Saturday, 27 February 2016 12:01

ምርጫ በአፍሪካ፣ ምርጫ በአሜሪካ

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(19 votes)

• አምባገነኖች፤ ቤተመንግስት በዕጣ የደረሳቸው ኮንዶሚኒየም ይመስላቸዋል
• ዲሞክራሲ ለአሜሪካውያን ኦክስጂን፣ ለአፍሪካውያን ውድ ጌጥ ነው


የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ክርክር (ፉክክር) በጣም ተመቸኝ፡፡ ፉክክሩ የሃይል ወይም የጉልበት ሳይሆን የሃሳብ፣ የዕውቀት፣ የብልጠት፣ የብስለት፣ የመራጩን ህዝብ ልቡና የመግዛት ---- በመሆኑ ደስ ይላል፤ ያስቀናል፡፡ የዳበረ የዴሞክራሲ ባህል፣ ስልጡን ፖለቲካዊ አስተሳሰብ፣ለግለሰቦች መብትና ነጻነት የቆመ ሥርዓት፣ አገሩን የዓለም ፊታውራሪ ለማድረግ ምሎ የሚገዘት እጩ ተወዳዳሪ ---- እኒህ ሁሉ ያሉባት ናት አሜሪካ፡፡ ቀላል ትመቻለች!!
  እውነቱን ልንገራችሁ አይደል------በየማታው በአሜሪካ ዕውቅ ኮሌጆች የሚካሄዱትን የጦፉ የምርጫ ክርክሮች ስከታተል፣ በስሜት ከመወሰዴ የተነሳ ለዚያች ቅጽበት አገሬ አሜሪካ፣ ዜግነቴ አሜሪካዊ የሆነ ሁሉ ይመስለኛል፡፡ እናም ስንት ቀን መሰላችሁ----ከእጩ ፕሬዚዳንታዊ ተፎካካሪዎች መካከል ---- (ከእነ ዶናልድ ትረምፕ፣ ቴድ ክሩዝ፣ ማርኮ ሩቢዮ፣ ጄብ ቡሽ፣ ዶ/ር ቤን ካርሰን) ----- ለመጨረሻው የዋይት ሃውስ ፉክክር መድረስ አለበት ያልኩትን እጩ የመረጥኩት፡፡ እንዴት ቀልቤን ቢማርኩኝ ይሆን? (God bless America!)
 ክርክራቸው አልቆ ወደ ቀልቤ ስመለስ ----- አገሬ ትዝ ትለኛለች፡፡ አገሬ ታሳዝነኛለች፡፡ አገሬ ታስቆጨኛለች፡፡ አገሬ ታስመርረኛለች፡፡ አንዳንዴ በእርዳታ ከሚለግሱን ዶላር እየቀነሱ ከሥልጣኔያቸው ---- ከዲሞክራሲያቸው ----- ከሳይንሳቸው ----- ከቴክኖሎጂያቸው ---ቢያበድሩን ብዬ እመኛለሁ፡፡ የብድር ሥልጣኔ፣ የብድር ዲሞክራሲ----- (የኛ አገሩ ሂደት ብቻ ሆነብኛ!) ይሄ ሁሉ የማይሆን ከንቱ ቅዠት መሆኑን ስረዳ ----- ወደ ቅናቴ እመለሳለሁ፡፡ ያለ አቅሜ ተንጠራርቼ እቀናለሁ፡፡ ለጊዜው እሱ ሳይሻል አይቀርም!! ቅናት ----
አንድ የገባኝ ነገር ምን መሰላችሁ ---- እንደ አሜሪካውያን አገሩን የሚወድ የለም፡፡ (በፈለጋችሁት እንወራረድ!)  ከምር ነው ፍቅራቸው፡፡ ግን ስልጡን ነው፡፡ የኛ ግን እንደ  ፖለቲካችን ነው - ኋላቀር! (ያልሰለጠነ ፍቅር!) የውሸት ቅልቅል! የተቀሸበ ፍቅር! እውነተኛውንማ ------እነ እምዬ ምኒልክ በልባቸው ሸክፈው ሳይወስዱት አልቀረም፡፡ (ሰማይ ቤትም ቢሆን ያለ ጦቢያ ፍቅር አይችሉትም!)  
በነገራችሁ ላይ በአሁኑ ሰዓት ከሪፐብሊካን እጩ ተፎካካሪዎች ውስጥ በአንደኝነት እየመሩ ያሉት የሪል እስቴት ከበርቴው ዶናልድ ትራምፕ ናቸው፡፡ ወደ ምርጫ ፉክክር ከመጡ ጀምሮ እንዳሻቸው በመናገር አወዛጋቢ ሆነው ቆይተዋል። ተፎካካሪዎቻቸውን He is nasty, he is a loser, በማለት ማጥላላት የሚያዘወትሩት ትረምፕ፤ አሜሪካ ከሜክሲኮ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር በረዥም ግንብ አሳጥራለሁ፣ ህገወጥ የሜክሲኮ ስደተኞችን ወደ አገራቸው አባርራለሁ፣ አይሲስ የተባለውን አሸባሪ ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እደመስሳለሁ፣ በአጠቃላይ የአሜሪካን ልዕለ ሃያልነት አስጠብቃለሁ----እያሉ ነው ለዚህ ውጤት የበቁት፡፡ ትረምፕ በአንደበተ ርዕቱነት፣ በፖለቲካ ብስለት፣በሰለጠነ አነጋገር ---- ከአብዛኞቹ ተፎካካሪዎቻቸው የሚልቁ አይደሉም፡፡ እናስ ---- የአሜሪካውያንን ልቡና በምን ረቱት? በወኔ ነው ---- በአገር ፍቅር ስሜት! የዶናልድ ትረምፕ የማሸነፍ ምስጢር ደጋግመው÷ “አሜሪካን ዳግም ታላቅ አገር አደርጋታለሁ!” ማለታቸው ነው ብላለች፤አንድ ታዋቂ የአሜሪካ ጋዜጠኛ፡፡
 የማወዳደር ጉዳይ ነው እንጂ በሁሉም እጩ ተፎካካሪዎች ላይ የሚጋባ የሚመስል ጥልቅ የአገር ፍቅር ስሜት ይንቀለቀላል፡፡ ዲሞክራት በሏቸው ሪፐብሊካን----አገራቸውን ይወዷታል፤ያመልኳታል። ከፓርቲ በፊት አሜሪካዊነት ይቀድማል ይላሉ - ቃል በቃል፡፡ (ኢህአዴግነት ይቀድማል ኢትዮጵያዊነት? እንደማለት ነው!)
እኔ የምለው --- ይሄንን የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ የምርጫ ክርክር ከኢህአዴግ ይሁን ከተቃዋሚ የሚከታተለው ይኖር ይሆን? (አብደው ነው?!)
አሁን በቀጥታ ወደ አፍሪካ ልወስዳችሁ ስለሆነ ምቾታችሁ ከፍተኛ መንገራገጭ ቢገጥመው እንዳይገርማችሁ፡፡ ከአሜሪካ ወደ አፍሪካ እኮ ነው፡፡ ከምርጫ ወደ ቡጥጫ፡፡ ከነጻነት ወደ ባርነት፡፡ ከገነት ወደ ሲኦል፡፡ ወድጄ ግን አይደለም፤ ወዳጆቼ፡፡ ወደ እናት ክፍላችን እንመለስ ብዬ ነው፤ ወደ አፍሪካ፡፡
 እናላችሁ ---- እቺን ምስኪን አህጉር ዛሬም በ21ኛው ክ/ዘመን አንቀጥቅጠው የሚገዟት ሥልጣኔና ዲሞክራሲ አለርጂክ የሆነባቸው አምባገነን አዛውንቶች ናቸው፡፡ (ቤተመንግስት በዕጣ የደረሳቸው ኮንዶሚኒየም የሚመስላቸው!) ለነገሩ አሁን ሙጋቤ ከቤተመንግስት ቢባረሩ መኖሪያቸው የት ነው? ለሳቸውና መሰሎቻቸው ቤተመንግስት በእርግጥም ኮንዶሚኒየም ነው፡፡ ለዚህ እኮ ነው ምርጫ በመጣ ቁጥር ያልተገመተ ሃሪኬን ወይም ሱናሚ የሚያስመስሉት፡፡ በእርግጥም አገሩን ለማይወድ አምባነን መሪ ከሥልጣን መውረድ የሱናሚዎች ሁሌ ሱናሚ ነው፡፡ (የእግዜር ቁጣ በሉት!)
እኔ የምላችሁ… እነ ሙጋቤ ከሥልጣናቸው ነቅነቅ እንኳን ሳይሉ ስንት የአሜሪካ ምርጫ ተካሂዶ፣ስንት ፕሬዚዳንቶች ተፈራረቁ? “ሥልጣንን የዕድሜ ልክ አታድርጉት” በማለት የአፍሪካ አምባገነኖች ላይ ታሪካዊ ተጽዕኖ ለመፍጠር የሞከሩት ኦባማ ራሳቸው፤ ከዋይት ሀውስ ሊወጡ አንድ ሃሙስ ነው የቀራቸው፡፡ (ዲሞክራሲ ለአሜሪካውያን ኦክስጂን፣ለአፍሪካውያን  ግን ውድ ጌጥ ነው!)
ኦባማ፤ መሪዎቹን በሥልጣን ጉዳይ ለመምከር የሞከሩ ጊዜ እነሙሴቪኒ፣ ካጋሜ፣ ሙጋቤ ወዘተ… በየቤተመንግስታቸው (ማለቴ ኮንዶሚኒየማቸው) አድፍጠው እንዴት እንደተሳለቁባቸው አልታያችሁም? (ኦባማ እኮ ሰው አገኘሁ ብለው ነው) ከዚያስ ምን ሆነ? የሆነውማ… ሙጋቤ ሥልጣናቸውን ለሚስታቸው ይሁን ለሴት ልጃቸው ያወርሳሉ ሲባል የነበረው እንኳ ቀረ፡፡
 የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት የ58 ዓመቱ ፖል ካጋሜ ደግሞ ከሁለት ጊዜ በላይ በሥልጣን ላይ መቆየት የሚገድበውን ህግ ለመቀየር ህዝበ ውሳኔ አካሄዱ። በውዴታ ይሁን በግዴታ ባይታወቅም 98 በመቶ ሩዋንዳውያን የስልጣን ዘመን ገደቡ እንዲነሳ ድምጽ ሰጥተዋል፡፡ እናም ካጋሜ እስከ 2034 በስልጣን ላይ መቆየት እንደሚችሉ አረጋገጡ - 86 ዓመት እስኪሞላቸው ማለት ነው፡፡ አሜሪካ በካጋሜ ውሳኔና እርምጃ ብትከፋም ፕሬዚዳንቱ ግን “የውጭ መንግስታት መከፋት እኔን አያስጨንቀኝም” ብለዋል፡፡ (የሚያስጨንቃቸውንማ በእጃቸው አስገቡ!!)
የኡጋንዳው መሪ ዩዌሪ ሙሴቪኒም ባለፈው ሳምንት በአገራቸው በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ  ከ60 በመቶ በላይ በሆነ ድምጽ ለ5ኛ ጊዜ ማሸነፋቸውን ብሄራዊ የምርጫ ኮሚሽን አስታውቋል። (ባሸንፍም ድምጽ አንሶኛል አለማለታቸው!!) ኡጋንዳን ለ30 ዓመታት አንቀጥቅጠው የገዙት ሙሴቪኒ፤ ከምርጫው በፊት በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ባደረጉት ንግግር፤ “ኡጋንዳን ለመምራት ከእኔ ውጭ ብቃት ያለው የለም” ብለው ነበር፡፡ (ደግነቱ አሸነፉ!)  
 በርግጥ ይህቺ ከ60 ፐርሰንት በላይ የሆነች ድምጽ በህዝብ ተወዳጅነት ብቻ የተገኘች አትመስልም፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት የበዛ ወከባ፣ እስርና አፈና ውጤት ናት፡፡ ከምርጫው በፊትና በኋላ የኡጋንዳ ነፃ ሚዲያዎች በእስር…በወከባ --- በመዘጋት በመከፈት መከራቸውን በልተውበታል፡፡ የኡጋንዳውያን መብትና ነፃነት ተገብሮበት ነው የ72 ዓመቱ ሙሴቪኒ የቤተመንግስት ሌጋሲያቸውን ያስቀጠሉት (ለሳቸው ኮንዶሚኒዬም ሊሆን ይችላል!)
ከ7 የሙሲቪኒ ተፎካካሪዎቻቸው መካከል 35.4 በመቶ ድምጽ በማግኘት 2ኛ ደረጃን ያገኙት የፎረም ፎር ዲሞክራቲክ ቼንጅ መሪ ኪዛ ቤሲጅዬ፤ በዚህ ሳምንት ብቻ 3 ጊዜ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለው እንደነበር የዘገበው ቢቢሲ፤ አሁንም በቤታቸው የ“ቁም” እስረኛ መደረጋቸውን ጠቁሟል። ምርጫው መጭበርበሩን የገለፁት ቤሲጅዬ፤ ውጤቱም ተቀባይነት እንደሌለው አስታውቀዋል፡፡ የቀድሞው የአገሪቱ ጠ/ሚኒስትር፣ የአሁኑ የሙሴቪኒ ተቀናቃኝም ምርጫው ተጭበርብሯል በማለት ውግዘትና እርግማን አውርደዋል፡፡ “የምርጫው ውጤት የህዝቡን ፍላጐት አያንፀባርቅም” ብለዋል - ተቀናቃኙ ለቢቢሲ፡፡ (የህዝቡ ፍላጐት እንዲንፀባረቅ መች ተፈለገ?) የኡጋንዳን የዘንድሮ ምርጫ የታዘበው አውሮፓ ህብረት ባወጣው ሪፖርት፤ ምርጫው ግልጽነት እንደሚጎድለው ጠቁሟል፡፡ በምርጫው ዕለት በመራጮችም ሆነ በእጩ ተወዳዳሪዎች ላይ የፍርሃት ድባብ መፈጠሩንም ቡድኑ ገልጿል፡፡
 ከሁሉም በላይ ብዙዎቹን ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋቾች ያስቆጣው ግን መንግስት የምርጫው ዕለት ፌስቡክና ትዊተርን የመሳሰሉ ማህበራዊ ሚዲያዎችን መዝጋቱ ነው፡፡ ምክንያቱን ሲጠየቅም፤ብሄራዊ የደህንነት ስጋት በመፈጠሩ ነው ብሏል፡፡ (ሙሴቪኒ ተሸነፉ ማለት እኮ ብሄራዊ የደህንነት ስጋት ነው!!)  ይሄ ሁሉ መስዋዕትነት ተከፍሎ ነው እንግዲህ ሙሴቪኒ ለ30 ዓመት ከኖሩበት ቤተመንግስት እንዳይወጡ ማድረግ የተቻለው፡፡ (የስልጣን ሌጋሲያቸውም የቀጠለው!)
ሙሴቪኒ ሰሞኑን በድል ፌሽታ ላይ እያሉ እናት ፓርቲያቸው “ናሽናል ሬዚስታንስ ሙቭመንት” እንዲህ ሲል መግለጫ አወጣ፡- “የሙሴቪኒ ድል፣ተቃዋሚዎች ከባዶ ተስፋ ውጭ ለህዝቡ ምንም አማራጭ ማቅረብ እንዳልቻሉ የሚያሳይ ነው” (ድል የሱ ነዋ!)
እንደ አብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት ሁሉ ኡጋንዳም ከምርጫ ማግስት ቀውስ አልዳነችም፡፡ (እንዴት ትድናለች?) የተቃዋሚ ደጋፊዎች በምርጫ ተጭበርብሯል ተቃውሞ ክፉኛ  ተጠምደዋል። ፖሊስ በአስለቃሽ ጭስና በሌሎች አማራጮች ተቃውሞውን ለመበተን እየሞከረ ነው ተብሏል። ሲፒጂ እንደገለፀው፤ በኡጋንዳ ነጻ ሚዲያ ላይ እገዳው፣አፈናውና ማዋከቡ ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ (አወይ መመሳሰል አላላችሁም!)
እስካሁን የምርጫ ታዛቢዎችን ሪፖርት ተመርኮዞ፣የሙሴቪኒን አሸናፊነት አልቀበልም ለማለት  የደፈረው የቦትስዋና መንግስት ብቻ ነው። ሌሎቹ አገራት ግን እንደተለመደው ሙሴቪኒን “ኮንግራ” ለማለት እሽቅድምድም ይዘዋል፡፡

Read 5667 times