Print this page
Saturday, 27 February 2016 11:51

በሁለት ጐሽ መሀል የተደበቀ በሬ

Written by 
Rate this item
(21 votes)

    ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ሌባ በአንድ መለስተኛ ሆቴል አንድ ክፍል ለመኝታው ይከራያል፡፡ እዚህ መኝታ ክፍል ብዙ ቀናት በመቆየት የሚሰርቀው ነገር ሲፈልግ ቆየ፡፡ ዕድሉ አልተገኘለትም፡፡ አንድ ቀን ግን አንድ አጋጣሚ ተከሰተ፡፡ አንድ ድል ያለ ድግስ ተደግሷል፡፡ የሆቴሉ ባለቤት አንድ ምርጥ ውድ ኮት ለብሷል፡፡ እግሩን አንፈራጦ በሩ አካባቢ ተቀምጧል፡፡ ሌባው ያንን ኮት የመስረቅ ስሜቱ ወዲያውኑ ተነሳሳ፡፡ ሌላ የሚሠራው ነገር ስለሌለው ቀጥ ብሎ መጥቶ የሆቴሉ ጌታ ጐን ተቀመጠና በወሬ ጠመደው፡፡ ለተወሰነ ጊዜ ሲያወጉ ቆዩ፡፡ በመካከል ሌባው ወሬውን ትቶ እንደ ተኩላ አዛጋና መጮህ ጀመረ፡፡
የሆቴሉ ጌታ ደንግጦ፤
“ምነው አመመህ እንዴ?”
ሌባውም፤
“ጌታዬ የዚህን ሚስጥር እነግርሃለሁ፡፡ ሆኖም ያንን ላንተ ከመንገሬ በፊት አንድ ነገር ቃል ግባልኝ፡፡ እኔ ስሄድ ልብሴን እንድትጠብቅልኝ እፈልጋለሁ፡፡ ላንተ እተወዋለሁ ልብሴን፤ ምክንያቱም ራቅ ብዬ መሄዴ ስለሆነ ነው”
ጌታው፤
“የዚህ የማዛጋትህ ሚስጥር ግን ምንድነው?”
ሌባውም፤ “ጌታዬ፤ ምናልባት ከላይ እንደ እርግማን ተልኮብኝ ይሆን ይሆናል፡፡ ብቻ ዞሮ ዞሮ፤ ሰበቡ ምንም ይሁን ምን፣ ሦስት ጊዜ አዛግቼ ከጮህኩ ወደ ቁጡ ተኩላነት እለወጥና የሰው ጉሮሮ ማነቅ ነው ቀጥሎ፡፡”
ሌባው ንግግሩን እንዳበቃ ለሁለተኛ ጊዜ አዛጋ፣ አንፋሸከ፡፡ ይሄኔ የውቴሉ ጌታ ሌባው ያለውን እያንዳንዱን ቃል በማመንና በተኩላ የመበላት ነገር እየሰቀቀው፣ በጥድፊያ ተነስቶ ወደ ጓዳ መሮጥ ጀመረ፡፡ ሌባው ግን የጌታውን ኮት ከኋላ ጨምድዶ ያዘውና እየጮኸ፤
“ጌታዬ ጌታዬ፤ እባክዎ ልብሶቼን ይጠብቁልኝ፡፡ አለዚያ ይጠፉብኛል” አለና ለሶስተኛ ጊዜ ማዛጋቱን ቀጠለ፡፡ ጌትዬው ለሦስተኛ ጊዜ ሌባው ካዛጋ አይለቀኝም፣ መበላቴ ነው፤ ብሎ በፍርሃት ተጥለቅልቆ ኮቱን አውልቆ ለሌባው ትቶ መጭ አለ፡፡ ጓዳ ገብቶም በሩን ከርችሞ ቁጭ አለ፡፡
ሌባው እጁ ላይ ታላቁ ኮቱ ቀርቶለታል፡፡ አጅሬ ሌባ፤ ያን ውድ ኮት ተሸክሞ በኩራት እየሳቀ ከሆቴሉ ወጥቶ ሄደ!
*   *   *
ሌብነት የተሰራቂውን አስተሳሰብ ይፈልጋል፡፡ ተሰራቂው ሲፈራ፣ ሰራቂው ልብ ያገኛል፡፡ በቁማችን ኮታችንን ከሚገፍ ጃውሳ ይሰውረን፡፡ ሰው እንደ አውሬ ጮሆ ከሚያስፈራራን ጊዜ ያውጣን፡፡ የሰውን ማንነት እያወቅን ተኩላ ነኝ ሲለን ወደ ማመንና ወደ መፍራት ከተሸጋገርን ሁኔታው አደገኛ ነው ማለት ነው፡፡ በየራሳችን ንፅህና መተማመን፣ በየራሳችን ጥንካሬ መጽናት ያስፈልገናል፡፡ ራዕያችን መገደብ የለበትም፡፡ ይሄን ይሄን ግብ እንመታለን ብለን ስናበቃ፤ ቀጥሎስ ወዴት እንደርሳለን ማለት አለብን፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የማይቆም የማይገታ ራዕይ ምንጊዜም ወሳኝ መሆኑን አንዘንጋ፡፡
ዱሮ ከማንነት የሚመነጭ ክብር ነበረን፡፡ መልካም ስም ያኮራን ነበር፡፡ ስማችንን ከምንም ነገር በላይ እንጠብቀው፣ ቦታ እንሰጠው ነበር፡፡ ሼክስፒር በኦቴሎ ውስጥ በሎሬት ፀጋዬ አንደበት እንዲህ ብሎ ነበር፡-
“ገንዘቤን የወሰደ ሰው፣ ወሰደ እንበል ከንቱ ነገር
 ዋጋ አለው ግን ከንቱም ነው፣
የእኔም የእሱም የዛም ነበር
ግና ስሜን የሰረቀኝ
የማያከብረውን ወስዶ፣ እኔን በግልጽ አደኸየኝ”
ይሄ ትላንትና ነበር፡፡ ዛሬ የስም ጉዳይ ሳይሆን ፈተናው የገንዘብ፣ የንብረት፣ የቤት፣ የመሬት ብቻ ሆኗል!! ከህዝብ ቆጠራ ወደ ቤት ቆጠራ መሸጋገራችን የዚህ ውጤት ነው፡፡ ቤት የሚቆጠረው ትርፍ ቤቶች ያሏቸውን ሰዎች ኢ-ህጋዊ መንገዶችን ለማጠር ነው፤ ይላሉ፡፡ ከዚያ የከፋ ነገር ሳይኖር አይቀርም፡፡ ባለሥልጣኑ ለእገሌ ስጡ ያላቸው ቤቶች የቶቹ እንደሆኑ አይታወቁም፡፡ በር እየሰበረ፣ ቤት እየመዘበረ የገባው ጉልቤ ብዙ ነው፡፡ ደላላ “ባለቤት የለውም” እያለ የቸበቸበውም አይጠፋም፡፡ ይሄን ፈተና ለመወጣት መንግሥት አያሌ ቆጣሪዎችን መድቦ ማሰራቱ የሚያስመሰግን ቢሆንም፤ ቆጣሪዎቹም ሙስና ውስጥ ቢገቡ የሚደርሰውን ጥፋት ከወዲሁ ማጤን ተገቢ ይሆናል፡፡ ልክ “የትራፊክ አዲሱ ህግ ትራፊኩን ያበለፅገዋል” እያለ ህዝቡ እንደሚያማ ግንዛቤ ወስደን መጠንቀቅ አስፈላጊ ነው እንደሚባለው ማለት ነው፡፡ ሲጀመር የሚሰጥ አደራ ሲጨረስ ከሚሰጥ ትችት የተሻለ ነው በሚል ነው ከወዲሁ መናገራችን ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን፣ ጧት ታቅደው ማታ ስለሚሞቱ ዕቅዶችና ሀሳቦች አንዳንድ ፍልስፍናዊ አባባሎችን አኑሯል፡፡ እነሆ
“አሁን እንደጥሬ ፍሬ፣ ሃሳብሽ ግንዱ ላይ ታዝሏል
ነገር ግን በስሎ ሲሟዥቅ፣ ማንም ሳይነካው ይወድቃል”
ራዕያችን በጥሬው ሲቀመጥና ሲበስል ልዩ ባህሪ አለው፡፡ በጥሬው እምንፈክርለት ሃሳብ፣ ሲበስል ምን እንደሚመስል ማስተዋል መሠረታዊ ሃላፊነታችን ነው፡፡ ያደገ የተመነደገ ሃሳብ የራሱ ምስል አለው፡፡ የራሱን አስተውሎት ይሻል፡፡
የአካባቢ ቀውስ፣ የተጠራቀመ ምሬት ውጤት መሆኑን አለማስተዋል ደካማነት ነው፡፡ የህዝብ እንቅስቃሴ፣ ወይም ሁከት እንደው በዘልማድ የረብሻ ሱስ ውጤት ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ፈርጀ ብዙ ጉዳዮች፣ ብሶቶች ጥርቅም ውጤት ሊሆን እንደሚችል በማጤን “የመልካም አስተዳደር ጉድለት” ብቻ ምክንያት ብሎ ማሰብ የራሱ ችግር ሊኖረው የሚችለውን ያህል፤ የሌሎች እጅ አለበት ብሎ መደምደምም የራሱን ጥንቃቄ ይሻላል፡፡ ህዝቡን ከልብ የማሳተፍ ባህል እንጂ ዘመቻ አይደለም መፍትሔው፤ ዘመቻ ጊዜያዊ ነው፡፡ ባህል ዘላቂ ነው!  የሌሎች እጅ አለበት ስንል ህዝብ ያላሰባቸውን በርካታ ባዕድ እጆች በማሰብ እንዳይውዥበረበር መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡ ሌላው ህዝብ የሚለውን ከመመሪያ ጋር ለማጣጣም በሚልም ሀቅ እንዳይጣመም ለማድረግ መጣር ሌላው ተገቢ አካሄድ ነው፡፡
ባንድ አንፃር ሁኔታዎች እየደፈረሱ መላ እንዳያጡ መታገል፤ ሥርወ አመጣጣቸውን መፈተሽ፣ መፍትሔአቸውን መሻት፣ አንዱ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ በሌላ አንፃር ወደ ታላቅ የአገር ፋይዳ የሚሸጋገሩ አገራዊ ዕቅዶችን ከሚያነቅፉ የኢ-ፍትሕ፣ የሙስና የኢ-ዲሞክራሲና የኢ-መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ጋር መጋፈጥ የሀገራችን ነባራዊ- ዕውነታዎች ሆነዋል፡፡ ይህ ማለት አንዳች አጣብቂኝ ነው - በሁለት ጐሽ ማህል የተደበቀ በሬ መሆን! ከዚህ እንወጣ ዘንደ ቆፍጣና መላ ይስጠን! እንደጥርስ ህመም ማታ ማታ የሚያመንን በሽታ ቀን ማዳመጥ እንድንችል ልብ ይስጠን!”

Read 10195 times
Administrator

Latest from Administrator