Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 11 February 2012 14:36

የዕውቀት በሮች “የማይጠይቅ አያውቅም

Written by 
Rate this item
(3 votes)

ዕውቀት መሰላል ነው፡፡ በዕውቀት መሰላልነት የማያመልጡት አዘቅጥ የለም፡፡ በዕውቀት መሰላልነት የማይወጡት ከፍታ የለም፡፡ ዕውቀት መሰላል ነው፡፡ ከድህነት አረንቋ ወደተሻለ የኑሮ ረባዳ ያወጣል፡፡ ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ ወደተደላደለ ኑሮ ከፍ ያደርጋል፡፡ ከለየለት የከፋ ድህነት ወደተጨበጨበለት የተደነቀ ሀብት ያደርሳል፡፡ ዕውቀት መሰላል ነው፡፡ ተግቶ የረገጠውንና የጨበጠውን ወደ ላይ ያስመነጥቃል፡፡ ሳይታክት ለሚፈልገውና ለሚጠቀምበት የስኬት ፍኖት ሆናል፡፡ “ሰው ሲፈጠር ከፍ ያለ አእምሮ ተሰጠው፤ ከፍ ባለው አእምሮውም ላይ በጊዜ ብዛት ዕውቀት ጨምሮበት የምድር ጌታ ሆነ፡፡ “ ይላሉ ነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ፡፡

የምድር ጌታ የሚያደርገው ዕውቀት ነው፡፡ ከምድር ባርነት ወደ ምድር ጌትነት ወይም ወደ ዓለም አለቅነት የሚያወጣው ዕውቀት ነው፡፡ ዕውቀት ይሞርዳል፡፡ ዕውቀት ይስላል፡፡ የተሞረደና የተሳለ ማንነት በዕውቀት አማካኝነት የተገነባ ማንነት እንደሆነ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ዕውቀት የታጠቀ በንግግሩ ለዛ ያስታውቃል፡፡ ዕውቀት ልዩነት ይፈጥራል፡፡ በተማረ እና ባልተማረ፤ ባነበበ እና ባላነበበ መካከል ግልፅ ልዩነት አለ፡፡ ዕውቀት ሲጨምር ብዙ ነገር አብሮት ይጨምራል፤ ሲያንስም ብዙ ነገር አብሮት ያንሳል፡፡ ገቢ፣ የኑሮ ደረጃ ወዘተ …በደሀ እና ሀብታም መካከል ትልቅ ልዩነት የሚፈጥረው ዕውቀት ነው፡፡ 
ነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ “መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር” በተሰኘ መጽሐፋቸው እንዲህ ይላሉ፤ “… ሰው በዓለም ላይ ጌታ የሆነው ግን በዕውቀት ብቻ ነው፡፡ በጉልበትማ ቢሆን አህያና ግመል ይበልጡት የለምን፤ ስለዚህ ዕውቀት የሌለው ህዝብ ለኑሮው የሚያስፈልገው ነገር ሁሉ ይወደድበታልና ሊመቸው አይችልም፡፡ ሰው ፈፅሞ የሚመቸው መሰናክልን ነገር ሁሉ አሸንፎ የምድር ጌታ ሁኖ በዓለም ከኖረ ወዲያ ነው፡፡ ስለዚህም ዕውቀት የሌለው ሕዝብ ሁሉ ለብቻው መንግሥት ቢኖረውም ባይኖረውም ዕውቀት ያላቸው ሕዝቦች ይገዙታል፡፡ አንዱን የበላይ ሌላውን የበታች፤ አንዱን ገዢ ሌላውን ተገዢ ሕዝብ የሚያደርግ ዕውቀት ነው፡፡ የሰለጠኑ ሀገራት በዕውቀት ስለበለጡን እንዳሻቸው ያደርጉናል፡፡ እኛ ዕውቀት ስለሌለን እንደፈለጉት እንሆንላቸዋለን፡፡ ልዩነት ዕውቀት ነው፡፡ ይኼ ዕውቀት ወደኛ የሚገባበት በርካታ በሮች አሉ፡፡ ጥያቄ የዕውቀት መግቢያ ዋና በር ነው፡፡ የማይጠይቅ አያውቅም፡፡ በሚያዩትና በሚሰሙት ነገር የጥያቄ ሽል በልብ ውስጥ ሳይላወስ እና ሳይጠይቁ ደግም ዕውቀትን መታጠቅ አይቻልም፡፡ ከመጠየቅ ማወቅ ይወለዳል፡፡ አዋቂዎች ጠያቂዎች ናቸው፡፡ ጠያቂዎች አዋቂዎች ናቸው፡፡ ሁለቱም እውነት ነው፡፡ የመጠየቅን ጠቃሚነትና መሠረታዊነት በህፃናት መመልከት ይቻላል፡፡ ህፃናት ብዙ በመጠየቅ የሚታወቁ ፍጡራን ናቸው፡፡ ወደ መረዳት የሚወስደው መንገድ የተዘረጋው በጥያቄ ወለል ላይ ስለሆነ አብዝተውና አጥብቀው ይጠይቃሉ፡፡ ጥያቄው መልስ ይወልዳል፡፡ መልሱ ዕውቀት ይሆናል፡፡ ህፃናቱ የሚጠይቁት ራሳቸውን ሳይሆን እኛን ነው፡፡ እኛን ይጠይቁናል፤ እኛም መልስ እንሰጣቸዋለን፡፡ (እርግጥ ነው አንዳንዴ መመለስ የማንችለውን ወይም ጭራሽ አስበነው የማናውቀውንና መረዳቱ ምንም የሌለንን ነገር ጠይቀው ክው ያደርጉናል፡፡ ይሄኔ መልስ በሚመስል ነገር ወይም በጫወታ አታለን እንሸውዳቸዋለን፤ “ይሞታል ወይ ታዲያን” እየዘፈንን፡፡)እንደ አዋቂ ጥያቄዎች የምንጠይቀው ግን ሌላ ሰውን ብቻ ሳይሆን እራሳችንን ጭምር ነው፡፡ ጥያቄውም ወደ ሌላው ተሰንዝሮ ወይም ወደ ራስ ተወርውሮ ዕውቀትን ያጠምዳል፡፡ የማይጠይቅ ሊማር አይችልም፡፡ የማይማር አዋቂ አይሆንም፡፡ ስለዚህ መማርም ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ ፒተር ሴጅ እንዲህ ይላል፤ “Real learning gets to the heart of what it means to be human. Through learning we re-create our selves. Through learning we become able to do something we never were able to do. Through learning we extend our capacity to create, to be part of the generative process of Life.” 
በእርግጥ በመማር ዳግም ራስን መፍጠር ይቻላል፡፡ በመማር ከዚህ በፊት የማይችሉትን መስራት ይቻላል፡፡ መማር የሚቻለው መጠየቅ ሲቻል ነው፡፡ አሪፍ ተማሪ አሪፍ ጠያቂ ነው፡፡ መጠየቅ የጥሩ ተማሪነት መስፈርት ነው፡፡ መማር ደግሞ ማወቅ! **
ኒውተን ቁጭ ብሏል፡፡ ቁጭ ብሎ አካባቢውን ይቃኛል፡፡ ቁጭ ብሎ አየር ይምጋል፡፡ በዚህ መሀል ከዛፍ ላይ ፍሬ ሲወድቅ አየ፡፡ በማየት ብቻ አላለፈም፡፡ ስላየው ነገር አብሰለሰለ፡፡ ለምን? አለ፡፡ እንዴት? ብሎ ጠየቀ፡፡ በማየቱ መነሻነት፣ በለምንና እንዴት ጥያቄው ግፊት አዲስ ነገር አወቀ፡፡ አውቆ ለዓለም አሳወቀ፡፡ ሰር አይዛክ ኒውተን የመሬትን የስበት ህግ አገኘ፡፡ “ነገር በዓይን ይገባል” ይላሉ አበው፡፡ ነገር ብቻ ሳይሆን ዕውቀትም በዓይን ይገባል” ማየት ማወቅ ነው፡፡ ከማየት ዕውቀት እኛ ውስጥ መሠራት ሊጀምር ይችላል፡፡ ወይም ቀድመን በጣልነው መሠረት 

ላይ በመመልከት ብዛት የዕውቀት ቤት እንገነባለን፡፡ ብዙ ሳይንሳዊ ግኝቶች አትኩሮና አጥርቶ ከማየት የተጠነሰሱ ናቸው፡፡ ድንገት ከማየት ሀሳብ ሊፀነስ ይችላል፡፡ በአትኩሮት በማየት ሀሳቡ ይጐለብታል፡፡ በጊዜ ሂደት ሀሳቡ ይመረመርና ነጥሮና ጠርቶ ይወጣል፡፡ ዕውቀትም ይሆናል፡፡ የብዙ ደራሲዎች የልብ-ወለዳቸው መነሻ ሀሳብ ከመመልከት የተገኘ ነው፡፡ ጥቃቅን የሚባሉ ነገሮች ወይም ሁኔታዎች እይታ ታላላቅ የሚባሉ ሀሳቦችን ይሰጣል፡፡ ትንሹን ከማየት ትልቁ ይፀነሳል፡፡ ተራውን ከመመልከት ክቡሩ ይረገዛል፡፡ ተረግዞም ይወለዳል፡፡ የታላላቅ ፈጠራ ሰዎች ዓይን ታናናሽ ነገሮችን ሳይቀር አትኩሮ ተመልካች ነው፡፡ አትኩሮ መመልከት ዓለም ትኩረት የሚሰጠውን ነገር ለማስገኘት ዋናው መሳሪያ ነው፡፡ ዶናልድ ላቱማሂና እንዲህ ይላል፤ “What is the key to innovation? The answer, or at least an important answer, is 

becoming an observer. By observing how we and other people do things, we will spot opportunities for improvement.”“የፈጠራ ቁልፍ ምንድነው? መልሱ ተመልካች መሆን የሚል ነው፡፡ ሌሎች ሰዎች እና ራሳችን ነገሮችን እንዴት እንደምንሠራ በመመልከት የመሻሻል ዕድሎችን እናውቃለን፡፡”ዕውቀት ከመመልከት ይሰራል፡፡ ዕውቀት በዓይን ይገባል ማለትም ሌላ ሳይሆን ይኸው ነው፡፡

 

Read 7844 times Last modified on Saturday, 11 February 2012 14:40