Saturday, 19 December 2015 10:21

መንገድ የምታውቅ አይጥ ፈረስ ትቀድማለች

Written by 
Rate this item
(51 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን አያ አንበሶ ታሞ እቤት ዋለ፡፡ ምግብ የሚያመጣለት በማጣቱ ወዳጁን ቀበሮን ይጠራና “ወዳጄ ቀበሮ፤ እባክህ ወደ ጫካው ሂድና ወጣቱን አጋዘን ጥራልኝ። የአጋዘን ልብና አንጐል አምሮኛል” ይለዋል፡፡ ቀበሮም የአያ አንበሶን ቃል ለመፈፀም ወደ ጫካው ይሄድና አጋዘንን ያገኘዋል፡፡ ከዚያም፤
“የመጣሁት አንድ የምሥራች ይዤልህ ነው፡፡ አያ አንበሶን የዱር አራዊትን ንጉሥ ታውቀዋለህ፡፡ ታሞ ሊሞት ተቃርቧል፡፡ አንተን መንግሥቱን እንድትወርስ ሊሾምህ ይፈልጋል፡፡ መቼም የነገሥክ ጊዜ በመንግሥትህ አትረሳኝም፡፡ አሁን ወደሱ መመለሴ ነው። ብልህ ከሆንክ አብረኸኝ ና” አለው፡፡
አጋዘን በዜናው በጣም ማለለ፡፡ ምንም ሳይጠራጠር ወደ አያ አንበሶ መኖሪያ ሄደ፡፡ አጋዘኑ ገና እንደገባ፤ አያ አንበሶ አጋዘኑን ለመያዝ ተወረወረ፡፡ ሆኖም በጣም ከመወርወሩ የተነሳ ጆሮውን ብቻ ጨርፎት መሬት ላይ ወደቀ፡፡ አጋዘን አምልጦ ሄደ፡፡ ቀበሮው በድን ሆኖ ቆመ፡፡ አንበሳ በጣም ተናደደ፡፡ በዚያ ህመሙ ላይ ረሀብ ሊገለው ደርሷል፡፡ ስለዚህም ቀበሮን እንደገና ለመነው፡፡
ቀበሮም፤ “አሁን እንኳ እሺ እሚለኝ አይመስለኝም፡፡ ሆኖም ልሞክር” ብሎ ወደ ጫካው ሄደ፡፡ አጋዘኑ ከቁስሉ ለማገገም ሲሞክር ያገኘዋል፡፡
አጋዘን፤ “አንት የማትረባ ልታስገድለኝ ነበር! በቀንዴ ወግቼ ሳልገድልህ ድራሽህ ይጥፋ!” አለው፡፡
ቀበሮው ግን በሀፍረተ - ቢስ ግትርነት፤
“ምን ዓይነት ፈሪ ነህ? አንበሳ እኮ ሊጐዳህ አላሰበም፡፡
አንዳች ንጉሣዊ ሚስጥር በጆሮህ ሹክ ሊልህ መሞከሩ ነበር፡፡ አንተ ግን እንደደነገጠች ጥንቸል ሮጠህ ሄድክ፡፡
አያ አንበሶን በጣም አስከፍተኸዋል፡፡ መቼም አንተን ትቶ ተኩላን የሚሾመው አይመስለኝም፡፡ ዕውነት ሀሞት ካለህ መጥተህ መንግሥትህን ተረከብ፡፡ ምንም የጉዳት ነገር አታስብ፡፡ ብቻ በመንግሥትህ የእኔን ውለታ እንዳትረሳ” አለው፡፡
አጋዘኑ ለሁለተኛ ጊዜ ጓጓ፡፡ ወደ አያ አንበሶ በረት መጣ፡፡ አሁን ግን አያ አንበሶ አልተሳሳተም፡፡ በቀጥታ አጋዘን ላይ ሰፈረበት፡፡ አንበሳ ከአጥንቱ ጋር ሲታገል፤ ቀበሮ ቀልጠፍ ብሎ የአጋዘኑን ልብ መነተፈና ዋጠው፡፡
አንበሳ አጥንቱን ቆረጣጥሞ ልቡን ቢፈልግ የለም፡፡
“አንተ ቀበሮ ልቡ የታለ?” ሲል ጠየቀው፡፡
ቀበሮም፤
“አያ አንበሶ፤ ወደ አንበሳ መኖሪያ ሁለት ጊዜ የመጣ ሞኝ አጋዘን ምን ልብ ይኖረዋል ብለው ነው?” ሲል መለሰ፡፡
*   *   *
አንድን ስህተት ሁለቴ ከመሳሳት ይሰውረን! “ትላንትና ማታ ወደ ቤትህ ስትገባ እንቅፋት ሆኖ የመታህ ድንጋይ ዛሬ ማታም ደግሞ ከመታህ፤ ድንጋዩ አንተ ነህ” ይላሉ ቻይናዎች። በየጊዜው እንቅፋት የሚሆኑብን ብዙ ሳንካዎች እንዳሉ እናውቃለን፡፡ ወሳኙ ጉዳይ ግን እንዴት ልናልፋቸው እንችላለን የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ አንዱ መንገድ አስቦ፣ አቅዶ፣ ተዘጋጅቶ፣ በሰከነ መላ ተወያይቶ መፍታትና መገላገል ነው፡፡ ይህም ግልፅነትና ጉዳዩን ቁልጭ አድርጐ በሁለት ዓይን ማየትን፤ የግድ ይጠይቃል፡፡ ይሄ በፈንታው ተጠያቂነትን ይወልዳል፡፡ “የእምዬን እከክ ወደ አብዬ ልክክ” ከማድረግ ያድነናል፡፡ ሁለተኛና ከባዱ መንገድ ደግሞ ችግርን በኃይል ለመፍታት መሞከር ነው፡፡ ይሄኛውም ቢሆን ግን በአቦ ሰጡኝና በዘፈቀደ ይሁን ከተባለ ሥርዓት አልባ ሁኔታን ሊያስከትልና ስሜታዊነትን ሊያሰፍን ይችላል፡፡ አያሌ ፀፃች ሁኔታዎች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ አንድ ፈላስፋ፤ “ከፀፀቶች ሁሉ የከፋ ፀፀት የሚፈጠረው፣ አብዛኛውን ጊዜ፤ ከስሜታዊነት ነው” ይለናል፡፡ ነገሮችን ረጋ ብሎና ሰክኖ ማየት መለኝነት ነው፡፡ የሚያልፉ የማይመስሉና በቀላሉ ሥጋት ላይ ሊጥሉን የሚችሉ ክስተቶችን አደብ ገዝተን፣ አስልተን ማስተዋል ትርፉ ብዙ ነው፡፡ ዋጋ ከመክፈልም ያድነናል፡፡
ሀገራችን፤
“የዘንድሮ ጉዴ ለኔም ገረመኝ
አንዱን ስለው አንዱ፣ አንዱ ባሰብኝ…”
የሚለው ዘፈን የሚመለከታት ይመስላል፡፡ የዲሞክራሲ፣ የፍትሕ፣ የመልካም አስተዳደር፣ የሰብዓዊ መብት፣ የጤና፣ የድርቅ ወዘተ. ያልተፈቱ አያሌ ችግሮች እያሉን፣ ባለቤት የሌላቸው ሌሎች ችግሮች እንደ አዲስ ይመነጫሉ፡፡ የበለጠ ችግር የሚሆነው ደግሞ ወዴት እንደሚያመሩ አለመታወቁ ነው፡፡ “አይጢቱ ድፍን ቅል ውስጥ ገብታ ወለደች” አለው፡፡ “በምን ገብታ” ቢለው “ጉዱ ምን ላይ ነው?!” አለው አሉ፡፡ ጉዱ ምን ላይ ነው የሚያሰኙ አያሌ ጉዳዮች አሉን፡፡ የመሬት ሽንሸናና ሽያጭ ሙስና አንዱና ዋንኛው ነው፡፡ ሰፊው ህዝብ “እማሆይ የተበላ ማሽላ ይጠብቃሉ” ዓይነት እስኪሆን ድረስ፤ የበይ ተመልካች ሆኗል፡፡
የበላ የበላው ደግሞ ሽፋን እየፈለገ “ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮህ” ሆኗል፡፡ ኪሱን ካደለበ፣ ፎቁን ከገነባ፣ በርካታ ደብተሮች ከያዘ በኋላ “አገር አደጋ ላይ ወድቃለች!” እያለ መልሶ ሰው ያደነቁራል፡፡ የዋሃን የዚህን ሽፋን መጫወቻ ይሆናሉ፡፡ አገሩ ባለቤት - አጥና ተጠያቂ አካል የሌለው መስሏል፡፡ በሁሉም ረገድ “ግርግር ለሌባ ያመቻል” ሆኗል ነገሩ። ዘዴና መንገድ ማስላት ግዴታችን ነው፡፡ ነገሮችን ሁሉ ያንድ ወገን ጉዳይ አድርጐ አለመመልከት አንዱ መንገድ ነው፡፡ አቋራጩንና የብልሁን መንገድ ማየት ጥልቅ ዓይን ይፈልጋል እንጂ ጨርሶ አዳጋች ነው ማለት አይደለም፡፡ ያልተደራጀ ኃይል፣ ኃይል አይደለም፡፡ ዋናው አስተውሎትና ትኩረት ግን “መንገድ የምታውቅ አይጥ፣ ፈረስ ትቀድማለች” የሚለው የወላይታ ተረት ቢሆን መልካም ነው!





Read 12533 times