Monday, 11 January 2016 12:20

የፀጉር ቀለሞችና የጤና መዘዛቸው

Written by 
Rate this item
(4 votes)

የሽበት ማጥፊያ ቀለሞችን አዘውትሮ መጠቀም ለካንሰር ያጋልጣል

ቀለም ተቀባ ወይ ወንዱ ሁሉ ዘንድሮ
ሽማግሌ ጠፋ ሽበት እንደ ድሮ ….
                           (ድምፃዊት በዛወርቅ አስፋው)
ዛሬ ዛሬ የሽምግልና ፀጋ የሆነው ሽበት በራስ ቅላቸው ላይ ሳይታይ የሚያረጁ ወንዶችና ሴቶች እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ ሽበት የብስለትና የአዋቂነት ምልክት መሆኑ እየቀረ የመጣ ይመስላል፡፡ አብዛኛው ሰው ነጭ ፀጉር ሳይታይበት ወደማይቀረው እርጅና መጓዝን መርጧል፡፡ በዚህም የተነሳ ሽበትን የሚያጠፉ የፀጉር ቀለሞች ተጠቃሚዎች በርክተዋል፡፡
በአገራችን በዚህ ዙሪያ የተደረገ ጥናት መኖሩን እንደማያውቁ የሚናገሩት የሥነ ውበት ባለሙያዋ ወ/ሮ ትርሀስ ሰለሞን፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የፀረ-ሽበት ቀለም ተጠቃሚው ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱን ይገልፃሉ፡፡ በቦሌ መድኀኒዓለም፣ በሣር ቤትና በሳሚት አካባቢ የሴቶችና የወንዶች የውበት ሳሎኖች ከፍተው አገልግሎት የሚሰጡት ባለሙያዋ፤ ከደንበኞቻቸው መካከል ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት የፀረ-ሽበት ቀለሞች ተጠቃሚ መሆናቸውን ይናገራሉ። የፀረ-ሽበት ቀለሞች ተጠቃሚ ደንበኞቻቸው በአማካይ በወር ሁለት ጊዜ ለዚሁ አገልግሎት ወደ ማዕከሉ እንደሚመጡ የጠቆሙት ወ/ሮ ትርሀስ፤ ቀለሙን ደጋግሞ የመቀባት ጉዳይ ደንበኞቻቸው እንደሚጠቀሙት የፀረ-ሽበት ቀለም አይነት እንደሚለያይ ገልፀዋል፡፡
ፀጉር ተፈጥሮአዊ ቀለሙን የሚይዘው በሰውነታችን ውስጥ በሚገኘው “ሜላሚን” የተሰኘ ኬሚካል ሳቢያ ሲሆን የኬሚካል መጠኑ መጨመርም ሆነ መቀነስ በፀጉራችን ተፈጥሮአዊ መልክ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ ዕድሜያችን እየጨመረ ሲሄድ የኬሚካል መጠኑ እየቀነሰ የሚመጣ ሲሆን በዚህም ምክንያት አዲስ የሚበቅለው ፀጉራችን ቀለም አልባ ሆኖ እንዲያድግ ያደርገዋል፡፡ ይህን ጊዜም ሽበት ይበቅላል፡፡ የፀጉር ቀለም አልባ ሆኖ ማደግ አንዳንድ ጊዜ በህመምና በዘር አማካኝነት ሊከሰት እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ አንዳንድ ሰዎች በወጣትነት ዕድሜ ላይ ሆነው ፀጉራቸው የሚሸብተውም በዚህ የተነሳ ነው፡፡
በዕድሜ መሸምገል የተነሳ የሚመጣውን የፀጉር መሸበት ለማጥፋት በተለይ የከተማ ነዋሪዎች የፀጉር ቀለም ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸው ይነገራል። እንደ ሥነ-ውበት ባለሙያዋ ወ/ሮ ትርሀስ አይነት ሥራቸው በቀጥታ ከፀጉር ጋር የሚያገናኛቸው ሰዎች ደግሞ፤ የዚሁ የፀረ-ሽበት ትግል አጋርና ምስክሮች ናቸው፡፡ በአገራችን በጉዳዩ ላይ የተደረጉ ጥናቶች ባይኖሩም፣ በአሜሪካ ኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ የተደረገ ጥናት፤ 68% የሚሆኑት ሴት አሜሪካውያን የፀረ-ሽበት ቀለም ተጠቃሚዎች መሆናቸውን አረጋግጧል፡፡ ታይም መፅሄት ያወጣው አንድ ዘገባም፤ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማን ጨምሮ ታዋቂ ፖለቲከኞች፣ የፊልምና የሙዚቃ ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች ዝነኞች የፀረ-ሽበት ቀለም ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡
Boomgril.com የተሰኘው በሴቶች ጤናና ውበት አጠባበቅ ላይ አተኩሮ የሚሰራው ድረ ገፅ ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው፤ በአሜሪካ የሴኔት አባላት ከሆኑና ዕድሜያቸው ከ46-74 ዓመት ከሆናቸው ሴቶች መካከል የፀረ ሽበት ቀለም ተጠቃሚ ያልሆነ አንድም ሰው አልተገኘም። በፀረ ሽበት ቀለሞች አጠቃቀም ላይ ሴቶች ከፍተኛ ድርሻ ቢኖራቸውም እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው ወንዶችም የፀረ ሽበት ቀለሙ ተጠቃሚ መሆናቸውንና የተጠቃሚው ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ድረ ገፁ አመልክቷል፡፡ የፀረ ሽበት ቀለም መቀባት ማራኪነትና ተወዳጅነት ይጨምራል የሚል እምነት በተጠቃሚዎች ዘንድ እንዳለም ተጠቁሟል፡፡ የፀረ ሽበት ቀለም ተጠቃሚዎች ለውበታቸው የሚጨነቁትን ያህል ለጤናቸውም ማሰብ እንዳለባቸው ያሳሰበው ድረ ገፁ፤ ቀለሙን አዘውትሮ መጠቀም ለተለያዩ የጤና ችግሮች እንደሚያጋልጥ ባለሙያዎችን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
የሥነ ውበት ባለሙያዋ ወ/ሮ ትርሀስ በአሁኑ ወቅት ለደንበኞቻቸው የተለያየ ዓይነት ደረጃ ያላቸውን የፀረ ሽበት ቀለሞች እንደሚጠቀሙ ያስረዳሉ፡፡ እንደ ደንበኛው ፍላጎትና ጥያቄም ቀለሞቹን በውበት ማዕከሎቻቸው ውስጥ በማቅረብ አገልግሎቱን ይሰጣሉ፡፡ በወ/ሮ ትርሀስ የውበት ማዕከል ውስጥ ለጥቂት ቀናት የሚያገለግሉ፤ በውሃና በዝናብ በቀላሉ የሚለቁ ዋጋቸው ርካሽ የሆኑ የፀረ-ሽበት ቀለሞች ይገኛሉ፡፡ ከተቀቡት በኋላ ለሳምንታት የማይለቁ፣ ወደ ፀጉር ውስጠኛው ክፍል በተወሰነ ደረጃ የሚዘልቅ በዝናብም በቀላሉ የማይለቁ፣ በዋጋ ወደድ ያሉ ቀለሞችም እንዳሏቸው የሚናገሩት ወ/ሮ ትርሀስ፤ እኒህ አይነቶቹ ፀረ ሽበት የፀጉር ቀለሞች በርካታ ተጠቃሚዎች እንዳሏቸውና በውበት ሳሎኖቻቸው ውስጥ በስፋት ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ይናገራሉ፡፡
በውስጠኛው የፀጉራችን ክፍል አልፎ ወደ ማዕከላዊው የፀጉራችን ክፍል የሚገባና በቀላሉ የማይለቅ፣ ለወራት እንደጠቆረ አሊያም እንደቀላ የሚዘልቅ የፀረ ሽበት ቀለም እንዳለ የሚገልፁት የሥነ ውበት ባለሙያዋ፤ ይህ አይነቱ ቀለም በዋጋው እጅግ ውድ በመሆኑ በአገራችን ገበያ ውስጥ እምብዛም እንደማይገኝ ይናገራሉ፡፡ አገልግሎቱን ፈልጎ ለሚመጣና የመክፈል አቅም ላለው ደንበኛ ግን የፀረ ሽበት ቀለሙን ከውጭ በማስመጣት ጥቅም ላይ እንደሚያውሉ ይገልፃሉ፡፡
የፀረ ሽበት ቀለም ተጠቃሚው ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄዱ ጥሩ ምልክት አይደለም የሚሉት የቆዳና የአባላዘር ስፔሻሊስቱ ዶ/ር አብርሃም ተከተል፤ ለፀረ ሽበትም ሆነ ለፀጉር ማቅለሚያነት ታስበው የሚሰሩ የፀጉር ቀለሞች በውስጣቸው ካንሰር አምጪ ኬሚካሎችን መያዛቸውንና የእነዚህ ኬሚካሎች ተደጋግሞ ጥቅም ላይ መዋል በካንሰር የመያዝ ዕድልን እንደሚጨምር አመልክተዋል። ቀደም ሲል በጥቅም ላይ ይውሉ የነበሩት የፀጉር ቀለሞች ከሰልና ታር የተባሉ ኬሚካሎችን የያዙ እንደነበሩ የሚናገሩት ዶክተር አብርሀም፤ በአሁኑ ወቅት የሚፈበረኩትና ጥቅም ላይ የሚውሉት በአብዛኛው ከፔትሮሊየም የሚሰሩና ሜቲክሲና ዲያሚይን የተባሉ ካንሰር አምጪ ኬሚካሎችን በውስጣቸው የያዙ ቀለሞች ናቸው ብለዋል። ምንም እንኳን እነዚህን ቀለማት አምራች የሆኑ አገራት ካንሰር አምጪ ኬሚካሎችን ለቀለም ምርቱ ግብአትነት ከማዋል መቆጠባቸውን የሚገልፁ ቢሆንም ምርቶቹ ሙሉ በሙሉ ከካንሰር አምጪ ኬሚካሎች የፀዱ ለመሆናቸው ማረጋገጫ መስጠት አለመቻላቸውንም ዶክተሩ ገልፀዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የፀረ ሽበት ቀለሞች ተጠቃሚው ቁጥር በአገራችን እየጨመረ መምጣቱ ጉዳዩን የበለጠ አሳሳቢ ያደርገዋል ያሉት የህክምና ባለሙያው፤ እነዚህ ሰዎች ቀለማቱን በሚጠቀሙ ጊዜ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባና አዘውትሮ ቀለሞቹን ከመጠቀም መቆጠብ እንደሚገባቸው ይመክራሉ። የፀረ ሽበት ቀለሞች ተጠቃሚዎች እጅግ ለከፋው የቆዳ ካንሰርና ለሌሎች የጤና ችግሮች ከመጋለጣቸው በፊት ከድርጊታቸው መቆጠብና እርጅና ተፈጥሮአዊ መሆኑን በመገንዘብ፣ ለውጦቹን በአግባቡ መቀበልና እንደ አመጣጣቸው ማስተናገድ እንደሚገባቸውም ዶ/ር አብርሃም ያስረዳሉ፡፡  


Read 15201 times