Saturday, 23 January 2016 13:31

“ከዝሆንና ከአንበሳ ማን ይበልጣል?” ቢለው፤ “ከሁሉም ከሁሉም አሣ ሙልጭልጭ ነው” አለው፡፡

Written by 
Rate this item
(23 votes)

     ከዕለታት አንድ ቀን አንድ እጅግ ጉረኛ ሰው በአንድ መንደር ከሚስቱ ጋር ይኖር ነበረ፡፡ በድፍረት የማይከራከርበት ጉዳይ የለም፡፡ የሱን አሸናፊነት አጉልቶ ሌሎች ወንዶችን አኮስሶ ከማውራት ቦዝኖ አያውቅም፡፡
“ዛሬ አንዱን አንድ ቡና ቤት አግኝቼ ሳይቸግረው ለከፈኝ” ይላታል ለሚስቱ፡፡
ሚስትም፤
“በምን ጉዳይ ለከፈህ?” ትለዋለች፡፡
ባል፤
“እንደው ቢፈርድበት ነው እንጂ ነገሩ የሚያጣላ ሆኖ መሰለሽ? “አጐቴ በጣም አጭር ድንክዬ ሰው ነው፡፡ እኔ ደግሞ ከጥንቱም ድንክ ሰው እጣ - ክፍሌ አይደለም” አይልልሽም?”
ሚስት፤
“በጄ፡፡ ከዛስ ምን ሆነ?”
ባል፤
“ሾርኔ ንግግሩ ገብቶናል፡፡ ወንድ ልጅ ግን በአግቦ ሳይሆን በቀጥታ ነው መናገር ያለበት” አልኩኝ፡፡
ሚስት፤
“ለምን እንደዛ አልከው፤ እሱ የሚያወራው’ኮ ስለአጐቱ ነው?”
ባል፤
“አንቺ የዋህ ነሽ፡፡ እኔ አጭር መሆኔን ስላየ’ኮ ነው በጐን ወጋ ሊያደርገኝ የሞከረው፡፡”
ሚስት፤
“ከዛስ ምን ሆነ?”
ባል፤
“ጊዜ የሰጠሁት መሰለሽ፤ እንደ ነብር ተወርውሬ በቡጢ ማንጋጭልያውን አወለቅሁለታ!”
ሚስት፤
“አንተ ሰውዬ ይሄ ግሥላነት አያዋጣህም፡፡ ባለፈው ሣምንት እንኳን ከሶስት ሰው ጋር ተጣላሁ ብለኸኝ ነበር፡፡ ትዕግሥት ቢኖርህ ይሻላል” አለችው፡፡
ባል፤
“እኔኮ ካልነኩኝ አልነካም” ይላታል፡፡
አንድ ቀን ማታ ባል በጣም አምሽቶ ደም በደም ሆኖ ይመጣል፡፡ ሚስት ደንግጣ ከበር ትቀበለዋለች፡፡
“ምነው ምን ሆንክ አካሌ?”
ባል፤
“ካንድ መናጢ ጋር ተደባድቤ ድንገት ቀደመኝ”
ሚስት፤
“እንዴ፤ አላስተረፈህም’ኮ! ጭንቅላትህ ደግሞ ተፈነካክቷል፡፡ ሰውዬው ዱላ ይዞ ነበር እንዴ?”
ባል፤
“ኧረዲያ፤ ደሞ ዱላ የመያዝን ያህል ወንድነት ከየት አባቱ አምጥቶ ነው! የኔኑ ነጥቆ ነው እንጂ!”
*    *    *
ያልሆነውን ነን፣ ያላደረግነውን አድርገናል ብሎ ጉራ መንዛት መጨረሻው አሰቃቂ ነው፡፡ ከቶውንም ጥቃቅን የሚመስሉ ግን በአጉሊ መነፅር ስናያቸው አገራዊ ፋይዳ ያላቸው አያሌ ነገሮች አሉ፡፡ የምንዋሸውም ሆነ ጉራ የምንነዛው ቅርባችን ላለ ሰው መሆኑ አስገራሚ ነው፡፡ ምክንያቱም ብዙም ውሎ ሳያድር መጋለጡ በጣም ግልጽና አይቀሬ በመሆኑ ነው፡፡ ዋሽተን የተናገርነውን ማጠፍ ሲያቅተን፣ በጉልበት ለማሳመን መሞከር ይመጣል፡፡ ያኔ መሠረታዊ ሰብዓዊ መብትንም ሆነ ዲሞክራሲያዊ መብትን መጣስ ይመጣል፡፡ ፍትሕን እኔን በሚያግዝ መልኩ ካላስቀመጣችሁ ማለት ይመጣል፡፡ እኔ ላልኩት ካላጨበጨባችሁ ሁላችሁም ልክ ያልሆናችሁት ነገር አለ፤ ማለት ይከተላል፡፡ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን የበላ ጅብ አልጮህ ይላል፡፡ የህዝብን ዕውነተኛ ችግር እንዳይገለጽ መጫን ይበራከታል፡፡ አመለካከትን በነፃነት መግለጫ መድረክ ይጨልምና ሆድ ለሆድ መነጋገር ዓይነተኛ ዘዴ እየመሰለ ይመጣል፡፡ መገናኛ ብዙሃን የህዝብ ድምጽ ማሰሚያ መሆናቸው ይቀራል፡፡ ከዚህ ዲበ - ኩሉ ይሰውረን!
ለአንድ አገር ህዝባዊ ውይይት መኖር አስፈላጊ ነው፡፡ ችግሮች ከአዕምሮ አዕምሮ ይዘዋወራሉ፡፡ ብሶቶች ይብላላሉ፡፡ የታፈኑ ሃሳቦች ይፍታታሉ፡፡ “አካፋን አካፋ” የማለት ባህል ይዳብራል፡፡ ሌባውን ከጨዋው የመለየት ዕድል ይሰፋል፡፡ ህዝብ ዕውነቱን የመናገር አጋጣሚ ሲያገኝ ሹማምንትን የማረም፣ የመተቸት፣ የመገሰፅ፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ከመንበራቸው የማውረድ ሁኔታዎች ይፈጠራሉ፡፡ “ዳቦ ራበን” ብሎ ለሚጮህ ህዝብ፤ “ለምን ኬክ አይበሉም?” ብላ እንደመለሰችው እንደ ንግሥት ሜሪ አንቷኔት ያለ ቅንጡ አመራር አይኖርም፡፡ “ህዝባዊ ሸንጐ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ነው” ይላሉ ፈላስፋ ፀሐፍት፡፡ ህዝባዊ ውይይትን አቅጣጫ በማስያዝ ሰበብ ጮሌ ሊጠቀምበት እንደሚችል ግን ልብ ብሎ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ማንም ይሁን ማን የህዝብን ትኩረት በመሳብ ወደግል ጥቅሙ ልጐትት ሲል ገመዱን ለመበጠስ ዝግጁ መሆን ብልህነትም፣ ኃላፊነትም ነው፡፡ የመልካም አስተዳደር የንቅናቄ መድረክ፣ በተለይ ምዝበራን ከማጋለጥ አንፃር በየቦታው እየተሞከረ ያለው ሂደት፣ የሀገርን ሀብትና በሺዎች የሚቆጠሩ ሄክታሮችን ያድናል፡፡
የዳነውን ሌሎች እንዳይመዘብሩት የሚቆጣጠሩ ጠንቃቃ አካላት ያስፈልጋሉ፡፡ ነገሮች እንዳይድበሰበሱ፣ ጥያቄዎች በተጠየቁበት ገጽ እንዲመለሱ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የተጠየቁትን ትተው ያልተጠየቁትን የሚመልሱ ተጋላጫ አመራሮችን ለነገሮች ልጓም አበጅቶ ፈራቸውን እንዳይለቁና በትክክል ወንጀላቸው እንዲለይ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ አለበለዛ በለመደ ምላሳቸው ወንጀሉን ለቀና ተግባር እንዳደረጉት ሊያስመስሉት ይችላሉ፡፡ ስለሆነም “ከዝሆንና ከአንበሳ ማን ይበልጣል” ቢለው፤ “ከሁሉም ከሁሉም አሣ ሙልጭልጭ ነው” አለው፤ እንደተባለው እንዳይሆን መጣር የአባት ነው!

Read 9199 times