Saturday, 02 January 2016 12:13

የክፉ ቀን ስንቅ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(0 votes)

      ገመርቱ ክንዴ ተወልዳ ያደገችው አዋሳ ከተማ እምብርቱ ላይ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን አጥርን ድጋፍ አድርገው በተሰሩ ላስቲክ ቤቶች ውስጥ ነው። የህይወትን ሀሁ በጎዳና ላይ የጀመረችው ገመርቱ የህይወትዋን አብዛኛውን ዕድሜ ያሳለፈችውም እዛው ጎዳና ላይ ነበር፡፡ እናትና አባቷ በጎዳና ህይወት ውስጥ ተዋውቀውና ትዳር መስርተው ከዛው ከጎዳናው ላይ እሷን ወደዚህች ዓለም ሲያመጧት ቀጣይ ህይወትዋና ኑሮዋ ጎዳናው ላይ እንደሚሆን አምነው ነበር። ህፃኗ ገመርቱ እናትና አባቷ ገብርኤል ቤተክርስቲን አጥር ስር በሰሩት የላስቲክ ቤት ውስጥ ማደጓን ቀጠለች ቤተሰቦቿ እሷን ትምህርት ቤት ልከው የሚያስተምሩበት አቅም ስላልነበራቸው የገመርቱ ውሎና አዳር እንደሷ ጎዳና ላይ ከሚኖሩ ልጆች ጋር ነበር፡፡ ሁኔታዋ ያሳዘናቸው አንድ በጎ አድራጊ ገመርቱ ወደ ትምህርት ቤት መግባት የምትችልበትን ሁኔታ አመቻቹና እዛው ገብርኤል ቤተክርስቲን ቅጥር ግቢ ውስጥ ወደሚገኝ የቤተክህነት ት/ቤት እንድትገባ አደረጓት። እስከ 6ኛ ክፍል ድረስም ትምህርቷን እንድትቀጥል ድጋፍ ሲያደርጉላት ቆይተው ከ6ኛ ክፍል በኋላ እርዳታቸውን አቋረጡ፡፡
የገመርቱም ትምህርት ቤት የመሄድ ተስፋ ከዚሁ ጋር አብሮ ጨለመ፡፡ ተመልሳ ከጎዳና ጓደኞቿ ጋር እዛው ጎዳና ላይ መዋልዋን ቀጠለች፡፡ የጎዳና ተዳዳሪነት በባህሪው ከቦታ ቦታ መዘዋወርን የሚፈልግ በመሆኑ በገብርኤል ቤተክርስቲያን አካባቢ ይኖሩ የነበሩ የጎዳና ተዳዳሪዎች ወደሃዋሳ ሥላሴ ቤተክርስቲያን አካባቢ መኖሪያቸውን አደረጉ፡፡ እነገመርቱ ሰፈር ቀየሩ፡፡ ኑሮ በአዲሱ ሰፈር የወትሮ ኡደቷን ቀጠለች ገመርቱ በአካልም በዕድሜም እያደገችና እየበሰለች መጣች። በአፍላ የወጣትነት ዕድሜዋ ህይወቷ በጎዳና ላይ በሚደርሱ የተለያዩ ችግሮች ሳቢያ እንዳይበላሽ ሥጋት ስለገባት እዛው ጎዳና ላይ ካገኘችውና ልቧን ከማረከው የጎዳና ወጣት ጋር ጋብቻ መሰረተች፡፡ ጎዳና ላይ የተወለደችው ገመርቱ እዛው እጎዳናው ላይ የመጀመሪያ ልጇን ተገላገለች፡፡ የቀኑ ፀሐይ፣ የሌቱ ቁር በእሷና በህፃን ልጇ ላይ መፈራረቁና የእሷ እድል በወለደችው ልጇ ላይ ሲደገም ማየቱ ሐሞቷን አፈሰሰው፡፡ ምንም አማራጭ አልነበራትምና ልጇን ይዛ እዛው ጎዳና ላይ መዋል ማደሯን ቀጠለች፡፡ አራሷ ገመርቱ እንደ አገር ባህልና ወግ ሳትታረስ፣ የረባ ምግብ እንኳን አግኝታ ጠግባ ሳትመገብ ጎዳና ላይ ሆና ልጇን ማሳደጉን ተያያዘችው። ብዙም ሳትቆይ ሁለተኛ ልጇን አርግዛ ወለደች፡፡ ኑሮ ለገመርቱ እጅግ ከባድ ሆነ፡፡ ከእርጥባን በሚገኝ ገንዘብ ሁለት ህፃናት ማሳደግ ምን ያህል ከባድ እንደሚሆን የሚያውቀው የደረሰበት ብቻ ነው። ኃላፊ አግዳሚውን ለምና በምታገኛት ጥቂት ሳንቲም ልጆቿን መግባ ማሳደር መቻሏ የተአምር ያህል ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ኑሮዋ እጅግ ከብዶና መሮባት በነበረበት ወቅት በሃዋሳ ከተማ ውስጥ የሚንቀሳቀስና የጎዳና ተዳዳሪ ህፃናት ላይ ትኩረት አድርጎ ከሚሰራው አዲስ ህይወት የጎዳና ተዳዳሪ ህፃናት መረጃ ማህበር ጋር ተገናኘች፡፡ ወደዚህ ማዕከል መጥታ በማዕከሉ የሚደረገውን ድጋፍ እንድታገኝ ለማድረግ የማዕከሉ የሥራ ኃላፊ ከባድ ጥረት አድርገው ነበር፡፡ በአብዛኛው የጎዳና ተዳዳሪ ህፃናት እንረዳለን እያሉ የሚመጡ ድርጅቶች እነሱን ፎቶ አንስተውና አነጋግረው ከመመለስ ውጪ የሰጧቸው ተጨባጭ እርዳታና ድጋፍ አለመኖሩ ልጆቹ ሁሉንም ድርጅቶች በጅምላ እንዲጠሏቸውና እንዲሸሿቸው አድርጓቸዋል፡፡ ከአዲስ ህይወት የጎዳና ተዳዳሪ ህፃናት መርጃ ማህበር የመጣችው የዚህች ወጣት ሁኔታ ግን ጠንከር ያለ ነበር “ኑና የህይወት ክህሎት ስልጠና ውሰዱ፤ ልጆቻችሁም በመደበኛ ት/ቤት መማር የሚያስችሏቸውን የተለያዩ የቁሳቁስ ድጋፎች ይገኛሉ፤ እናንተም መስራት የምትችሉበት የመንቀሳቀሻ ድጋፍ ታገኛላችሁ” በማለት እንደምንም አባብላና አግባብታ ገመርቱን በብሪቲሽ ካውንስል የሲቪል ሶሳይቲ ሣፖርት ፕሮግራም የበጀት ድጋፍ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን በሚያከናውነው ኢየሩሳሌም የህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት የሚመራው እና በማህበረሰብ ምስርት ተቋማት አስተባባሪነት የሚተገበረው “ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን በአጋርነት እንደግፍ!” የድጋፍ ፕሮግራም ይዛቸው መጣች፡፡
 ለአምስት ቀናት የሚሰጠውን የክህሎት ስልጠና ወስደው ሲያጠናቅቁም ለእያንዳንዳቸው መቋቋሚያ ይሆናቸው ዘንድ አራት አራት ሺህ ብር ተሰጣቸው፡፡ ኑሮዋን የመለወጥና ከጎዳና ህይወት የመላቀቅ ህልምን ለያዘችው ገመርቱ ይህ አራት ሺህ ብር የተአምር ያህል ነበር፡፡ ሸቀጥ ማከፋፈያ ሄዳ ጥቂት የሱቅ እቃዎችን ገዛችና ከባለቤቷ ጋር ስራዋን ጀመረች፡፡ ዕለት ከዕለት ኑሮዋ እየተሻሻለ ሥራዋ እየለመደ ሄደ፡፡ በተገባላት ቃል መሰረት ልጇ ዩኒፎርም ተሰፍቶለት ት/ቤት ገባ፡፡ ይህ ሁኔታ የገመርቱን ተስፋ ይበልጥ አነሳሳው፡፡ አቅሟን አበረታው። እሷ ባለፈችበት አስከፊ የጎዳና ህይወት ውስጥ ልጆቿ እንዳያልፉ አጥብቃ ትመኝ ስለነበርም ጠንክራ በመስራት ህይወቷን ለውጣ ከጎዳና ህይወት ለመላቀቅ ግብግቧን ተያያዘችው፡፡ የሱቅ የሸቀጥ ዕቃዎችን ገዝታ እየቸረቸረች የምታገኛት ጥቂት ትርፍ ልጆቿን አብልታና አጠጥታ ለማሳደር እንድትችል ከማድረጓም በላይ ዕለት በዕለት ጥቂት ሳንቲሞችን እየቆጠበች እንድታስቀምጥ አቅም ሆኗት ነበር፡፡ ከጥቂት ወራት በኋላም ቆጥባ ባስቀመጠችው ገንዘብ ከላስቲክ ቤቷ ወጥታ የቤት ዕቃዎቿ የተሟሉላት አነስተኛ ቤት ይዛ መኖር ጀመረች፡፡ ልጆቿንና ባለቤቷን ከጎዳና ህይወት አላቃ ኑሮዋን እያሻሻለች ያለችው ገመርቱ ዛሬ በሸቀጣሸቀጥ ንግድ ሥራ ላይ ተሰማርታ እየሰራች ልጆቿን በእንክብካቤ በማሳደግና በማስተማር ላይ ትገኛለች፡፡ “የጎዳና ህይወት በእኔ ይብቃ፤ልጆቼ ጎዳና ላይ ማደግ የለባቸውም” ብላ የቆረጠችው ገመርቱ በኢየሩሳሌም የህፃናትና የማህበረሰብ ልማት ድርጅት አስተባባሪነት በሚከናወነው የሲኤስኤስፒ ፕሮግራም ድጋፍ ህይወታቸው ከቀየሩ በርካታ ተጠቃሚዎች መካከል አንዷ ሆናለች፡፡ ባለፈው ሳምንት በአዋሳ ከተማ ውስጥ በተካሄደው በእየሩሳሌም የህፃናትና የማህበረሰብ ልማት ድርጅት የሚደገፈው የሲኤስኤስፒ ፕሮግራም ማጠቃለያ ምዘና ፕሮግራም ላይ ተገኝታ የምስክርነት ቃሏን ስትሰጥ ንግግሯን ሳግ እየቆራረጠው ነበር። “እኔ ዛሬ ሌላ ሰውነኝ፡፡ አሁን ያለሁበትን ህይወት አልመውነበር እንጂ እኖረዋለሁ ብዬ ፈፅሞም አስቤም አላውቅም ነበር ለዚህ ድርጅት ምስጋናዬ ከፍ ያለ ነው” በማለት ነው ስሜቷን የገለፀችው፡፡
እንደ ገመርቱ ሁሉ በዚህ የሲኤስኤስፒ ፕሮግራም ተጠቃሚ ሆነው ህይወታቸውን የለወጡና ኑሮአቸውን ያሻሻሉ በርካታ ሰዎች በዕለቱ ምስክርነታቸውን ሲሰጡ ውለው ነበር፡፡ የአብዛኛዎቹ ህይወት እጅግ አሳዛኝና አስከፊ የነበረ ቢሆንም አሁን ያሉበት ደረጃ ለማመን የሚያስቸግርና ድርጅቱን በእጅጉ የሚያስመሰግን ነው።
ከተመሰረተ 30 ዓመታትን ያስቆጠረው አንጋፋውና አገር በቀሉ እየሩሳሌም የህፃናትና የማህበረሰብ ልማት ድርጅት በ3 ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ አተኩሮ ይንቀሳቀሳል እነዚህም
የመሠረታዊ አገልግሎቶች ተደራሽነት
የአየር ንብረት ለውጥን ማጣጣም አደጋን መቀነስና ኑሮን ማሻሻል
አጋር ከሆኑ ምስርት የማህበራት ተቋማት ጋር በመሆን የድርጅታዊ የአቅም ልማት ስራዎችን ማካሄድ ናቸው።
ድርጅቱ ስራዎቹን በአብዛኛው የሚያከናውነው ከማህበረሰብ ምስርት ተቋማትና ማህበራት ጋር በመሆን ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ ስራዎቹ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለመሆን ያስቻሉ እንዲሆኑ አድርጎታል፡፡ የደቡብ ክልል ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ማህበራት አስተባባሪ አቶ መርዕድ አሰፋ በአዋሳ ከተማ ውስጥ ተካሂዶ በነበረው የፕሮግራም ግምገማና ምዘና ላይ እንደተናገሩት ድርጅቱ ስራዎቹ ስኬታማ እንዲሆን ያስቻለው ስራውን የሚያከናውንው በህብረተሰቡ ውስጥ ባሉና የችግሩ ተጠቃሚ የሆኑ ሰዎችን በቀጥታ ሊያገኙ ከሚችሉ ምስርት ማህበራት ጋር አብሮ መስራት በመቻሉ ነው ብለዋል፡፡ ይህም በተጨባጭ የሚታይ ውጤት ያስመዘገበ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ድርጅቱ ትኩረት አድርጎ የሚሰራው ለችግር ተጋላጭ በሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ሲሆን፣ የገንዘብ ድጋፍና እርዳታ ከመሰጠቱ በፊት አመለካከት ለውጥ ላይ መስራቱና ስልጠናና የክህሎት ማሳደጊያዎችን መስጠቱ ለስኬቱ ትልቅ እገዛ እንዳደረገለት አቶ መርዕድ ተናግረዋል። ተጠቃሚዎቹ በቂ ስልጠና በማግኘታቸው ገንዘቡን በሚወስዱበት ጊዜ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ጠንቅቀው ያውቃሉ ያሉት አቶ መርዕድ ስለዚህም የተሰጣቸውን ገንዘብ በአግባቡ ተጠቅመው ለውጥ ለማምጣት ችለዋል ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ድርጅቱን ስኬታማ እንዲሆን ያስቻለው ድጋፍ የተደረገላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በቅርብ የመከታተልና እገዛ የማድረግ ስራን ጠንክሮ በመስራቱ እንደሆነም አቶ መርዕድ አስገንዝበዋል፡፡
ከሁለት ዓመታት በፊት በተካሄደ ጥናት ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን በጋራ መደገፍ በሚል ፕሮጀክት ተቀርፆ በሲኤስኤስፒ (የሲቪል ማህበረሰብ ድጋፍ ፕሮግራም) በሚል ተቋም በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ላለፉት ሁለት ዓመታት ስራው መካሄዱን የገለፁት የእየሩሳሌም የህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት የፕሮግራም ማኔጀር አቶ ግርማ ከበደ ሥራው በአራት ክፍሎች ሲከናወን መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ እነዚህም ክፍሎች ተጋላጭ የሆኑ ህፃናት፣ ወጣቶችና ሴቶችን ለመሰረታዊ አገልግሎቶች ተደራሽ ማድረግ፣ የእነዚህን ክፍሎች ኑሮ ማሻሻል፣ ተጋላጭ የሆኑ ህፃናትና ችግር ውስጥ ያሉ የማህበረሰብ ክፍሎችን መሸከም አቅም ያለው ማህበረሰብ መፍጠርና በእነዚሁ የማህበረሰብ ተቋማት መካከል ድጋፍና ትብብር መፍጠርና ማጠናከር ዋንኞቹ መሆናቸውንም አቶ ግርማ ጠቁመዋል። በዚህም መሰረት ፕሮግራሙ ለ200 ህፃናት ለ200 አሳዳጊዎች፣ ለ100 ለችግር ተጋላጭ ወጣቶችና ወደ 30 ለሚጠጉ ረዳት ለሌላቸው አረጋውያን ድጋፍ አድርጓል። ይህንን ስራም ያከናወነው በከተማዋ ውስጥ ከሚገኙ ዘጠኝ ምስርት ማህበራትና ዕድሮች ጋር በመተባበር ነው ድርጅቱ ለችግር ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ለመድረስ የሚጓዝበትን መንገድ እና የፕሮግራሙ ተጠቃሚ ወገኖችን የስኬት ታሪክ በቀጣይ ክፍል ይዘን እንቀርባለን፡፡

Read 4114 times