Saturday, 20 February 2016 09:53

የቦር ተራራ የጤና ተዓምራት

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(79 votes)

      የማይድን የበሽታ ዓይነት የለም ማለት ይቻላል፡፡ ጋንግሪን (እግር ወይም እጅ እንዲቆረጥ የሚያደርግ ቁስል) ይፈወሳል፡፡ የሚጥል በሽታ (ኤፕሊፕሲ) ይድናል፡፡ የስኳር በሽታ፣ የኩላሊት በሽታ፣ የእብድ ውሻ በሽታ፣ የእባብ መርዝ፣ ቁርጥማት፣ ስንፈተ ወሲብ፣ የደም መርጋት፣ አሜባ፣…በአጠቃላይ ከ170 በላይ እጅግ በርካታ በሽታዎች ከቦር ተራራ ከሚለቀም ዕፅዋት መድኃኒት ይድናሉ፡፡
በዘመናዊ ሕክምና የእብድ ውሻ በሽታ እንብርት ላይ 40 መርፌ እየተወጋ ብዙ ቀን ይፈጃል፡፡ በባህላዊ ሕክምና ግን 3 ቀን መድኃኒቱን መጠጣት በቂ ነው፡፡ የእባብ መርዝ ሕክምናም ብዙ ቀን ይፈጃል፡፡ በባህላዊ ሕክምና ግን በ3 ቀን ሕክምና ይድናል፡፡ ሽንትና ሰገራ አልወጣ ብሎ ሲያስቸግር በዘመናዊ ሕክምና ኦፕሬሽን ይደረጋል፡፡ በባህላዊ ሕክምና ግን 3 ቀን መድኃኒት መውሰድ ብቻ ይበቃል፡፡
ዶ/ር ሰለሞን የተባሉ የሚዛን ሆስፒታል ሐኪም ጋንግሪን ይዟቸው እግራቸው እንዲቆረጥ ተወስኖ ነበር፡፡ ሶጃ መጥተው 3 ቀን ባህላዊ መድኃኒቱን ጠጥተው ድነው እንደተመለሱና አሁን ስለ ባህላዊ መድኃኒቱ እያስተዋወቁ መሆኑን ስለ ቦር ተራራ ባህላዊ መድኃኒት ያጫወቱን የባህል መድኃኒት አዋቂው አቶ ወ/መስቀል ጆርጋ በአስተርጓሚው በአቶ ኪዳኔ ከበደ በኩል ነግረውናል፡፡ የየም ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪም አቶ ሙሉጌታ ማሞ የሚጥል በሽታ (ኤፕሊፕሲ) ነበረባቸው፡፡ ለ3 ቀን ባህላዊ መድኃኒቱን ጠጥተው ከበሽታው መፈወሳቸውን ራሳቸው ነግረውናል፡፡
ይህ ሁሉ የፈውስ ተአምር የማገኘው የት ነው? እንደምትሉ እገምታለሁ፡፡ ፈውሱ የሚገኘው በደቡብ ክልል የም ልዩ ወረዳ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ በጅማ መስመር 2 ኪ.ሜ ሲደርሱ አዲሷን የየም ልዩ ወረዳ ዋና ከተማ ሳጃን ያገኛሉ፡፡ ከሳጃ በስተምሥራቅ ተገንጥለው 27 ኪ.ሜ እንደተጓዙ የቀድሞዋን የየም ልዩ ወረዳ ዋና ከተማ ፎፋን ይደርሳሉ፡፡ እዚያ ሆነው ከከተማዋ በቅርብ ርቀት የመድኃኒት ዕፅዋት የሚለቀምበትን ቦር ተራራ ያያሉ፡፡
በየም ልዩ ወረዳ በርካታ የባህል መድኃኒት አዋቂዎች ቢኖሩም ለእኛ በአስተርጓሚው በአቶ ኪዳኔ ከበደ ገለጻ ያደረጉልን የ68 ዓመቱ አዛውንት አቶ ወ/መስቀል ጆርጋ ናቸው፡፡ አቶ ወ/መስቀል ለአባታቸው ዘጠነኛ ልጅ ናቸው፡፡ አባታቸው አባ ጆርጋ ዋጂ የባህላዊ መድኃኒቱን ጥበብ የተማሩት ከአባታቸው ነው፡፡ እሳቸው ደግሞ ለልጃቸው ለአቶ ወ/መስቀል አስተማሩ፡፡ “እኔ ላንተ የማወርስህ የሰው መድኃኒትና ፍቅር የሆነውን ይህን የባህላዊ መድኃኒት ጥበብ ነው” በማለት ስለመድኃኒት ቅመማ አስተማሩን ብለዋል አቶ ወ/መስቀል፡፡
ጥቅምት 17 ቀን የአቡነ ኢስጢፋኖስ ዕለት የቦር ተራራ ከጧት እስከ ምሽት በባህል መድኃኒት አዋቂዎች ደምቆ ይውላል፡፡ ከአካባቢው፣ ከጅማ፣ ከጌዶ፣ ከሰቃ፣ ከቀርሳወረዳ፣ የመጣ የማንኛውም ሃይማኖት ተከታይ የባህል መድኃኒት አዋቂዎች ዕለቱቱን ሙሉ ለአንድ ዓመት የሚሆናቸውን ሳመታ (በየም ባህል የከረመ መድኃኒት ማለት ነው) የዕፅዋት መድኃኒት ይለቅማሉ፡፡ ሳመታ ከሌላ መድኃኒት ጋር እንደቅመም የሚጠቀሙት ነው፡፡ ቦታው (ቦር ተራራ ዲያቆን ኢስጢፋኖስ ሰማዕትነትን ያገኘበት ቦታ ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ ቦር ተራራ ከባህር ጠለል 2.939 ከባህር ጠለል ሜትር ከፍታ አለው፡፡ የተራራውን ሳር የሚበሉ ላሞች ወተት ይለያል፣ ሥጋቸው ጥፍጥናው ሌላ ነው፣ የቅቤው ሽታ ለየት ያለ ነው፡፡
አቶ ወ/መስቀል የዕፅዋት መድኃኒቱን ስለቅም በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ፀሎት አድርጌ ነው ይላሉ፡፡ ጥንት ግን መድኃኒት የሚለቀመው አዋስ ወይም ሙኑካም በሚባል አማልክት ስም ፀሎት ተደርጐ እንደነበረ አስተርጓሚው አቶ ኪዳኔ አክሎ ገልጿል፡፡ ተራራው በጥንት ጊዜ በጣም የተከበረ የተቀደሰ ተደርጐ ይቆጠር ነበር፡፡ የወር አበባ ላይ ያሉ ሴቶች በዚያ በኩል አያልፉም ነበር፡፡ የግብረ - ሥጋ ግንኙነት ያደረገ ሰው ከ7 ቀን በፊት በዚያ አያልፍም ነበር፡፡ በተራራው አጠገብ ማለፍ የሚቻለው ንፁህ ሆኖ ነው ይላሉ፤ አቶ ኪዳኔ፡፡ የቦር ተራራ መድኃኒት ለሰው ብቻ ሳይሆን ለከብቶችም ያገለግላል፡፡
ቱቶና ሱሉቶ ከሚባሉት በስተቀር ቦር ተራራ የሚገኙት ዕፅዋቶች ሁሉ መድኃኒት ናቸው፡፡ አንድ ዕፅ ከሌሎች ጋር ተዋህዶ ከ5 እስከ 14 ለሚሆኑት በሽታዎች መድኃኒት ይሆናል፡፡ በየም ባህል መድኃኒት የሌለው በሽታ የለም፤ ሰው በመቅሰፍት ካልሆነ በስተቀር በበሽታ አይሞትም የሚል እምነት አላቸው፡፡ ኬንቲሞ የሚባሉ የሕፃናት ስፔሻሊስት ሐኪም እናቶች አሉ፡፡ ከማዋለድ በተጨማሪ ሕፃኑ ከተወለደበት ከመጀመሪያው ዕለት ጀምሮ የመድኃኒት ሕክምና ይሰጣሉ፡፡
አቶ ወ/መስቀል ጂማና ጐጀብ አካባቢ በነበሩበት ጊዜ በርካታ ደንበኞች እንደነበራቸው ይናገራሉ፡፡ የም ልዩ ወረዳ መኖር ከጀመሩ አጭር ጊዜ ቢሆንም፣ እቤታቸው ወረፋ የሚጠብቀው ሰው ከጤና ጣቢያ ሳይሆን በአንድ ሆስፒታል ወረፋ ከሚጠብቅ ሰው አያንስም፡፡
የባህል መድኃኒት አዋቂው መድኃኒት ከሰጡ በኋላ ለሰጡት አገልግሎት የሚያስከፍሉት እንደታካሚው አቅም ነው፡፡ ሰውዬው ድሃ ከሆነ መድኃኒቱን ሰጥተው በነፃ ያሰናብቱታል፡፡ መክፈል የሚችል ከሆነ ደግሞ ኪስ የማይጐዳ መጠነኛ ገንዘብ ያስከፍሉታል፡፡
የባህል መድኃኒት ፈዋሽነቱ በዘመናዊ ሕክምናም የተረጋገጠ ነው፡፡ ችግሩ አወሳሰዱ ላይ ነው - ወይ ይበዛል ወይ ያንሳል፡፡ አቶ ወ/መስቀል መድኃኒት የምሰጠው እንደታካሚው አቅም መጥኜ ነው ይላሉ፡፡ በዘመናዊ ሕክምና የአንድ ወር፣ የሁለት ወር፣ የ6 ወር፣ የዓመት፣ የሁለት ዓመት፣ እንደሚባለው እኔም ዕድሜና አቅሙን አይቼ ነው የምሰጠው፡፡ ያለበለዚያማ ነገር ተበላሸ ማለት ነው ብለዋል፡፡
ቦር ተራራ ለየም ሕዝብ ልዩ መስህብና ሕይወት ነው ይላል ኅብረተሰቡ፡፡ ከተራራው በሚለቀመው መድኃኒት እንታከማለን፣ እንፈወሳለን፡፡ ምግባችን ውስጥ ጨምረን እንበላዋለን፣ ለከብቶቻችን እንመግባለን፡፡ በአጠቃላይ ቦር ተራራ መኩሪያና መከበሪያ ሕይወታችን ነው በማለት ያሞካሹታል፡፡  

Read 12959 times