Saturday, 20 February 2016 09:34

ተንከባክባ ያላሳደገችውን ልጅ፣ የእከሌ ልጅ እኩያ ነው ትላለች

Written by 
Rate this item
(16 votes)

    ስሙ ያልታወቀ ፀሐፊን ጠቅሶ አንድ የኛ ፀሐፊ ያቀረበውን ለዛሬ ተረት እናርገው
ዐጼ ቴዎድሮስ አንድ ቀን አንድ የሚያምኑትን ዘበኛ ይዘው፣ አልባሌ መስለው ከጨለመ በኋላ በሠፈሩ ይዞሩ ጀመር፡፡ በየጐጆው እየተጠጉ ያደምጡ ነበር፡፡ እኩሉ ያልተኛ እኩሉም ተኝቶ፡፡ ከዝያ ወዲያ ካንድ ወታደር ጐጆ ተጠግተው ቢያደምጡ ባልና ምሽት በግብረ - ሥጋ ሲጣሉ ሰሙ፡፡ ወንዱ ይለምናል፡፡ ሴቲቱ አይሆንም ትላለች፡፡ ከዝያ ወዲያ ወንድየው፤
“በማርያም”፣ በሥላሴ፣ “በጻድቃን በቅዱሳን” እያለ ቢለምን፤ ሴትዮዋ፣
“እምቢ አይሆንም” ትላለች፡፡
ሰውየው፤
“ኧረ በሥላሴ ይሁንብሽ?”
“በጭራሽ ስልህ? አሻፈረኝ አልኩኮ!”
“በጻድቃን በቅዱሳን?”
“ሰውየው፤ እምቢ ማለት አይገባህም?”
ሰውየው የመጨረሻ ሙከራ አደረገ፡፡
“በይ በቴዎድሮስ ሞት…” አላት፡፡
“ቴዎድሮስማ ከሚሞት፣ ጐንደር አይታረስም” አለችና ፈቀደች፡፡
ንጉሡ ይሄንን ከሰሙ በኋላ እየሳቁ ወደ አዳራሻቸው ገቡና፣ ያን አብሮአቸው የነበረ ዘበኛ፤ ያችን ጐጆ እንዳታሳስትህ አስተውላት ብለውት ነበረና በነጋታው ያንን ዘበኛ፤
“ባልና ሚስቱን ጠርተህ አምጣቸው” ብለው ሰደዱት፡፡
ባልና ሚስቱም፤
“ምን ተገኘብን ይሆን?” ብለው እየተንዘፈዘፉ፣ እየተንቀጠቀጡ መጡና ከጃንሆይ ፊት ቆሙ፡፡
ንጉሡም፤
“እንዴት አደራችሁ?” አሉ፡፡
እነዚያም እየተብረጀረጁ ሳይሰሙ ቀርተው ኖሮ ባጠገባቸው የቆመ ቢነግራቸው በግንባራቸው ተደፍተው እጅ ነስተው ቆሙ፡፡
ቀጥለውም ንጉሡ፤
“ትላንት ማታ በምኝታ ጊዜ ከቤታችሁ ሆናችሁ ተናገራችሁ?” ብለው ጠየቋቸው፡፡
“ጃንሆይ የተናገርነው የለም፡፡ ጠላት ነገር ሠርቶብን እንደሆነም ያጋጥሙኝ፤ ድኻ ወታደር ባሪያዎ ነኝ፡፡”
“ከመኝታችሁ ላይ ጥቂት የተናገራችሁት ነገር እንዳለ አስበህ ንገረኝ አይዞህ” አሉት፡፡
እሱም ሰውነቱን አጠናከረና አስቦ፣ ያንን ምሽቱ ያደረገችውን ነገር ነገራቸው፡፡ ንጉሡም ሳቁ፡፡ ሴቲቱም አፈረች፡፡
***
“በኃይለስላሴ አምላክ ተወኝ!”፣ “በንጉሥ ይዤሃለሁ ተወኝ”፣ “በህግ አምላክ” ዱሮ ቀረ፡፡ የንጉሥ ስም ተጠርቶ አትንካኝ፣ አትምታኝ፣ መብቴን አትንካ፣ ማለት ጥንት የተለመደ ነበር፡፡ ዛሬ ያ ልማድ ቀርቷል፡፡ ማንም አይሰማም፡፡ ነገሥታቱ በህዝቡ የየዕለት ህይወት ውስጥ ይገቡ ነበር፡፡ የመፈራታቸውም መጠን ወሰን የለውም፡፡ ዛሬ ህጉ እየተለወጠ፣ ዘመኑ ጤና እያጣ መጥቷል፡፡
ዛሬ ከሽማግሌው ይልቅ ወጣቱ ጤና አጥቷል፡፡ በቀላሉ ይሸነፋል፡፡ የትምህርት አቅሙ ደካማ በመሆኑ ዕውቀቱ አገም ጠቀም ነው፡፡ ከመማር ማማረር የሚመርጠው እየበረከተ፤ የሚያመረው እየሳሳ መጥቷል፡፡ ቁርጠኝነት ጠፍቷል፡፡ ለሱስ ተገዥነት የማያጠያይቅ አደጋ ነው፡፡ የወሲብ ማጠናከሪያ ዕንክብል ካዋቂው ይልቅ የለጋው ወጣት ማዳበሪያ ሆኗል፡፡ ዛሬ በሪህ በሽታ የሚያዘው ወጣቱ ሆኗል፡፡ ንቅዘት (degeneration)  የወቅቱ ትዕዛዝ ይመስላል፡፡ ይቅር ይበለን እንጂ ምን ይባላል፡፡ እጅግ አሳሳቢ ነው!
“አረጋዊውን ባንቀልባ፣ ከምንሸከም እንኮኮ
ጐልማሳውን ከወኔ ጣር፣ ካልፈታን ከፍርሃት ምርኮ” የሚለን ነው ፀጋዬ ገ/መድህን፡፡
ሌላው ጣራችን ዲሞክራሲ ነው፡፡ ማንም መንግሥት፣ ገዢ ፓርቲ ወይም ተቃዋሚ ድርጅት ልብ ሊል የሚገባው ዲሞክራሲ የትግል ሂደት ውጤት እንጂ መና እንዳልሆነና አሸናፊ ከተሸናፊ ጋር የመቻቻል ግዴታ እንዳለበት ነው፡፡ በዚህ ረገድ ስለባለጋራዎቻችን ኡምቤርቶ ኢኮ የሚለንን ማዳመጥ እጅግ ተገቢ ነው፤
“መልካም ምግባር የሚከሰተው የባለጋራዎቻችንን መኖር በመካድ ሳይሆን፣ ባላጋሮቻችንን በቅንነት በመረዳት፣ በነሱ ቦታ ሆነን ነገሮችን በመመልከት ነው፡፡ ሌሎችን በቅንነት መረዳት ማለት ልዩነትን ሳንክድ ወይም ቸል ሳንል፣ የአድልኦ አስተያየቶችን ማስወገድ ማለት ነው”
አንድ የሀገራችን ፀሐፊም “መቻቻል መቻል ነው፡፡ መቻል ሳይኖር መቻቻልን ማሰብ ከባድ ነው” ይለናል፡፡ ትላንት ያሳደግነውን ቂም በቀል ነቅለን መጣል አለብን፡፡ ከዓመት ዓመት አንድ ዓይነት መላ ምት እየተለምን፣ በ21ኛው ክፍለ ዘመን በአቦ ሰጡኝ መጓዝ፣ ባለበት ሂድ እንጂ ወደፊት አያራምደን፡፡ One step forward two steps back እንደሚሉት እንዳይሆን እንጠንቀቅ፡፡ አንድ ወደፊት ሁለት ወደኋላ ጐታች ጉዞ ነው፡፡ የለማውን ግብ ለማድረስ ሙስና ማነቆ ከሆነ፣ የለማውን ፍሬ ሳንበላ ኢ - ፍትሐዊነት ካገደን፣ የለማውን ወደበለጠ ደረጃ እንዳናደርስ “የአብዬን እከክ ወደምዬ ልክክ” እንቅፋት የሚሆንብን ከሆነ አካሄዳችን ውሽልሽል ነው፡፡ ዕድገታችን ቁልቁል ነው፡፡ በወጉ ያልተንከባከብነው ዕድገት ለወሬ እንጂ ለተግባር አይመችም፡፡ ከጐረቤቶቻችን በዚህ በዚህ እንበልጣለን፤ በዚህ በዚህ እንሻላለን፤ በዚህ በዚህ በአብዛኛው አብረን እየተጓዝን ነው፣ ማለት በተጨባጭ ዕድገትና ማንነታችንን አያሳይም፡፡ ይልቁንም፤ “ተንከባክባ ያላሳደገችውን ልጅ፣ የእከሌ ልጅ እኩያ ነው ትላለች” የሚለውን ተረት ነው የሚያረጋግጥ!  


Read 6079 times