Saturday, 16 January 2016 10:09

በአቋራጭ የበለጸጉ የመንግስት አመራሮች የሃብት ምንጭ ምንድን ነው?

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(24 votes)

መንግስት ራሴን መፈተሽ ጀምሬአለሁ አለ!!!
200 ገደማ የአማራ ክልል አመራሮች ከሃላፊነት ተባረሩ

   ማስተርፕላኑ እንኳንስ በፊንፊኔ ዙሪያ ጂማን ተሻግሮ መላ ጦቢያን ቢያካልል ነፍሴ በሃሴት ጮቤ ትረግጥ ነበር፡፡ ዋናው ነገር ግን የእኔ ደስታ ወይም ፍላጎት አይደለም፡፡ (የኦህዴድና የመንግስት ራዕይና ዕቅድም ቦታ የላቸውም!) ከሁሉ የሚቀድመው የኦሮሚያ ህዝብ ፍላጐትና ምርጫ ነው፡፡

    ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች “ሂዩማን ራይትስ ዎች”፤ በኦሮሚያ ክልል ማስተርፕላኑን መነሻ አድርጐ በተቀሰቀሰው ተቃውሞና እሱን ተከትሎ በተከሰተው ግጭት 140 ሰዎች መሞታቸውን አስታውቋል፡፡ (አሳዛኝ የታሪካችን አካል ነው!) መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው “ሂዩማን ራይትስ ዎች”፤ በኦሮሚያ በተከሰተው ግጭት የሞቱትን ዜጎች ቁጥር ይፋ ካደረገ አንድ ሳምንት አልፎታል። የኢትዮጵያ መንግስት፣ አገር በቀሎቹ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች እንዲሁም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ግን እስካሁን የሞቱትንና የቆሰሉትን ዜጎች ቁጥር አልነገሩንም፡፡ (መንግስት የመንገር ሃላፊነት፣ እኛ የማወቅ መብት ያለን መስሎኝ!?) ለነገሩ የክልሉ መንግስት፤ የደረሰውን ጉዳት በጥንቃቄ እያጣራ መሆኑን ጠቁሞ፣ ማጣራቱ እንደተጠናቀቀም ለህዝብ ይፋ አደርጋለሁ ብሎ ነበር፡፡ (ዝንተ ዓለም ፈጀ እኮ!)
የሚያሳዝነው ደግሞ ነገርዬው በዚህ አለመቋጨቱ ነው፡፡ በሁካታውና ዕልቂቱ ማግስት ረብሻውን ቀስቅሰዋል ተብለው የተጠረጠሩ፣ የተጠቆሙ፣ የተጋለጡ …ብዙ ሺዎች --- ወህኒ ወርደዋል ተብሏል። ግን ስንት ሺዎች? ለመሆኑ ከጅምሩ እስካሁን ድረስ ምን ያህል ሰዎች ተጠርጥረው ተያዙ? ምን ያህሎቹ ፍ/ቤት ቀረቡ? ስንቶቹስ በነፃ ተለቀቁ? ህዝባዊ መንግስታችን ይሄን መረጃ የሚነግረን መቼ ነው? ይሄም እየተጣራ ይሆን? (ግን እኮ የታሰሩትን ዝም ብሎ መቁጠር ነው!) አለዚያ ግን ብቸኛው አማራጫችን መቀመጫቸውን በአሜሪካ ያደረጉት እነ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እንደተለመደው ሪፖርት እስኪያወጡ መጠበቅ ነው። (ከኒዮሊበራሊዝም አቀንቃኞች ነጻ የምንወጣው መቼ ነው?)
በእስከዛሬው ልምዳችን መሰረት፣ እነ ሂዩማን ራይትስዎች ወይም ፍሪደም ሃውስ አሊያም ዊዝአውት ቦርደርስ ----በኦሮሚያ በተከሰተው ፖለቲካዊ ቀውስ ሳቢያ ለእስር የተዳረጉትን ዜጎች ቁጥር ከማንም በፊት ቀድመው ይነግሩናል። በእርግጥ የቁጥር ከፍና ዝቅ ሊኖር ይችላል፡፡ አሜሪካ ሆነው እቅጭዋን ሊነግሩን አይችሉም፡፡ (እቅጭዋን የሚያውቀውማ አሳሪው ነው!) አንድ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ በዕድለ ቢሱ የ97 ምርጫ ሰሞን የተከሰተ ነው፡፡ የምርጫ ውጤት ተጭበርብሯል የተባለ ሰሞን ታክሲዎች አድመው ነበር፡፡ ለ3 ቀናት ገደማ ሳይሆን አይቀርም፡፡ በ4ኛው ቀን ላይ ሚኒባስ ታክሲዎች አገልግሎት መስጠት ጀመሩ፡፡ አዲስ አበባ ከድብርቷና ከኦናነቷ ተላቃ ወደ ቀድሞው ድባብ የመመለስ ፍንጭ አሳየች፡፡ የዚያን ላይ ማታ የድሮው ኢቲቪ ያስተላለፈው ዘገባ መቼም አይረሳኝም፡፡ (ሃሳቡን እንጂ ቃል በቃል ትዝ አይለኝም!) “በዛሬው ዕለት የአዲስ አበባ ሚኒባስ ታክሲዎች አገልግሎት ሲሰጡ መዋላቸውን ሮይተርስ ዘገበ” (ለሸገር የሚቀርባት ሮይተርስ ነው ኢቲቪ?)
በነገራችን ላይ በኦሮሚያ በተከሰተው ረብሻና ግጭት እንዲሁም ዕልቂት አንድ አሳዛኝ እውነታ ተገንዝቤአለሁ፡፡ (ታዝቤአለሁ ማለት ይቀለኛል!) ለሳምንታት በዘለቀው ግጭት የመንግስት የፀጥታ ኃይል ለተቃውሞ በወጡ ዜጎች ላይ ያልተመጣጠነ እርምጃ ከመውሰድ እንዲቆጠብ ያሳሰቡት ውቅያኖስ ማዶ ያሉት የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ብቻ ናቸው፡፡ (ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ውጭ ማለቴ ነው!) በመንግስት የተቋቋመው “ኢሰመኮ” እና በፕ/ር መስፍን  የተቆረቀረው “ሰመጉ” ትንፍሽ ያሉት ነገር የለም፡፡ (የሰብአዊ መብት ተቋማት መስለውኝ?!) ወዳጆቼ፤ በዚያ ቀውጢ ሰዓት መንግስትን ለምን አላወገዙም ወይም አልተቃወሙም እያልኩ አይደለም፡፡ መንግስት አቅሉን ስቶ ግብታዊ ነገር እንዳይፈጽም የምታሳስብ፣ የምታስታውስ መግለጫ ቢጤ ማውጣት ማን ገደለ? ሌላው ቢቀር እንደ እነ አሜሪካ ኤምባሲ፤ “የሞቱት ዜጐች…የታሰሩት ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች ጉዳይ ያሳስበኛል” ማለት እንዴት ያቅታል?! ይሄን በማድረጋቸው መንግስት የሚያስራቸው ከመሰላቸው ከ25 ዓመት በፊት ወደነበረው ሥርዓት ተመልሰናል ማለት ነው፡፡
ሌላው ሁሌም እዚህ አገር የማይገባኝ ምን መሰላችሁ?… የሃይማኖት ተቋማትና መሪዎች (አባቶች) ሚና ነው? በአማራ ክልል በሉት በኦሮሚያ ያ ሁሉ ሁከትና ግጭት ሲከሰት …ዜጐች ሲሞቱ ---- ተቋማቱ የት ነበሩ? ያንዳቸውም ድምጽ አልተሰማም፡፡ (ፖለቲካና ሃይማኖትን መቀላቀል ስለማይፈቀድ ይሆን?) ለነገሩ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሃይማኖት መሪዎች በየበዓሉ የሚሰጡትን መግለጫ ከተከታተላችሁልኝ ----- እያደር አንደበታቸው የፖለቲከኛ እየመሰለ መጥቷል። አንዳንዶቹማ የካድሬ ቋንቋ ሁሉ ለምደዋል፡፡ ግና---- ሰላምና ፍቅርን፣ መከባበርና መቻቻልን… መስበክ አልቻሉም፡፡ እርቅ ማውረድ ተስኗቸዋል። ህዝብን ----- ከህዝብ፣ ህዝብን ------ ከመንግስት ----- መምከር፣ ማስማማት፣ ማስታረቅ አቅቷቸዋል።   ከእግዚአብሄር ይልቅ መንግስትን ይፈራሉ፡፡ ከሰማያዊው ዓለም ምድራዊው ግምኛ ያጓጓቸዋል፡፡
 በእርግጥ መንግስት እንዳይጠምዳቸው ሰግተው ይሆናል፡፡ ነገር ግን ይሄ መሰረተ - ቢስ ስጋት ነው፡፡ ይልቁንም የእነሱ አስተዋጽኦ መንግስትን አማራጭ አጥቶ ወደ ሃይል እርምጃ ከመግባት ሊያድነው ሁሉ ይችል ነበር፡፡ ችግሩ ግን እነሱ ከኛ ከተራ ተርታዎቹ ምድራዊ ሰዎች እንኳን ብሰዋል፡፡ ይሄን በማድረግ ዓለማዊው ምቾታቸውን እንዲቀንሱ አይሹም፡፡ የሆኖ ሆኖ እኛ አዝነንባቸውና ታዝበናቸው አልፈናል። እንግዲህ በውስጤ ሲብሰለሰል የሰነበተውን ቅሬታና ቁጭታ፣ እቺን ታህል ከተነፈስኩ ይበቃኛል፡፡ (ክብር ለህገ-መንግስቱ!)
ይህ በዚህ እንዳለ ባለፈው ማክሰኞ ማታ፣ ከኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ያልተጠበቀ መግለጫ ወጥቷል (በኢቢሲ ማለቴ ነው!) በግሌ ደስ ነው ያለኝ፡፡ “ለጋራ ልማት የታሰበው የአዲስ አበባና ፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ የጋራ ልማት ሙሉ ለሙሉ እንዲቆም የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ውሳኔ አስተላለፈ” ይላል የኢቢሲ ዜና፡፡ ሌሎች ቅሬታዎችና ጥያቄዎች ቢኖሩም ዋናው የኦሮሚያ ክልል ተቃውሞ መነሻ፣ ይሄው ማስተርፕላኑ ነው። እናም ውሳኔው ተገቢ ይመስለኛል፡፡ (ልማት ተግባብቶ እንጂ ተለያይቶ የለም!) በነገራችን ላይ እኔ በግሌ ማስተርፕላኑ ቢተገበር ደስታውን አልችለውም፡፡ እንኳንስ ልማት ሌላውም ሁሉ በክልል፤ በጐሳ፣ ወዘተ ----- ባይገደብ እመርጣለሁ። እናም ማስተርፕላኑ እንኳንስ በፊንፊኔ ዙሪያ ጂማን ተሻግሮ መላ ጦቢያን ቢያካልል ነፍሴ በሃሴት ጮቤ ትረግጥ ነበር፡፡ ዋናው ነገር ግን የእኔ ደስታ ወይም ፍላጎት አይደለም፡፡ (የኦህዴድና የመንግስት ራዕይና ዕቅድም ቦታ የላቸውም!) ከሁሉ የሚቀድመው የኦሮሚያ ህዝብ ፍላጐትና ምርጫ ነው፡፡ ለዚህ ነው መግለጫው ደስ ያለኝ፡፡ (መዘግየቱ ቢያበሳጨኝም!)  
ኢቢሲ በድረገፁ ላይ ባወጣው ዘገባ እንዲህ ሲል ይቀጥላል፤ “ኦህዴድ በልማት፣ በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ከህዝቡ ጋር በመሆን መጠነ ሰፊ ስራዎችን በማከናወን ህዝባዊነቱን ያረጋገጠ ድርጅት መሆኑን ማዕከላዊ ኮሚቴው ገልጿል” (ዜና ነው ፕሮፓጋንዳ?) ቀጣዩ አንቀፅ ሳይሻል አይቀርም። እንዲህ ይላል፡- “በክልሉ የጋራ ፕላኑን መነሻ በማድረግ ህዝቡ የግልፅነት ጥያቄ መጠየቁ ድርጅቱ እየገነባ ያለው ሥርዓት ውጤት በመሆኑ፣ በታላቅ አክብሮት ይመለከተዋል”  (እኛም የኦህዴድን መግለጫ በታላቅ አክብሮት እንመለከተዋለን - የህዝብ ውጤት በመሆኑ!)
የኦህዴድ መግለጫ በዚህ ብቻ አያበቃም፡፡ ክልሉ ከአዲስ አበባ ማግኘት ባለበት ጥቅም ዙሪያ በህገ መንግስቱ በተቀመጠው አቅጣጫ፣ በአጭር ጊዜ ምላሽ እንደሚሰጠውም አስታውቋል፡፡ (የእስከ ዛሬውን ዳተኝነት በምን ፍጥነት ያካክሰው ይሆን?)
ኢቢሲ ዘገባውን ሲቀጥልም፤ “የክልሉ ከተሞችን ልማት ለማፋጠን በጨፌ ኦሮሚያ በፀደቀው የከተሞች ልማት አዋጅ አንዳንድ አንቀፆች ዙሪያም ህዝቡ ያነሳቸውን የግልፅነት ጥያቄዎች ለመመለስ የክልሉ መንግስት አዋጁ እንደገና በጨፌ እንዲታይ እንዲያደርግ ድርጅቱ ውሳኔ አስተላልፏል” ብሏል። (“የቸገረው እርጉዝ ያገባል” እንዳይሆን እንጂ አስገራሚ ለውጥ ነው!!) በነገራችን ላይ ኦህዴድ … ትንሽ በጥሞና ቢያስብ ኖሮ ዛሬ የወሰዳቸውን እርምጃዎችም ሆነ ያስተላለፋቸውን ውሳኔዎች ቀውስ ከመፈጠሩ ቀደም ብሎ ሊያደርጋቸው ይችል ነበር፡፡ (አገር በተቃውሞ እስክትናጥ መጠበቅ ዋጋ ያስከፍላል!!)
አሁን ደግሞ ወደ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን “ጮማ” የሆነ ወሬ ልምራችሁ፡፡ “በአቋራጭ የበለፀጉ የመንግስት አመራሮችን የሀብት ምንጭ የመፈተሽ ሥራ ተጀምሯል” ይላል ዜናው፡፡ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የኢኮኖሚና የፋይናንስ ክላስተር አስተባባሪና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ለፋና እንደገለፁት፤ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ መንግስት ከአመራሩና ኃላፊዎቹ ጀምሮ ራሱን መፈተሽ ጀምሯል (“ጉድ ፈላ አትሉኝም!)
በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ልዩ ትኩረት የተሰጠው የመልካም አስተዳደር ችግር ምንም እንኳን በአንድ ሌሊት የሚፈታ ባይሆንም ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ የተግባር እንቅስቃሴዎች በየደረጃው መጀመራቸውን የገለፁት ሚኒስትሩ፤ “ለዚህም በራሳቸውና በቤተሰቦቻቸው ያለ አግባብ ሀብት ያካበቱ የመንግስት አመራሮችን የመፈተሽ ሥራ መጀመሩን ለአብነት አንስተዋል” ሲል ዘግቧል ፋና፡፡ (ይሄኔ ነው እንግዲህ “እናቴ፤ ምነው በእንቁላሉ ጊዜ በቀጣሽኝ” የሚለው የሚበዛው!) አንዳንዴ እኮ እናት በደንብ ቆንጥጣ ብታሳድገውም ፓርቲና ሥልጣን የሚያበላሸው ሞልቷል (በእናት መፍረድ አይገባም ለማለት ነው!)
ዜናው አልተቋጨም…“ይህን እንቅስቃሴ መንግስት ጥቆማ ሳይጠብቅ የሚሰራው ስራ ሲሆን ችግሩን ለመቅረፍ ግን የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ ነው” ብለዋል - ሚኒስትሩ፡፡ መንግስት እንደ ሌላው ነገሩ ሁሉ እዚህም ላይ ዘገየ እንጂ የሚደገፍ እርምጃ ነው፡፡ (ሌላው ቢቀር አዳዲስ “የመንግስት ሌቦች”ን ተስፋ ያስቆርጣል!)
እኔ የምለው ግን … በአቋራጭ የበለፀጉ የመንግስት አመራሮች የሀብት ምንጭ ምን ይመስላችኋል? ሀ) ዓለም ባንክ ለ) ኪራይ ሰብሳቢ ባለሀብት ሐ) ደላላ መ) የመንግስት ካዝና ሠ) ከሀ በስተቀር ሁሉም መልስ ናቸው
(ስፖንሰር አድራጊ ባለማግኘቴ ሽልማት የለውም!)
አሁን ደግሞ ወደ አማራ ክልል ላሻግራችሁ። እዚያ የምናገኘው ደግሞ ከመልካም አስተዳደር ጋር ተያይዞ ችግር ፈጥረዋል የተባሉ ከ190 በላይ አመራሮችና ሰራተኞች ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውን የሚዘግብ ዜና ነው፡፡ ለመሆኑ ከመልካም አስተዳደር ጋር የተያያዘ ችግር … ሲባል ምን ማለት ነው? (አብስትራክት አልሆነባችሁም?!) ዘገባውን ስታነቡ ግን ምን ዓይነት ትራጄዲ እንደሆነ ትገነዘባላችሁ፡፡ እንዲህ ይላል፡- “… ለድርቅ ተጎጂዎች እንዲደርስ የታሰበውን ድጋፍ ለግል ጥቅማቸው በማዋል ችግር የፈጠሩ (ችግር የፈጠሩ ሳይሆን ከተራበ  ወገን ላይ የነጠቁ!) 90 አመራሮች ከኃላፊነታቸው ተነስተው ጉዳያቸው በህግ እንዲያዝ ተደርጓል” (ይሄማ በጦር ፍርድ ቤት ነው መታየት የነበረበት!)
የፋና ዘገባ እንደሚጠቁመው፤ ሌሎች 6 የዞን አመራሮች ደግሞ ከህብረተሰቡ ለልማት የተሰበሰበ ገንዘብን ለግል ጥቅማቸው በማዋላቸው (ያፈጠጠ ያገጠጠ ምዝበራ በሉት!) ከኃላፊነት ተነስተዋል ተብሏል፡፡ (ለልማት እያሉ ህዝቡን ሲገፉት ኖረዋላ?!) ፍትህ ለህብረተሰቡ ያሰፍናሉ ተብለው የሚታመኑት ዳኞችም በአማራ ክልል “ከደሙ ንፁህ ነኝ” ለማለት አልቻሉም፡፡ (ሁሉም ባይሆኑም!) እናላችሁ…በዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ህብረተሰቡን ሲያጉላሉ የነበሩ የሁለት ዳኞችን ጉዳይ በማጣራት ከኃላፊነት እንዲነሱ ታዟል፡፡
የአማራ ክልል የመልካም አስተዳደር “ጉድ”፤ በዚህ ብቻ የሚያበቃ እንዳይመስላችሁ፡፡ ፖሊሶችንም አነካክቷል፡፡ እጅ መንሻ (ተሽሞንሙኖ ነው እንጂ “ጉቦ” እኮ ነው!) የሚጠይቁና ህዝቡን በማጉላላት የባለጉዳዩን መብት ተጋፍተዋል የተባሉ 45 የፖሊስ አካላት፤ ትጥቃቸውን እንዲፈቱ መደረጋቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ ሌሎች 32 የቀበሌ አመራሮች በፈጠሩት የመልካም አስተዳደር ችግር ከኃላፊነታቸው ተነስተው ጉዳያቸው በህግ እየታየ መሆኑን አመልክቷል፡፡ “የመልካም አስተዳደር ችግር የፈጠሩ…” የሚለው ከወንጀሉ ድርጊት ጋር ስለማይመጣጠን ተመጣጣኝ ቃል ይፈለግለት፡፡ መልካም ሰንበት!

Read 8069 times