Tuesday, 29 December 2015 07:13

አዞው ወደ ውሃ ሲስብ ጉማሬው ወደ ሳሩ ይስባል

Written by 
Rate this item
(14 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት በቅሎ ስለማንነቷ ጌታዋን ጠየቀች፡፡
“ስላንቺ ማንነት ለማወቅ አንድ ቀላል ጥያቄ ብቻ እጠይቅሻለሁ”
“ምን? ይጠይቁኝ”
“እሺ፡፡ ከእኔ ጋር እስከነበርሽ ድረስ ምን አገልግሎት ስትሰጪኝ ነበር?”
“ያው ሁልጊዜ የማደርገውን ነዋ!” ስትል መለሰች
ጌትዬውም፤
“እኮ ምን?”
“ከአገር አገር እየሰገርኩ እርስዎን ያሻዎ ቦታ ማድረስ”
“መልካም፡፡ እንደዛ ከሆነ መስገር የማን ሥራ ነው ብለሽ ታስቢያለሽ?”
“የፈረስ”
“እንግዲያው አባትሽ ፈረስ ነው”
“ስለዚህ ፈረስ ነኝ ማለት ነዋ!” አለች እየፈነጠዘች፤ “በቃ ለእንስሳት ሁሉ እነግራቸዋለሁ” ብላ ሄደች፡፡
አንድ ቀን ግን ጌታዋ በጠዋት ወደሚቀጥለው ከተማ በርካታ ስልቻ እህል ይዞ መሄድ ነበረበትና ብዙ አህዮች ጭኖ ሲያበቃ፤ የተረፉትን ስልቾች በቅሎዋ ላይ ቀርቅቦ ጫነ፡፡
ይሄኔ በቅሎዋ፤
“ምነው ጌታዬ፤ እንደ ፈረስ እየሠገርሽ የምትሄጂ፤ የፈረስ ልጅ ነሽ ሲሉኝ ቆይተው አሁን እንደ አህያ እንዴት ይጭኑኛል” ስትል ጠየቀች፡፡
ጌትዬውም፤
“በአባትሽ ፈረስ ብትሆኚም፤ በእናትሽኮ አህያ ነሽ፤” አላት፡፡
ቁርጧን ያወቀችው በቅሎ፣ ሸክሟን ይዛ መንገዷን ቀጠለች፡፡
*   *   *
ሀገራችን ሥር ነቀል ለውጥ (Transformation) ያስፈልጋታል ካልን “ማ ቢወልድ ማ?” የሚል አካሄድ ሳይሆን ጠንካራ የሥራ ባህልና የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ እንዲሁም ጽኑ ሥነልቦናዊ እመርታ ያስፈልጋታል፡፡ ይህም በፈንታው ዕውቀት ላይ የተመሠረተ አስተሳሰብና ሙያዊ ብቃትን ይጠይቃል፡፡ ማንነታችን ለውጥን ማገዣ መሰላል እንጂ በራሱ ግብ ስላይደለ እየደጋገምን በአባቴ ፈረስ በእናቴ አህያ የምንልበት ዘመን አይደለም፡፡ ዕድገትን ለማምጣት የሥራ ባህላችንና የአምራችነት ብርታታችን ነው ወሳኙ፡፡ ሁሉም ሰው የፖለቲካ ኮርቻ ላይ ለመፈናጠጥ የሚሽቀዳደም ከሆነ የሚሠሩ እጆች ይዝላሉ፡፡ ጠንካራ መንፈሶች ይዳከማሉ፡፡ ሀገር ተስፋ ታጣለች፡፡
ዛሬ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ግልጽነትና ተጠያቂነት አስፈላጊነቱ ጉልህ ነው፡፡ በቃል ሳይሆን በተግባር መፈተሽ አለበት፡፡ ከቀን ቀን የተጠራቀመው ብሶቶች ወይ መተንፈሻ ወይ መፈንጃ ቅጽበትና ቦታ መሻታቸው አይቀሬ ነው፡፡ ሰበቦቹ ምንም ይሁኑ ምን እንዳመረቀዘ ቁስል መፈንዳታቸው አሊያም ካንሰር አከል በሸታ መሆናቸው ሁሌም የሚታይ ገሀድ ክስተት ነው፡፡ ያ ደሞ ለጊዜው ሳይሆን ለዘለቄታው አስጊ ነው፡፡
በዚህ ላይ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንደሚወራው አለመሆናቸው ፍተሻን ይፈልጋል፡፡ ዲሞክራሲ “የሚታይ እንጂ የማይበላ ፍሬ” እንደሚባለው አይደለም፡፡ ፓርቲ እንደፈለገው የሚቃኘው (guided democracy) የፖለቲካው መነጋገሪያ መድረክም ሆነ የመጫወቻ ሜዳው እንዲሁም የአጨዋወት ሕጉ ተሳታፊ ቡድኖችን ተስፋ የሚያስቆርጥ መሆን የለበትም፡፡ ለጊዜው ያሸነፍን የሚመስለን ግጥሚያ ሁሉ በረዥሙ ሲታይ ዲሞክራሲን የሚያቀጭጭ ሆኖ ይገኛል፡፡ ያ በፈንታው “አንድ ወደፊት ሁለት ወደ ኋላ” መሄድን ያመጣል፡፡ ዞሮ ዞሮ ጣጣው ላገር የሚተርፍ ጐጂ ባህል ነው፡፡ ኢ-ፍትሐዊ የሆነ የሀብት ክፍፍል አሟጋች ኢኮኖሚያዊ ዝንፈትን፣ ውሎ አድሮም ምሬትን መውለዱ በዐይን የሚታይ ሀቅ ነው፡፡ የፈጠጠ ሙስና ውስጥ የተዘፈቀ ሥርዓተ - ኢኮኖሚ፣ ሹሞች ከማስወገድ ያለፈ ማስተካከያ ይፈልጋል፡፡ ህዝብ የሚያየውን እንከን ያለሥጋት በግልጽ እንዲናገር የማሪያም መንገድ ሊሰጠው ይገባል፡፡
ችግሮች ሲተሳሰሩ አንዱ አንዱን ይዞ ይወድቃል፡፡ እኛንም ይዞ ይወድቃል፡፡ (Domino Effect እንዲሉ) ሁሉም ወደየወገኑ እየዞረ አገር ሊጠብ አይገባውም፡፡ እንዲያ ከሆነ የሙስናው መረብ በተቃራኒው ይሰፋልና፡፡ የአሁኑ ዘመን የሙሰኞች መረብ “አዞው ወደ ውሃ ሲስብ ጉማሬው ወደሳር ይስባል” የሚለው ተረት ዓይነት ሆኗልና፤ ሁሉ ወደየራሱ ገመዱን እየጐተተ መሆኑን የሚመለከተው የመንግሥት አካል ዐይኑን ከፍቶ ይመልከት!  

Read 6166 times