Saturday, 12 March 2016 11:54

“ደማቸውን የሚለግሱ ለወገናቸው ልባቸውን የሰጡ ናቸው”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(16 votes)

 ኦባማን ባገኘው ኖሮ ደም እንዲለግስ ከመጠየቅ ወደ ኋላ አልልም
       በአገራችን የሚለገሰው የደም መጠን ከሚጠበቀው በታች መሆኑን ያስታወቀው ብሔራዊ ደም ባንክ፤ እንዲያም ሆኖ ከዚህ ቀደም ይሰበሰብ ከነበረው መሻሻል እየታየበት እንደሆነ ገልጿል።  ባለፈው ዓመት 300 ሺህ ዩኒት ደም ያስፈልግ የነበረ ቢሆንም የተሰበሰበው ግን 128 ሺህ ዩኒት ደም ብቻ ነው፡፡ 300 ሺህ ከረጢት ደም ለማግኘት ደግሞ በየሶስት ወሩ 70 ሺህ ለጋሾች የሚያስፈልጉ ሲሆን አሁን በየሶስት ወሩ ደም እየለገሱ ያሉት በጎ ፈቃደኞች ግን ከ10 ሺህ አይበልጡም ተብሏል። በአሁኑ ወቅት በአገራችን በየቀኑ 30 እናቶች እንደሚሞቱ ያስታወቀው ባንኩ፤ ከእነዚህ ውስጥ አስሩ በወሊድ ጊዜ በሚያጋጥማቸው ከፍተኛ ደም መፍሰስ እንደሚሞቱ ይገልፃል፡፡
በብሄራዊ ደም ባንክ የደም ለጋሾች አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ዘለቀ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ “ሆስፒታሎች የሚፈልጉትን ያህል ደም አያገኙም፤ ይሄ ማለት በደም እጥረት ሰው ይሞታል ማለት ባይሆንም ለምሳሌ አንድ ታካሚ አምስት ዩኒት ደም ቢያስፈልገው በሁለትና በሶስት ዩኒት ደም ሊድን ይችላል፤ ነገር ግን ጥራት ያለው ህክምና አያገኝም” ለዚህም ነው ህብረተሰቡ ደም እንዲለግስ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች የሚደረጉት። የእናቶችን ሞት ለመቀነስና ህብረተሰቡ የበለጠ ደም እንዲለግስ በያዝነው ወር መጨረሻ ላይ በርካታ ነፍሰ ጡር እናቶች ከመሳይ ፕሮሞሽንና ከብሄራዊ ደም ባንክ ጋር በመተባበር “እኛም ወልደን መሳም እንፈልጋለን፤ ደም ለግሱ” በሚል መሪ ቃል የእግር ጉዞ ያደርጋሉ፡፡
መሳይ ፕሮሞሽን ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ የታዋቂ ሰዎች መታሰቢያ የሚሆን የደም ለጋሾች አምባሳደር በመምረጥ፣ህብረተሰቡ ደም እንዲለግስ እያንቀሳቀሰ ሲሆን የመጀመሪያው አምባሳደር ዶ/ር ተወልደ ብርሃን ገ/እግዚአብሔር ነበሩ፡፡ በአሁኑ ሰዓት በአምባሳደርነት የደም ልገሳ ዘመቻ እያደረጉ ያሉት ደግሞ አንጋፋው የማስታወቂያ ባለሙያ አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ ናቸው፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ ከአቶ ውብሸት ጋር በነበራት ቆይታ በደም ልገሳ ቅስቀሳና እንቅስቃሴያቸው፣በውጤቱና በገጠማቸው ተግዳሮቶች ዙሪያ አነጋግራቸዋለች፡፡

       የደም ልገሳ አምባሳደር የሆኑት መቼ ነው? እንዴትስ ወደ እንቅስቃሴው ሊገቡ ቻሉ?
በመጀመሪያ የደም ልገሳ አምባሳደርነቱ የተጀመረው በእኔ ሳይሆን በዶ/ር ተወልደብርሃን ገ/እግዚአብሔር ነው፡፡ ሀሳቡን የፈጠረው፣ ለብሄራዊ ደም ባንክ አቅርቦ ሥራውን የጀመረውና እኔንም አምባሳደር እንድሆን የጠየቀኝ የመሳይ ፕሮሞሽን ባለቤት ወጣት መሳይ ሽፋ ነው፡፡ እኔንም ከብሄራዊ ደም ባንክ ኃላፊዎች ጋር ያስተዋወቀኝ ይሄው ወጣት ነው፡፡ ነገሩ እስከሚገባኝ ድረስ ፈቃደኛ አልነበርኩም፡፡ ጉዳዩን በደንብ ከተረዳሁና ለበጎ አድራጎት መሆኑን ከተገነዘብኩ በኋላ የእኔ ስም በስራው ላይ በመግባቱ ህዝቡ ደስ ካለውና ለወገኑ ክቡር ደሙን የሚለግስ ከሆነ፣ ከዚህ የበለጠ ክብር የለም ብዬ ገባሁበት፡፡ እንቅስቃሴውን የጀመርኩት በ2007 ዓ.ም ነበር፤ እኔ ግን ዘንድሮም ቀጥዬበታለሁ፡፡ ዘንድሮን የደገምኩት ዓምና የሰራኸው አልበቃም፤ጨምር ተብዬ ነው፡፡
ከአዲስ አበባም ውጭ በተለያዩ ክልሎች እንቅስቃሴ ያደርጋሉ፡፡ እስኪ ስለ አጠቃላይ ሁኔታው ያብራሩልኝ?
ልክ ነው አዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ጋምቤላ፣ ሶማሌ፣ አፋር፣ ደብረ ብርሃን፣ ኦሮሚያ ውስጥ ቢሾፍቱ፣ የተወለድኩበት ቦታ ሸዋሮቢት ሄጃለሁ፡፡ ምን አለፋሽ… አገሪቱን አዳርሻለሁ፡፡ ሰው በሰልፍ ይጠብቀኝ ስለነበር፣በየቦታው እየሄድኩኝ ደም የሚለግሱትን እያመሰገንኩና እየመረቅሁ፣ ሌላውም ለወገኑ ደም በመስጠት ህይወት እንዲታደግ እያስተማርኩና እየቀሰቀስኩ ስሰራ ቆይቻለሁ፡፡ ይሄን የማደርገው ብቻዬን ሳይሆን ከብሄራዊ ደም ባንክ ባለስልጣናትና ሰራተኞች እንዲሁም ከመሳይ ፕሮሞሽን ጋር በጋራ ነው። እንደሚታወቀው ብዙ እናቶች በደም እጦት እየሞቱ ነው። ደም አንሷቸው ያደጉ ህፃናትም በሌላ በሽታ እንደሚያዙ የህክምና ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ አስፋልት ላይ በመኪና አደጋ ደም እየፈሰሰና መተኪያ ደም እያጣ ወገን እያለቀ ነው፡፡ ይህን ለማስቀረት በሚደረገው ትግል በነዚህ ሁለት ዓመታት የእኔ ስም በመግባቱና ዘመቻው ደግሞ “የውብሸት ወርቃለማሁ መታሰቢያ” ተብሎ በመሰየሙ ተደስቼ አቅሜ የፈቀደውን እያደረግሁ ነው። ቀጣይ ፕሮግራሞችም እየተመቻቹ ነው፡፡ ጋምቤላ፣ መቀሌ ድሬደዋና ደሴም ጥሪ አለ፡፡ ጉዟችን ይቀጥላል፡፡
እርስዎ አምባሳደር ሆነው መንቀሳቀስ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን የደም ልገሳ ግንዛቤን ከመፍጠርና ማህበረሰቡን ከማንቀሳቀስ አኳያ ምን ያህል ለውጥ አምጥቻለሁ ብለው ያስባሉ? ከሌሎች የሚያገኙትስ አስተያየት ምን ይመስላል?
እኔ በበኩሌ በኔ ጊዜ ይሄን ሰራሁ፣ እኔ መንቀሳቀስ ከጀመርኩ ይሄን ያህል አደገ እያልኩ ለመመፃደቅና ጉራ ለመንዛት አልፈልግም፡፡ የምሰራውም ይሄን ለማለት አይደለም፤ ይሄን መግለፅ የሚችል አካል ሌላ ነው። እሱም ብሄራዊ ደም ባንክ ነው፡፡ እኔ አሁንም በባህር ዳር፣ በጎንደር ሄጄ፤ በመቀሌ አቋርጬ በሁሉም የአገሪቱ ክፍል ቅስቀሳና ዘመቻ ማድረግ እፈልጋለሁ፤ የኔ ስራ ይሄ ነው፡፡ ምን አይነት አስተያየት ታገኛለህ ላልሺው፣ሁሉም አድናቆቱን ይገልፅልኛል፤ ለእኔ ሆይ ሆይ ይለኛል፤ ከጀርባዬ የሚናገረውን አላውቅም፡፡ እኔ በዚህ አላምንም። እኔ የማምነው አንድ ሰው ልቡን ሲሰጠኝ እንጂ ስላጨበጨበልኝና በአፉ ስለነገረኝ አይደለም። ሰው ሰውን አመነ፣ ወደደ አከበረ የሚባለው ልቡን ሲሰጥ ብቻ ነው፡፡ መንግስትም የህዝብን ልብ ካላገኘው፣ ህዝብም የመንግስትን ልብ ካላገኘው አንድ ሆኑ ማለት አይቻልም፤ ልቡ ሲገኝ ብቻ ነው፡፡
 እርስዎ አንድ ሰው ከልቡ እንደወደደዎትና ልቡን እንደሰጠዎት የሚለኩት በምንድን ነው?
በጣም ጥሩ! እኔ አንድ ሰው ልቡን እንደሰጠኝ የማውቀው፤ “ላንተ ክብር ለወገናችን ህይወት ደም እንሰጣለን” ሲለኝና በተግባር ደሙን በመለገስ መውደዱንና ክብሩን ሲገልፅ ብቻ ነው፡፡ አፋሩም ሱማሌውም፣ አማራውም ኦሮሞውም ክቡር ደሙን ሲሰጥ ስመለከት እኔንም እንደወደደኝ፣ በክቡር ደሙም ህይወቱን ሊያጣ የነበረውን ወገኑን ሲታደግ፣ ያኔ ልቡን ሰጥቶኛል፤ አበቃ! የእኔ መመዘኛ ይሄ ነው፡፡ እኔ አምባሳደር ከመሆኔም በፊት በበጎ ፈቃደኝነት በቋሚነት ደማቸውን የሚለግሱ ቅን ወጣቶችና ጎልማሶች አሉ፤ እነዚህ ሰዎች ለወገናቸው ልባቸውን የሰጡ ናቸው። አሁንም በርካታ ወጣቶች በየሶስት ወሩ ያለማቋረጥ ደም እንዲለግሱና ለወገናቸው ያላቸውን ፍቅር በተግባር እንዲገልፁ እማፀናለሁ፡፡ እንደማያሳፍሩኝም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እስካሁንም አላሳፈሩኝም፡፡
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ወደ አገራችን በመጡበት ወቅት አብረው እራት እንዲመገቡ ከተመረጡት 40 ሰዎች መካከል እርስዎ አንዱ እንደነበሩ ሰምቻለሁ፡፡ እርስዎ ግን በወቅቱ ሀረርና ድሬደዋ የደም ልገሳ ቅስቀሳ ላይ ነበሩ፡፡ እንደውም ባራክ ኦባማም ደም መለገስ አለበት ብለው ነበር አሉ፡፡ ይሄ ነገር እውነት ነው?
/ረጅም….. ሳቅ/ እናንተ ጋዜጠኞች ነገር ሞቅ ታደርጉና ሰውን ገደል መጨመር ትወዳላችሁ /ሳ….    ቅ/ እውነት ለመናገር በወቅቱ ድሬደዋ ነበርኩኝ፤ እዛ የነበርኩት ግን ለደም ልገሳው ብቻ ሳይሆን ቁልቢ ገብርኤልንም ለመሳለም ነበር፡፡ ቅዳሜ ማታ ከሁለት ሬዲዮ ጣቢያዎች ተደውሎ፤ “40 ሰዎች ከኦባማ ጋር እራት ለመመገብ ተጋብዘዋል፤ ከነዚያ ውስጥ የአንተና የአትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ ስም መጀመሪያ ላይ ይገኛል፤ትመጣለህ ወይ?” አሉኝ፡፡ በነጋታው እሁድ የአመቱ ሐምሌ ገብርኤል ነበር፤ “እዛ ነኝ ያለሁት አቋርጬ መምጣት አልችልም” አልኳቸው። ለምን? አሉኝ፤“በእምነቴ ቅዱስ ገብርኤል ከኦባማም ከሁሉም ይበልጣል” አልኩኝ፤ “ሰኞስ አትደርስም?” ሲሉኝ፤ “አይ አልችልም፤ምክንያቱም የድሬደዋና የአካባቢውን እንዲሁም የሀረርና የሀሮማያን ሰው ክቡር ደሙን በደም እጥረት ለሚያልቀው ወገኑ እንዲለግስ አስተምራለሁ፤ይሄንንም አቋርጬ አልመጣም” ብዬ ምላሽ ሰጠሁ፡፡ ከፕሬዚዳንት ኦባማ ጋር እራት ብመገብ ደስ ይለኝ ነበር፤ ምክንያቱም ኦባማ የአሜሪካ ብቻ ሳይሆን የዓለም ፕሬዚዳንት ማለት ነው። ነገር ግን ከወገኔ ህይወት አይበልጥብኝም፡፡ ስለዚህ በግብዣው ላይ አልተገኘሁም፡፡
ኦባማ ደም ይለግስ  ብለዋል የተባለውስ?
በእርግጥ አላልኩም፤ነገር ግን ባገኘው ከመጠየቅ ወደኋላ አልልም ነበር፡፡ “ክቡር ፕሬዚዳንት፤ እንኳን ወደ ኢትዮጵያ በደህና መጡ፤ የእርስዎ ደም ግማሹ ጥቁር በመሆኑ፣ ኢትዮጵያም የመጀመሪያው የሰው ዘር መገኛ ስለሆነች፣ የእርስዎ ደም ከኢትዮጵያ ህዝብ ደም ጋር ቢቀላቀል ለእኛም ኩራት ነው፤ ለእርሶም ክብር ነው፤; ብዬ ለማሳመን ወደ ኋላ አልልም ነበር፡፡ በነገራችን ላይ እኔ ከኒክሰን በኋላ የነበሩትን ፕሬዚዳንት ጀነራል ፎርድን ኋይት ሀውስ ውስጥ የመጨበጥና ሰላምታ የመስጠት እድልም ገጥሞኛል፡፡ በ1975 እ.ኤ.አ ማለት ነው፡፡ 43 የዓለም አገራትንም ጎብኝቻለሁ፡፡ የቤልጂየሙን ንጉስ ቦዱዋንም አግኝቻቸዋለሁ፡፡ ኦባማንም ባገኛቸው ጥሩ ነበር፤ግን ከወገኔ አላስቀደምኳቸውም፡፡
መጋቢት መጨረሻ ላይ “እኔም ልጅ ወልጄ መሳም እፈልጋለሁ፤ ደም ለግሱ” በሚል መሪ ቃል በርካታ ነፍሰጡሮች የእግር ጉዞ የሚያደርጉበት ዘመቻ እንዳዘጋጃችሁ ሰምቻለሁ፡፡ እስኪ ስለ ዘመቻው ያብራሩልኝ?
የዚህ ሀሳብ ፈጣሪ ወጣት መሳይ ሽፋ ነው፡፡ መሳይ ብዙ አያወራም፤ ነገር ግን አምጦና ተጨንቆ የሚያወጣው ሀሳብ ትልቅ ሀሳብ ነው፤ማንም ያላየው ሀሳብ፡፡ በጣም ነው የማደንቀው፡፡ አንዳንድ ሰው ብዙ ያወራል ግን ትንሽ ነው የሚሰራው፤ አሊያም ምንም አይሰራም። መሳይ ይህን ሀሳብ አመንጭቶ ለብሄራዊ ደም ባንክ አቀረበ፤ በከፍተኛ ክብር ተቀባይነትን አገኘለት፡፡ ነፍሰ ጡር እናቶች “ልጅ ወልጄ መሳም እፈልጋለሁ፤ደም ለግሱ” ሲሉ ደም የማይለግስ ጨካኝ ኢትዮጵያዊ አለ ብዬ አላስብም፤ምክንያቱም የዓለም ጀግኖች፣ ሊቃውንት፣ የጤና ዶክተሮችና ሳይንቲስቶች ሁሉም የእናት ውጤቶች ናቸው፤ ይህ ትልቅ ሀሳብ ላይ አሁን እንቅስቃሴ ጀምረናል። መሳይ ይህን ሀሳብ ሲነግረኝ በየመኖሪያ ቤቱ መዞር ጀምሬ ነበር፡፡ ጀሞ፣ ጎተራ፣ ባልደራስ ያሉ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሄድኩኝ፡፡ እዚያ ስሄድ ብቅ ሲሉ 40 በመቶ ያህሉ ነፍሰጡር ሴቶች ናቸው፡፡ መሳይ ይህን አይቶና አሳስቦት ይመስለኛል  ሀሳቡን የፈጠረው አልኩኝ። እኔም መንገድ ላይ ስሄድ የባንክ ቅርንጫፎች በብዛት፣ ቡና ጠጡ በብዛት፣ የመኪና መሸጫ ሱቆች በብዛት፣ ነፍሰጡሮች በብዛት ነው የማየው ---- እናም  ለዚህም ደም ያስፈልጋል፡፡    
ከመጋቢት መጨረሻ የነፍሰጡር እናቶች የእግር ጉዞ፣ እስከ ሰኔ ሰባት የዓለም ደም ለጋሾች ቀን ድረስ የምታካሂዱት ሌላ ፕሮግራም እንዳለም ሰምቻለሁ፡፡ ምንድን ነው?
ከነፍሰጡር እናቶች ጋር በየኮሌጆቹና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም በዩኒቨርስቲዎች በመዘዋወር ወጣቶችን እናስተምራለን፤ እንቀሰቅሳለን። ወጣቶች ለእናቶቻቸው፣ በመኪና አደጋ ለሚሞቱት ወገኖቻቸው ደማቸውን በመለገስ ህይወት እንዲያተርፉና ደም መለገስን ባህል እንዲያደርጉ እናስተምራለን፡፡ ኢትዮጵያዊያን ጥሩ ጥሩ ባህል አለን፤ በዚያው ልክ ጥሩ ያልሆኑ ባህሎችም አሉን፡፡ ለምሳሌ ሰዓት አጠቃቀማችን ወደ ኋላ ከሚያስቀሩን ጐታች ባህሎች አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ በሌላ በኩል የራሳችንን የሚያኮራ ነገር ትተን የውጭዎቹን ማንጠልጠል እንወዳለን፣ ይሄም ተገቢ አይደለም፡፡ ለምሳሌ አንድን ወጣት ቦርከና ወንዝ የት ነው ብትይው አያውቅም፤ ስለ አርሰናል ተጫዋች ቢጠየቅ ከነአያቱ በደንብ ያውቃል፡፡ ለምን አወቀ አይደለም ግን የአገሩን ማስቀደም አለበት፡፡ ወጣቱን እኛም አላስተማርነው፤ ስለዚህ በየኮሌጁ እየሄድን ከነፍሰጡር እናቶች ጋር እናስተምራለን፡፡ በዚህ ብዙ ለውጥ እናመጣለን ብለን ተስፋ አድርገናል፡፡
በዚህ ዓመት መጨረሻ የደም ልገሳ አምባሳደርነትዎን ያጠናቅቃሉ፡፡ ከዚያስ በኋላ ምን አስበዋል?
የበጐ አድራጐት ስራ ለመስራት የግድ በአምሳደርነት ብቻ መመረጥ አስፈላጊ አይደለም፤ በዚሁ ተግባር እቀጥልበታለሁ፡፡ አምባሳደር ሳይሆን ለደም ልገሳ ቅስቀሳ አደረገ ብሎ ፍርድ ቤት የሚያቆመኝ ያለ አይመስለኝም፡፡ በእድሜዬ በበጐ አድራጐት ስራ ተሳትፌ ከ155 ሚሊዮን ብር በላይ ሰብስበናል፡፡ በቀደመው ረሀብ ጊዜም “ስጋውን ብሉና ቆዳውን ስጡን” ብለን ቆዳ ሸጠን ለተራቡት ሰጥተናል፡፡ በበጐ ስራ ላይ ስሰራ አምስት ሳንቲም ኮሚሽን ተቀብዬ አላውቅም፡፡ አሁንም የህዳሴውን ግድብ ማስታወቂያ፣ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበርን ማስታወቂያ፣ ይሄንንም የደም ልገሳ ቅስቀሳ ደስ ብሎኝ ያለ ክፍያ ነው የምሰራው፡፡ ለዚህ ሁሉ ስራ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፡፡ ከጐኔ ያሉትን ሁሉ አመሰግናለሁ። በእውነቱ ብሔራዊ ደም ባንክ ውስጥ የሚሰሩት ሁሉም ሰራተኞች በንፁህ ልብና በቅንነት ስራቸውን  የሚያከናውኑ ናቸው፡፡ ይህን በጐ ሀሳብ ያመነጨውንና ለወገኑ ትልቅ ስራ እየሰራ ያለውን ወጣት መሳይ ሽፋንም እንዲሁ እግዚአብሔር ይባርከው እላለሁ። አክብረውኝ ክቡር ደማቸውን እየለገሱ ያሉትንም… በአጠቃላይ ለዚህ ፕሮግራም መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉትን ግለሰቦችና ድርጅቶች አመሰግናለሁ፡፡ አሁንም እናቶች፣ እህቶች፣ ሚስቶችና ሴት ልጆች ደም ያስፈልጋቸዋልና ደም ለግሱ፤ ህይወት አድኑ ----- የሚል ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፤ አመሰግናለሁ፡፡

Read 5403 times