Tuesday, 29 December 2015 07:32

አላትዮን - ዘመናዊው የግል ሆስፒታል

Written by 
Rate this item
(9 votes)

ባለሃብቱ የመንግስትን ድጋፍ አድንቀው፣ የጉምሩክ አሰራርን ነቅፈዋል
ለህክምና ባለሙያዎች የድህረ ምረቃ ትምህርት እንዲመቻችላቸው ጠይቀዋል

   ከሆስፒታሉ ስያሜ እንጀምርና አላትዮን ማለት ምን ማለት ነው?
አላትዮን የሶስት ቋንቋዎች ማለትም (የሶሪያ፣ ላቲንና ግሪክ) ውህድ ነው ትርጉሙም ቅን፣ ሐቀኛ፣ እውነተኛ (አማናዊ) እንደማለት ነው፡፡
በህክምና ሙያ ውስጥ ለምን ያህል ጊዜ ቆዩ? ትምህርትዎንስ የት ነው የተከታተሉት?
በህክምና የመጀመሪያ ድግሪዬን ያገኘሁት ከጐንደር ዩኒቨርስቲ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የህክምና ፋኩሊቲ ደግሞ ሁለተኛ ዲግሪዬን አግኝቻለሁ፡፡ ከ10 ዓመት በላይ በህክምና ስፔሻሊቲ በአገር ውስጥና በውጪ አገር ሰርቻለሁ፡፡
የት የት ሰርተዋል?
በአገር ውስጥ የተለያዩ ቦታዎች ላይ ሰርቻለሁ። በጅማና በአዋሳ ዩኒቨርስቲም ለተወሰኑ ጊዜያት ሰርቻለሁ፡፡ ከአገር ውጪ ላይቤሪያ ውስጥ ነው የሰራሁት፡፡ መርሊን በተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ተቀጥሬ ነው የሄድኩት፡፡
ለምን ያህል ጊዜ በዚያ ቆዩ? በምን ሁኔታስ ነበር የሚሰሩት?
ከዚህ ስሄድ የተዋዋልኩት ለአንድ አመት ነበር። ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ከውል ጊዜዬ በፊት ነው ወደ አገሬ የተመለስኩት፡፡ 96 አልጋዎች ባሉበት ሆስፒታል ውስጥ ብቻዬን ነበር የምሰራው፡፡ ቀዶ ህክምናውንም፣ የማዋለድ ሥራውንም፣ የህፃናት ህክምናውንም እኔው ነበርኩ የማከናውነው፡፡ ፈፅሞ ጊዜ አልነበረኝም፤ በውጥረት ነበር የምሰራው፡፡ የሚከፈለኝ ክፍያና የምሰጠው አገልግሎት ፈፅሞ አልመጣጠን ሲለኝ ወደ አገሬ መመለስ እንዳለብኝ ወሰንኩና መጣሁ፡፡
ወደ አገርዎ ከተመለሱ በኋላስ?
ከላይቤሪያ እንደተመለስኩ እዚሁ አዋሳ ከተማ ውስጥ ተከፍቶ አገልግሎት በመስጠት ላይ የነበረ ክብሩ ሆስፒታል የተባለ የግል ሆስፒታል ባለቤት ጋር ተገናኘሁ፡፡ አቶ ክብሩ ወርቁ ይባላል። ምንም አይነት ዝምድናም ሆነ የቅርብ ትውውቅ የለንም። ግን በቃ ሆስፒታሉን ስራበት ብሎ ሰጠኝ፡፡ አንተ አስተዳድረው፤የኪራዩንና የመልካም ስሙን ትከፍላለህ፤እኔ በፋርማሲው እጠቀማለሁ ብሎ ሆስፒታሉን ሰጠኝ፡፡ በጣም የሚገርም ነገር ነበር። አምስት ሳንቲም በወቅቱ አልሰጠሁትም፤እኔ ከላይቤሪያ ይዤ የመጣሁትን ገንዘብ ሆስፒታሉን ለማደራጀት ተጠቀምኩበት እንጂ ለእሱ ምንም አልከፈልኩትም፡፡ ሰርተህ ትከፍላለህ መጀመሪያ ሥራውን ሥራ ብሎ ነው በእምነት የሰጠኝ፡፡
በዚህ አጋጣሚ አቶ ክብሩን በጣም ላመሰግነው እፈልጋለሁ፡፡ ቀና አመለካከት ያለው፣ የሰዎችን እድገት የሚፈልግ፣ በጣም ቅን ሰው ስለሆነ ሊመሰገን ይገባዋል፡፡ ይህንን ለማድረግ የልብ ቅንነትን ይጠይቃል፡፡ ከዚያም የኦፕሬሽን ክፍሉን በደንብ አደራጀሁ፣ ሌሎች የሚጐድሉ ነገሮችን አስተካከልኩና ስራውን በደንብ መስራት ጀመርን። ሃኪም ስለሆንኩ ከሃኪሞች ጋር ተግባብቶና ተስማምቶ መስራቱን ቻልኩበት፡፡ ጥሩ ውጤታማ ስራ መስራት ጀመርን፡፡ ለአምስት አመታት በዚህ ሆስፒታል ውስጥ ስሰራ ቆይቻለሁ፡፡ በዚህ መሃከል ባለቤቴ ይህንን አሁን ያለንበት ሆስፒታል የተገነባበትን ቦታ በግዢ አግኝታ ግንባታ ማካሄድ ጀመረች፡፡ ባለቤቴ በጣም ጐበዝ ሴት ነች፡፡ ጥሩ ፕላን ታደርጋለች፤ባልታሰበ ሁኔታ ነው ይህንን ግራውንድ ፕላስ 6 የሆነ ህንፃ ለመስራት የቻልነው፡፡
ሆስፒታሉ መቼ ነው ግንባታው ተጠናቆ ወደ ስራ የገባችሁት?
ነሐሴ 17 ቀን 2007 ዓ.ም ሆስፒታሉ ተመርቆ በ2ኛው ቀን ነው ሥራችንን የጀመርነው፡፡ ሆስፒታሉ በተመረቀበት ወቅት የህክምና መሳሪያዎቹና የህሙማን መኝታ ክፍሎች ሙሉ በመሉ ተደራጅተውና ሁሉም ነገር ተሟልቶ ነበር፡፡ የባንክ ብድር በመውሰድ አስፈላጊ ነገሮቹን በሙሉ ካሟላን በኋላ ነው ወደ ሥራ የገባነው፡፡ መጀመሪያውኑ ለሆስፒታል ታስቦ የተገነባ በመሆኑም ለሥራ በጣም አመቺ ነው፡፡ ታካሚው እየተዝናና እንዲታከም ታልሞ የተሰራ ነው፡፡
ሆስፒታላችሁ  ምን አዲስ ነገር ይዞ መጥቷል? በህክምና መሳሪያዎችም ሆነ በህምና ረገድ?
የታካሚዎችንም ሆነ የአስታማሚዎችን ፍላጐት ያሟላሉ ብለን ያሰብናቸውን ነገሮች በተቻለ መጠን ልናሟላ ጥረት አድርገናል፡፡ የመኝታ ክፍሎቹም ሆኑ መታጠቢያ ቤቶቻቸው እጅግ ንፁህ፣ ሰፋፊ፣ ለህሙማኑ አመቺ የሆኑና የተሟሉ ዕቃዎች ያሉባቸው ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በክልሉ ውስጥ በሌሉና እጅግ አስፈላጊ በሆኑ መሣሪያዎች የተደራጀ ሆስፒታል ነው፡፡ ከእነዚህ መሣሪያዎች መካከል MRI፣ 3D4D አልትራ ሳውንድና ዲጂታል ኤክስሬይ ከፍሎሮስኮፒ ጋር ይገኙባቸዋል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ህሙማን በእነዚህ መሣሪያዎች የሚሰጠውን የምርመራ አገልግሎት ለማግኘት ወደ አዲስ አበባ በመሄድ የሚደርስባቸውን እንግልት፣ የጊዜና የገንዘብ ኪሳራ ሁሉ ያስቀርላቸዋል፡፡
ምን ያህል አልጋዎች አሏችሁ?
60 የአዋቂ፣ 5 የጨቅላ ህፃናትና 5 የህፃናት በድምሩ 70 አልጋዎች አሉን፡፡ 3 የቀዶ ህክምና ክፍሎች፣ ሰዎች ከኦፕሬሽን በኋላ የሚያገግሙበት የሪከቨሪ ክፍልና የፅኑ ህሙማን ማቆያ ክፍሎች አሉን፡፡ የፅኑ ህሙማን ማቆያ ክፍላችን አንዳንድ ዕቃዎች የሚጐድሉት በመሆኑና በሚገባ ተደራጅቶ ባለመጠናቀቁ አገልግሎት እየሰጠ አይደለም። ሌሎቹ ክፍሎች ግን በተሟላ እቃና መሣሪያ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡
በዋናነት ምን አይነት ህክምናዎች ናቸው በሆስፒታላችሁ የሚሰጡት?
የቀዶ ህክምና፣ የማህፀንና ፅንስ፣ የውስጥ ደዌ፣ የህፃናት ህክምና --- ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ ከዚህ ሌላ በትርፍ ጊዜያቸው እየመጡ በሚሰሩ ስፔሻሊስት ሃኪሞች የምንሰጣቸው ህክምናዎች አሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የልብ፣ የቆዳ፣ የአንገት በላይና የስነ አዕምሮ ህክምናዎች ይጠቀሳሉ፡፡
በባለሙያ ምን ያህል የተደራጀ ነው? ዶክተሮች፣ ነርሶች፣ የላብቴክኒሺያኖችን ጨምሮ በዘመናዊ መሳሪያዎች ላይ የመስራት ብቃት ባላቸው ሙያተኞች ምን ያህል ተደራጅተናል ይላሉ?
በስፔሻሊስት ሃኪምነት በቋሚነት ብዙ ሃኪሞችን ቀጥሮ ማሰራቱ ከባድ ነው፡፡ በቋሚነት 3 ስፔሻሊስቶች አሉ፡፡ የቀዶ ህክምና፣ የማህፀንና ፅንስ እንዲሁም የውስጥ ደዌ ሃኪሞቻችን በሙያው ስፔሻላይዝድ ያደረጉ ናቸው፡፡ ከዚህ ውጪ በትርፍ ጊዜያቸው የሚሰሩ የህፃናት ህክምና፣ የልብ፣ የስነ-ደዌ፣ የቆዳና አባላዘር፣ የአንገት በላይ ስፔሻሊስት ሃኪሞች አሉን፡፡ በተመላላሽነት የሚሰሩ 7 ጠቅላላ ሃኪሞች አሉ፡፡ አሁን ደግሞ የአጥንትና የነርቭ ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስቶችን ከደቡብ ኮርያ ለማስመጣት ዝግጅታችንን አጠናቀናል፡፡
እነዚህ ኮሪያውያን ስፔሻሊስቶች ወደ ሆስፒታላችሁ የሚመጡት በምን መልኩ ነው?  ለጊዜያዊ ሥራ ነው ወይስ በቋሚነት ሊሰሩ?
ሃኪሞቹ ወደዚህ የሚመጡት ከኮሪያ ኤምባሲ ጋር ባደረግነው ስምምነት መሰረት ነው፡፡ የመድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣንና ጤና ቢሮን አስፈቅደን በኤምባሲያቸው በኩል ከሃኪሞቹ ጋር ተነጋግረንና ተስማምተን ነው የምናስመጣቸው፡፡ አሁን ለጊዜው ለ3 ወራት በጊዜያዊነት እንቀጥራቸውና የሙያ ብቃታቸውን እናያለን፤ብቁ መሆናቸውን ካረጋገጥን በኋላ ለቀጣዮቹ 2 አመታት በቋሚነት እንዲሰሩልን ልንቀጥራቸው ተስማምተን ነው የሚመጡት፡፡ በዚህ ወር መጨረሻ ላይ ይደርሳሉ ብለን እየጠበቅን ነው፡፡ የእነዚህ ሁለት ባለሙያዎች መጨመር ሆስፒታላችን ያለውን የባለሙያ ቁጥር ከፍ በማድረግ፣ ታካሚው ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲያገኝ ያደርገዋል የሚል እምነት አለን፡፡
በነርስ ደረጃስ ምን ያህል ነርሶች አሏችሁ?
በአሁኑ ወቅት 16 የነርሲንግ ስታፎች አሉን። የሥራው ሁኔታ እየጨመረ ሲሄድ እየፈተንን እንቀጥራለን፡፡ ዛሬ ጥሩ ነርስ ከገበያ ውስጥ ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ጉዳይ ሆኗል፡፡ አንድ የላብራቶሪ ቴክኖሎጂስትና አምስት የላብ ቴክኒሺያኖች አሉን። ራዲዮሎጂስትም አለን፡፡ በአዳዲስና ዘመናዊ መሣሪያዎቹ ላይ መስራት የሚችሉ ባለሙያዎችን ለማሰልጠን 3 ባለሙያዎችን ወደ ቻይና ልከን እንዲሰለጥኑ አድርገናል፡፡ ይህ ደግሞ ባለን መሣሪያዎች በብቃት ለመጠቀም እንድንችል ትልቅ እገዛ አድርጎልናል፡፡ ሆስፒታላችን የሃያ አራት ሰዓት የአምቡላንስ አገልግሎትም ይሰጣል፡፡ ለሃያ አራት ሰዓት የመብራት አገልግሎቱን እንዳይቋረጥ የሚያደርግ ብቁ የሆነ ጀኔሬተርም አለን፡፡
ብዙ ጊዜ ሆስፒታሎች በውሃ እጥረት ይታማሉ፤እናንተስ ጋ የውሃ አቅርቦቱ ምን ያህል ነው?
የውሃ ችግር እንዳልሽው የብዙ ሆስፒታሎች ችግር ነው፡፡ የጥልቅ ውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ለማከናወን አቅደን የነበረ ቢሆንም ወጪው በጣም ከፍተኛ በመሆኑ ለጊዜው አልቻልንም፡፡ ከጐናችን የሚገኘው የደቡብ ኢትዮጵያ ት/ቤት ቀደም ሲል ያስቆፈሩት የጥልቅ ውሃ ጉድጓድ ስለአለ የተወሰኑ ወጪዎችን እየሸፈንን ውሃ እንዲሰጡን ጠይቀናቸው፣ የምንሰጠውን የማህበራዊ አገልግሎት ታሳቢ አድርገው፣ ውሃውን እንድንጠቀምበት ፈቅደውልናል፡፡ አሁን እኛ ጋ ውሃ 24 ሰአት የተሟላ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ እነዚህን ሰዎችም ለማመስገን እፈልጋለሁ፡፡
የአገልግሎት ክፍያችሁስ ምን ይመስላል? የብዙኃኑን ተገልጋይ የመክፈል አቅም ያገናዘበ ነው ብላችሁ ታምናላችሁ?
የአገልግሎት ክፍያችን ሁሉንም ህብረተሰብ ያገናዘበ ነው የሚል እምነት አለን፡፡ ለምሳሌ ለካርድ 30 ብር ነው የምናስከፍለው፡፡ እንደየስፔሻሊቲው እስከ 50 ብር ሊደርስ ይችላል፡፡ ከዚህ ውጪ ሌሎች የላብራቶሪ ምርመራዎችም በተመጣጣኝ ዋጋ ነው የሚሰጡት፡፡ ለMRI ምርመራ እኛ የምናስከፍለው በአዲስ አበባ ለዚሁ ምርመራ ከሚጠየቀው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ የህክምና ወጪው የአብዛኛውን ህብረተሰብ የመክፈል አቅም የሚፈታተን እንዳይሆን ከፍተኛ ጥረት አድርገናል፡፡
በመንግስት በኩል የሚደረግላችሁ ድጋፍ አለ? እንዴት ይገለፃል?
የከተማው ማዘጋጃ ቤት ያለንን የሥራ እንቅስቃሴ በማየት ከጐናችን ያለውን ወደ 420 ካሬ የሚጠጋ ቦታ ሰጥቶናል፡፡ ከዚህ ውጪ እቃዎችን ከቀረጥ ነፃ ለማስገባት እንድንችል በማድረግም በእጅጉ አግዞናል፡፡ ጉምሩክ አካባቢ ያለው ችግር እንዳለ ሆኖ ማለቴ ነው፡፡
ጉምሩክ አካባቢ ምን አይነት ችግር ገጠማችሁ?
እዚያ በጣም ትልቅ ችግር ነው ያለው፡፡ ለምሳሌ እኛ የገጠመንን ልንገርሽ፡፡ አንድ ካርዲያክ ዲፍዩሬተር የተባለና በልብ ችግር የሚሞቱ ሰዎች ልባቸው ሲቆም እንዲነሳ ለማድረግ የምንጠቀምበት መሳሪያ ከቻይና አገር ገዝተን ከሌሎች መሳሪያዎች ጋር አስመጥተን ነበር፤ መሳሪያው ሲፈተሽ በማሽኑ ውስጥ የነበረውንና የራሱ አካል የሆነውን አንድ ዕቃ አውጥተው፤ ይሄ ትርፍ ነው በማለት ልጅቷ ታሰረች። እኔ ተጠርቼ ሄድኩና እቃውን አየሁት። ይሄ የማሽኑ የራሱ እቃ ነው፤ ነገር ግን የየትኛው ማሽን እንደሆነ ማወቅ የምችለው ሲገጣጠምና ሳየው ነው። ምናልባት በፍተሻ ወቅት አውጥታችሁት ሊሆን ስለሚችል አስቀምጡትና ስንገጣጥም ትሰጡናላችሁ አልኩ፡፡ በኋላም ማሽኑን ስንገጥመው እውነትም ደረት ላይ የሚቀመጠው ፓድ የለም። ሄደን ጠየቅናቸው፤ ምንም ነገር የለም ተባልን፤ በደብዳቤም በአካልም ተመላልሰን ጠየቅን፤ምንም አላገኘንም፤ በቃ ጠፍቶ ቀረ፡፡ በዚህ ምክንያትም ያ ሁሉ ገንዘብ ወጥቶበት የተገዛው ማሽን ያለ ስራ ቆሞ እንዲቀር ሆኗል፡፡ ይህ በጣም የሚያሳዝን ነገር ነው፡፡ መንግሥት በቀረጥ ሥርዓቱ ላይ ያለውን ነገር ቢመረምርና ቢያየው ጥሩ ይመስለኛል፡፡ መንግሥት ለዘርፉ ማድረግ ይጠበቅበታል ብለው የሚያስቡት ነገር ምንድነው?
መንግሥት በተለይ የማህበራዊ አገልግሎቶችን በሚሰጡ የሥራ ዘርፎች ላይ ትኩረት ቢያደርግ፣ በዚህ ዘርፍ ኢንቨስት የሚያደርጉ አካላትን የሚያበረታታበት መንገድ ቢኖረው ጥሩ ነው። የታክስ ሲስተሙን ግልፅና በአግባቡ ሊተረጎም የሚችል ቢያደርገው ጥሩ ነው። ሌላው እንደ ባለሙያ ቅሬታ ያለኝ የመንግስት የፖስት ግራጅዌሽን ስልጠናዎች በግል የህክምና ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ባለሙያዎችን አለማካተቱ ነው፡፡ በግል የጤና ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ባለሙያዎች ቢያንስ ከፍለው የሚማሩበት ሁኔታ እንኳን ሊመቻች ይገባዋል፡፡ ይሄ  ባለሙያው ሙያውን ለማሻሻል እንዲችል የሚያደርግና የሚያነሳሳ ነው፡፡
በመንግስት ተቋማት ውስጥ እንዳሉት ባለሙያዎች ሁሉ በግል የህክምና ተቋማት ውሰጥ የሚሰሩት ባለሙያዎች የትምህርት ዕድል ለማግኘት እንዲችሉ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ሌላው አዲሱ የጤና ተቋማት እስታንዳርድ ብዙ የተመከረበት አይመስለኝም። አንዳንድ ነገሮች በደንብ ቢታሰቡበትና ቢታዩ ጥሩ ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ መልቀቂያ የሌለውን ባለሙያ ቀጥሮ ሲሰራ የተገኘ ተቋም ይዘጋል ይላል መመሪያው፡፡ ግን መልቀቂያ ለማግኘት አንድ ዶክተር በትንሹ 14 ዓመት መሥራት መቻል አለበት፡፡ ይህ ደግሞ በጣም ከባድ ነው፡፡ ስለዚህም መልቀቂያ ያለው ሰው በገበያው ውስጥ ማግኘት በጣም ከባድ ነው፡፡
አሁን እኛ የህፃናት ሰፔሻሊስት መቅጠር ያልቻልነው መልቀቂያ ያለው ሰው በገበያ ውስጥ ባለማግኘታችን ነው፡፡ ኒውሮሎጀስት ከውጪ ለማምጣት የተገደድነው እኛ አገር ገበያ ውስጥ ባለማግኘታችን ነው፡፡ የአጥንት ስፔሻሊስቶቻችን እንዲሁ በቁጥር ናቸው፡፡ አገሪቱ ውስጥ ያሉት 20 የሚሞሉ አይመስለኝም፡፡ ለዚህ ነው ከውጭ ለማስመጣት የተገደድነው ስለዚህም መንግስት የሚያወጣቸው ደንብና መመሪያዎች ሁሉ የግሉ የጤና ተቋማትን ታሣቢ ያደረገ መሆን ይኖርበታል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ለከንፈርና ላንቃ ስንጥቅ ህሙማን የነፃ ህክምና አገልግሎት መስጠት የጀመራችሁት መቼ ነው ?
ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ ነው መሥራት የጀመርነው። የከንፈርና ላንቃ ስንጥቅ ህክምና በሌላ ኘሮጀክት የሚደገፍ ቢሆንም ለህሙማኑ ህክምናውን የምንሰጠው በነፃ ነው፡፡ በዘመቻ መልክ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር እየሄድንም ብዙ ሰርተናል፡፡ ሰዎች ከንፈራቸው ተሰርቶላቸው መልካቸው ተለውጦ በጣም ደስተኛ ሆነው ሲሄዱ ማየቱ ትልቅ የአዕምሮ ርካታን ይሰጣል ስለዚህም በዚህ ዘርፍ ብዙ ሥራ ሰርተናል፡፡ ኒውዩርክ ካለ ድርጅት ጋር በመተባበር ማለቴ ነው፡፡
አሁን እንደውም በዚሁ በአዲሱ ሆስፒታላችን ልንጋብዛቸውና መጥተው እንዲሰሩና ስልጠናም እንዲሰጡልን ለማድረግ ሃሣብ አለን፡፡
ባለቤትዎ የህክምና ባለሙያ መሆናቸውን ሰምቻለሁ፡፡ ደጋግመው ሲያነሷቸውም ነበር፡፡ እንዴት ነው የምትደጋገፉት በእርስዎ ሙያ ውስጥ የባለቤትዎ ሥፍራ ምንድን ነው ?
ባለቤቴ ፈትለወርቅ ታደሰ ትባላለች ፡፡ የዓይን ህክምና ባለሙያ/ካታራክት ሰርጂን/ ነች፡፡
ይህ ሁሉ ነገር የሆነው በእሷ ነው፡፡አንዳንድ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ የሚገለጽልሽ ሲደርስ ነው፡፡ መልካም ሴት ለባሏ ዘውድ ናት ይባላል፡፡ ሰው ግን ለዘውዱ ክሬዲት አይሰጥም፡፡ ክሬዲት የሚሰጠው ዘውዱን አጥልቆ ለተቀመጠው ሰው  ነው፡1 ልክ እንደዛ ማለት ነው፡፡ ሆስፒታሉን በተመለከተ ሰዎች አድናቆታቸውን የሚሰጡት ፊት ለፊት ለምገኘው ለእኔ ነው ፡፡ ግን ዋናውን ሸክም ተሸክማ የኖረችው ሆስፒታሉን ከጽንሰቱ እስከውልደቱ ድረስ ያደረሰች እሷ ነች፡: እኔ እንደው አንዳንድ ነገሮች ላይ ከመሳተፍ ውጪ በሙያዬ ቁጭ ብዬ ስሰራ ነው የቆየሁት። ብዙም አስተዋጽኦ የለኝም፡፡ ስለዚህም ሁሉም አድናቆትና ምስጋና መሄድ ያለበት ወደሷ ነው፡፡
የወደፊት ዕቅድዎ ምንድን ነው?
የቅርብ ጌዜ ዕቅዴ አሁን መንግስት በሰጠን ቦታ ላይ ተጨማሪ ክፍሎችን በመሥራት የህሙማን አልጋ ክፍሎቹን መጨመርና ሆስፒታሉን ማስፋፋት ነው፡፡ የወደፊት ራዕያችን ግን ሆስፒታሉን  ጥሩ የህክምና ሙያ ማሰልጠኛ ማዕከል አድርገን የተሻሉና ብቁ ባለሙያዎች ሰልጥነው የሚወጡበት ስፍራ ማድረግ ነው፡፡

Read 6369 times