Saturday, 05 March 2016 11:13

የሙዚቃ ኮንሰርትም እንደተቃውሞ ሰልፍ ይከለከላል!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(28 votes)

• የቴዲ አፍሮ ኮንሰርት ለ3ኛ ጊዜ የተከለከለበትን ምክንያት ማወቅ ናፈቀኝ!!
• የሙዚቃ ኮንሰርቱን ከአዲስ አበባ ይልቅ ናይሮቢ ማቅረብ ይቀላል
• “የከተማውን ትራንስፖርት ከታክሲ ተፅዕኖ ለማውጣት”… ታስቧል

  ከአራት ወራት በላይ የዘለቀው የኦሮምያ ተቃውሞና ግጭት (የፖለቲካ ቀውስ ሊባል ይችላል!) አሁንም ሙሉ በሙሉ አለመቆሙ በእጅጉ ያሳዝናል፡፡ አሁንም ሰዎች መሞታቸው … አሁንም ንብረት መውደም መቀጠሉ በእጅጉ ያሳዝናል፡፡ … አሁንም ወደ ወትሮ ህይወት … ወደ ወትሮ እንቅስቃሴ መመለስ አለመቻሉ በእጅጉ ያሳዝናል፡፡ … አሁንም የችግሩ መንስኤና መፍትሄ ፈፅሞ አለመታወቁ ደግሞ ከምንም የበለጠ ያስፈራል፡፡
እውነቴን ነው የምላችሁ … ተቃውሞና ግጭቱን በኃይልና በጉልበት ሳይሆን የህዝቡን ልብ በማሸነፍ የሚያበርድና የሚያረጋጋ ብልህ መሪ አለመገኘቱ ክፉ እርግማን ነው (ምርቃትማ ሊሆን አይችልም!!) ግዝቱ የሚፈራ የሃይማኖት መሪ … ቃሉ የሚከበር የአገር ሽማግሌ … የእርቅ ሃሳቡ የሚታመን የሰላም ተቋም … ፖለቲካዊ መፍትሄው ይሁንታን የሚያገን የፖለቲካ ፓርቲ የሌለበት ዘመን ላይ መድረሳችን በጣሙን ያሳዝናልም - በጣሙን ያሳፍራልም!! ለመጪው ትውልድ ምን ዓይነት አገር … ምን ዓይነት ኢትዮጵያ … ለማስረከብ እንደተዘጋጀን አንድዬ ይወቀው፡፡
ሰሞኑን  አባይ ኤፍኤም ህብረተሰቡን በኦሮምያ ክልል ችግሮችና መፍትሄዎች ዙሪያ ማወያየት እሰየው ያሰኛል። ህብረተሰቡ ስለ ችግሮቹ … ስለ መንግሥት ጥፋት … ስለ ካድሬዎች ሥራ ፈትነት … ስለ ሙስና ጥልቀት … ስለ መሬት ወረራ … ስለ በደል መብዛት …. ስለ ነፃነት መታፈን … ስለ ሁሉም ነገር … የልባቸውን መናገራቸው፣ የሆዳቸውን መተንፈሳቸው፣ የዳመነውን ድባብ ያፈካዋል። የአባይ ኤፍኤም የሰሞኑ “ሥልጡን ሥራ” ይቀጥል አይቀጥል ፈፅሞ አይታወቅም … (“ማምሻም ግን ዕድሜ ነው” አለ አበሻ!)
በነገራችን ላይ ሰሞኑን አባይ ኤፍኤም በኦሮምያ ችግሮች ዙሪያ ህብረተሰቡ ሃሳቡን በነፃነት የሚተነፍስበት ዕድል መፍጠሩ ለብዙዎች “ሰርፕራይዝ” እንደሚሆን እሙን ነው፡፡ (እስኪለመድ እኮ ነው!) በእርግጥ ባህሉ በቅጡ እስኪዋሃደን ድረስ ጊዜ ሊወስድ ይችላል፡፡ (ዲሞክራሲም ሆነ ነፃነት በአንድ ጀንበር አይመጣም!) ግን ሁሌም ወደፊት እንጂ ወደኋላ መመለስ የለብንም። እናላችሁ … ነፃ ሚዲያዎች … እየጎለበቱ በመጡ ቁጥር ፊታችንን ወደ “ቪኦኤ” ወይም ወደ “ኢሳት” የምናዞርበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ሌላው ቀርቶ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም የውጭ ሚዲያ የሚጠቀሙት ወደው አይደለም፤ የህዝብ ሃብት ናቸው የሚባሉት እነ ኢቢሲ፤ … በራቸውን ስለከረቸሙባቸው ይመስለኛል፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት ለምን ለኢሳት ቃለ ምልልስ እንደሚሰጡ ሲገልፁ፣ “ኢህአዴግ ቴሌቪዥኑን በሞኖፖል ያዘው፤ እኛ ከህዝባችን ጋር በምን እንገናኝ?” ብለው ነበር፡፡ (ተቃዋሚዎች በመንግስት ሚዲያ ይጠቀሙ አይጠቀሙ በሚለው ዙሪያ ለምን ‹ዲቤት› እና ‹ሪፍረንደም› አይደረግም?!)
እውነቴን እኮ ነው … በተቻለን አቅም ችግሮቻችንን ሁሉ በውይይት - በክርክር፣ ባስ ሲልም በህዝበ ውሳኔ የመፍታት ባህል በእጅጉ ያስፈልገናል፡፡ (ግን መቼ ነው ወደ 21ኛው ክ/ዘመን የምንገባው?!)
እኔ የምላችሁ … የሰሞኑን የታክሲዎች አድማ እንዴት አያችሁት? (የ“ጎሪጥ” የሚለው አባባል አልፎበታል!) እውነቱን ልንገራችሁ አይደል … ለእኔ ከአድማው ይልቅ የበለጠ ትኩረቴን የሳበው የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የወሰደው ከብርሃን የፈጠነ እርምጃ ነው፡፡ (አዎንታዊ እርምጃ እኮ ነው!) በ2003 ዓ.ም ፀድቆ ሳይተገበር ከ5 ዓመት በኋላ ወደ ዘንድሮ የተላለፈው አዲሱ የመንገድ ደህንነት ደንብ (የታክሲ ሹፌሮች ከጭራቅ ለይተው አያዩትም ይላል!) ዕድለቢስ ይመስለኛል፡፡ ያኔም ተሞክሮ ቆመ፤ አሁንም ተሞክሮ ቆሟል፡፡ ለአንድ ሳምንት ብቻ! የታክሲ ሹፌሮች ደንቡን በመቃወም የ2 ቀናት የሥራ ማቆም አድማ ሊያደርጉ እንደሆነ መረጃ የደረሰው የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ከመቅፅበት የደንቡን ተፈፃሚነት ለ3 ወራት ማራዘሙን አስታውቋል (የ3 ወር አድማ በሉት!) በነገራችን ላይ ውሳኔው አስገራሚ ቢሆንም እኔ ግን በቢሮው ፈጣን እርምጃ ተደምሜአለሁ፡፡ ለምን መሰላችሁ? ሌላኛው አማራጭ ቢያንስ ለእኔና ለናንተ ፍትሃዊ አይሆንም፡፡ ይታያችሁ … የስራ ማቆም አድማውን ያደረጉ የታክሲ ሹፌሮች ላይ በህግ ያልተቀመጠ እርምጃ ሊወስድባቸው ሁሉ ይችል ነበር፡፡ በእርግጥ ቢሮው የደንቡን ተፈፃሚነት ለ3 ወራት ያራዘመውም ሆነ የሥራ ማቆም አድማ ባደረጉት ታክሲዎች ላይ እርምጃ ከመውሰድ የተቆጠበው ኢ - ፍትሃዊ ላለመሆን ብሎ አይደለም፡፡ አንዳንዶች እንደሚሉትም፤ ሆደ - ሰፊ ለመሆን አምሮትም አይደለም፡፡ (ድንገት ሆደ ሰፊ አይኮንማ!) እናላችሁ … ቢሮው የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ዘርፍ በቋፍ ላይ መሆኑን ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ስለዚህም እርምጃ በመውሰድ ተጨማሪ ምስቅልቅል በመፍጠር ራሱን ተጠያቂ ማድረግ አይሻም፡፡ እናም በደንቡ ላይ የ3 ወር አድማ ለማድረግ ወሰነ ቢሮው፡፡
በነገራችን ላይ የአዲስ አበባ የታክሲ እጥረት መከሰት የጀመረው የኢህዴግ መንግስት እንደ ደርግ የታፔላ (ቀጣና) አሰራር በታክሲዎች ላይ እንዲተገበር ከወሰነ በኋላ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የታክሲ አሽከርካሪዎች እንደጉድ ይፈሩታል የተባለው የመንገድ ደህንነት ደንብ ለ3 ወር የተራዘመበትን ምክንያት ቢሮው ሲያብራራ ብትሰሙ … በእጅጉ ትገረማላችሁ፡፡ በእነዚህ 3 ወራት ጊዜ ውስጥ አሽከርካሪዎች አዲሱን ደንብ ተፈፃሚ ለማድረግ እንቅፋት ናቸው በሚል የዘረዘሯቸውን ችግሮች ለመፍታት ከታክሲዎች ጋር ከስምምነት ላይ ደርሶ ነበር ይባላል፡፡ (ችግሮቹ ቅዠት ሳይሆኑ እውን ናቸው ማለት ነው!) እንዲያ ከሆነ ታዲያ ቢሮው ቀድሞውኑስ ደንቡን ለመተግበር ለምን ተጣደፈ? ታክሲዎች አድማ ያደርጋሉ ብሎ አልገመተማ! (ራሱን እኮ ነው የሸወደው!)  
በ97 ምርጫ ማግስት ምርጫው ተጭበርብሯል በሚል መጠነ ሰፊ የስራ ማቆም አድማ ያደረጉት ታክሲዎች፣ ከአድማው ማግስት ጀምሮ ከመንግስት ጋር ሆድና ጀርባ ሆነዋል ይላሉ ምንጮች፡፡ አሁንም ግን ያው ነው ተብሏል፡፡ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ሰሞኑን በአዲሱ ደንብና በታክሲዎች አድማ ዙሪያ በሰጡት መግለጫ፤ “ዓላማችን የትራንስፖርት ዘርፉን ከታክሲዎች ተፅዕኖ ማላቀቅ ነው” ብለዋል፡፡ (ከዚህ በላይ ሆድና ጀርባ የለም እኮ!)
የአፍሪካ መዲናዋ አዲስ አበባ ዘወትር እንዲህ ባሉ ችግሮችና ውዝግቦች የተሞላች ናት፡፡ በነገራችሁ ላይ የአዲስ አበባ አስተዳደር ፈቃድ ባይከለክል ኖሮ፣ ዛሬ ማታ በጊዮን ሆቴል የቀለጠ የሙዚቃ ኮንሰርት ሊካሄድ ታቅዶ እንደነበር ታውቋል፡፡ ዝነኛው ድምፃዊ ቴዲ አፍሮ የሚያቀነቅንበት!! (ኮንሰርትም እንዴ!) የሙዚቃ ኮንሰርቱ ፈቃድ ሲነፈገው ለ3ኛ ጊዜ መሆኑን በፌስቡኩ የገለፀው ድምፃዊው፣ በጳጉሜ 2007 በዘመን መለወጫ በዓል ዋዜማ በላፍቶ ሞል ሊቀርብ የነበረው ዝግጅትና በመስከረም 16 ቀን 2008 ለመስቀል በዓል በተመሳሳይ ስፍራ “በሰባ ደረጃ ወደ ፍቅር” በሚል ስያሜ ሊካሄድ የታቀደው  ኮንሰርት “ከሚመለከተው አካል” ተገቢውን ፈቃድ ባለማግኘቱ መሰረዙን አስታውሷል፡፡ (“የሚመለከተው አካል”ግን ማነው?)
በተመሳሳይ ሁኔታ የዛሬው የቴዲ አፍሮ ኮንሰርትም የክልከላ ሰለባ መሆኑ ታውቋል፡፡ ቴዲ አፍሮ፤ በተፈጠረው ክስተት ወዳጆቹንና አድናቂዎቹን ከፍ ያለ ይቅርታ ጠይቋል - በፌስቡኩ፡፡ (ይቅርታ መጠየቅ የነበረበት እኮ ከልካዩ ነው!!)
እናላችሁ … የቴዲ አፍሮ ኮንሰርት ለ3 ተከታታይ ጊዜያት ምክንያቱ ሳይታወቅ መከልከሉን ስንሰማ እንቆቅልሽ ሊሆንብን ይችላል፡፡ ያውም የማይፈታ እንቆቅልሽ! (“የቤቶች” ድራማዋ አዛሉ “አደጋ አለው!” አለች!) እናንተም እንደኔ ከሆናችሁ እንግዲህ “የሚመለከተው አካል” የቴዲን ኮንሰርት የከለከለበትን ምክንያት ለማወቅ ትጓጓላችሁ ብዬ እገምታለሁ፡፡ (ከከልካዩ በቀር ሁሉም መጓጓቱ አይቀርም! እንግዲህ እንቆቅልሹ እስኪፈታ ድረስ እጅን አጣምሮ ከመቀመጥ ይልቅ ደህና ስፖንሰር ፈልጎ የቴዲ አፍሮን ቀጣይ የሙዚቃ ኮንሰርት በናይሮቢ ማካሄድ ሳይቀል አይቀርም። (የባሰ አታምጣ ነው)

Read 10197 times