Saturday, 02 January 2016 11:48

ኢህአዴግ የሚያዋጣው እውነታውን መጋፈጥ ነው!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(19 votes)

“ብቸኛው የነፃነት መንገድ የቡዳ ፖለቲካችንን ማቆም ነው” - ዶ/ር መረራ ጉዲና”
     የዕድሜያቸውን አጋማሽ በማስተማር ከፈጁበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መንገድ (“ኢህአዴግን በመቃወሜ” ማለታቸው ነው!) መባረራቸውን የሚናገሩት የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ዶ/ር መረራ ጉዲና፤“የኢትዮጵያ የታሪክ ፈተናዎች እና የሚጋጩ ህልሞች” በሚል ርዕስ ሁለተኛ መጽሐፋቸውን ለንባብ አብቅተዋል፡፡ “የኢህአዴግ ቆርጦ - ቀጥል ፖለቲካ” የሚል ንዑስ ርዕስም ተሰጥቶታል - መፅሀፉ፡፡
ከተማሪነት እስከ መምህርነት የዘለቁበትን አንጋፋውን የአገሪቱን ዩኒቨርሲቲ ሳይወዱ በግድ  እንዲለቁ መደረጉ ሳያንስ ከመቅጽበት ከሚኖሩበት ቤት መፈናቀላቸውንም ይተርካሉ -በመጽሃፋቸው፡፡ የዩኒቨርሲቲውን አስተዳደር በተመለከተ በውስጣቸው ያኖሩትን ትዝብትና በደልም አቅርበዋል፡፡ ከእሳቸው በተጨማሪ ኢንጂነር ግዛቸው እንዲሁም ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ --- የአስተዳደሩ ሰለባ እንደሆኑም ይጠቅሳሉ፡፡  (ዩኒቨርሲቲውን መልካም አስተዳደር አያውቀውም ማለት እኮ ነው?)
ምናልባት ለረዥም ዘመን ካገለገሉበት ዩኒቨርሲቲ፣ በጡረታ መውጪያቸው ግድም  የሚገባቸውን ክብር ሳያገኙ መባረራቸው ስሜታቸውን ይጎዳው ይሆናል፡፡ ግን ደግሞ ፈረንጆቹ፤ “A blessing in disguise” እንደሚሉት ዓይነትም የሆነላቸው ይመስላል፡፡ (አበሻ “ሳይደግስ አይጣላም” ይላል!) እናላችሁ----በተለይ ከሥራቸው መባረራቸውን ተከትሎ ከመኖሪያቸውም እንዲለቁ መገደዳቸው፣ጎጆአቸውን አዲስ አበባ ዳርቻ ላይ የማድረግ ድፍረት ሳያስታጥቃቸው አልቀረም፡፡ (#so what?; እንዳትሉኝ!) ዶ/ር መረራ እንደሚሉት ታዲያ፤የአሁኑ መፅሃፋቸው የአዲሱ የመኖሪያ ሰፈር ውጤት ነው፡፡
የአገራችንን ፖለቲካ ከአፄው አንስቶ እየዳሰሰ፣ በአስቂኝ ገጠመኞች እያዋዛ፣እስከ ኢህአዴግ የግንቦቱ ምርጫ ድረስ በጥልቀት የሚተነትነው መፅሃፉ፤አንዴ ከገለጡት መልሰው የሚከድኑት ዓይነት አይደለም፡፡ እኔ መቼም ተደምሜበታለሁ፡፡ (እንኳንም ሳንሱር ታሪክ ሆነ!!) የዶ/ሩ መጽሐፍ በዘመኑ የአራዳ ቋንቋ “ፀዴ” ነው፡፡ ጥንቅቅ ብሎ የተሰናዳ፡፡ ኢህአዴግን በትችትና በነቆራ አፈር ድሜ የሚያስግጠውን ያህል ተቃዋሚዎችንም ሆነ ዳያስፖራዎችን አይምራቸውም፡፡ አሜሪካንን ራሷንስ መች ተዋት! የታሪኩ ፍሰትና ቀለል ብሎ መቅረብ ለመጽሐፉ አንባቢን ያበዛለታል የሚል ግምት አለኝ፡፡ ከሁሉም ያስደነቀኝ ግን ዶ/ሩ፤ ፀለምተኝነት የሞላውን የጦቢያን ፖለቲካ፤እንደ አጓጊ ልብወለድ ከሽነው መተረካቸው ነው፡፡ እንዲህ ልባችሁን አንጠልጥዬ ዝም ብላችሁ ፌር አይደለምና ቢያንስ በፖለቲካ ወጋችን መግቢያና መውጪያ ላይ ከዶ/ሩ መጽሐፍ ቆንጥሬ ጥቂት አቀምሳችኋለሁ፡፡ ስለ ዩኒቨርሲቲ ከጻፉት ውስጥ የቀነጨብኩላችሁን ቆጥባችሁ አንብቡ፡-
“---ኢህአዴግ የምር በኔ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ መኖር መጨነቅ የጀመረው ውሎ፤ አድሮ ይመስለኛል፡፡ የመጀመሪያውን ምልክት የሰማሁት በፓርላማ ውስጥ በነበርኩበት ጊዜ ነው፡፡ አንድ ቀን ዩኒቨርሲቲ ቆይቼ ወደ ቤቴ ለመሄድ 4 ኪሎ አካባቢ ስደርስ የሆነ ነገር ትዝ ብሎኝ መኪናዬን አቁሜ ስልክ ደወልኩ፡፡ በሁለተኛው ቀን ይሁን፣ በሦስተኛው ቀን ፓርላማ ስሄድ፣ የኢሕአዴግ የፓርላማ አባላት ለሚቀርቡዋቸው የኛ ድርጅት አባላት፣ “አለቃችሁ አዘጋጅቷቸው ወጥቶ፣ 4 ኪሎ ደርሶ ደውሎላቸው፣ የኦሮሞ ተማሪዎች አመፅ እንዲቀሰቅሱ አደረገ” የሚል ሰማሁ፡፡ የኦሮሞና የትግራይ ተማሪዎች መጋጨታቸው እርግጥ ቢሆንም፣ እኔ ግን ከነጭራሹ ሁኔታውን የሰማሁት በማግስቱ ነበር፡፡ ምናልባት፣ እኔን ይከታተል የነበረ መንገደኛ ደህንነት በመላምት አገናኝቶ፣ ለአለቆቹ ነግሯቸው ይሆናል ብዬ ገርሞኝ ዝም አልኩ፡፡
አሁን ወደ ኋላ ሳየው፤ በእኔ አስተማሪ መሆን ዲፓርትመንት አካባቢ የተቸገሩ የኢሕአዴግ አባላት እንዳሉ ለማወቅ ችያለሁ፡፡ ለአብነት፣ ቆየት ብሎ አንድ ኢሕአዴግ መሆኑን ለማሳየት የሚጥር ልጅ፣ እኔ ጋ ዝቅተኛ ውጤት አግኝቶ ለውጥልኝ ብሎ ይጠይቀኛል፡፡ “እኔ በሕይወቴ በልመና ውጤት ለውጬ አላውቅም፣ ተጎዳሁ ካልክ እንደገና በሌላ ሰው እንዲታረምልህ ለዲፓርትመንቱ አመልክት” አልኩት፡፡ ያለመቀየሬን ሲያውቅ በዛው ጠፋ፡፡ እንዴት የዩኒቨርሲቲ አስተማሪ እንደሆነ፣ ምን ትምህርት እንደሚያስተምርም ባላውቅም፣ዩኒቨርሲቲ ውስጥ አሁንም አየዋለሁ…፡፡”
ቀደም ብዬ እንደነገርኳችሁ ዶ/ር መረራ በዚህ መጽሐፋቸው፤ ስለ ዩኒቨርሲቲው ብዙ አሳዛኝ ታሪኮችንና ትዝብቶችን በማስረጃ እያስደገፉ ይተርኩልናል፡፡ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ለ6 ዓመት ገደማ ሳያሰልሱ የጠየቁትን የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ እንዴት እንዳስቀረባቸው፣(ለማን ሊሰጡት ነው?) ከዩኒቨርሲቲው ሊባረሩ አካባቢ ለ6 ወር ገደማ ያለ ደሞዝ ማስተማራቸውን፣ (#የኮሙኒቲ ሰርቪስ; እኮ አይደለም፣ለመክፈል ጠመው ነው!) እናም ሌሎች ብዙ የፖለቲካ ታሪኮች ይነግሩናል፡፡ ለጊዜው ግን ወደ ዛሬው የፖለቲካ ወጋችን ልውሰዳችሁ፡፡ (ወደ ወቅታዊው የፖለቲካ ትኩሳት ማለቴ ነው!) ሰሞኑን እንደሰማነው  
በኦሮሚያ ክልል ተከስቶ የነበረውን ከ3 ሳምንት በላይ የዘለቀ ተቃውሞ የፈጠረው ሁከት፤  መንግስት ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሬዋለሁ ብሎ ነበር፡፡ (እዚህም እዚያም ግን ረብሻ አልጠፋም!) ባሳለፍነው ሳምንት በአምቦ ዩኒቨርሲቲና በወለጋ ዩኒቨርሲቴ ተቃውሞ ተነስቶ ነበር ተብሏል፡፡  #ከግቢያችን ፌደራል ካልወጣ አንማርም; ያሉ ተማሪዎችም እንደማይወጣ ሲነገራቸው፣ ሻንጣቸውን ሸክፈው ከግቢው ወጥተዋል አሉ፡፡
በክልሉ በተማሪዎች የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ በተፈጠረው ግጭትና ሁከት ሳቢያ በብዙ ሚሊዮን ብሮች የሚገመት ሃብትና ንብረት መውደሙን ኢቢሲ በተደጋጋሚ ነግሮናል፡፡  እርግጥ ነው ለእንደኛ አይነቱ ምስኪን ድሃ አገር፣ማንኛውም የሀብትና ንብረት ውድመት ከፍተኛ ጉዳትና ኪሳራ እንደሚያደርስ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ኢቢሲ የወደመውን የንብረት መጠን በሚሊዮኖች እያሰለ በውስጣችን ሊማስረጽ መሞከሩን እንደ ኃጢዓት አልቆጥርበትም፡፡ (ትዕዛዝ እኮ ነው የሚፈጽመው!) እንዲያም ሆኖ ግን ቅሬታዬን ከመሰንዘር ወደ ኋላ አልልም፡፡ እናም ከንብረት ባሻገር በግጭቱና በሁከቱ የጠፋውስ ህይወትስ? ስል ቢያንስ ራሴን እጠይቃለሁ፡፡ እነ ኢቢሲን ደግሞ እታዘባቸዋለሁ፡፡ ቅድሚያ መሰጠት የነበረበት ለጠፋው የሰው ልጅ ህይወት ነበር፡፡ የጠፋው ህይወት በገንዘብ ሊሰላ የማይችል የትየለሌ ኪሳራ ነው! ለወላጆች---ለቤተሰብ----ለማህበረሰብ-------ለአገር ጭምር ጉዳቱ ግዙፍ ነው፡፡ ይሄን ሁሉ የምለው በአገራችን ለህይወት እምብዛም ዋጋ አለመስጠታችን ጠፍቶኝ አይደለም፡፡ ነገር ግን ጎጂ ባህል በመሆኑ፣የሰብዓዊነትን ስሜት ስለሚያጠፋ -----መወገድ እንዳለበት ይሰማኛል፡፡ አመለካከቱ ከሰው ተራ የሚያወጣ ስለሆነ አይረባንም፡፡   
ይሄ ሁሉ ሃተታ ለምን አስፈለገ? ወደ መንግስት ለመምጣት አስቤ ነው፡፡ እስካሁን በተፈጠረው ግጭትና ሁከት ሳቢያ የጠፋው የሰው ህይወት ቁጥር አልተገለጸም፡፡ በማተሚያ ቤት የማሽን ብልሽት ሳቢያ ባለፈው ማክሰኞ የወጣው የቅዳሜው እንግሊዝኛ ሪፖርተር እንደዘገበው፤ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ከምክር ቤት አባላት በሁከቱ ሳቢያ በህይወት ላይ የደረሰውን ጉዳት አስመልክቶ ጥያቄ ቢቀርብላቸውም ዘለው አልፈውታል፡፡ የሟቾች ቁጥር እንዳሁኑ ሳያሻቅብ ተመሳሳይ ጥያቄ ከጋዜጠኞች የቀረበላቸው የመንግስት ኮሙኒኬሽን ፅ/ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ጌታቸው ደሬሳ፤“የቁጥር ጨዋታ አይደለም የያዝነው” ብለው አልፈውታል፡፡   ያኔ ምናልባት በሁከቱ መባባስ ተረብሸው ይሆናል ልንል እንችላለን፡፡ በወቅቱ የተጣራና የተጠናቀረ የቁጥር መረጃ በእጃቸው ላይኖር ይችላል ብለን ሰበብ ልንፈጥርላቸውም እንችላለን፡፡   ሆኖም ግን ይሄው እስከዛሬ የሟቾችንም ሆነ የቆሰሉ ዜጎችን ቁጥር ከመንግስት አልሰማንም፡፡  (ኢህአዴግ የቁጥር ፎቢያ አለበት የሚባለው ከምር ነው እንዴ?!)
የሆኖ ሆኖ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች የተገኙ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤እስካሁን በብጥብጡ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከ100 በላይ ደርሷል፡፡ (አሳዛኝ ክስተት ነው!) ከ1500 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ቆስለው በተለያዩ ሆስፒታሎች ህክምና እየተከታተሉ ነው ተብሏል፡፡
በኦሮሚያ ክልል የብጥብጡ ቀስቃሽ ናቸው በሚል የታሰሩ ዜጎችን በተመለከተ እስካሁን ከመንግስት የተሰጠ መረጃ ባይኖርም ብዙ ሺዎች እንደሆኑ ይነገራል (መረጃ ሲጠፋ ወደ ግምት መገባቱ አይቀርም!) የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ባወጣው መግለጫ፤የፓርቲውን ከፍተኛ አመራሮች ጨምሮ 500 የሚደርሱ አባላቱ እንደታሰሩበት አስታውቋል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ በበኩሉ፤አባላቱ እየታሰሩበት መሆኑን ጠቁሞ ወቅቱ የፓርቲ ፖለቲካ የምናደርግበት አይደለም ብሏል፡፡ የሰማያዊ አመራሮች በሁኔታዎች  ተስፋ መቁረጣቸውንም ተናግረዋል - እነሱም ለመታሰር ተራቸውን እየጠበቁ እንደሆነ በመግለፅ፡፡
እንግዲህ እንዳለመታደል ሆኖ የጦቢያ የተቃውሞ ማግስት ድባብ፣ በጣም አስቀያሚና ጨፍጋጋ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ወደፊት ከመጣነው ርቀት የበለጠ ወደ ኋላ የምንጓዘው በእንዲህ ያለው ክፉ ወቅት ነው፡፡ የ97 ምርጫ ማግስት የፖለቲካ ቀውስ ያስከተለውን አሳምረን እናውቀዋለን፡፡ ዛሬም ድረስ ውጤቱን እየኖርነው እንገኛለን፡፡ የበለጠ የሚያሳዝነው ደግሞ ካለፈው ስህተታችን ለመማር ዝግጅቱም ሆነ ፈቃደኝነቱ የሌለን መሆኑ ነው፡፡ (ከርሞ ጥጃ ማለት እኛ ነን!) ይታያችሁ … እስካሁን ያወራነው በኦሮሚያ ክልል የተከሰተውን ችግርና ያስከተለውን ጥፋት ብቻ ነው፡፡ በአማራ ክልል በተቀሰቀሰው ግጭት ስለደረሰው ጥፋትና ጉዳት የተነገረ ነገር የለም፡፡ ከመንግስት የሰማነው ብቸኛ መረጃ ቢኖር፣ሁሉን ነገር በቁጥጥር ስር ማዋሉን ብቻ ነው፡፡ በሰው ህይወት ላይ ምን ያህል ጉዳት ደረሰ? ግጭቱ ዳግም እንዳይከሰት ምን ተዘይዷል? (የሃይል እርምጃ ጊዜያዊ እንጂ ዘላቂ መፍትሄ አይሆንም!)
 ዓላማዬ መንግስት “አለርጂክ ነው; እየተባለ ስለሚወራበት የቁጥር ጉዳይ መሞገት  አይደለም፡፡ ይልቁንም ኢህአዴግ ሁሌም ከእውነቱ ጋር መጋፈጥ እንደሚሻለው ለማሳሰብ ነው፡፡  ግን እውነቱ ምንድን ነው? ለምሳሌ የኦሮሚያ ክልል ተቃውሞ (ረብሻ) በውጭ የፀረ-ሰላም ኃይሎች ጉትጎታና ቅስቀሳ የተከሰተ አይመስለኝም፡፡ (ከስንት ሺ ማይል ርቀት መምራት ከቻሉማ አደጋ አለው!) አያድርገውና ረብሻውና ሁከቱ ሙሉ በሙሉ በ“ፀረ-ሰላም ኃይሎች” ቀንደኛ መሪነትና ትዕዛዝ ሰጭነት የተከናወነ ከሆነ እኮ የህዝቡን ቀልብ ማርከዋል ማለት ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ወላ ለኦህዴድ በሉት ለኢህአዴግ አሊያም ለመንግስት ትልቅ ኪሳራ ነው፡፡ የውጭ ኃይሎች የህዝቡን ልብ እስኪማርኩት ድረስ የት ነበሩ? (ሥራቸውን ትተውታል እንዴ?!) ደግነቱ ደሞ መንግስትም የረብሻና ሁከቱ መንስኤ ሙሉ በሙሉ የውጭ ፀረ-ሰላም ኃይሎች ነው አላለም፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ በፓርላማ ለተወካዮች ም/ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ፤ በሥራ እጦት ሳቢያ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ያደረበት የኦሮሚያ ወጣትና ከኢኮኖሚው ዕድገት ተጠቃሚ መሆን ያልቻለ አርሶ አደር በሁከቱ ተሳታፊ ነበር ብለዋል፡፡ (የሚያዋጣው ከዚህም የበለጠ እውነታውን ለመጋፈጥ መድፈር ነው!) የመንግስት ኮሙኒኬሽን ፅ/ቤት በበኩሉ፤በኦሮሚያ ክልል ለተቀሰቀሰው ሁከት ሰበቡ ሙሉ በሙሉ የውጭ ፀረ ሰላም ኃይሎች ናቸው የሚል ድምዳሜ ላይ አልተደረሰም ብሏል፡፡ (እንኳንም አልተደመደመ!) ከዚህ በተረፈ ሰላሙን ያውርድልን-----ከመለያየታችን በፊት ዶ/ር መረራ የቡዳ ፖለቲካችን በሚል ካሰፈሩት ጽሁፍ ጥቂት ቅንጭብ እነሆ፡-    
“ከሕልም ዓለም ሳንወጣና የሚጋጩ ሕልሞቻችንን ይዘን የፖለቲካ ጉዟችንን ቀጠልን፡፡ ጨርሶ ቅርጫ እንኳ የማይመስሉ ምርጫዎች ውስጥ ገብተን ወጣን፡፡ በፖለቲካ አካሄዳችን መሰረታዊ ለውጥ ካላመጣን፣ ይኸው ሁኔታ የሚቀጥል ይመስለኛል፡፡ ከኢሕአዴጎች መጫወቻነትም የምንወጣ አይመስለኝም፡፡ ለቡዳ ፖለቲካችን መድኃኒት ፈልገን፣ መሐል መንገድ በመሰብሰብ የህዝቦችን የጋራ ትግል በጋራ ካልመራን፣ በሕልሞቻችን ዓለም ውስጥ ቀጥለን ስንዋዥቅ ከመኖር ያለፈ ሥራ እንደማንሰራ ያለፈው የአርባ አመታት፣ ወይም የሃያ አምስት ዓመታት የትግል ታሪካችን በማያሻማ መንገድ አረጋግጦልናል፡፡ ሁላችንም ከሕልሙ ዓለም ወጥተን በእውኑ ዓለም በውል ካልታገልን መስዋእትነታችን ፍሬ አልባ ከመሆን አያልፍም፡፡ እዚህ ላይ የኢሕአዴግ ቀለብተኛ ላልሆኑ የተቃዋሚ ኃይሎች አስምሬ ማስረዳት የምፈልገው፣ ለሕዝቡ ሆነ ለራሳቸው መብትና ክብር ለመታገል የቆረጡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወጣቶች አሉ፡፡ የማይሳካ ሕልሞቻችሁን ለማሳካት ብላችሁ ይህንን ወጣት ከንቱ መስዋእትነት አታስከፍሉ፡፡ ብቸኛው የነፃነት መንገድ የቡዳ ፖለቲካችንን በማቆም፣ ለተባበረ የጋራ ሕዝባዊ ትግል መሰለፍ መሆኑን ለአንድ አፍታ እንኳ መዘንጋት እንደሌለባችሁ ነው፡፡ ----”  

Read 4795 times