Monday, 11 January 2016 11:34

“ሳይቃጠል በቅጠል” … “ዕባብን መቅጨት በእንጭጩ”

Written by 
Rate this item
(16 votes)

     ከዕለታት አንድ ቀን አንድ እጅግ ሀብታም ሰው ወደ ገበያ ሄዶ ዕቃ እየገዛ ሳለ አንዲት በቀቀን (Parrot) ያያል፡፡ በቀቀኗ አንድ ጊዜ ጠዋት የነገራትን ነገር በቃሏ ይዛ ቀኑን ሙሉ የመድገም ችሎታ ያላት ናት፡፡ ነጋዴው በዚህ ችሎታዋ በጣም ተደስቶ ሻጩ የጠየቀውን ገንዘብ ሰጥቶ ለመግዛት ይወስናል፡፡
“ስንት ነው ዋጋዋ?” ሲልም ይጠይቃል፡፡
ያ ነጋዴም፤
“ጌታዬ ይቺን በቀቀን ለመሸጥ አደለም ይዣት የመጣሁት፡፡ እቤት ያደገች በመሆንዋ ሁሌም እጐኔ ሆና ታጫውተኛለች፡፡ እኔ የምነግደው ሌላ ሌላ ነገር ነው” አለው፡፡
ሀብታሙ ሰው፤
“ግዴለህም፤ ያልከውን ዋጋ እከፍልሃለሁ” አንተ ቤት ከምትቀመጥ እኔ ቤት ብትሆን ብዙ ሰው ያያታል፡፡ እኔን ብዙ ትላልቅ ሰዎች ሊጠይቁኝ ስለሚመጡ በቀቀኗ የመጐብኘትም ዕድል ታገኛለች” ይለዋል፡፡
ነጋዴው፤
“ጌታዬ፤ እንደልጄ የማያትን በቀቀን በገንዘብ አልለውጣትም፡፡ ሰው የነገራትን ደግማ የመናገር ችሎታ እንድታዳብር ዕድሜ ልኬን ደክሜያለሁ፡፡ ስለዚህም በጭራሽ ለሰው አሳልፌ አልሰጣትም” ብሎ ግትር አለ፡፡
ሀብታሙ ሰውም ተስፋ ቆርጦ ወደሌላ ገበያው ዞረ፡፡ ሆኖም በቀቀኗ ከአዕምሮው ልትወጣ አለቻለችም፡፡ ስለሆነም፤ አንድ ሰው ቀጥሮ፣ የዚያን ነጋዴ ቤት አስጠንቶ፣ ጥሩ አጋጣሚ ሲገኝ በቀቀኗን ሊያሰርቃት ዕቅድ አወጣ፡፡ ዕቅዱ ተሳካና በቀቀኗ ተሰርቃ መጣችለት፡፡
በዚያን ዕለት ሀብታሙ ሰው ቤት ቅልጥ ያለ ግብዣ ተደርጐ ትላልቅ ሰዎችም ጥተዋል፡፡ ከተበላ ከተጠጣ በኋላ ሀብታሙ ሰው አስገራሚዋን በቀቀን እንግዶቹ እንዲያዩለት ጋበዘ፡፡ ተራ በተራ ሳይሆን አንድ ላይ እንዲመጡም አደረገ፡፡
እንግዶቹ ወደበቀቀኗ ቀርበው የምትለውን ለመስማት ጓጉተዋል፡፡
“በይ የፈለግሺውን ተናገሪ” አላት ሀብታሙ ሰው፡፡
በቀቀኗም፤
“ሰርቀህ ነው ያመጣኸኝ፤ አንድ ቀን ትጠየቅበታለህ!” አለችው፡፡
ለካ ይህንን ቃል ጠዋት ያስጠናት ሰርቆ ያመጣት ቅጥረኛ ኖሯል!
“ለክፉና ለአመንዝራ ትውልድ ምልክት አላሳየውም፡፡ እንዲሁ አጠፋዋለሁ!” ይላል ፍካሬ - ኢየሱስ፡፡ ያለምልክት እንዳንጠፋ ያሰጋናል፡፡ የክፉ ዘመን ሌብነት እጅግ ያፈጠጠ ይሆናል፡፡ ሌብነት ለጊዜው ያስደስት ይሆናል፡፡ ውሎ አድሮ ግን መጠየቅ የግድ ይሆናልና የአገርም የህዝብም ዋጋ ያስከፍላል፡፡ የሚሊዮኖች ዐይን ከገባንበት ገብቶ ፈልፍሎ ያወጣናልና!
ሀብትን በንፁህ ታታሪነት ማግኘት ንፁህ እንቅልፍ እንድንተኛ ያደርገናል፡፡ በአንፃሩ ለአንዲት ቤሣ ማትረፊያ እንኳን የተጠቀምንበት ዘዴ፣ “ቢዝነስም ይሁን አራዳነት” ፣ ሌብነት ያለበት ከሆነ፣ ይዋል ይደር እንጂ እንቅልፍ መንሳቴ አይቀርም፡፡ “ማክቤት እንቅልፍን ገደላት፣ በእኩለ-ሌሊት አፍኖ” እንዳለው ነው ሼክስፒር፤ በፀጋዬ ቃል-ቀመር፡፡ “የሰው ሚስት ይዞ የተኛ ኮሽ ሲል ይደነብራል” እንደሚባለው እንቅልፍ ያሳጣል - በማደንዘዣ ካልተኛን በስተቀር! በቃኝን አለማወቅም ትልቅ በሽታ ነው፡፡ ይብቃኝ፤ ማለትም ለከት ማበጀት ነው! አንድ ቀን መያዜ አይቀርም ማለትም ያባት ነው!
ሀገራችን በንፁህ የሥራ ጥረት ሀብት የሚፈራባት ሀገር መሆኗ ካቆመ ቆይቷል። ወደ ሙስና ሀገርነት ከተሸጋገረች ሰንብታለች! ምዝበራ የዕለት የሰርክ-እንጀራ ሆኗል። የኢኮኖሚ አቅማችን ደካማ ስለመሆኑ ጧት-ማታ እያወሳን፤ ዝርፊያው ላይ አለመስነፋችን አስደናቂ ግርምቢጦሽ (Irony) ነው፡፡ ጥንት “የቢሮክራሲ አሻጥር” ሲባል የነበረው ዛሬ በይፋ መጥቷል፡፡ “ክራይ-ሰብሳቢም” ይባል “ደላላ” ድልብ ድልብ ሙሰኛ እያየን ነው፡፡ ጥንት “አሻጥረኛ ነጋዴ” ይባል የነበረው ዛሬ ህጋዊ ህገ-ወጥ ሆኖ ብቅ ብሏል፡፡ ጥንት “አቀባባይ ከበርቴ” የተባለውን ዛሬ “ደላላ” ብለን ስሙን አኮሰስነው እንጂ በተቋማዊም፣ በቡድናዊም፣ በግላዊም መልኩ ፈጦ ይታያል፡፡ ከሁሉም የሚከፋው ደግሞ የቢሮክራቱ ነው፡፡ አንድ ቦታ ያስቸገረን ሰው ከማስወገድ ይልቅ ሌላ ቦታ ኃላፊነት መስጠት አስገራሚ ልማድ ሆኗል፡፡ “በአዲስ መልክ ሥራ ጀምረናል” እንደማለት መሆኑ ነው፡፡ “በአዲስ መልክ ምዝበራ ጀምረናል” ለማለት እየተንደረደርን ነው! መታወቅ ያለበት በግልፅ ፈጠው የወጡ አሻጥሮች እንዳሉ ሁሉ ረቂቅ የሆኑ አሻጥሮችም እንዳሉ ነው፡፡ የስልጣን ሽፋን፣ የወገን ሽፋን የፖለቲካ ሽፋን፣ የሀብት ሽፋን፣ የማዕረግ ሽፋን፣ የኔትወርኩ ሽፋን … ምኑ ቅጡ፣ የረቂቅ አሻጥር ግብዓቶች ናቸው፡፡ ዞሮ ዞሮ የሌብነት ሽፋኖች ናቸው! መፈተሽ ያለባቸው ሽፋኖች ጥልቅ ዐይን ይፈልጋሉ፡፡ መርማሪ ዐይን ይፈልጋሉ፡፡ ሀገርን አስቀድሞ ማየትን ይጠይቃሉ፡፡ የራስ ንፁህ ልቡናን ይፈልጋሉ፡፡ በዚያው ልክ በመረጃና በዕውቀት መታገዝን ይሻሉ፡፡ “ሳይቃጠል በቅጠል”፣ “ዕባብን መቅጨት በእንጭጩ” የሚሉን አበው፣ የሚያቆጠቁጠውን የሥልጣን ብልግናና ሙስና እንድንገታ ነው፡፡ ልብና ልቡና ይስጠን!!

Read 8138 times