Print this page
Saturday, 23 January 2016 14:03

ጓያን ሲበሉ በዕውቀትና በብልጠት ----

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(10 votes)

•    አንድ ሰው ከዕለታዊ ምግቡ 1/3ኛው ከጓያ የተዘጋጀ ከሆነ፣ ከወገብ በታች ሽባ ይሆናል
•    በህክምና ስለማይድን የችግሩ ተጠቂዎች የዕድሜ ልክ አካል ጉዳተኞች ይሆናሉ
•    ኢትዮጵያን ጨምሮ ቻይና፣ ህንድና ባንግላዲሽ ለችግሩ ተጋላጭ ናቸው
በሳይንሳዊ ስሙ ላትረስ ሣቲቫ (Latres Sativa) እየተባለ የሚጠራው ጓያ፤አስከፊ የሆነ የጐርፍና የድርቅ አደጋን ተቋቁሞ ከባህር ወለል በላይ ከ1800-2000 ሜትር በዋልካ አፈር ላይ ይበቅላል፡፡ የጓያ ሰብል ከ150 በላይ ዝርያዎች አሉት፡፡ በአገራችን ጓያ በስፋት ከሚመረትባቸው አካባቢዎች መካከል ጐጃም፣ ጐንደር፣ ሸዋ፣ ወሎና ትግራይ ዋንኞቹ ናቸው፡፡ አነስተኛ እርጥበት ወይም ከፍተኛ የውሃ ክምችት ባለበት ሥፍራ መብቀል የሚችል ሲሆን በእርሻ ላይ የናይትሮጂን መጠን በመጨመር፣ የአፈርን ለምነት የማሻሻል ብቃት አለው፡፡
ጓያ ከፍተኛ የካርቦሃይድሬትና የፕሮቲን ምንጭ ነው፡፡ ከክብደቱ 58% የሚሆነው ካርቦ ሃይድሬት፣25% ደግሞ ፕሮቲን ሲሆን ዝቅተኛ የቅባት ይዘትና ከፍተኛ የካልሺየምና የፎስፎረስ ማዕድናትን በውስጡ ይዟል፡፡
ሰሞኑን የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ባዘጋጀው አውደጥናት ላይ የቀረበ መረጃ እንደሚጠቁመው፤ጓያን በስፋት እያመረቱ ለምግብነት የሚጠቀሙ ሰዎች በተለይም ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 45 የሚደርሱ ወንዶች፣ ከወገብ በታች ያለውን የሰውነት ክፍሎቻቸውን በመሰባበር ለአስከፊ ጉዳት የሚዳርጋቸው ሲሆን ችግሩ በህክምና ሊፈወስ የማይችል በመሆኑ ተጠቂው የዕድሜ ልክ ሽባ ይሆናል፡፡  
በኢንስቲቲዩቱ የምግብ ሳይንስና ስነ ምግብ ምርምር ይፋ የሆነው ጥናት እንደሚያመላክተው፤አንድ ሰው ከዕለታዊ የምግብ ፍጆታው 1/3ኛው ከጓያ የተዘጋጀ ከሆነ  ከወገቡ በታች ሰውነቱን ማንቀሳቀስ የማይችል ሽባ ያደርገዋል፡፡  
ጓያን በተደጋጋሚ መመገብ መርዛማነቱ በተለያየ መጠን ወደ ሰውነታችን እንዲገባ መፍቀድ ሲሆን በጓያ ውስጥ የሚገኘው ቤታ አዶኝ የተባለው ንጥረ ነገር በአንጐላችንና በህብለ ሰረሰራችን ውስጥ በመከማቸትና የነርቭ ስርዓታችንን በማዛባት፣ ከወገብ በታች ስብራትን ያስከትላል ተብሏል፡፡ ጉዳቱ እንደ ሰውየው የጤንነትና የአቅም ሁኔታ የሚለያይ ሲሆን ከቅጽበት እስከ አስር ዓመት በሚደርስ የጊዜ ገደብ ውስጥ በጓያ ሳቢያ ለሚከተለው የጤና ችግር ተጠቂ ይሆናል፡፡ በጓያ ምክንያት የሚመጣው ስብራት፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ የቻይና፣ የህንድና የባንግላዲሽ ህዝቦችን ለዓመታት ሲያጠቃ መቆየቱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡  
በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት የምግብ ሣይንስና የኒውትሪሽን ምርምር ዳይሬክቶሬት በተዘጋጀውና በምግብና ሥርዓተ ምግብ ዙሪያ የተሰሩ ጥናቶች ይፋ በተደረጉበት ብሔራዊ የምግብና ሥርዓተ ምግብ ምርምር አውደ ጥናት ላይ የጓያ ስብራት መንስኤዎችና መከላከያ መንገዶች በሚል ርዕስ የቀረበው መረጃ፤የጓያ ሰብል ካለው ሥነ ምግባዊ ጠቀሜታ በበለጠ አስከፊ የጤና ችግርን ማስከተሉ መረጋገጡን ይጠቁማል፡፡
ጓያን ለአንድ ወይንም ለሁለት ሣምንታት በተከታታይ መመገብ አሊያም ከዕለታዊ የምግብ ፍጆታ 1/3ኛውን ከጓያ ማዘጋጀት ከወገብ በታች ያለውን አካል በማሽመድመድ ሽባ እንደሚያደርገው ይኸው መረጃ ያመለክታል፡፡  
የጓያ ስብራት ተጠቂው ለህመሙ የሚጋለጠው በቅጽበት አሊያም በአዝጋሚ ሁኔታ ሊሆን ይችላል፡፡ የጅማት መሸማቀቁ ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረና ስር እየሰደደ ሄዶ ተጠቂው በድንገት መንቀሳቀስ ያቅተዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ለህመሙ የሚጋለጡት ደግሞ በአብዛኛው ወንዶች ናቸው፡፡ በአዝጋሚ ሁኔታ ለችግሩ የሚጋለጡት ደግሞ በቁርጭምጭሚታቸውና በእግሮቻቸው መገጣጠሚያዎች ላይ ውስጥ ውስጡን የማሳከክ ስሜት ይኖራቸዋል፡፡ ይህ ስሜት ከ2-3 ወራት ለሚሆን ጊዜ ይቆያል፡፡
ቀስ በቀስም ከወገብ በታች ያለው የሰውነት ክፍል እየከበዳቸው ይሄዳል፡፡ በመጨረሻም በጊዜ ሂደት ሙሉ በሙሉ መንቀሳቀስ ይሳናቸዋል፡፡  
የጓያ ስብራት ህመም ምልክቶች
•    ቅጽበታዊ የሆነ የጡንቻ መሸማቀቅ ስሜት በእግር ላይና ባት አካባቢ ይሰማል
•    በእግር ባት ላይ አነስተኛ እብጠት ይኖራል
•    በጭንና በታፋ ላይ የህመም ስሜት ይፈጠራል  
•    የእግር አውራ ጣትና መዳፍ በቀላሉ አልታዘዝም ይላል
•    የእግር ጡንቻዎች ላይ የህመም ስሜት ይከሰታል  
የጓያ ስብራት አስከፊ ደረጃ ላይ ደርሶ ከወገብ በታች ያለውን የሰውነት አካል ጉዳት ላይ ከመጣሉ በፊት የችግሩ ተጠቂ ገና የመጀመሪያ ምልክቶቹን እንዳየ ጓያ ከመመገብ ቢታቀብ  ችግሩ ባለበት እንዲቆም በማድረግ፣ከአስከፊው የአካል ጉዳት ራሱን ሊጠብቅ ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ ተጠቂው በስብራቱ ሳቢያ ሙሉ በሙሉ መንቀሳቀስ ባያቅተውም መጠነኛ የቁርጭምጭሚት መታጠፍ እንዲሁም የመራመድና የመሮጥ ችግር ያጋጥመዋል፡፡
በኢንስቲቲዩቱ የምግብ ሳይንስና ሥነ-ምግብ ምርምር ዘርፍ በቅርቡ የተሰሩት ጥናቶች፣ ጓያ በውስጡ በጣም አደገኛ የሆነ ንጥረ ቅመም እንዳለው ያረጋገጡ ሲሆን የበሽታውን ጉዳት ለመከላከል ለህብረተሰቡ ተከታታይነት ያለውና መሠረታዊ የሆነ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ሊሰሩ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡
የጓያ ስብራት አራት አይነት ደረጃዎች አሉት፡፡ የመጀመሪያው ደረጃ በርካታ የጓያ ስብራት ተጠቂዎች የሚገኙበትና የበሽታው ምንነት በደንብ የማይታወቅበት ደረጃ ነው፡፡ በመጀመሪያው የጓያ ስብራት ደረጃ ላይ የሚገኙ ተጠቂዎች መለያቸው አጭር እርምጃና ያልተለመደ የሰውነት እንቅስቃሴ ነው፡፡ በታችኛው የጭናቸው ክፍል ላይ የጡንቻ መጨማደድ፣ በተረከዝ ሙሉ በሙሉ መርገጥ አለመቻል ---- የመጀመሪያ ደረጃ የጓያ ስብራት ምልክቶች ሲሆኑ በዚህ ደረጃ ላይ የሚገኙ ህሙማን ያለድጋፍ መንቀሳቀስ የሚችሉ ናቸው፡፡
በጓያ ስብራት የመጀመሪያ ደረጃ ህመም ላይ የሚገኙ ሰዎች ወደ ሁለተኛው የበሽታ ደረጃ ለመሻገር ከወራት እስከ 10 ዓመታት ጊዜ ሊወስድባቸው ይችላል፡፡ ይህ የሚወሰነው በሽታን በመቋቋም አቅማቸው ነው፡፡ የጡንቻ መጠንከርና አለመታዘዝ፣ የሰውነት ሚዛንን መጠበቅ አለመቻል በዚህ ደረጃ ላይ ባሉ ህሙማን በስፋት ይታያል፡፡
ህሙማኑ ሚዛናቸውን ጠብቀው መራመድ ስለማይችሉም የዱላ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፡፡ በጓያ ስብራት የደረጃ ሶስት ህመም ውስጥ የሚገኙ ህሙማን፤ከደረጃ አንድና ሁለት በቁጥር ያነሱ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ችግሩ በሁለቱ ላይ እያለ ረዘም ላለ ጊዜ መቆየት ስለሚችል ነው፡፡ የጡንቻ አለመታዘዝና በጣም መጠንከር ዋንኛ ምልክቱ ሲሆን የእግር አቅጣጫ እንዲዞርና የተመሰቃቀለ አረማመድ እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ በእንቅስቃሴ ወቅት ከወገብ በታች ያለው የዳሌ ክፍል ወደ ጐን ስለሚገፋ፣ ጡንቻ በከፍተኛ ሁኔታ ስለሚጠነክርና ስለማይታዘዝ የሰውነት ሚዛንን ለመጠበቅ ያስቸግራል፡፡ ስለሆነም ህመምተኛው የሁለት ዱላ ድጋፍ ማግኘት ግድ ይለዋል፡፡ የጓያ ስብራት የመጨረሻውና አራተኛው ደረጃው፣ በእግር ለመቆምና ለመንቀሳቀስ የማያስችል ነው፡፡ የቁርጭምጭሚት በከፍተኛ መጠን መታጠፍ፣ የጭንና የታፋ ጡንቻዎች መጠንከር ይፈጠራል፡፡ በዚህም ምክንያት ታማሚው በእንቅስቃሴ ወቅት ሙሉ ክብደቱን በእጁ ለመሸከም ይገደዳል፡፡ ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስም በእጅጉ ይቸገራል፡፡
የጓያ ስብራት ከሚያሳድረው የጤንነት ችግር በተጨማሪ ስነልቦናዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተፅዕኖው እጅግ አስከፊ እንደሆነ የጠቆመው ጥናቱ፤በሽታው ከመከሰቱ በፊት በተለያዩ መንገዶች መከላከል እንደሚቻል ገልጿል፡፡ ዋንኛ የጓያ ስብራት መከላከያ መንገድ ጓያን ለምግብነት ከማዋል በፊት በውስጡ የያዘውን አደገኛ መርዛማ ንጥረ ነገር በተለያዩ ዘዴዎች  ማስወገድ ነው፡፡ ለምሳሌ በፈላ ውሃ መዘፍዘፍ አንዱ መንገድ ነው፡፡ ከሚዘፈዘፈው ጓያ በአራት እጅ የሚበልጥ ውሃ አፍልቶ ለሰዓታት መዘፍዘፍና ደጋግሞ በቀዝቃዛ ውሃ እያጠቡ መርዛማ ንጥረ ነገሩ አስወግዶ በፀሐይ ማድረቅ፣ አሊያም ጓያውን በቀዝቃዛ ውሃ ውስጥ ለ12 ሰዓታት ያህል በመዘፍዘፍ ውሃውን ማስወገድ፣ በመቀጠልም እርጥቡን የጓያ ፍሬ በእንፋሎት ከ20 እስከ 30 ደቂቃ ማፈን፣ በመቀጠልም በቀዝቃዛ ውሃ ለአንድ ሰዓት ያህል መዘፍዘፍ፤ ከዚያም ውሃውን ማጥለልና በፀሐይ ማድረቅ፡፡ ሁለቱ ዘዴዎች በጓያው ውስጥ የሚገኘውንና ከ80-90% የሚሆነውን መርዛማ ንጥረ ነገር ለማስወገድ እንደሚያስችሉ ታውቋል፡፡     

Read 9024 times