Monday, 11 January 2016 12:15

የተለወጠ ህይወት

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)

      የስብሰባ አዳራሹን የሞላውን ተሰብሳቢ ስሜት የሚፈታተን፣ የብዙዎችን ልብ በሃዘን የነካና “ወይ ሰው መሆን” የሚያሰኘው የህይወት ውጣ ውረድ ታሪካቸው ስሜት ይነካል፡፡ የኑሮ ሸክሙ ከብዷቸው፤ በልቶ ማደሩ ብርቅ ሆኖባቸው፣ ለእህል ያላነሱ ለሥራ ያልደረሱ ህፃናት ልጆችን ይዘው ለችግር የተጋለጡ እናቶች ያሳለፉትን መሪር የህይወት ውጣውረድና አሁን ያሉበትን የተሻለ ህይወት እያነፃፀሩ ሲናገሩ ፊታቸው በእንባ ይታጠባል፡፡ መሥራት እየቻሉ የሥራ ፈጠራ ስልጠናና መቋቋሚያ አጥተው የሰው እጅ ተመልካችና ምጽዋት ጠባቂ ለመሆን የተገደዱ ወጣት ወንዶች አሳዛኝ ታሪክና የዛሬው መድረሻ የስኬት ታሪካቸው በአዳራሹ የተገኙትን ተሰብሳቢዎች ቀልብ በእጅጉ የሣበ ነበር፡፡
 በብሪትሽ ካውንስል የሲቪል ሶሳይቲ ሰፖርት ፕሮግራም (ሲኤስኤስፒ) የበጀት ድጋፍ ተደርጐለት በኢየሩሳሌም የህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት ለሁለት ዓመታት ተግባራዊ የተደረገው ፕሮጀክት በሃዋሣ ከተማ የቆይታ ጊዜውን አጠናቆ ሲወጣ የፕሮጀክቱ የሥራ ኃላፊዎች፣ የፕሮጀክት ተጠቃሚዎችና የማህበረሰብ ምስርት ተቋማት ኃላፊዎች የጋራ ውይይታቸውን ለማካሄድ የተሰበሰቡበት አዳራሽ ድባቡ ለየት ያለ ነበር፡፡
 ኢየሩሳሌም የህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት በአምስት የተለያዩ አካባቢዎች (ድሬዳዋ፣ ሃዋሣ፣ ደብረዘይት፣ ባህርዳርና ደብረብርሃን) ከተሞች ላይ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችን ከፍቶ የሚንቀሳቀስ ድርጅት ሲሆን ድርጅቱ ህፃናትን ማዕከል አድርጐ፣ በቤተሰብ ላይ አተኩሮና ህብረተሰብን መሠረት አድርጎ በማህበረሰብ አቀፍ የልማት ሥራዎች በንቃት እየተሳተፈ ያለ ድርጅት ነው፡፡
ድርጅቱ ከልማት አጋሮች ጋር በትብብር ከሚሰራባቸው የልማት መስኮች አንዱ በብሪትሽ ካውንስል የሲኤስኤስፒ የበጀት ድጋፍ የሚደረግለት ፕሮግራም በርካታ ለችግር የተጋለጡ ህጻናት፣ አሳዳጊዎቻቸውንና ለችግር የተጋለጡ ወጣቶችን ተጠቃሚ አድርጓል፡፡
 ኢየሩሳሌም የህጻናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት (ኢሕማልድ) ሥራውን የሚያከናውነው ቀደም ሲል ተመስርተው በማህበረሰቡ ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ባሉና በርካታ ማህበራዊ ኃላፊነቶችን ከሚወጡ የማህበረሰብ ምስረት ተቋማት ጋር በመተባበር ነው፡፡ ይህ አሠራር ደግሞ ድጋፍ ማግኘት የሚገባቸውን ወገኖች በአግባቡ ለማግኘትና ፕሮጀክቱ የታለመለትን ግብ ለመምታት እንዲያስችል ያደረገው ተግባር ነው፡፡
 ኢሕማልድ ታህሳስ 8 ቀን 2008 ዓ.ም በሃዋሳ ባዘጋጀው የልማት ስኬት መመዘኛ ፕሮግራም ላይ የተገኙ ታዳሚዎች የውይይት መነሻቸው በዋናነነት መሠረት ያደረገው በሃዋሣ ከተማ በአዲስ ከተማ ክ/ከተማ ወስጥ ባሉ የፊለደልፊያ እና ዳካ ቀበሌዎች ላለፉት ሁለት ዓመታት ተግባራዊ ሲደረግ የቆየው ፕሮጀክት በተጠቃሚዎቹ ህይወት ላይ ምን ለውጥ አምጥቷል? ፕሮጀክቱ ተግባራዊ በተደረገበት ወቅት ያጋጠሙ ችግሮችና መሰናክሎች ምን ነበሩ? በሚሉ ጉዳዮች ላይ ነበር፡፡
በድርጅቱ የሥራ ኃላፊዎች፣ በመንግሥት ተጠሪዎችና በማህበረሰብ ምሥርት ተቋማት ኃላፊዎች ፕሮጀክቱን አስመልክቶ የተደረገው ሪፖርት ከቀረበ በኃላ የፕሮጀክቱ ተጠቃሚዎች ሃሳባቸውን እንዲገልፁና በፕሮጀክቱ ተጠቃሚ በመሆናቸው ያገኙትን ለውጥ እንዲሁም መሻሻል ይገባዋል ስለሚሏቸው ጉዳዮች እንዲናገሩ ዕድል ተሰጣቸው፡፡
በሃዋሣ ከተማ ውስጥ ከሚገኙ ሲቪል ማህበራትና ዕድሮች መካከል ዘጠኝ ያህሉ በዚህ ፕሮጀክት ውስጥ መታቀፍ የሚገባቸውን ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን በማሰባሰቡ ሥራ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ አምስቱ የመረዳጃ ዕድሮች (የአዲስ ከተማ ክፍለከተማ የከፍተኛ 1 ቀበሌ 01 ነዋሪዎች መረዳጃ ዕድር፣ የሴራሚክስ አካባቢ መረዳጃ ዕድር፣ ቅዱስ ሚካኤል መረዳጃ ዕድር፣ የሃዋሳ አዲስ ከተማ አስተዳደር የወጣቶች መረዳጃ ዕድርና የሃዋሣ ዕድሮች ጥምረት ኤች.አይ፣ ቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ልማት ማህበር) እንዲሁም አራቱ ምስርት ማህበራት (እናት ብድርና ቁጠባ ህብረት ስራ ማህበር፣ አዲስ ህይወት የጐዳና ተዳዳሪ ህፃናት መርጃ ማህበር፣ እኛው ለእኛው የነገ ተስፋ የማህበረሰብ ልማት ማህበርና ፌዝ ኦፍ ላቭ ፋሚሊ ሰርቪስ አሶሲዬሽን) ከኢየሩሳሌም የህፃናትና የማህበረሰብ ልማት ድርጅት ጋር በመተባበር ያከናወኗቸውን ተግባራት የሚያመለክቱ ሪፖርቶች በየማህበራቱ የሥራ ኃላፊዎች ቀርበዋል፡፡ ውይይቱ ድርጅቱ በቀጣይ ለሚያከናውናቸው ማህበረሰብ አቀፍ የልማት ሥራዎች ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው የገለፁት የድርጅቱ የፕሮግራም ማኔጀር አቶ ግርማ ከበደ የተጠናከረ ውጤት ተኮር የክትትልና የምዘና ሥርዓቶችን ዘርግቶ የሚንቀሳቀስ ድርጅት በመሆኑ ውጤታማ ተግባራትን ለማከናወን ችሏል ብለዋል፡፡
 በብሪትሽ ካውንስል የሲኤስኤስፒ ፕሮግራም በተገኘ የበጀት ድጋፍ ተጠቃሚ ከሆኑት ወገኖች አብዛኛዎቹ በከተማዋ ነዋሪ የሆኑና እጅግ አነስተኛ በሆነ የኑሮ ደረጃ ላይ ይኖሩ የነበሩ ወገኖች ከመሆናቸውም በላይ በፕሮጀክቱ በተደረገላቸው የስልጠናና የገንዘብ ድጋፍ ህይወታቸውን ለመቀየር የቻሉ ናቸው፡፡ የብዙዎቹ የህይወት ተሞክሮና ልምድ የሚሰጠው ትምህርት በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም። በወንድሟ ቤት እየኖረች ትምህርቷን ስትከታተል ጐረቤት በሚኖር ጐረምሣ ተገዳ በመደፈርዋና በማርገዝዋ ምክንያት እጅግ በርካታ መከራና ስቃይ የተፈራረቁባትና የወለደቻትን ህፃን በአግባቡ ማሳደግ ባለመቻልዋ ልጅዋ ለአዕምሮ ውስንነት ችግር የተጋለጠችባት እናት የዚሁ ስብሰባ ተካፋይ ነበረች፡፡ ይህቺ እናት ዛሬ በዚህ ፕሮጀክት በተደረገላት ድጋፍ ልጅዋን በአግባቡ ለመመገብና ከዚያም አልፎ ትምህርትዋን ለመከታተል እንድትችል ለማድረግ አግዟታል። ይህን እርዳታና ድጋፍ ቀደም ሲል አግኝታው ቢሆን ኖሮ ልጄ ለዚህ ችግር አትጋለጥብኝም ነበር በማለት ትናገራለች፡፡ የዚህ ፕሮጀክት እውን መሆን የሰዎችን ህይወት ከማሻሻልና ከመለወጥም በላይ የእሷን አይነት በርካታ ሰዎችን ህይወት ከሞት ለመታደግ የሚያስችል መሆኑንም ትገልፃለች፡፡
እናት ብድርና ቁጠባ ህብረት ስራ ማህበር ይህቺን ሴት ወደዚህ ፕሮጀክት በማምጣትና በፕሮጀክቱ በሚደረገው ድጋፍ ተጠቃሚ እንድትሆን በማድረጉ ረገድ ከፍተኛ ሚናውን ተጫውቷል፡፡ ይህ ሁኔታም ድርጀቱ የሚያከናውናቸውን ህብረተሰብ አቀፍ የልማት ሥራዎች ከማህበረሰብ ምስርት ተቋማት ጋር በጣምራ መስራቱ ምን ያህል ውጤታማ እንዳደረገው አመላካች ነው፡፡
 በዚህ የፕሮጀክት ማጠቃለያ ግምገማ መድረክ ላይ በኢየሩሳሌም የህፃናትና የማህበረሰብ ልማት ድርጅት የሃዋሣ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ማስረሻ ክብረት እንደተናገሩት ፕሮጀክቱ ውጤታማ ለመሆን የቻለው ከማህበረሰብ ምሰርት ተቋማት ጋር በጋራ በመሥራቱ፣ ሥራዎች ከመጀመራቸው በፊት የአመለካከት ለውጥ በማምጣት ላይ በመሠራቱና ተከታታይነት ያለው ክትትልና ድጋፍ ማድረግ በመቻሉ ነው፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ ተገኝተው የህይወት ተሞክሮአቸውንና በፕሮጀክቱ ያገኙትን ለውጥ ከተናገሩት ተጠቃሚዎች መካከል የአብዛኛዎቹ ታሪክ እጅግ አሳዛኝና አስከፊ የነበረ ቢሆንም አሁን በፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ከሆኑ በኋላ በህይወታቸው ላይ ያሳዩት ለውጥና መሻሻል ለማመን የሚያስቸግርና ድርጅቱን በእጅጉ የሚያስመሰግን ነው። ከእነዚህ እጅግ መሳጭ፣ አሳዛኝና አስከፊ ህይወት ውስጥ አልፈው ዛሬ አስገራሚ ለሆኑ የኑሮ መሻሻልና ለውጥ ከበቁ በርካታ የፕሮጀክቱ ተጠቃሚዎች መካከል በአንዱ ታሪክ እንሰነባበታለን፡፡
 ባለታሪካችን የሰላሳ ሁለት ዓመት ወጣት ነው፡፡ አሸናፊ ጃሞሎ በእግሩ ላይ በደረሰበት ጉዳት ሳቢያ እንደልቡ ለመራመድና እየተሯሯጠ ሥራ ለመሥራት ባይችልም በወንዶች ፀጉር ማስተካከል ሙያ ላይ ተሰማርቶ ቤተሰቡን ያስተዳድር ነበር፡፡ በትዳር ውስጥ ያፈራትን አንዲት ሴት ልጅ በሚገባ እየተንከባከበና ቤተሰቡን በአግባቡ እየመራ ባለበት ወቅት የኑሮ ውድነቱ፣ የቤት ኪራይ ንረቱና የሥራው እየደከመ መሄድ ኑሮው ዕለት ከዕለት እየከበደው እንዲሄድና ድህነት እንዲበረታበት ግድ አለው፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ ባልና ሚስቱ በአንድ ጣራ ስር መኖር እንዳይችሉ አደረጋቸው፡፡ ሚስት የቤተሰቡን የድህነት ኑሮና የልጇን ረሃብ ቁጭ ብላ ከማየት አረብ አገር ሄዳ ሠርታ ለመለወጥ ማሰቧን ለባሏ ነገረችው፡፡ አሸናፊ ሁኔታው እጅግ ቢያስደነግጠውም አይሆንም ብሎ ለመሞገት እና ሚስቱን ከሃሳቧ ለማስቀረት የሚችልበት ዕድል አልነበረውምና “ነገ ያልፍልኛል ብሎ” ሃሳቧን ተቀብሎ በቤት ውስጥ የሚገኝና በደህና ጊዜ ያፈራቸውን ንብረቶች በሙሉ ሸጦ ሚስቱን ወደ አረብ አገር ላካት፡፡ ከንብረቶቹ በቤት ውስጥ ያስቀረው አንዲት የስፖንጅ ፍራሽ ብቻ ነበረች። ህፃን ልጁን ታቅፎ በባዶ ቤት ኑሮውን ተያያዘው፡፡ ፀጉር የማስተካከል ሥራ አምሽቶ መሥራትን የሚጠይቅ ቢሆንም እሱ ህፃን ልጁን ከቤት ጥሎ ይህንን ለማድረግ ባለመቻሉ ከሥራው ተሰናበተ፡፡ ኑሮ የበለጠ መራራ ሆነበት ችግሩ እየበረታ፣ ረሃቡ እየጠና ሄደ፡፡ ህፃን ልጁ በረሃብ ልትሞትበት ሆነ፡፡ እንደ ልቡ ተሯሩጦና የቀን ሥራ ሠርቶ ልጁን ለማሳደግ እንዳይችል አካል ጉዳተኛነቱ፣ በሙያው ተቀጥሮ እንዳይሰራ ደግሞ ቀጣሪ ማጣቱ ኑሮውን የበለጠ መሪር አደረጉበት፡፡ አረብ አገር ሄጄ ልሥራና ኑሮአችንን ላሻሽል ብላ የሄደችው ባለቤቱ የውሃ ሽታ ሆነችበት፡፡ ሁኔታውን እያዩ ጥቂት እርዳታና ፍርፋሪ በሚሰጡት ሰዎች እየታገዘ ልጁን ለአንድ ዓመት ያህል አብራው እንድትቆይ አደረጋት፡፡ ከዚህ በላይ ግን መቀጠል አልቻለም፡፡
የሚላስ የሚቀመስ ነገር በሌለበት ባዶ ቤት ውስጥ ልጁን ማቆየት በረሃብ እንድትሞት ከማድረግ ሌላ ምንም ጥቅም የሌለው መሆኑን ሲረዳ ህፃኗን ወስዶ ለባለቤቱ ቤተሰቦች ሰጠ፡፡ ከዚያም ረሃቡንም ሆነ እርዛቱን ለብቻው ለመጋፈጥ ወስኖ ለልመና ሰው አያውቀኝም ወዳለበት ሃገር ዲላ ሄደ፡፡
 እዚያው በጐዳና ህይወት ከአንድ አመት ከሁለት ወራት ቆይታ በኃላ ወደ ሃዋሳ ተመልሶ ጐዳና ላይ እየኖረ ቀደም ሲል ያውቁት የነበረና በፀጉር ማስተካከል ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ጋር እየሄደ ለዕለት ጉርሱ የምትሆን ትንሽ ትንሽ ሥራ መሥራቱን ጀመረ፡፡
 በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለ ሃዋሳ አዲስ ከተማ አስተዳደር የወጣቶች መረዳጃ ዕድር አገኘውና አሸናፊን በብሪትሽ ካውንስል የሲኤስኤስፒ ፕሮግራም የበጀት ድጋፍ እየተደረገለት በኢየሩሳሌም የህፃናትና የማህበረሰብ ልማት ድርጅት ተግባራዊ ወደሚደረገው የድጋፍ ፕሮጀክት ይዞት መጣ፡፡ በፕሮጀክቱ የሚሰጠውን የህይወት ክህሎት ስልጠና እና የገንዘብ ድጋፍ በማግኘት ወደ ሥራ ገባ፡፡
 ከፕሮግራሙ “የወጣቶች ራስ የማስቻል ድጋፍ” ያገኘውን አራት ሺህ ብር አስቀምጥልኝ ብሎ የሰጠውና በዛው የፀጉር ሥራ ላይ ተሰማርቶ በነበረበት ጊዜ ያገኘው ጓደኛው ከራሱ 12 ሺህ ብር ጨምሮ በ16 ሺህ ብር ፀጉር ቤት ከፍቶ ሰጠው፡፡ የሚልስ የሚቀምሰው አጥቶ ጐዳና የወጣው፣ የዕለት ጉርሷን መሸፈን አቅቶት የገዛ ልጁን ለሚስቱ ቤተሰቦች የሰጠው አሸናፊ ህይወት ፊቷን አዞረችለት “አሼ የወንዶች ፀጉር ቤት” በማለት በስሙ በከፈተው የወንዶች የፀጉር ማስተካከያ ቤት ውስጥ ሥራውን በትጋት መሥራት ቀጠለ፡፡ ሁለት ዓመት በማይሞላ ጊዜ የጓደኛውን 12 ሺህ ብር እና ከፕሮጀክቱን ተመላሽ መደረግ የሚገባውን ገንዘብ ከፍሎ አጠናቀቀ፡፡
 ፀጉር ቤቱንም ከስር ከስር እያሻሻለና እያስተካከለ በአሁኑ ወቅት ካፒታሉን ሃያ ሁለት ሺህ ብር አድርሶና በሥሩ መሰል የህይወት ታሪክ የነበራቸውን አራት ሰራተኞች ቀጥሮ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ “የዚህ ፕሮጀክት ቀጣይ መሆን እንደ እኔ ላሉና ጐዳና ላይ ወድቀው ለነበሩ ወገኖች ሁሉ መድህን ነው” ሲል ይናገራል፡፡

Read 4178 times