Saturday, 12 March 2016 10:27

እቃ ስላጣን አብረን በላን፤ እንጂ መች እኩያሞች ሆንን

Written by 
Rate this item
(19 votes)

በድሮው ዘመን አንድ አዛውንት እስር ቤት ይገባሉ፡፡ በዚያን ጊዜ እስረኞች እራሳቸው ባወጡት ህግ መሰረት፤ አዲስ ገቢ ሲመጣ ለእስር ቤቱ መኖሪያ ማዋጣት ያለበት ገንዘብ ነበር፡፡ የእስር ቤቱ የህዝብ ግንኙነት፤
“እንግዲህ በክፍላችን ህግ መሰረት ያቅምዎትን አዋጡ” አላቸው አዛውንቱን፡፡
አዛውንቱም፤
“ቤተሰቤ ምን ይስጠኝ ምን ሳላውቅ ይሄን ያህል አዋጣለሁ ማለት ያስቸግረኛል” አሉ፡፡
“ግዴለም ከመጣልዎት ውስጥ ይሄን ያህሉን እለግሳለሁ፤ ቢሉና ቃል ቢገቡ እንኳ በቂ ነው” አላቸው፡፡
ይሄኔ አዛውንቱ፤
“እስቲ አሳቤን በወግ ልግለጥ” አሉና፤ “ጥንት ጎጃም ውስጥ ሁለት ሴቶች ሜዳ ሊወጡ ከቤት ወደ ደጅ ይሄዳሉ፡፡ ቅዳሜ ለእሁድ አጥቢያ ማታ ነው፡፡
አንደኛዋ፤ ‹እንግዲህ አደራ፣ ነገ በተስኪያን ጠዋት ስንመጣ፣ አንቺ ከቀደምሽ አንቺ፤ እኔ ከቀደምኩ እኔ፤ ቀድመን ቦታ እንያዝ - እሴቶች መቆሚያ ቦታ› አለቻት፡፡
በተስኪያን ውስጥ ማልዶ መጥቶ ቦታ ካልያዙ ሰው ብዙ ስለሆነ ደጅ ሆኖ ማስቀደስ ግድ ስለሚሆን ቀድሞ መገኘት ዋና ነገር ነው፡፡ ይሄኔ፤ ሁለተኛይቱ ሴት፣ በሚያቅማማ ድምፅ፤
“እንግዲህ ማልዶ ቦታ ለመያዙም፣ በተስኪያን ውስጥ ገብቶ ለማስቀደሱም፤ ወንዶቹ እንዴት እንዳሳደሩን አይተን ነዋ!” አለች፡፡
(በዕምነታቸው መሰረት ከወንድ ተገናኝታ ያደረች ሴት፤ በተስኪያን ውስጥ መግባት ክልክል በመሆኑ ነው፡፡ ያ ደግሞ በድሮው ዘመን በተለይ የወንዱን ፍቃድና ፍላጎት የሚሻ ጉዳይ ነው!)
የእሥር ቤቱ አዲስ እስረኛ አዛውንት አሳሪዎቻችን (ወንዶቹ) እንዴት እንደሚያሳድሩን ሳናይ ‹እንዴት ብዬ ቃል ልግባላችሁ … ሊገድሉንምኮ ይችላሉ፤ በሰው እጅ ያለን ሰዎች ነን› ማለታቸው ነው!
*             *           *
በሰው እጅ ያለ ሰው በራሱ ለመቆም እጅግ ያዳግተዋል፡፡ በተለይ ፍትሕ በሌለበትና” “ንጉሥ የቆረጠው እጅ እንዳለ ይቆጠራል” በሚባልበት ዘመን ከሆነ፤ በማናቸውም ሰዓት ህይወት ስጋት ላይ መውደቋ የዕለት የሰርክ ጉዳይ ይሆናል፡፡ ካጠፉ ቅጣት አይቀሬ ነው! ዘረፋና ምዝበራ ሲበዛ ጥርጣሬ አንድ የማሰሪያ ቅድመ ሁኔታ መሆኑ አያጠያይቅም። በተለይ ህጋዊ ሽፋንን ተጠቅሞ ምዝበራውን የሚያካሂድ ሹም ራሱ መዝባሪ፣ ራሱ ጠርጣሪ ስለሚሆን በቀላሉ የሚደረስበት አይደለም፡፡ ከተደረሰበት ግን “የነብርን ጅራት አይይዙም ከያዙም አይለቁም” የሚባል መሆን ይኖርበታል፡፡ አያሌ ሹማምንት ከሙስናም ከፖለቲካዊ ሁኔታም ጋር በተያያዘ የሚገመገሙበት ሰዓት እነሆ ደረሰ፡፡ በማናቸውም የሥራ ኃላፊነት ላይ የተቀመጠ ሹም ማለትም ሚኒስትር፣ ኤክስፐርት፣ አማካሪ፣ ፖሊስ፣ ትራፊክ፣ ሳይንቲስት፣ ኦዲተር፣ የመሬት አስተዳዳሩ፣ የፖለቲካ መሪ፣ ካድሬ ወዘተ … እከሌ ከእከሌ ሳይባል የሚመረመሩበት፣ የሚፈተሹበት ወቅት መጣ፡፡ “ጊዜ የሥልጣን እጅ ነው” ይላሉ ፀሐፍት፡፡ የቪላ መዓት፣ የውድ ውድ መኪናዎች ጥርቅም፡፡ በዘር - ሐረግ የተያዘ መሬት ብዛት … አንድ የመንግሥት ሰራተኛ እንዴት ሊኖረው ይችላል? ብሎ መጠየቅ ማንም ጅል የማይስተው ነገር ነው፡፡ በሙስና የተገኘ ሐብት መሆኑ ከታወቀ ደግሞ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ መንግስትን መንግስት የሚያሰኝ ተግባር ነው፡፡ የመንግስት ሰራተኛ ከየትኛውም ነጋዴ ወይም ሀብት ያካበተ - ዜጋ ጋር በመመሳጠር ያንድ ጀምበር ባለፀጋ (nouveau riche ኑቮ ሪሽ እንዲሉ) ለመሆን የቻለበትን ሁኔታ ለማጣራት፣ መፈራራት ከሌለ በስተቀር፣ ያፈጠጠ ያገጠጠ ነገር ነው፡፡ ዛሬ በአገራችን ማናቸውም ሌብነት፣ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ የሚፈፅሙት፣ ስሙ “ቢዝነስ” ሆኗል፡፡ “ይሄኮ እልም ያለ ዘረፉ ነው” ሲባሉ “የሥራው ፀባይ ነው” ብሎ መመለስ እንደመመሪያ ተወስዷል፡፡ “የማይበላ ሰው” ፋራ መባሉም እንደ እለት ሰላምታ ተለምዷል፡፡
“ኢንቨስተሩ ከባንክ የወሰደውን ገንዘብ ለጥገኛ ጥቅም አውሎታል” ካልን፤ የደረስንበትን ማስረጃ ለፈጣን እርምጃ ማዋል መዘግየት የሌለበት ጉዳይ ነው፡፡ ያውም እስካሁን ካልረፈደ! በችሎታውና በሙያው የሚተዳደር እንደ ሐቀኝነት ነውር ሆኗል፡፡ እንዲህ ባለው ሁኔታ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ አሠራር ይኖራል ማለት እጅግ አስቂኝ ጨዋታና ስላቅ (irony)  ይሆናል፡፡ ዊንስተን ቸርችል፤ “የዲሞክራሲ ሥርዓት ከሌሎች ተሞክረው ከከሸፉ ሥርዓቶች ጋር ሲነፃፀር ነው እንጂ ደግ ነው የሚባለው፤ በራሱ ፍፁም ሥርዓት አይደለም” ይሉናል፡፡ ዲሞክራሲ እንደኛ ባለና በሙስና አዘቅት በገባ አገር ውስጥ ሲታሰብ እንዴት ውስብስብና አያዎአዊ (paradoxical) እንደሚሆን መገመት አያዳግትም፡፡ ከዚሁ ባልተናነሰ መልኩ፤ የመልካም አስተዳደርን አናሳነት፣ የጠንካራ ተቋማትን መጥፋት፣ ወገንተኝነትን፣ የዕውቀት መንማናነትን፣ አለመቻቻልን፣ ከልብ አለመነጋገርን፣ ራስ - ወዳድነትን፣ የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብት መታጣትን ወይም መሟሸሽን ወዘተ አክለን ስናስበው… “አይ ዲሞክራሲ እኔን ክንብል ያርገኝ!” ማለታችን አይቀርም፡፡ “አግዝፈው ያሞገሱት ለማማት ያስቸግራል” ነው ነገሩ፡፡ አሳሳቢ መንታ መንገድ ላይ ቆመን ነው ግምገማ እያካሄድን ያለነው። ሆኖም መገማገም ግዴታ ነው፡፡ አንዲት ክር ስትነካ አገሩ የሚታመስ ከሆነ ሁኔታውን መገምገም ግዴታ ነው፡፡
የተነካካውን ሰው ሁሉ ስናጠራ ጊዜ ማለፉ ደግሞ አይቀሬ ነው፡፡ ሆኖም በአቅም ካልፈጠንን ሁኔታዎች ሊቀለበሱ ይችላሉ ብሎ መስጋት ያባት ነው፡፡ ወትሮውንም ሰዎቹን እናውቃቸው ነበርኮ፡፡ “እቃ ስላጣን አብረን በላን፤ እንጂ መች እኩያሞች ሆንን” የሚለውን ተረት ስናሰላስል፣ የዛሬው የበሰለ ቀን እንዳያመልጠን ጠንክረን እንሥራ፡፡ ሙስና የድህነት አቻ ጠላት የሆነበት ሰዓት ደርሷልና!

Read 7727 times