Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 18 February 2012 12:20

እንደ ሩጫው ሁሉ በቢዝነሱም ቀዳሚ መሆን ነው ፍላጐቴ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ቢዝነስ ያለ ትርፍ አይታሰብም

በዚች አገር በዓላት በዝተዋል - የማይሠራበት ቀን ይበልጣል....

አብዛኛውን ሀብት ያፈራሁት በቢዝነስ ሳይሆን በስፖርት ነው፡፡

በርካታ ተደጋጋሚ ድሎችን አጣጥሞ የአገሩን ሕዝብም በደስታ አስፈንድቋል፡፡ አያሌ ክብረ ወሰኖችን በጨበጠባቸው የአውሮፓ፣ የአሜሪካ፣ የኤስያ፣ የአፍሪካ አገራትም በጣም ይታወቃል፡፡ እንዲያውም ክብርና ሞገሱ በውጭ አገራት ሳይሆን ይቀራል? በውጭ አገራት በጣም ይከበራል፣ ይወደዳል፡፡ ለምሳሌ፣ በቻይና፣ የአገር መሪዎች ብቻ የሚሄዱበት ልዩና የተከበረ ጎዳና አለ፡፡ በዚያ ጎዳና የአገሪቱ ዜጐች እንኳ መኪና አያሽከረክሩም፡፡ እሱን ግን በዚያ ጎዳና ነው የሚቀበሉት በማለት አንድ ጓደኛዬ አጫውቶኛል፡፡ በጣም ይወደዳል፣ በጣም ይከበራል፡፡ ከዚህም በላይ በወጣትነቱ የታሪክ ባለውለታ፣ መኩሪያና መመኪያ፣ የአገሩ አምባሳደር፣ … መሆን የቻለ ብርቅዬ ጀግና ነው - ታላቁ አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ፡፡

በስፖርት ብቻ ሳይሆን በቢዝነሱም አንደኛና ቀዳሚ መሆን ነው ምኞቱ፡፡ “እኔ መቀደምን አልወድም፡፡ ሁልጊዜ ከፊትና አንደኛ መሆን ነው የምፈልገው” ይላል፡፡ ለራዕዩ ስኬት  ወኔና እልህ ሰንቆ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡

ወደ ቢዝነስ የገባው ከዛሬ 20 ዓመት በፊት ነው - በሩጫ አሸንፎ በተሸለመው 900 ዶላር (በዚያን ጊዜ ምንዛሪ 6,300 ብር ገደማ ማለት ነው)፡፡ ኃይሌ፤ “ያገኘ ሳይሆን የከተተ (ያጠራቀመ) ከበረ” የሚለው ባህላዊ አባባል ትክክል እንደሆነ ያምናል፡፡ በመሆኑም ባሸነፈ ቁጥር የሚሸለመው ገንዘብ ላቡን አንጠፍጥፎ ያገኘው ስለሆነ በከንቱ አያባክንም - ያጠራቅመዋል፡፡ “አብዛኛውን ሀብት ያፈራው በቢዝነስ ሳይሆን በስፖርት ነው” ይላል ኃይሌ - ስለሀብቱ ሲጠየቅ፡፡

ኃይሌ በት/ቤት፣ በሪል እስቴትና በሆቴል (በሪዞርት) ዘርፍ ተሰማርቷል፡፡ በአሰላና በባህርዳር ሁለት ት/ቤቶች አሉት - ከመዋለ ሕፃናት እስከ ሁለተኛ ደረጃ ያስተምራሉ፡፡ በትምህርቱ ዘርፍ አዲስ ትውልድ ከመቅረፅ በስተቀር ምንም ትርፍ እንደማይገኝበትና አክሳሪ መሆኑን ይናገራል፡፡ ት/ቤት ሲከፈት ከሁለት ነገሮች አንዱን መምረጥ ያስፈልጋል፡፡ ትርፍን ወይም ጥሩ ትምህርት መስጠትን ይላል ኃይሌ፡፡ ጥሩ ትምህርት ለመስጠት የማስተማሪያ ቁሳቁስ በጣም ተወድዷል፡፡ ለጥሩ አስተማሪም የሚከፈለው ደሞዝ ከፍተኛ እንደሆነ ይናገራል፡፡ “የሚፈለገው ትርፍ ከሆነ በጣም ጫን ያለ ዋጋ ታስከፍላለህ፡፡ ያ ደግሞ እንደ እኔ ላለ ሰው ጥሩ አይደለም - መጥፎ ስም ያሰጣል፡፡ በወር ከ200 ብር ያነሰ እያስከፈሉ እንዴት ትርፍ ይገኛል? የኔ አና የባለቤቴ ትርፍ ልጆቹ ናቸው፡፡ እንደ ራሳችን ልጆች በየዓመቱ እየሄድን እናያቸዋለን፡፡ ጥሩ መሠረት ይዘው ትውልድ የመቅረፅ ዓላማችን ሰምሮ ስናይ እንደሰታለን - ያ ነው ትርፋችን ብሏል፡፡

በሪል እስቴት በአሰላ፣ በአዳማ ናዝሬት እና በአዲስ አበባ በርከት ያሉ ሕንፃዎች ሠርቶ እያከራየ ነው፡፡ ሲኒማ ቤት፣ የአካል እንቅስቃሴ ጂም አለው፡፡ ሌላ ጂም መገናኛ አካባቢ ለመክፈት ዝግጅቱ እየተጠናቀቀ ነው፡፡ እነዚህ ጥሩ ትርፍ ያስገኛሉ፣ የሀዋሳውም ሆቴል ጥሩ እየሠራ እንደሆነ አትሌት ሃይሌ ይናገራል፡፡

በ1988 አትላንታ አሸንፎ ሲመለስ 450 ካሬ ሜትር ቦታ አሮጌው አውሮፕላን ማረፊያአካባቢ የተሰጠው ኃይሎች፡፡ በዚያ ቦታ ላይ ቤት ሠርቶ ማከራየት ጀመረ፡፡ ከዚያም ኡራኤል አካባቢ ያለውን ቦታ በሊዝ ገዝቶ ሕንፃ ሠራ፡፡ ያ ግንባታ እንዳለቀ፣ ቦሌ መንገድ ላይ አሁን ዓለም ሕንፃ የተሠራበትን ቦታ በጨረታ ተገዛ፡፡ ሕንፃው እየተሠራ ሳለ፣ አሁን ዓለም ሲኒማ የተሠራበትን ቦታ የገዙት ሴት “ይኼ ሕንፃ ፊቴ ቆሞ (ከልሎኝ) ቤት አልሠራምና ገንዘቤን መልሱልኝ” አሉ፡፡ ያንን ቦታ፣ ለፊልም ቤትና ለመኪና ማቆሚያ እንፈልገዋለን ብለው እነ ኃይሌ በሊዝ ገዙት፡፡ እነዚህ አዲስ አበባ ያሉት ናቸው፡፡ የአሰላው ሕንፃ ከተሠራ ቆይቷል፡፡ እንግዳ ማረፊያ፣ ሬስቶራንት፣ ሱቆች፣ ት/ቤት ያሉት ነው፡፡ አሰላና ባህርዳር ላይ ለት/ቤት መሥሪያ የተሰጠው ቦታ ከሊዝ ነፃ መሆኑን ይናገራል፡፡ በመጨረሻ የሃዮንዳይ መኪና ወኪል ሆኖ መገናኛ ከዳያስፖራ አደባባይ አጠገብ ያለውን ሕንፃ ሠሩ፡፡

ከሁሉም በጣም ፈታኝ የነበረውና የኃይሌና ዓለም ኢንተርናሽናል ኩባንያን ሀብት ከ60-70 በመቶ የበላው የሀዋሳው ሆቴል ነው፡፡ ሆቴሉ ሲመረቅ የፈጀው ወጪ 220 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ ያኔ ያላለቁ ብዙ ሥራዎች አሁን ተጠናቀዋል - በአጠቃላይ 250 ሚሊዮን ብር ፈጅቷል፡፡ ለሆቴሉ የተገዙት ዕቃዎች ዋጋ፣ ሕንፃው ከተሠራበት ዋጋ እጥፍ ሳይሆን እንደማይቀር ይናገራል፡፡

ሀዋሳ በፍጥነት እያደገች ያለች ከተማ መሆኗን ኃይሌ ይናገራል፡፡ የከተማዋ ነዋሪ፤ ከአዲስ አበባ የሚሄዱ ሰዎችና በርካታ ቱሪስቶች ወደ ሆቴሉ ይመጣሉ፡፡ ከአዲስ አበባ ለመዝናናት የሚሄደው ቀላል አይደለም፡፡ ስለዚህ ጥሩ አገልግሎት እየሠጠ ነው፡፡ “እኛ ሆቴሉን የሠራንበት ዋናው  ምክንያት ለስብሰባ (ለኮንፈረንስ) ነው፡፡ ከ10 ሰው እስከ 1000 ሰው መያዝ የሚችሉ ሰባት አዳራሾች አሉት ብሏል፡፡

ይህ ሆቴል በጣም የፈተነውና ስለ ሆቴል አሠራርም ብዙ ትምህርትና እውቀት ያገኘበት እንደሆነ ይናገራል፡፡ ብዙ ሰዎች ሕንፃ ብቻ በማየት “ፓ! ይህ ሆቴል እንዴት አሪፍ ነው?” ይላሉ፡፡ እሱም ተመሳሳይ አመለካከት ነበረው፡፡ ወደ ሥራው ሲገባ ነው ይህ አባባል ትክክል እንዳልሆነ የተረዳው፡፡ አንድን ሆቴል፤ ጥሩና ደረጃውን የጠበቀ ነው የሚያሰኘው ሕንፃው ሳይሆን የተሟሉለት የውስጥ ዕቃዎች፣ ፎጣና ሳሙና፣ ሻምፑና ኮንዲሽነር የመሳሰሉ ጥቃቅን ነገሮችም ጭምር ፣ … ናቸው፡፡

አንድ እንግዳ ሲመጣ በቅድሚያ የሚጠይቃቸው ነገሮች የ24 ሰዓት የንፁህ ውሃና የመብራት አገልግሎት መኖሩን ነው፡፡ ሀዋሳ ደግሞ፣ በእነዚህ መሠረታዊ አቅርቦቶች ብዙ ትታማለች፡፡ ማዘጋጃ ቤቱ ለከተማዋ ነዋሪ የሚያቀርበው ውሃ በቂ አይደለም፡፡ ስለዚህ የ200 ሜትር ጥልቀት ያለው የጉድጓድ ውሃ ቆፍረው ነው የሚጠቀሙት፡፡ ውሃው ተጣርቶና ታክሞ ለአገልግሎት ይውላል፡፡ የመብራት አቅርቦትማ በጣም የባሰበት ነው፤ በቀን ውስጥ ለበርካታ ጊዜያት ስለሚቋረጥ ትልቅ ጀነሬተር ከነመጠባበቂያው ገዝቷል፡፡

ሌላው ደግም የምግብ ዝግጅትና አቀራረብ ነው፡፡ የምግቡ ጥፍጥና ብቻ ሳይሆን እንግዳው የተበከለ (የተመረዘ) ምግብ በልቶ ቢታመምና ጤናው ቢጓደል ሆቴሉ ተጠያቂ ስለሆነ፣ ዕንቁላሉ፣ ሥጋው፣ ወተቱ፣ አትክልቱ፣ ፍራፍሬው፣ … ከየት ነው የሚገዛው? እንዴት ነው የሚመረተው? ንፅህናቸው ምን ያህል ነው? … የሚለው በጣም አስጨናቂ እንደሆነ ገልጿል፡፡ የፎጣ አስተጣጠብ እንኳ ቀላል አይደለም - የሚያነፃ፣ የሚያለሰልስ፣ ጀርሞችን የሚገድል ኬሚካል እየተጨመረበት ብዙ ጊዜ ይታጠባል፡፡ የመዋኛ ውሃ ደግሞ ሌላው ከፍተኛ ችግር ነው፡፡ አንድ እንግዳ ዋኝቶ ቆዳዉ ላይ ሽፍታ ቢወጣ፣ በቆሻሻ ውሃ ታጥቤ ነው የታመምኩት ብሎ ኡ!ኡ! ይላል፡፡ ያ ችግር እንዳይመጣ ገንዳው በየጊዜው መታጠብ፣ ውሃው መቀየርና መታከም፣ … አለበት፡፡ እነዚህና ሌሎች በርካታ ችግሮች ናቸው የሆቴልን ሥራ ከባድ የሚያደርጉት፡፡

ውሃ የአብዛኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ችግር እንደሆነ ኃይሌ ይናገራል፡፡ በክልል ከተሞች ቀርቶ በአዲስ አበባም የውሃ ችግር አፋጣኝ መፍትሔ ካልተበጀለት፣ ወደፊት፣ ከፍተኛ ችግር እንደሚሆን ይናገራል፡፡ “ዘመናዊ አኗኗር፣ የአዲስ አበባን የውሃ ፍጆታ እጥፍ እያደረገው ነው፡፡ የውሃ እጥረት ወደፊት ከተማዋን እንድንጠላ ሊያደርገን ይችላል የሚል ስጋት አለኝ” ይላል ኃይሌ፡፡

ለምን መሰላችሁ? በርካታ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በሁሉም የመዲናዋ አቅጣጫዎች እየተሠሩ ነው፡፡ የእነዚህ ቤቶች መፀዳጃ በየጊዜው ውሃ መለቀቅ አለበት፡፡ በቂ የውሃ አቅርቦት የለም፡፡ ቤቶቹ ደግሞ ውሃ ማጠራቀሚያ ታንከር የላቸውም፡፡ ውሃ ቢኖር እንኳ አራትና አምስት ፎቅ ገፍቶ የሚያወጣ የኤሌክትሪክ ኃይል ሁልጊዜ መኖር አለበት፡፡ መብራት ደግሞ በየጊዜው ይቆራረጣል፡፡ በዚያን ጊዜ ውሃ የሌለው መፀዳጃ ቤት ምን ሊሆን እንደሚችልና ምን ሊፈጠር እንደሚችል እስቲ ገምቱ፡፡ በዚህ ዓይነት መኖር ሕይወትን ያስጠላል፡፡

በዚህ ችግር ላይ ኃይሌ ግፊት እያደረገ መሆኑን ይናገራል፡፡ “ኮንዶሚኒየም ሲገነባ ሁሉም መፀዳጃ ቤቶች ውሃ ይፈልጋሉ፡፡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሲሠሩ ውሃ፣ ሳኒቴሽንና የፍሳሽ ማስወገጃ አብራችሁ ማየትና ማሰብ አለባችሁ እያልኩ ግፊት አደርጋለሁ፡፡ በየፎቁ የውሃ ጋን  አይታይም፡፡ ነዋሪው በየቤቱ ወይስ መሬት እየወረደ ነው የሚፀዳዳው? ወይም በፖፖ? ሁለቱም አስፈላጊ ቢሆኑም ከመብራት ይልቅ ውሃ ቅድሚያ ሊሰጠው  ይገባል፡፡ ይኼ ችግር ካልተፈታ በስተቀር ኮንዶሚኒየም መገንባት በኋላ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንዳያመዝን ስጋት አለኝ፡፡” ብሏል - ውሃ የሀዋሳ ብቻ ሳይሆን የአዲስ አበባም ጭምር መሆኑን በማመልከት፡፡

በሆቴል አገልግሎት፣ ሌላው ችግር፣ የሆቴል ባለሙያ ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ በአገር ውስጥ የሠለጠነ የሰው ኃይል ማግኘት አስቸጋሪ ነው ያለው ኃይሌ፣ ከውጭ አገር ለማስመጣት ደግሞ የሚጠይቁት ክፍያ ውድ ከመሆኑም በላይ የአገሪቱን ባህልም ተላምደው የመሥራት ችግር እንዳለ ተናግሯል፡፡ በሆቴል ዘርፍ መሠማራት፣ ከችግሩ ባሻገር ጥሩ ነገርም እንዳለው አልሸሸገም፡፡ መንግሥት ለሆቴል አገልግሎት የሚውሉ ዕቃዎችን ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡ መፍቀዱ ከፍተኛ እገዛ እንዳደረገላቸው ይናገራል፡፡ “ከቀረጥ ነፃ መብት ባይኖር የሆቴሉ ሥራ አይታሰብም - ይቀራል” ብሏል፡፡

ኃይሌ የኮሪያ ስሪት የሆነውነን ሃዮንዳይ መኪና በወኪልነት ማስመጣት ከጀመረ ከረምረም ብሏል፡፡ ከዚህም በላይ መኪናውን እዚህ ለመገጣጠም፣ መግባባት ላይ ደርሰው ነበር፡፡ ነገር ግን ረዥም ጊዜ ይወስዳል፡፡ “እነሱ፣ የመኪናውን ጥራት ለመጠበቅ፣ ለሦስትና አራት ዓመት ኮሪያውን ባለሙያዎች እዚህ ወጥተው መገጣጠም አለባቸው ይላሉ፡፡ የሚጠይቁት ክፍያ በጣም ውድ ነው፡፡ እንደዚያ ከሆነ፣ እዚህ ከመገጣጠም ከዚያ አምጥቶ መሸጡ ይቀላል፡፡ ሱዳን፣ መገጣጠሚያ ነበራቸው - ያ፣ በጥራት ጉድለት መዘጋቱም ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡ መጨረሻ የደረስንበት ውሳኔ፤ የእኛን ሰዎች ወደ ፋብሪካው እየላክን እንዲሠለጥኑ ማድረግ ነው” ብሏል ኃይሌ፡፡

ስለ ቢዝነስ ስንነጋገር፣ በጣም ሀብታም የሆኑ ሰዎች ለምንድነው ትርፍ ላይ የሚያተኩሩት? ድሃም ሆነ ሀብታም ከአንድ እንጀራ በላይ አይበላም፡፡ ቱጃሮች እስካሁን ያፈሩትን ሀብት “ተመስገን” እያሉ ቁጭ ብለው መብላት ትተው ምንድነው ትርፍ ላይ ሙጭጭ የሚሉት? በማለት የሚኮንኑ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ኃይሌ ግን በዚህ ሐሳብ በፍፁም አይስማማም፡፡ የትም ሆነ የት ቢዝነስ ከተባለ፣ ግቡ፣ አንድና አንድ ብቻ ነው - እሱም ትርፍ ብቻ ነው የሚል ፅኑ እምነት አለው፡፡

ቢዝነስ፣ ለትርፍ የሚሰራ ካልሆነ፤ በጎ አድራጐት ይሆናል ያለው ኃይሌ፣ ኅብረተሰቡ በሚያራምደው በዚህ የተሳሳተ እሳቤ ኢትዮጵያ ውስጥ ሠርቶ ማትረፍ እንደኃጢአት እየተቆረጠ ነው፡፡ ስለዚህ ብዙ ባለሀብት መፍጠር ያስቸግራል፤ የስራ እድልም በብዛት አይፈጠርም፡፡ ብዙ ቱጃሮች ካልተፈጠሩ፤ አገሪቷ ከታክስ የምታገኘውን ገቢ ታጣለች፡፡ መንግሥት ከባለሀብቶች ታክስ ካልሰበሰበ፣ መሠረተ ልማቶች መገንባትና ማስፋፋት አይችልም፡፡ ስለዚህ፣ አገሪቷ፣ መሻሻልና ማደጓ ቀርቶ ድህነት ውስጥ ስትዳክር ትኖራለች፡፡ እንደኔ እምነት የሚያድገው ይደግ ወይም ይውጣ፡፡ ይበልጽግ፡፡ ከተቻለ የታችኛውንም ወደ ላይ ማውጣት ነው፡፡ ነገር ግን ወደ ላይ የወጣውን የምታወርድ ከሆነ ሁለት ነገር ታጣለህ - ሀብታሙንም ታጣለህ (ታደኸያለህ)፣ ድሃውንም አታሳድግም፡፡

በቅርቡ በአሜሪካ የተፈጠረውን ነገር መጥቀስ ይቻላል፡፡ ሕዝቡ፣ መንግሥት 99 በመቶ የሆንነውን ህዝብ ትቶ አንድ በመቶ የሆኑትን ይደግፋል በማለት ሰልፍ ወጥተው አይተናል፡፡ ቢዝነስ ኃጢአት ነው በሚሉ ሰዎች አመለካከት፤ መንግሥት፣ ብዙሃኑን ትቶ ጥቂቶቹን መደገፉ እብደት ሊመስል ይችላል፡፡ መሪዎቹ ጥቂቶቹን የደገፉት ብልህ በመሆናቸው ነው፡፡ የሀብታሞቹ ኩባንያ ከተዘጋ፣ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ያውቃሉ - በርካቶች ከሥራ ይባረራሉ፤ የሥራ አጡ ቁጥር እጅግ ይንራል፡፡ የሚበላና የሚላስ ጠፍቶ አገሪቷ በቀውስ እንደምትናጥ ያውቃሉ፡፡ ስለዚህ ጥቂቱን ሀብታሞች፣ እባካችሁ ፋብሪካችሁን አትዝጉ፤ ብትከስሩ እንኳ ታክስ ልቀንስላችሁ ወይም ታክስ ልተውላችሁ፣ … ነው ያላቸው፡፡ አገራችንም ይህን መመሪያ ብትከተል ብዙ የቢዝነስ ሰዎችን መፍጠር ይቻላል በማለት አስገንዝቧል፡፡ በአገሪቷ ለሚታየው የኑሮ ውድነት በርካታ ምክንያቶች መጥቀስ ይቻላል፡፡ የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ የአቅርቦትና ፍላጐት ያለመጣጣም፣ የማይሠሩ እጆች መበርከት፣ ሙስና፣ የሕዝቡ መኖር መጀመር፣ የፍላጐት በጣም መጨመር … ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ ኃይሌ አዲስ አበባን ሲረግጥ የሚያውቀው ኬክ ቤት በላይ ተክሉን ነበር፡፡ “አሁን በመዲናይቱ በሙሉ ሳይሆን ከቦሌ እስከ መስቀል አደባባይ ያሉትን ኬክ ቤቶች ብቻ ብትቆጥሩ በጣም ብዙ ናቸው፡፡ ታዲያ ስኳር ለምን አይወደድ?” ብሏል፡፡

የፍላጐት ከፍ ማለት፣ ለሙስናም በር ይከፍታል ይላል፡፡ ሌሎችን እያየ፣ ልጆቼን ጥሩ ት/ቤት ማስተማር፣ ማልበስ፣ ማብላት፣ … አለብኝ፡፡ ጥሩ ቤት መሥራት አለብኝ፣ ሚስቴ መኪና ያስፈልጋታል፣ .. እያለ የሚመኝ ሰው፣ በገቢው ምኞቱን ማሳካት ሲያቅተው ወደ ሙስና ተገፋፍቶ ይገባል፡፡ የአረብ አገሮች አብዮት የተቀሰቀሰው በፍላጐት መጨመር ነው - ህዝቡ የሚበላና መኖሪያ አጥቶ አይደለም፡፡ ወደ ውጭ አገር ወደ አውሮፓ ወደ አሜሪካ ሄዶ በሚያየው ይገረማል - ለካንስ እንዲህም አለ ብሎ ፍላጐቱ ይጨምራል፡፡ ወደ አገሩ ተመልሶ ለምንድነው እኔስ በአገሬ እንዲህ ዓይነት መብትና ነፃነት የማይኖረኝ? ብሎ ተነሳ - በመሪዎቹም ላይ አመፀ፡፡ እኔ፣ ሊቢያውያን ጥሩ የሚኖሩ ይመስሉኝ ነበር፡፡ እነሱ ግን፣ ጋዳፊ! የገንዘብ ድጐማህም፣ ቤትም፣ የምትሰጠን ነገር ሁሉ ገደል ይግባ ብለው ገፍትረው ጣሉት፡፡ ይህን ችግር ለማስወገድ መፍትሔው የበለጠ መሥራት፣ የሥራ ገደብ ያለመኖር፣ ምርትና አቅርቦትን ማመጣጠን ብቻ ነው ይላል ኃይሌ፡፡

ከአገራችን ጋር የተያያዘ አንዱ እንቅፋት፤ የበዓላት መብዛት እንደሆነ ተናግሯል፡፡ ብሔራዊ የበዓላት ቀናት፣ እሁድ ቅዳሜ፣ ከአሁን በፊት የማይከበሩ ሁሉ የዓመቱ … እየተባለ ሥራ አይሠራም፡፡ ሌላም አለ፤ ሠርጉም - ለቅሶውም ቅጥ አጥቷል፡፡ ይህ ሁሉ እየተደማመረ የሥራ ቀኑ አንሷል፡፡ ከቀረውም ውስጥ በተለያዩ ችግሮች ሳቢያ ከሚሠራበት የማይሠራበት ቀን በዝቷል፡፡ “ሕዝባችን ሥራ ከተባለ ተአምር ይሠራል፡፡ ባለፈው ሳምንት አዳማ (ናዝሬት) ነበርኩ፡፡ አዳማ፣ የመላው ኢትዮጵያ ሻምፒዮና አዘጋጅ ናት፡፡ ለዚያ ሻምፒዮና ስታዲዮም እየተሠራ ነው፡፡ ሰው፣ እሁድ፣ ቅዳሜ ሳይል አቧራ ለብሶ በአራት ወር የሠራው ሥራ በጣም የሚደንቅ ነው፡፡ በዕቅድ ከተመራ ሕዝብ የማይሠራው ነገር የለም፡፡” ብሏል ኃይሌ፡፡ ከችግር ለመውጣትና ከድህነት ለመላቀቅ እነዚህን እንቅፋቶች ትተን ጠንክረን መሥራት አለብን፡፡ ዓላማ ኖሮን ከሠራን ማድረግ የማንችለው ነገር አይኖርም በማለት አሳስቧል - አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ፡፡

ኃይሌ ብዙ ዕቅዶች እንዳሉት ይናገራል፡፡ ውድድሩ በአገር ውስጥ ብቻ መሆኑ  ቀርቶ ዓለም አቀፍ እየሆነ ነው፡፡ በዚያ ውድድር አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት በትናንሽ ቢዝነሶች አይቻልም - ትላልቅ ቢዝነሶች መጀመር ያስፈልጋል፡፡ ያ ደግሞ በእኔ እውቀት ብቻ አይሆንም፡፡ የተማረ የሰው ኃይል መኖር አለበት፡፡ የማንችለውን አምነን መቀበል አለብን፡፡ እንዲሁ ያለ እውቀት እየተንገታገቱ “ዘራፍ” ማለት የትም አያደርስም፡፡ ማሠራት ያለብህን በተማረ፣ እውቀቱ ባለው ሰው ማሠራት አለብህ በማለት አስገንዝቧል፡፡

ኃይሌ ወደፊት ለመሠማራት ካቀደባቸው ቢዝነሶች አንዱ ግብርና ነው፡፡ አሁን የእኔ ችግር መሬት ማግኘት አይደለም የሚለው ኃይሌ፤ የተማረ ሰው ወይም እውቀቱ ያለው ባለሙያ ማግኘት እንደሆነ ተናግሯል፡፡ “በባለሙያ የማይመራ ሥራ የትም አያደርስም፡፡ ዘመዴን ልጥቀም ብለህ ሙያው በሌለው ሰው የምታሠራ ከሆነ ዋጋ የለውም- ምናልባት ንብረቱን ሊቆጣጠርልህ (ሊጠብቅልህ) ይችል ይሆናል፡፡ ንብረቱን አንቀሳቅሶ እሴት (ዋጋ) አይጨምርልህም፡፡ እኔ አይቼዋለሁ፡፡ ያለ ሙያ አሠራቸው የነበሩ ብዙ ሥራዎች ውጤት አላመጡልኝም፡፡ በመጨረሻ ግን ከባለሙያ ጋር መሥራት ስጀምር ዕድገት ማሳየት ጀመሩ፡፡ እኔ በባለሙያ አምናለሁ፡፡”

ኃይሌ ትዳር የመሠረተው በ1988 ዓ.ም ሲሆን ሦስት ሴቶችና አንድ ወንድ ልጅ አፍርቷል፡፡ ልጆቹ የሚማሩት ሳንፎርድ ት/ቤት ነው፡፡ “ኃይሌ ልጆቹን አቅብጧል፤  አማርኛ በደንብ ሳይችሉ በእንግሊዝኛ ይናገራሉ፣ ይዘፍናሉ” የሚል ትችት ተጽፎ እንደነበር አስታውሼ ጠየቅኩት፡፡ ለካ እሱም አንብቦታል፡፡ እናም ለልጆቹ ነገራቸው - እንዲህ ተብላችኋል ብሎ፡፡ ልጆቹም፣ “አማርኛ መቻል ማለት አማርኛ ማወቅ ማለት አይደለም፡፡ ከፈለጉ እሱም እኛም አማርኛ እንፈተንና ማን የተሻለ እንደሚያውቅ ይታይ” እንዳሉ ተናግሯል፡፡

በዓለም ገንኖ ያለው እውቀት የምዕራቡ ስለሆነ ልጆቼን ሳንፎርድ ት/ቤት አስተምራለሁ ያለው ኃይሌ፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ እየገነነ ያለው የቻይና ኢኮኖሚ ነው፡፡ እኔ፣ ጥሩ የቻይንኛ ት/ቤት ባገኝ ልጆቼ የዚያንም ትምህርት እንዲያገኙ አደርጋለሁ፡፡ ልጆችን ጥሩ እውቀት ማስተማር ምን ክፋት አለው? ሃይማኖት እና ኢትዮጵያዊነት በቤተሰብ ሊወረስ ይችላል፡፡ ልጆችን ጥሩ ት/ቤት ማስተማር ኢትዮጵያዊነታቸውን አያስረሳም ሲል አስረድቷል፡፡

ኃይሌና ዓለም ኢንተርናሽናል ኩባንያ ለ 1,640 ያህል ዜጐች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡

የባለቤትህ የወ/ሮ ዓለም ጥላሁን የሥራ ድርሻ ምንድነው?

አለቃችን እሷ አይደለችም እንዴ? ዋና አለቃዋ እሷ ናት፡፡ በኃይሌና ዓለም ኢንተርናሽናል ውስጥ እሷ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ናት፡፡ እኔ ውጭ ውጭ ስለምል በአብዛኛው እሷ ናት የምትሠራው፡፡ በተለይ ወጣ ስል የእሷ ሥራ ይበዛል፡፡ ቤት ውስጥ ልጆች ማስተዳደር፣ ቢሮ ውስጥ ሥራ መምራት አለ፤ የእሷ ሥራ በዛ ይላል፡፡

በማኔጅመንት ደግሞ ሴቶች ከወንዶችም ጠንከር ያሉ ናቸው፡፡ በዚህ በኩል ኢትዮጵያ በሴቶች ስትመራ በነበረችበት ጊዜ ውጤታማ ነበረች፤ ከአንዷ ንግሥት በስተቀር - ንግሥት ዮዲት ጉዲት ብቻ ናት ጥሩ ስም ያልነበራት፡፡

በቢዝነስ ጉዳይ ትመካከራላችሁ?

እንዴ መመካከር ብቻ ሳይሆን ቢዝነስ ሁልጊዜ ያለ ውይይት አይሆንም፡፡

ቢሮ ውስጥ በሥራ ጉዳይ ትጨቃጨቃላችሁ

ምን ማለትህ ነው? ቢዝነስኮ ሳይመካከሩ፣ ሳይነጋገሩ፣ ሳይጨቃጨቁ አይሆንም፡፡ በተለይም ከቢዝነሱም በላይ ሰው ማስተዳደሩ በጣም ከባድ ነገር ነው፡፡ ለእኛ ከባዱ ነገር ገንዘብ እንዴት እናፍራ? እንዴት እንሽጥ? የሚለው አይደለም፡፡ ለእኛ ከባዱ ነገር ሰውን ማስተዳደር ነው፤ ለእኛ ትልቁ ሥራ ሰውን መምራት ነው፡፡

በአንድ ጉዳይ ላይ ስትነጋገሩና ስትጨቃጨቁ ቆይታችሁ ባለቤትህ የተሻለ ሐሳብ ካቀረበች ትቀበላለህ?

እንዴ! የምንወያየው የመንጨቃቀው ለምን ሆነና! እንዲያውም እኔ የተሻለ ሐሳብ ሳቀርብ እሷ አትቀበል ይሆናል እንጂ በአብዛኛው እኔ ነኝ የምቀበለው፡፡ በነገራችን ላይ በትምህርት እንኳ ትበልጠኛለች፡፡ እኔ ያው 12+ጭጭ ነው፡፡ እሷ ከዚያም ትንሽ አለፍ ብላ ተምራለች፤ እኔ ስሮጥ፣ እሷ ትማር ነበር፡፡

እኔን ከት/ቤት ውጭ ያስተማረኝ፣ ወደተለያዩ አገሮች የማደርገው ጉዞ ነው፡፡

አሁን አሁን በማስታወቂያ ሥራም እየተሳተፍክ ነው፡፡ ከውጪውና ከአገር ውስጥ ማስታወቂያ የትኛው ይሻላል ምን ያህልስ ሠርተሃል?

የውጪው ይሻላል፡፡ አገር ውስጥ ከባድ ነው፡፡ ለምን መሰለህ? ዓለምአቀፍ ቢዝነስ የሚያውቁ ካልሆነ በስተቀር፣ የአገር ውስጥ ምርት ለማስተዋወቅ ትንሽ አስቸጋሪ ነው አልተለመደም፡፡ በቅርቡ አንድ የአምቦ ውሃ ማስታወቂያ ሠርቻለሁ፡፡ አምቦ ውሃ በኢትዮጵያዊና በደቡብ አፍሪካዊ የተያዘ ስለሆነ፣ ስለማስታወቂያ ብሎ ስለሚያውቁ አሠሩኝ፡፡ ሌላው ባለፈው ሳምንት ለዘመን ባንክ አምባሳደር ሆኛለሁ፡፡ እሱም ቢሆን አመራሮቹ በአብዛኛው ዓለምአቀፍ አሠራር ስለሚያውቁ ነው፡፡ ቆመ እንጂ ቀደም ሲልም አረቄ ላይም ሠርቼ ነበር፡፡

ውስኪ አይደለም እንዴ?

አዎ! ውስኪ ነው ቆመ እንዴ? ለአንድ ዓመት ነበር ኮንትራቴ

የአየር መንገዱስ

እሱ እንኳን እኔ ከመጀመሪያው ከአየር መንገድ የተገኘሁ ስለሆነ ግዴታዬ ስለሆነ ነው የሠራሁት፡፡

ያለ ክፍያ

አዎ! ኧረ እባክ አንድ ነገር እንበል ሲሉኝ በነፃ ሠራሁ፡፡ እነሱ ግን 6 ቲኬቶች ሠጥተውኛል፤ ቀላል አይደለም፡፡ ከሲድኒ ኦሎምፒክ ስንመጣም 10 በረራዎች በነፃ ሰጥተውኛል፡፡ በነገራችን ላይ በ1980 ዓ.ም በባሌ፣ አርሲና ሸዋ የፓይሌት ፕሮጀክት ሲጀመር ደሞዝም ትጥቅም የማውቀው የአየር መንገድን ነው፡፡ ስለዚህ ለእነሱ በነፃ የመሥራት ግዴታ አለብኝ፡፡

በውጭ አገርስ

ያው አዲዳስ ነው፤ ከዚያ ውጭ በየውድድሩ በምትለብው ማሊያ ላይ የሚፃፈው ነው፡፡ አትሌቲክስ እንደ እግር ኳስና ቅርጫት ኳስ አይደለም፡፡ አትሌትቲክስ በአብዛኛው የሚታወቀው በምሥራቅ አፍሪካ ነው፡፡ ስፖንሰር የሚያደርጉ ድርጅቶች ደግሞ የመጀመሪያ ጥያቄያቸው በእነዚህ አገሮች ምን ያህል ምርት እሸጣለሁ የሚል ስለሆነ ብዙ ማስታወቂያ የለም፡፡

አሁን ሀብትህ ምን ያህል ይሆናል?

የሴት ዕድሜና የወንድ ሀብት አይጠየቅም

በማስታወቂያ ምን ያህል ታገኛለህ?

ነገርኩህ ‘ኮ ሀብት አይጠየቅም፡፡

እሺ ከማስታቂያ ገቢና ከአንድ ሕንፃ ኪራይ የቱ ይበልጣል

ሕንፃው የተሠራው ከማስታወቂያ ገንዘብ በላይ ነው፡፡ ውጭ አገር የማስታቂያ ክፍያ ጥሩ ነው፡፡ እዚህ ግን እንዲያው ለማለማመድ ነው እንጂ ይህን ያህልም የሚጠቅም አይደለም፡፡

በምንድነው የምትተዳደረው? ደሞዝ አለህ? ወይስ ካለው ላይ እየዘገንክ ነው?

ደሞዝ አለኝ፤ አሁን 11ሺህ ደርሶልኛል፡፡

ይበቃሃል?

በደሞዝ ብቻ የሚተዳደር አለ? እኔኮ ዓለም አቀፍ ሯጭም ነኝ፡፡ በጣም ብዙ ብር የሚያስፈለገው ወጣ ስትል ነው፡፡ እዚህ እንኳ ችግር የለም - 11ሺ ብር ብዙ  ነው፡፡ ወጣ ስትል አንድ ሆቴል አድረህ ስትወጣ ያልቃል፡፡

ዕለታዊ ወጪህ ምንድነው?

ኧረ ባክህ ተወኝ፡፡ ሰው እጋብዛለሁ፡፡ የቤት አስቤዛ አትጠይቀኝ፤ እኔን አይመለከተኝም፡፡ አንዳንድ ሰው ደግሞ ይመጣና ይጠይቅሃል፡፡

ለልጆችህ የኪስ ገንዘብ ትሰጣለህ

አልሰጥም፤ አልደረሱም. ገና ናቸው፡፡

ስንት ዓመታቸው ነው

ትልቋ 14 ዓመት ሊሆናት ነው፡፡ ቀጥሎ ያለችው 12 ከዚያ ቀጥላ ያለችው 10 የመጨረሻው ደግሞ ስድስት ዓመቱ ነው፡፡ የሚያስፈልጋቸው ነገር ይገዛላቸዋል፤ ት/ቤት የሆነ ነገር ሲኖር ይሰጣቸዋል፡፡ ከዚያ ውጭ በዚህ ዕድሜ ገንዘብ ያስፈልጋቸዋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ አሁን ገንዘብ ከሰጠኻቸው በምን እንደሚያጠፉት ማሰብ ይጀምራሉ፡፡ ትልቋ ከሦስትና ከአራት ዓመት በኋላ ያስፈልጋታል፡፡ ያኔ ለምን ለምን ማውጣት እንዳለባት ታውቃለች፡፡

የዕረፍት ጊዜህን በምንድነው የምታሳልፈው?

እኔ ሥራ ላይ ብሆን ነው የምመርጠው፡፡ ለነገሩ ምን ትርፍ ጊዜ አለኝ ብለህ ነው? ትንሽ ጊዜ (ቀዳዳ) ሳገኝ ከባለቤቴና ከልጆቼ ጋር መሆን ደስ ይለኛል፡፡ እነሱን ይዤ ወጣ እላለሁ፡፡ አሁን ሆቴሉ ከተከፈተ ወዲህ በጣም ከባድ ሆኗል፡፡ ለምን መሰለህ እታች ስለምወርድ እሁድ - ቅዳሜ ብሎ  የቢሮውን በር ከፍቶ ሲያይ እሱን ማነጋገር የሚፈልጉ ብዙ ተረኞች አየ፡፡

በቃ - በቃ፤ ሻይም አልጋበዝኩህም ብሎ ጨብጦኝ ተለያየን፡፡

 

 

Read 21447 times Last modified on Saturday, 18 February 2012 12:31