Saturday, 30 January 2016 12:04

ከመሪዎቻችን “በትህትና የተጠቀለለ ሥልጣኔ” አማረን!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(8 votes)

በቴክስት ይቅርታ የላከልን መ/ቤት ወግ አሳየን!
ኢቢሲ በዓሉን እስኪያከብር ድረስ በጥያቄ እናጣድፈው!

“ፖለቲካ በፈገግታ” ሁልጊዜ ድረስ ነቆራ ነው ብሎ የበየነው ማነው? (ተፈጥሮው ይመስለኛል!) እውነቴን ነው የምላችሁ… የግድ ሆኖብኝ እንጂ አንዳንዴ እንኳን የምስጋናና የውደሳ መድረክ ላደርገው ይዳዳኛል፡፡ ችግሩ ግን ፖለቲካ ለውዳሴ ሩቅ ነው፡፡ ለማንኛውም ግን በዚህ ሳምንት አንድ ሁለት ነገሮችን አግኝቻለሁ - ለአድናቆትና ለውዳሴ፡፡
እኔ የምላችሁ ግን … ሰሞኑን በሞባይል ለየት ያለ አጭር መልእክት አልደረሳችሁም? ለነገሩ ሁሉም በየፊናው ያሻውን (ያለፈቃዳችን) ስለሚልክብን ባትመለከቱት አይገርመኝም፡፡ (ፕራይቬሲያችን ቀላል ይጣሳል መሰላችሁ!) በነገራችን ላይ ሰሞኑን የተላከልኝ ቴክስት እንደሌላው ጊዜ አላበሳጨኝም፡፡ ቴክስት ሜሴጁ የተላከው ደግሞ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ነው። እንዲህ ይላል፡- “The Ministry of Foreign Affairs apologizes in advance for any inconvenience during the upcoming AU Summit. Thank you for your cooperation.” (በትህትና የተጠቀለለ ሥልጣኔ ይመቻል!)
እናላችሁ … ይህቺ አጭር መልእክት የፈጠረችብኝን ግሩም ስሜት ልነግራችሁ  አልችልም! ጨረቃ ላይ የወጣሁ ነው የመሰለኝ (እንኳንም ሥልጣን ላይ አልመሰለኝ!) ልብ አድርጉ … “ህዝቡን የሚያከብር ትሁት መንግስት የለም” … አልወጣኝም! ቢያንስ ለእኛና ለአብዛኛው የአፍሪካ ህዝብ ግን ትሁት መንግስት ብርቃችን ነው፡፡ (ሥልጣን ለማራዘም ህገ መንግስት የሚፍቁ አምባገነን ገዢዎች ናቸው - ለአፍሪካ የተረፏት!)
እውነቱን ልንገራችሁ አይደል … በኢህአዴግ የ25 ዓመት የሥልጣን ዘመን “… ለሚፈጠረው እንግልት በቅድሚያ ይቅርታ እንጠይቃለን” የሚል የመንግስት መስሪያ ቤትም ሆነ የመንግስት ባለሥልጣን ገጥሞኝ አያውቅም፡፡ (የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን አከበርኩት!) ወዳጆቼ፤ የትራንስፖርት ጉዳይ የሚመለከተው የአዲስ አበባ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ … ስንት ዓመት ጠዋትና ማታ ለታክሲ ወረፋ ሲያሰልፈን … መቼ ይቅርታ ጠይቆን ያውቃል? እነ መብራት ኃይል (ኑሮአችንን ሲያጨልሙብን!) … ውሃና ፍሳሽ (ብጫ ጀሪካን ሲያሸክሙን!) እነ ቴሌ (በኔትዎርክ መቆራረጥ ከቢዝነስ አጋሮቻችንና ከህይወት አጋሮቻችን ሲያቆራርጡን!) ወዘተ… መቼ ይቅርታ ጠየቁን? (ሰውየው፤ “ሚስትህ ወለደች ወይ?” ቢሉት “ማንን ወንድ ብላ!” አለ) የእኛም ነገር እንዲያ ነው - ባንተነፍሰውም! እናላችሁ…የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን  መልዕክት ደጋግሜ ሳስበው ግን እኮ እንደ ዜጋ ይገባን ነበር አልኩ፡፡ እውነቴን ነው ብዙ ዓመት ስለቆየን ዘንግተነው እንጂ እንደ መንግስት ተደጋጋሚ ጥፋት… ብዙ ተደጋጋሚ ይቅርታዎች ይገቡን ነበር፡፡ (“ይቅርታችን ተጭበርብሯል” እንበል እንዴ?!) ግዴለም በሰሞኑ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር የሚያጠግብ ይቅርታ ተክሰናል!! አድናቆቴን እጥፍ ድርብ ያደረገው ደሞ ምን መሰላችሁ? መ/ቤቱን የሚመሩት ሰውዬ … ባይፈርሙልኝም “አድናቂያቸው” ነኝ፡፡ ዛሬ ሳይሆን ከጥቂት ወራት በፊት በሚሊኒዬም አዳራሽ ከአሊ ቢራ ጋር ሲዘፍኑና ለአድናቂዎቻቸው ሲፈርሙ… አመሹ የተባለ ጊዜ ነው … በይፋ “አድናቂነቴን” የገለፅኩት፡፡ ልብ በሉ! ኢህአዴግን የማልደግፍ (የምጠላ …አልወጣኝም!) የዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም “አድናቂ” ነኝ!! (“ኢህአዴግን የማልቃወም የግል ተወዳዳሪ ነኝ” ያሉት ሰውዬ ትዝ አሉኝ!)
እናንተዬ … ለካስ ዘንግቼው ነው እንጂ ሌላም ቴክስት ተልኮልን ነበር - በዚሁ ሳምንት!! በእርግጥ ይሄኛው ትህትናም … ሥልጣኔም… በሚል የምናሽሞነሙነው ዓይነት አይደለም፡፡ በቃ መረጃ ነው የላከልን፡፡ (ዕወቁልኝ ዓይነት!) መልዕክቱ ምን መሰላችሁ? የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የ50ኛ ዓመት የልደት በዓሉን ከጥር 24-29 እንደሚያከብር የሚገልፅ ነው፡፡ ብዙዎች “So what?” እንደሚሉ እገምታለሁ፡፡ እኔ ግን “ምን ይጠበስ?” ብዬ… ኩርፊያ  አልፈልግም፡፡ የሆዴን እንዳልጫወት እንቅፋት ይሆንብኛል፡፡ እናም …  “Happy Anniversary” ብያለሁ ለኢቢሲ!!
በነገራችን ላይ  የዛሬ 50 ዓመት የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ ሥርጭቱን ሲጀምር ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የተናገሩት ንግግር ተቀንጭባም ቢሆን መቅረቡ ተገቢ ነው፡፡ (ታሪክን ለባለቤቱ መስጠት “በጨዋነት የተጠቀለለ ሥልጣኔ” ነው!) እኔ የምለው… ብዙዎቹ የመንግስት ተቋማት የተመሰረቱበትን 50ኛ … 60ኛ… 70ኛ ወዘተ… ዓመት እያከበሩ እንደሚገኙ አስተውላችሁልኛል? እነ ብሔራዊ ቲያትር… ባንክ… ወመዘክር… ወዘተ ሁሉም ከ50 ዓመት በላይ ዕድሜ አስቆጥረዋል፡፡ የሚገርመው ደግሞ በሁሉም ላይ የንጉሱ አሻራ አርፎባቸዋል፡፡ (ምን ማረፍ ብቻ ራሳቸው ናቸው ያሳነጿቸው፡፡) ስለንጉሱ ሳነሳ! በዚህ ሳምንት በኢቢሲ ያየሁት ድንቅ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ ምን መሰላችሁ? (የቅድሙ የይቅርታ ቴክስት ዓይነት ነው የሆነብኝ!) አንድ ሚኒስትር ቤተመንግስት ግቢ ውስጥ ሆነው ይመስለኛል (ህልም አስመሰልኩት እኮ!) … የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቤተ-መንግስት አርጅቶ የእድሳት ያለህ እያሉ እንደሚፈልግ የገለፁ ይመስለኛል (ካልተሳሳትኩ!) ከዚያስ? “የኃይለ ሥላሴ ታሪክ ማለት የህዝቡ ታሪክ ነው!!” ሲሉ ጆሮ ውስጥ ጥልቅ አለች! ማነው የተናገረው? እኔ ነኝ እሳቸው? ግን እርግጠኛ ነኝ ሚኒስትሯ ስለመናገራቸው፡፡ አምልጧቸው አይደለም፤ ሆን ብለው ነው፤ አስበውበት፡፡ እሳቸው ሥራቸውን እየሰሩ ሊሆን ይችላል፡፡ ለኛ ግን ዱብዕዳ ነው! ድንገተኛ! ተዓምር! (የልምምድ ጊዜ አይሰጠንም እንዴ?!) ግን ሴትየዋን አደነቅኋቸው ( “በብልሃት የተጠቀለለ ፖለቲካ” ይሏል ይሄው ነው!) ኢህአዴግ የጐደለው ይሄ ነበር!!
እኔ የምለው … ኢቢሲ የ50ኛ ዓመት ኢዮቤልዩ በዓሉን ካከበረ በኋላ ለኛ ለተመልካቾቹ ምን አስቦልናል? (ነግሯችሁ ከሆነ ብዬ እኮነው!) መቼም እንደወትሮው ዝም ብሎ ልቀጥል ማለት አይችልም፡፡ ከግማሽ ክ/ዘመን በኋላማ ለውጥ የግድ ነው፡፡ (“በዕውቀት የተጠቀለለ ለውጥ!”) እኔ ደግሞ በዚያ ሰሞን ከቢቢሲ ጋር በትብብር እንደሚሰራ ሰምቼ … ትልቅ ተስፋ አድሮብኝ ነበር፡፡ ትንሽ ቆይቶ ግን ከቻይናው CCTV ጋር በትብብር ለመስራት መስማማቱን ሰማሁላችሁ፡፡ ቆይ ግን ቻይና ከመቼ ወዲህ ነው የሚዲያ አጋር መሆን የጀመረችው? (ኮሙኒኬሽንና ኮንስትራክሽን ተምታታባት እንዴ?!) የሆኖ ሆኖ … እሷ ብትፈልግም እንኳ እኛ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ሳናስቀይማት ልንፋታት ይገባ ነበር፡፡ ለምን መሰላችሁ? የኮሙኒስት አገር፣ የሚዲያ አሰራርና ፍልስፍና እንኳን ለወዳጅ አገር ለራሱም አይበጅም፡፡ ከዚህ ቀደም እንዳወጋነው ደግሞ ቻይና … ነፃ ሚዲያ … የሰብዓዊ መብት ጥበቃ … ዲሞክራሲያዊ መብቶች … ወዘተ በመዝገበቃላቷ ውስጥ የሉም፡፡ (ባቡር መጓጓዣ እንጂ መረጃ እኮ አይሆንም!)
እውነቱን ለመናገር … ኢቢሲ የሚዲያ አጋር በትክክል የሚፈልግ ከሆነ ቢቢሲን መምረጥ አለበት፡፡ (እኔ ከእሱ አላውቅም!!) 50 ዓመት ሙሉ በነፃነት እንዳይሰራ ተቀፍዶ ክፉኛ ለማቀቀው ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያችን፤ የቻይናን ሚዲያ አጋር ማድረግ እግረ - ሙቁን ማጥበቅ ይመስለኛል፡፡ ከምሬ ነው የምላችሁ … ከቻይና ቲቪ ጋር በመስራትም ሆነ በልማታዊ ጋዜጠኝነት መርህ በመቀጠል ፋይዳ ያለው ውጤት አይገኝም፡፡ “የብዝሃነትና የህዳሴ ድምፅ” መሆንም ጨርሶ አይታሰብም፡፡ እናም … የዛሬ 50 ዓመት የተሻለ ቁመና ያለው የቴሌቪዥን ጣቢያ ለመገንባት ከልቡ የሚመኝ ፊቱን ወደ እነ ቢቢሲ ማዞር ይገባዋል፡፡ ሮይተርስ… ሲኤንኤን… ኤቢሲ…ብቻ የኒዮሊብራሉስት ርዕዮተ ዓለም አቀንቃኞች ይመረጣሉ፡፡ (ወደፊት መገስገሱ ይቀራል እንጂ ወደኋላስ አንመለስም!)
እኔ የምላችሁ ኢህአዴግ በ10ኛ ጠቅላላ ጉባኤው ላይ … መንግስታዊ ሚዲያዎችን ምን ብሎ እንደገመገማቸው ዘነጋው እንዴ? “ከልሳንነት ያለፈ ሚና የላቸውም”፤ “አዝማሪ ሚዲያ አንፈልግም!”… ሲል የሰማሁት መስሎኛል፡፡ ይሄን የሆኑት የልማታዊ ጋዜጠኝነት አስተምህሮን ሳያዛንፉ በመተግበር እኮ ነው፡፡ እና በተመሳሳይ አስተምህሮ የተለየ ውጤት መጠበቅ የዋህነት ነው፡፡
ኢህአዴግ በGTP 2 ውስጥ ማካተት እያለበት ያላካተተው አንድ ነገር ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? ኢቢሲን ከፓርቲ ልሳንነት … ከመንግስት አፈቀላጤነት ነፃ የማውጣት ዕቅድ!! የጭንቁ ጊዜ ከመደነባበር አሁን በሰላሙ ጊዜ መለማመድ ይሻላል ብዬ እኮ ነው፡፡ የኢቢሲን 50ኛ ዓመት በዓል ምክንያት በማድረግ አንድ ግልፅ ጥያቄ ለኢህአዴግ አመራሮች ላቅርብ፡፡ በ25 ዓመታት ውስጥ ኢቢሲን የነፃ ሚዲያ ሞዴል ለማድረግ እንዴት ተሳናችሁ? ለሌላ እኮ አይደለም… ህዝብና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሃሳባቸውን ለመግለፅ ባህር ማዶ መሻገራቸው እየገረመኝ ነው (ከ25 ዓመት በፊትም አሁንም ቪኦኤን የሙጥኝ ያሉት ወደው አይመስለኝም!) አንድ ጥያቄ ልጨምር ዛሬም ለኢህአዴግ አመራሮች፡፡ የኢቢሲ “የብዝሃነትና የህዳሴ ድምፅ” የሚለው አዲሱ  መራሄ ቃል (ሞቶ) ኮርፖሬሽኑን ይገልፀዋል? የተለያዩ ድምፆች መች ሰምተን እናውቃለን? (የተለያዩ ስል ብዙ ሳይሆን ተቃራኒ ማለቴ ነው!) ህዳሴውስ ምኑ ላይ ነው? (ድፍረቴ መልካም አስተዳደር ለማስፈን እንደሚደረግ ጥረት ይቆጠርልኝ!)
በነገራችን ላይ… ኢቢሲ በያዘው መንገድ ልግፋም ቢል አያዋጣውም፡፡ .. በሙከራ ሥርጭት ላይ ያሉትን የሳተላይት ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ብዛት አይታችሁልኛል?! የኢህአዴግን ቋንቋ ልዋሰውና… “በፍጥነት እንደሚወርድ ናዳ” ነው የሚሆንበት - ፉክክሩ ማለቴ ነው፡፡ (እውነተኛው ነፃ ገበያ ያኔ ነው!)
እናላችሁ … የ50 ዓመቱ ጎልማሳ ኢቢሲ ከለጋዎቹ የሳተላይት ቲቪዎች ጋር በነፃ ገበያ ሥነ-ሥርዓት ተፎካክሮ እጅ ሳይሰጥ ይቀጥል ዘንድ ከሁሉ በፊት የሥነ ልቦና ዝግጅት ሳያስፈልገው አይቀርም (ፉክክርን በወሬ እንጂ በተግባር አላየውም!) ይሄ ብቻ ግን አይበቃም፡፡ የአመለካከት … የአስተሳሰብ … የአተያይ… ለውጥም ይጠበቅበታል፡፡ የመፈክር ሳይሆን የእውነት የብዝሃነትና የህዳሴ ድምፅ መሆንም የግዱ ነው፡፡ የአየር ሰዓት ወስደው በአጋርነት ሊሰሩ የሚሹ ደንበኞችን የሚቀበልበትና የሚያስተናግድበትን አሰራርም መፈተሽ ይኖርበታል፡፡ ከዚህ ቀደም ሊሰማቸው የማይሻቸውን ደንበኞችን መንከባከብ … መሳብ … መማረክ … ኮሚሽን መክፈል (ለማስታወቂያ ኤጀንቶች) … በአጠቃላይ “ደንበኛ ንጉስ ነው” የሚለውን የቢዝነስ መርህም ሊለማመድ ግድ ይሆናል፡፡ (የነፃ ገበያ ሥርዓት ጣጣ እኮ ነው!) ያለበለዚያ ደግሞ የራሴ ማምለጫ መንገድ አለኝ ሊልም ይችላል - አቋራጭ! አያዛልቀውም እንጂ!
ለማንኛውም ግን መልካም የ50ኛ ዓመት በዓል ይሁንለት!! (ለብዝሃነትና የህዳሴ ድምፃችን!)

Read 4056 times