Saturday, 05 March 2016 11:09

አስወርተህ ሹመኝ፣ ዘርፌ አበላሃለሁ (ኣውሪኻ ሽመኒ፣ ዘሪከ ከብልኣካ)

Written by 
Rate this item
(19 votes)

ከኤዞፕ ተረቶች አንዱ እንዲህ ይላል፡-
ከዕለታት አንድ ቀን፣ አንዲት የተራበች ቀበሮ፣ በአንድ ውስጡ ባዶ በሆነ ግንድ ውስጥ እየኖረች ከመንገድ ሲመለሱ ሊበሉት ያስቀመጡትን ዳቦና ስጋ ታገኛለች፡፡
በጣም እየተስገበገበች እዚያ የተቦረቦረ የግንድ ስንጥቅ ውስጥ ገብታ እንደ ጉድ ትውጠው፣ ትሰለቅጠው ገባች፡፡ ያንን ዳቦና ስጋ በላች በላችና ሆዷ እንደ ከበሮ ተነረተ፡፡ አስቀድማ በቀላሉ ገብታበት የነበረችው ቀዳዳ አሁን በጭራሽ የሚሞከር አልሆነም፡፡ ሆዷን ብትጨምቀው እጅ እግሯን ብታጥፈው በምንም ዓይነት ለመውጣት የምትችልበት ዘዴ ጠፋ፡፡ በምሬት እየተንሰቀሰቀች፤
“አወይ የክፉ ቀን
አወይ የአበሳ ቀን
መከራው መርዘሙ
እንኳን መወፈሩ ያቅታል መክሰሙ
የገቡበት በራፍ
አርቡ ጠቦ ጠቦ
አላሳልፍ ይላል መውጫውን ገድቦ!”
ቀበሮ እንዲህ እያለች ስታለቅስና ዕጣ - ፈንታዋን ስታማርር፤ በአጋጣሚ በዚያው ግድም የሚያልፍ አንድ ቀበሮ፤ “ምን ሆነሽ ነው የምታለቅሺው እመት ቀበሮ?” ሲል ይጠይቃታል
እመት ቀበሮም፤
“ሳይቸግረኝ እዚህ ግንድ ውስጥ ገብቼ፣ የእረኞቹን ስንቅ በልቼ በልቼ ሆዴ ተነፍቶ፣ ሰውነቴ ተወጣጥሮ በጭራሽ ከገባሁበት መውጣት አቃተኝ፡፡ ምን እንደማደርግ መላው ሲጠፋኝ፣ ይሄው እያለቀስኩኝ አምላኬን አውጣኝ ብዬ በእንጉርጉሮ እለምናለሁ፡፡”
አያ መንገደኛ ቀበሮም፤
“የእረኞቹን ስንቅ መብላትሽ ደግ አላደረግሽም፡፡ የሰው ንብረት መውሰድ ምን ጊዜም ዋጋ ያስከፍላል፡፡ መፀለይ ያለብሽ እረኞቹ ከሄዱበት በቶሎ እንዳይመለሱ ነው፡፡ ያ ካልሆነ እዚያው ባለሽበት ቆዪ፡፡ ወደ ዱሮው ከሲታ አካላትሽ ትመለሺያለሽ፡፡ ከዚያ ትወጫለሽ” ብሏት መንገዱን ቀጠለ፡፡
*   *   *
የሰው ንብረት መዝረፍም፣ ማስዘረፍም ዋጋ ያስከፍላል፡፡ አንዴ ከተቆዘሩበት በቀላሉ ከስቶ ወደነበሩበት መመለስ የአንድ ጀምበር ጉዳይ አይደለም፡፡ ይዋል ይደር እንጂ የህዝብ ዐይን ማንንም ከተደበቀበትም ይሁን ከተኮፈሰበት ሥፍራ መንጥሮ ያወጣዋል፡፡ መረብም ካለ ቋጠሮው መፈታቱ አይቀርም! “አንተ፤ ብሳና ይሸብታል ወይ?” ብሎ ቢጠይቀው፤ “ለዛፎች ሁሉ ያስተማረው ማን ሆነና?” የሚለው የሩሲያውያን አነጋገር ትልቁንም ወንጀለኛ ትንሹንም ወንጀለኛ፣ ድሮውንም ሙልሙሉንም፣ እንድናይ ያግዘናል፡፡ አለቃም ሆነ ምንዝር ተጠያቂነት ሊዳስሰው ይገባል፡፡ በሀገራችን በተደጋጋሚ ከታዩት ችግሮች አንዱ ሰሞነኛነት ነው፡፡ ለአንድ ሰሞን ዘመቻ ማጧጧፍ! ለአንድ ሰሞን ዘራፍ ማለት! ቆይቶ ሁሉንም መርሳት! ወንጀል ይሥሩም አይሥሩም የፊተኞቹ ብቻ “ሰለባ” ሆነው ይቀራሉ፡፡ ይህን አባዜ መገላገል አለብን፡፡ ፍትህ ዘላቂ ጎዳና ላይ መውጣት አለበት፡፡ እንደ ውሃ ማቆርም የአንድ ሰሞን ዜና መሆን የለበትም፡፡ የአገር ጉዳይ “ፉርሽ ባትሉኝ!” የሚባልበት የልጆች ጨዋታ አይደለም፡፡ የሚወሰዱ እርምጃዎች አመርቂ መሆን አለባቸው፡፡ ለውጥ መምጣት ካለበት በአገም ጠቀም አይሆንም፡፡
ደራሲ ተክለፃዲቅ መኩሪያ ስለግል ታሪካቸው ሲፅፉ፤ እግረ - መንገዳቸውን ስለ አፄ ኃይለ ሥላሴ ሹማምንት ያነሳሉ፡፡ ከነዚህ መካከል የፀሀፊው ትዕዛዝ ወልደጊዮርጊስን ከሥልጣን መገለል ሲናገሩ እንዲህ ይላሉ፡-
“የበላይ ያደባይ ነውና፤ ፀሐፊ ትዕዛዙ ተዋርደው፤ ግማሽ ሹመት፣ ግማሽ - ግዞት ተደርጎላቸው፣ ወደ አርሲ ተላኩ፡፡”
አካሄዱ ጊዜው የፈቀደው ሆኖ ሊሆን ይችላል፡፡ ዛሬ “ግዞት” ቃሉም ጠፍቶ ሳይሆን አይቀርም፡፡ “ግማሽ - ሹመት ግማሽ - ግዞትም” በረቂቅ ዘዴ ካልሆነ ለሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ማገልገሉ አጠራጣሪ ነው! መልካም አስተዳደር መልካም አስተዳዳሪ ይፈልጋል፡፡ በስልጣን የሚመኩ መልካም አስተዳዳሪ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ “ብቆጣም እመታሻለሁ፣ ብትቆጪም እመታሻለሁ” ዓይነት ዕብሪት ያለባቸው ሹማምንት፤ መልካም አስተዳደር ሊያሰፍኑ ከቶም አይችሉም፡፡ “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል” የሚሉ ከመልካም አስተዳደር ሩቅ ናቸው፡፡ በጥበትም ይፈረጁ በትምክህት ቀናነት የሌላቸው መልካም አስተዳደርን  አይወርሱም፡፡ አያወርሱም፡፡ ኩራትና ትዕቢት የመልካምነት ፀር ናቸው!
ደራሲ ከበደ ሚካኤል ስለ እንደነዚህ ዓይነት ባለሥልጣናት ሲገጥሙ እንዲህ ይሉናል፡-
“ኩራትና ትዕቢት የሞሉት አናት
ሰይፍና ጎራዴ የመቱት አንገት
አይገላገሉም እንዲህ በቀላሉ
እመሬት ላይ ወድቀው ሳይንከባለሉ!!”
ዕውነትም ዛሬ መሬት መንከባለያ ሆኗል፡፡ የመሬት አስተዳደር ዓይነተኛ መጠያየቂያ ፈተና፤ ዋና ጉዳይ ሆኗል፡፡ በመሬት ዙሪያ የሚፈፀመው ሙስና ደሀውን ያስለቀሰ፣ ጌታውን ያለቅጥ ያስፈነጠዘ፣ የምዝበራዎች ሁሉ ጉልላት ነው፡፡ በሀገራችን የመሬት ኢ-ፍትሐዊ ብዝበዛ ጉዳይ ዛሬ ሳይሆን ትላንት ከትናንት በስቲያ ፈጦ ናጦ ወጥቷል” “በሕግ አምላክ!”፣ “የመንግስት ያለህ!” እያልን ስንጮህበት የነበረ ነው፡፡ በርካታ ሹሞች ከሥልጣን ወደ ሌላ ሥልጣን እየተዛወሩ ሽፋን ያገኙበት ነው፡፡ ላጠፉት ይጠየቃሉ ሲባል ሌላ ሹመት የወረሱበት ነው፡፡ አሁን እየተወሰደ ያለው እርምጃ ለኢትዮጵያ አልረፈደም፡፡ ተመስገን የሚባል ነው፡፡ ሙስና እንደ ናይጄሪያ፣ እንደ ኬንያ፣ አልናጠጠብንም ብሎ መፅናናትም ያባት ነው፡፡
ይህ ማለት ግን በዚያ መንገድ ላይ አይደለንም ማለት አይደለም፡፡ ካልገደብነው እነዚያ አገሮች የደረሱበት የማንደርስበት፣ አልፈንም የማንሄድበት አንዳችም ምክንያት አይኖርም፡፡ “እናቴ፤ በእንቁላሉ ጊዜ በቀጣሽኝ በሬ ሰርቄ ባልታሰርኩ” ያለውን ሰው ልብ ብሎ ማሰብ ብቻ ነው የሚያስፈልገው፡፡
“ሞኞች ናቸው
ዳኞች ሞኞች ናቸው
ዋስ ጥራ ይላሉ
ከነዋሱ ቢሄድ፣ ማንን ይይዛሉ፡፡”
የሚለውን የቀረርቶ ግጥም አለመዘንጋትም ብልህነት ነው! አንድ መሰረታዊ ጉዳይ ግን አለመርሳት ዋና ነገር ነው፡፡ ይኸውም ዛሬ እጃቸው በሙስና ውስጥ ተነክሮ ያሉ አለቃና ምንዝሮች እንደምን ለሥልጣን በቁ? እንደምን አለቃ ሆኑ? ሿሚና አስሿሚ፣ ዕድገት ሰጪና ተሰጪ ምን ሰንሰለት አላቸው? እከክልኝ ልከክልህ ምን ሚሥጥር አለው? ይሄን መፈተሽ ተገቢ ነው፡፡ “አስወርተህ ሹመኝ፣ ዘርፌ አበላሃለሁ” የሚለው ተረት ትልቅ ቁምነገር እንዳለው የምናየው እዚህ ላይ ነው!!

Read 7418 times