Saturday, 30 January 2016 12:48

መድኃኒት በህገ-ወጥ መንገድ በመግባት ከቀዳሚዎቹ ተርታ አይደለም ተባለ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

 ለገበያ የሚቀርቡት ዘይትና ጨው ደረጃቸውን የጠበቁ አይደሉም
                              
      የኢትዮጵያ የምግብ፣ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ባለፉት 6 ወራት ባከናወናቸው ተግባራት ላይ ከመድኃኒትና ምግብ አስመጪ፣ አከፋፋይና ላኪ ድርጅቶች ጋር ውይይት ያካሄደ ሲሆን መድሃኒቶች በህገወጥ መንገድ በመግባት ቀዳሚ እንዳልሆኑ ተገለፀ፡፡
ባለሥልጣኑ፣ በሳምንቱ ሁለት የመጀመሪያ ቀናት በግሎባል ሆቴል ባካሄደው ስብሰባ፣ መ/ቤቱ በበጀት ዓመቱ ለመስራት ያቀዳቸውንና ጥሩ ውጤት አግኝቼባቸዋለሁ ያላቸውን ነጥቦች ያቀረበ ሲሆን፣ በራሱና በባለድርሻ አካላት ላይ ያያቸውን ድክመቶች አቅርቦ ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡
በዚሁ ወቅት የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ የሁሉ ደነቀው በሰጡት መግለጫ፤ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ የመድኃኒትና የመሳሪያዎች አቅርቦት እጥረትና ቁጥጥር ማነስ፣ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ድክመት፣ በዋናነነት የሚጠቀሱ ችግሮች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ጊዜ ያለፈባቸው መድኃኒቶችና ምግቦች በገበያው በርክተዋል፤ አንዳንድ የጤና ባለሙያዎች በሥነ-ስርዓት አያስተናግዱንም ያመናጭቁናል፣ የመድኃኒቶች ጥራትና ፈዋሽነት አጠራጣሪ ሆኗል፣ ወደ መ/ቤቱ ስንመጣ ፈጣን ምላሽ አናገኝም … የሚሉ ጥያቄዎች በኅብረተሰቡ ዘንድ እንደሚነሱ ጠቅሰው ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት አቅደው እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኅብረተሰቡ ከሚያነሳቸው ጥያቄዎች በዋነኝነት የህገ-ወጥ መድኃኒቶች በከተማው መብዛት ስለሆነ ይህን ችግር ለመቅረፍ ምን እየሰራችሁ ነው? ተብለው በጋዜጠኞች የተጠየቁት አቶ የሁሉ፣ ችግሩን ለመከላከል እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው መድሃኒት በሕገ-ወጥ መንገድ በመግባት መድኃኒት በቀዳሚዎቹ ተርታ ውስጥ እንደሌለና በ8ኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።  በቀዳሚዎቹ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኮስሞቲክስ እንደሆነና እርምጃ እየወሰዱ መሆኑንም ሃላፊው አክለው ተናግረዋል፡፡
ከምግብ አስመጪ አከፋፋይና ላኪ ድርጅቶች ጋር በተደረገው ውይይት፣ የምግብ ጥራት ደህንነትና ብቃት መጠበቅ አለበት ያሉት ጽሑፍ አቅራቢ፤ በምግብ መስፈርቶች ዙሪያ ችግሮች እንዳሉ ጠቅሰው የምግብ ዘርፍንና አምራቾችን መደገፍ እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል፡፡
ምግብ ማዘጋጃ ፋብሪካ ንፁህና ደረጃውን የጠበቀ መሆን እንዳለበት ጠቅሰው አንድ በሱፐርማርኬት በሰልፍ የሚሸጥ ምርት ፋብሪካው የት እንደሆነ ለማየት ሄደው ጭቃው መኪና የማያስገባ ገጠር፣ በጭስ የጠቆረ ደሳሳና ቆሻሻ በሆነ ቤት ውስጥ እንደሚመረት፣ የማምረቻ ዕቃዎቹም ንፅህና የጎደላቸውና የዛጉ መሆናቸውን፣ እንደተመለከቱ ተናግረዋል፡፡
ሌላው ጽሑፍ አቅራቢው ለገበያ የሚቀርቡ ምግቦች በንፅህና እንደማይዘጋጁ ጠቅሰው፣ የምግብ ዘይትና ጨው ከደረጃ በታች እንደሚቀርቡ፣ ዘይት በነብሳት መራቢያ፣ በቆሻሻ መጣያ፣ መጥፎ ሽታ ባለው ቦታ፣ ኬሚካል ወይም መርዝ በሚከማችበትና በአጠቃላይ ምግብን ሊበክሉ በሚችሉ እንዲሁም የሰውን ጤናና ደህንነት ለአደጋ በሚያጋልጡ ስፍራዎች እንደሚመረት ገልፀዋል፡፡ አዮዲን የገባበት ጨው ቤት ውስጥ በጆንያ መቀመጥ ሲገባው ውጭ ተቀምጦ ፀሐይ እየመታው አዮዲኑ እንደሚጠፋም ፅሁፍ አቅራቢው … ገልፀዋል፡፡   

Read 3347 times