግድ ስለሚሆን ነው፡፡ “ግምገማ ድሮ ቀረ” እያሉ በፀፀት የሚናገሩ ሰዎች አልጠፉም፡፡ ሆኖም አንድ እፍኝ ጨው ውቂያኖስን አያሰማ ሆኖባቸዋል፡፡ ከልብ ስለሀገር የማሰብና የመወያየት ነገር የተመናመነው ለዚህ ነው፡፡ በየስብሰባው ላይ ሲፋጠጡ ማየት አስገራሚ ነው፡፡ የልብ አውቃው፤ “መብላት ያስለመድከው ሲያይህ ያዛጋል” የሚለው ይሄኔ ነው!   

Read 6979 times