Saturday, 06 February 2016 11:20

ራሳችንን ሳናበራማ…ሌላውን አናበራም!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(14 votes)

• በመላው ዓለም የተበተኑ “አንበሶቻችንን” እንሰብስብ…
• “ቤቶች” ድራማ ከማዝናናት መምከር ቀሎታል!

    እኔ የምላችሁ … በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ በኢትዮ - ሱዳን ድንበር አካባቢ “Surprise አደረጉን የተባሉት አንበሶች … ጉዳይ ምን ደረሰ? አንበስነታቸውን አምነዋል አይደል?  የጀርባ ታሪካቸውስ ተጠና? … (“ጠርጥር አይጠፋም ከገንፎ መሃል ስንጥር…” አለ አበሻ!) መቼም እስካሁን “ኢትዮጵያዊ አንበሶች” መሆናቸው ተረጋግጧል ብዬ እገምታለሁ፡፡ (“እየጠረጠረች የምትናገረው” የ“ደንብ 5” ድራማ ሴትዮ ትዝ አለችኝ!)?
ለማንኛውም ግን ገለልተኛ አካል (ኢህአዴግም ተቃዋሚም ዳያስፖራም ያልገባት!) ተቋቁሞ የማጣራቱ ተግባር ቢጀመር አይከፋም (እርግጠኛ ለመሆን እኮ ነው!) ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያ በአንበሶቹ ዙሪያ አስተያየታቸውን ያሰፈሩ አንዳንድ ፌስቡከሮች… እኔን ያስጨነቀኝ ጉዳይ እንዴት አያስጨንቃቸውም ብዬ ተናድጄ ነበር፡፡ (ቢያንስ አንበሳ ጉዳይ እንኳን እንዴት አንድ አንሆንም?!)፡፡ እናላችሁ እነሱን ያስገረማቸው ምን መሰላችሁ? አንበሶቹ… ኢትዮ - ሱዳን ድንበር አካባቢ መገኘታቸው ነው! በቃ… ድንበሩን ከሱዳን ለመከላከል አንድዬ የላካቸው አስመሰሏቸው!!
ይልቁንስ እኔ ያሰብኩትን ልንገራችሁ… ለብቻዬ!! እንግዲህ እኒህ አንበሶች ከዚህ ቀደም እዚያ ቦታ መኖራቸው ሳይታወቅ አይደል ድንገት ከች አሉ የተባለው፡፡ እናላችሁ ምናልባት በየቦታው መኖራቸው የማይታወቅ አያሌ የኢትዮጵያ “አንበሶች” እንደሚኖሩ … ጠረጠርኩላችሁ፡፡ ትንሽ ቆይቼ ግን እርግጠኛ ሆንኩኝ፡፡ (ጦቢያ እኮ የ “አንበሶች” አገር ናት!) የእኛ ዋነኛ ችግራችን ምን መሰላችሁ? የአንበሶች አያያዝ! አናውቅበትም (አናሳዝንም!) እንጂማ የጦቢያ አንበሶች እኮ አገር ናቸው፡፡ አገር ይሁኑ እንጂ አገራቸው ላይ ለመቀመጥ… አገራቸውን ለማቅናት ግን አልታደሉም፡፡ እናም…  በመላው ዓለም እንደ አሸዋ ተበትነው ይገኛሉ - የጦቢያ አንበሶች!!
እውነቴን እኮ ነው በየዓለማቱ አንበሳ - ዶክተሮች፣ አንበሳ - ኢንጂነሮች፣ አንበሳ - ፕሮፌሰሮች፣ አንበሳ - ፓይለቶች፣ አንበሳ አትሌቶች፣ አንበሳ - ምሁራን፣ አንበሳ የኩባንያ ባለቤቶች  …ወዘተ አሉን፡፡ ግን ለባዕድ አገራት ዕውቀታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ገንዘባቸውን፣ ፍቅራቸውን፣ ደስታቸውን፣ አንዳንዶቹም ኢትዮጵያዊነታቸውን ገብረው እየኖሩ ነው፡፡ (ግማሽ ኑሮ በሉት!)፡፡ እነዚህኞቹ እንደ ሰሞነኞቹ አንበሶች ድንገት ተከስተው “Surprise” የሚያደርጓችሁ ከመሰላችሁ ተሳስታችኋል፡፡ ገፍተን… አማረን… አበሳጭተን… አስፈራርተን… ገፍትረን… ከገዛ አገራቸው ያባረርናቸው እኛው ነን፡፡ አሁንም ፊት የነሳናቸው እኛው! እናም ልብ እንግዛና ሰርፕራይዝ እናድርጋቸው ለአገራቸው አፈር እናብቃቸው! እስቲ ለአገራቸው ይትጉ! አገራቸውን ያንጿት! እኛም ከቀድሞ ሃጢያታችን እንንፃ!!
አሁን በቀጥታ ከአንበሶቻችን ወግ ወጥተን ወደ ኢቢሲ እንለፍ፡፡ ሰሞኑን ኢቢሲን የሙጥኝ ያልኩት በዓሉን አብረነው እንድናከብር በሚል እንጂ… የትችት ሱስ ኖሮብኝ ብቻ አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ የEBC ዋና ሥራ አስፈፃሚ በዚህ ሳምንት ለሁለተኛ ጊዜ በአጭር የስልክ መልዕክት እንዲህ ብለውናል፡- “Your time with us is precious: We are grateful of your being with us in the past 50 years. Thank you! Grow old with EBC” በእውነቱ ወፍራም ምስጋና ነው፤ ሥራ አስፈፃሚው ለደንበኞቻቸው የላኩት፡፡ እኛም ታዲያ በአክብሮት “ይገባናል” እንበላቸው፡፡ - ምስጋና መቀበል የአገር ወግ ነው፡፡ ለቀጣዮቹ ዓመታትም አብረናቸው እንድንዘልቅ - እንድናረጅ እንድናፈጅ ተመኝተውልናል። ልባዊ ምስጋናችን ይድረሳቸው፡፡ አብረን የምናረጀው ለቀጣዮቹ 50 ዓመታት ስለሆነ በቅጡ ማሰብ የግድ ነው። እናም እኛም በበኩላችን ኢቢሲን “እጅህ ከምን?!” ልንለው እንወዳለን፡፡ ህልሙን ልናውቅ… ራዕዩን ልንፈትሽ እንሻለን፡፡ አዲስ የደንበኝነት ውል ከማሰራችን በፊት፡፡ (ቪቫ ነፃ ገበያ!)
በነገራችን ላይ … ኢቢሲ በዓሉን ምክንያት በማድረግ የልግስና “ሃራራውን” እኮ ተወጣ፡፡ (646 ሺ ብር መለገስ ቀልድ ነው!) እንደ 50ኛ ዓመት የልደት በዓል ሰርፕራይዝ ድንገት ይፋ የተደረገው ግማሽ ሚ. ብር የሚደርስ ገንዘብ፤ ለተለያዩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ነው የተከፋፈለው፡፡ (ህዝባዊ ወገንተኝነት ይሏል ይሄ ነው!) እርግጠኛ ነኝ …ኢቢሲ ለብዙዎቹ መንግስታዊ ተቋማት አርአያ ይሆናል። የኢህአዴግ ግንባር ድርጅቶችም የበዓል ወጪያቸውን በልግስና በመስጠት ህዝባዊነታቸውን እንደሚያሳዩ ይጠበቃል፡፡
አሁንም ኢቢሲ በዓሉን በተለያዩ ዝግጅቶች ማክበሩን ቀጥሏል፡፡ (የግማሽ ክ/ዘመን ልደት መሆኑን እንዳትዘነጉ!) እናላችሁ… ሰሞኑን ደግሞ በኦሮሚያ የባህል ማዕከል የ50 ዓመት የካበተ ታሪኩን (ከጨቅላነት እስከ ጉልምስና ማለት ነው!) የሚያስቃኝ አውደ ርዕይ አዘጋጅቶ ለጐብኚዎች ክፍት ያደረገ ሲሆን አብዛኞቹ ጐብኚዎችም በተመለከቱት የቴክኖሎጂ ዕድገት መደነቃቸውን ጠኢቢሲ ዘገባ ጠቁሟል፡፡ አንድ ከውጭ አገር የመጡ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያ (የኢቢሲ ቤተኛ መሆናቸው ተጠቁሟል!) ጣቢያው ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ረገድ ያሳየውን ከፍተኛ መሻሻል መስክረዋል፡፡ የእኔ ጥያቄ - እኛ ተመልካቾቹ ከዚህ ሁሉ የቴክኖሎጂ ግስጋሴ ምን አተረፍን? ቴክኖሎጂው ድካምን በመቀነስ ሥራን እንደሚያቀላጥፍና የጥራት ደረጃን እንደሚያሳድግ… ወዘተ ሰምተናል፡፡ እኛ ጋም መድረስ አለበት!
ሌላው ደግሞ ኢቢሲ ከሙያዊ ስነምግባር አንፃር ራሱን አለማስገምገሙ ትንሽ ቅር አሰኝቶኛል፡፡ ለምሳሌ ከተዓማኒነት፣ ከሚዛናዊነት፣ ከሃቀኝነት፣ ሁሉን በእኩል ከማገልገል ወዘተ … አንፃር ምን እመስላለሁ? ተመልካቹ እንዴት ያየኛል… የሚሉ አስተያየቶችን ከተለያዩ ወገኖች ማሰባሰብ ቢችል… የወደፊት ግስጋሴውን ለማቅናትና ለማስላት እንዲሁም… ጠንካራ ተፎካካሪ ለመሆን ያግዘው ነበር ብዬ አስባለሁ፡፡ (ከፈለገ ማለቴ ነው!)
በነገራችን ላይ ምክትል ጠ/ሚኒስትር የተከበሩ አቶ ደመቀ መኮንን፤ ከኢቢሲ ፕሮግራሞች የቱን እንደሚመለከቱ ወይም እንደሚመርጡ ሰሞኑን በራሱ በኢቢሲ ተጠይቀው ነበር፡፡ (ብቻ “መለከት” ድራማ እንዳትሉኝ፡፡ “ማያ” ቶክሾው ብትሉም አልሰማችሁም። “ቤቶች” ድራማ ካላችሁኝ ደግሞ … በሳቅ ነው የምፈርሰው፡፡ (“ከስብሰባ ወደ ስብሰባ ነዋ!”) በቃ እኔ ልንገራችሁ፡፡ ምክትል ጠ/ሚኒስትሩ ከኢቢሲ ፕሮግራሞች የሚመለከቱት “ዜና” እና የ “ዜና ትንተና” መሆኑን እንደተናገሩ ተገልጿል፡፡ … ሌሎች ባለስልጣናትስ ከኢቢሲ የሚወዱት ፕሮግራም (ነፍሳቸው እስኪወጣ ማለቴ ነው!) ምን ይሆን? ጣራው ሁሉ በዲሽ የተወረረ በሚመስልበት በዚህ ዘመን እንደኔ ያለ ተራ ተርታው ህዝብን ኢቢሲን የሚያየው መቼ እንደሆነ ወይም የቱ ፕሮግራም እንደሚመስጠው ማወቅ ያጓጓል (እኔ “ኑሮና ቢዝነስ” ይደላኛል!)  
እናንተዬ …አንዳንድ በኢቢሲ የሚተላለፉ ድራማዎችን እያያችሁልኝ ነው? ከሳምንት ሳምንት ይሻላቸዋል ስንል እኮ ጭራሽ ባሰባቸው፡፡ ልማታዊነታቸው ቀላል ጨመረ!። (ማን ነበር “ፍቅር ጨምሯል” እያለ ያቀነቀነው?!) እስቲ አስቡት…  አንዳንዶቻችን ልማታዊ ስብሰባ ውለን አዕምሮአችንን ዘና ለማድረግ ቲቪ ከፍተን ስንቀመጥ፣ ሌላ “ልማታዊ ስብሰባ!” (አንደኛ ዓመቱን ሲያከብር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፤ “My favorite tv drama” ብለው ያደነቁት “ቤቶች” የተሰኘው የቲቪ ድራማ፤ በፈጠራ ሀሳብ ድርቀት ክፉኛ የተጠቃ ይመስላል፡፡ እናላችሁ ምክር … ግብረ ገብ .. የአገር ገጽታ ግንባታ ወዘተ… ሥራ ጀምሯል፡፡ በድራማ እኮ ነው! (በጦቢያ ብቸኛውን የ “ግብረገብ ሾው” በኢቢሲ ለመጀመር አስቤአለሁ!)
ከድራማ ጉዳይ ሳንወጣ… እስቲ ሁሌም “ድራማ” ስለሚሆንብኝ “መብራት ኃይል” የተባለ የመንግስት ተቋም ላውጋችሁ…ማለቴ ልውቀስላችሁ! (የድራማው ዘውግ ትራጃይ ኮሜዲ ይባላል!) ሃቁን ለመናገር ታዲያ… የዚህ ተቋም በደል “የመልካም አስተዳደር ችግር” በሚል ብቻ የሚገለፅ አይደለም፡፡ (አይገርምም በደል በድራማ!)
አንዳንዴ ይሄን ተቋም ሳስበው … (ሻማ በገዛው ቁጥር ማለቴ ነው!) ትራንስፎርመርና ትራንስፎርሜሽኑ የተምታታበት ይመስለኛል፡፡ (ትራንስፎርመር ፈነዳብኝ እያለ… ትራንስፎርሜሽኑን እያፈነዳ ይሆን እንዴ?
በነገራችን ላይ አብዛኞቹ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩ የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ኢንቨስተሮች በስራቸው ላይ ስለሚያጋጥማቸው ችግሮች ሲጠየቁ፤ በአንደኛ ደረጃ የኃይል መቆራረጥን ነው በምሬት የሚጠቅሱት፡፡ ወደው ነው! በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ፣ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ግቡን ያላሳካበት አንዱና ዋነኛው ምክንያት፤ የኃይል መቆራረጥ እንደሆነ እኛም… መንግስትም… ኢንቨስተሮቹም… መብራት ሃይልም… እናውቀዋለን፡፡
አሁንም ግን ለውጥ የለም፡፡ ነገስ? እንኳን ነገ የዛሬ ዓመት? 2 ዓመት? 5 ዓመት? … ለውጥ እንደሚመጣ ዋስትና የሚሰጠን የለም፡፡ ትራጃይ ኮሜዲው ምን መሰላችሁ? እኛን የብርሃን ድርቀት ክፉኛ እያጠቃን መብራት ሃይል ግን (ሌላ ተቋም ቢሆንም ያው ነው!) ለተለያዩ የአፍሪካ አገራት … የኤሌክትሪክ ሃይል ለማቅረብ ውል መፈራረሙን በየሚዲያው ይነግረናል፡፡ በዚህ ሳምንት በኢቢሲ ድረገጽ ላይ የሰፈረውን ዜና ደግሞ እነሆ፡-
“ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀዳሚዋ የኤሌክትሪክ ሃይል ላኪ ለመሆን እየሰራች መሆኗን አሳወቀች” ይላል - ዘገባው። እንዴት ነው ነገሩ? አገሯን ሳታበራ ሌላውን ልታበራ? አገሯን ሳታጠግብ ሌላውን ልታጠግብ? ምንም የውጭ ምንዛሪ ቸገረን ቢባል … የእኛ የመብራት መቆራረጥ መፍትሔ ሳያገኝ የኤሌክትሮክ ኃይል ኤክስፖርት ማድረግ … የመብት ጥሰት ነው፡፡ (“የብርሃን ጥሰት” በሉት!) እኔ የምለው … ህዝብ መክሰስ አይችልም እንዴ? (95ሚ. ህዝብ ማለቴ ነው!)
እኔማ … ዜናውን አንብቤ ስጨርስ ለራሴ ምን አልኩ መሰላችሁ… “የጦቢያ ልጆች የተሟላ የኤሌክትሪክ ኃይልና ዲሞክራሲ የሚያገኙት መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገራት ተርታ ሲደርሱ ብቻ ነው”፡፡ እስከዛው እንዲህ እያልን እንቆዝማለን… “የአፍሪካ ቀዳሚዋ የኤሌክትሪክ ሃይል ላኪ ለመሆን እየተጋች ያለች ኩሩ አገር - ኢትዮጵያ!!” (እኔ የምለው…የስኳር ፋብሪካዎቻችንስ ምነው ድምፃቸው ጠፋ!) 

Read 5732 times