Saturday, 11 February 2012 10:56

በስኳር ምርት ብዙ ቢታቀድም ተጓትቷል

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

የመተሃራ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞች አስተዳደሩን ያማርራሉ

በረዣዥም ጐማዎቹ 360 ዲግሪ እየተንፏቀቀ ከሰማይ ውሃ ሲለቅ፣ በአየር ላይ ተንሳፍፎ፣ በግራና ቀኝ ጐኑ ውሃ የሚረጭ በጣም ረዥም ዘንዶ ይመስላል፡፡ ግማሽ ክብ ሲዞር፣ 500 ሜትር ያጠጣል፡፡ እየተንፏቀቀ አንድ ዙር ተሽከርክሮ መጀመሪያ ከተነሳበት ስፍራ ተመልሶ ሲደርስ ደግሞ አንድ ኪ.ሜ ሸንኮራ አገዳ ውሃ ያጠጣል - በአየር ላይ፡፡ አንድ ዙር ሲንቀሳቀስ 75 ሄክታር መሬት ውሃ ያጠጣል - በሰሜን ዶዶታ (ወንጂ) የእርሻ ማስፋፊያ ያለው ዘመናዊ የመስኖ መሳሪያ፡፡ ኦቨርሄድ ኢሪጌሽን ሲስተም ፈረንሳይ ሰራሽ ሲሆን፣ ዘርፈ - ብዙ ጥቅም እንዳለው ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ እንደ ዝናብ ውሃ ለሁሉም አገዳ በእኩል መጠን ውሃ ስለሚያዳርስ የአገዳው ዕድገት መጠን እኩልና መተጣጣኝ ይሆናል፡፡ “ሌላም ትልቅ ጥቅም አለው፡፡ ፀረ - አረም፣ ፀረ - ተባይ ኬሚካልና ማዳበሪያ ለመርጨት ያገለግላል፡፡ ይህ መሳሪያ፣ ለአገራችን አዲስ ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ዘጠኝ መሳሪያዎች ስላሉን በአንድ ጊዜ 675 ሄክታር መሬት ውሃ ማጠጣት እንችላለን” በማለት በስፍራው ጉብኝት ላደረገ የጋዜጠኞች ቡድን ያስረዱት የወንጂ ስኳር ፋብሪካ የማስፋፊያ ፕሮጀክት ሲቪል ኢንጂነር መምሪያ ኃላፊ አቶ ታምሩ ምትኩ ናቸው፡፡

ዛሬ ሕፃን አዋቂው፣ ከዕለት ምግቡ እንዳያጣ አቅራቢውን ወገን ሰቅዞ ይዞ የሚጮህለት መንግሥትም ፍላጐትና አቅርቦትን ማጣጣም ተስኖት ግራ የተጋባበት፣ በዋጋ ንረት፣ ሸማችና ነጋዴው የተዛዘቡበት ስኳር፣ ሆላንዶች የዛሬ 65 ዓመት ወንጂ ስኳር ፋብሪካን ሲመሰርቱ ሕዝቡ ጥቅሙን ስለማያውቅ፣ ለማስለመድ ተቸግረው እንደነበር ይነገራል፡፡ በዚህም የነሳ በነፃ ሰጥተዋል፣ ልጆች ዕቃ ለመግዛት ሱቅ ሲሄዱ፣ በምርቃት መልክ ስኳር ወይም ከረሜላ ይታደላቸው ነበር፤ ዛሬ “ጨው” ሆኖ በራሽንና በወረፋ የምንገዛው ስኳር፡፡

ለእጥረቱ መባባስ ብዙ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከ60ዓመት በላይ ያገለገሉት ሁለቱ አሮጌ ፋብሪካዎች (ወንጂና ሸዋ) አንድ ላይ ሆነው በቀን በአማካይ የሚያመርቱት 3ሺ 500 ኩንታል ስኳር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ከዚያን ጊዜው በእጥፍ ጨምሯል፤ ፍላጐትም በብዛት አድጓል፡፡ ዘርፉን መንግሥት በብቸኝነት መያዙ፣ ሙስና (ኪራይ ሰብሳቢነት) በርካታ ምክንያቶች መደርደር ይቻላል፡፡

በአሁኑ ወቅት ሦስቱ የስኳር ፋብሪካዎች:- መተሃራ፣ ፊንጫና ወንጂ - ሸዋ በዓመት 3 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ነው የሚያመርቱት፡፡ ፍላጐት ግን ከአቅርቦት በእጥፍ ይበልጣል፡፡ ይህን እጥረት ለማካካስ፣ መንግስት በአጭር ጊዜ 1.5 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ከውጭ እያስገባ ነው፡፡ በረዥም ጊዜ ደግሞ አሮጌዎቹን ፋብሪካዎች ማስፋፋትና ሌሎች አዳዲስ ፋብሪካዎች የማቋቋም እቅድ ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ነው፤ ምንም እንኳ ከፍተኛ ተጨማሪ ወጭ ቢያስከትሉና ለዓመታት ቢጓተቱም፡፡ ዕቅዱ የአገር ውስጥ ፍላጐት ማሟላት ብቻ አይደለም - በአምስት ዓመቱ መጨረሻ ከሚሊዮን ኩንታል በላይ ስኳር ለውጭ መሸጥ ነው፡፡

የወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ በዚህ ዓመት 768ሺ ኩንታል ስኳር ለማምረት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ አቶ መካሻ ቀጥ ይበሉ ተናግረዋል፡፡ የእርሻ ማስፋፊያው በሁለት ምዕራፍ የተከፈለ ነው፡፡ በመጀመሪያው ምዕራፍ በ3ሺ ሄክታር መሬት ላይ በዘመናዊ የመስኖ ሲስተም አገዳ ይለማል፡፡ እስካሁን 2ሺ ሄክታር ያህል አገዳ የተተከለ ሲሆን ቀሪው በዚህ ወር መጨረሻ እንደሚጠናቀቅ ገልፀዋል፡፡

የሁለኛው ምዕራፍ የአገዳ ተከላ በየካቲት ወር ይጀመራል፡፡ ከ2-3 ዓመት በሚቆየው ፕሮጄክት፣ 7ሺ ሄክታር መሬት የሚለማ ሲሆን፤ 4 እና 5 ሄክታር ጨምሮ 11 ሄክታር ለማድረስም ታቅዷል፡፡ በዚህ ዓመት በ3ሺ ሄክታር መሬት ላይ አገዳ የሚተከል ሲሆን፤ እስካሁን የፕሮጀክቱ 30 በመቶ መከናወኑን ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

ከ60 ዓመት በላይ ያገለገሉት አሮጌዎቹ የወንጂና ሸዋ ስኳር ፋብሪካዎች በመጪው ዓመት ይዘጋሉ፡፡ በምትካቸው ከሕንዱ ኢምፖርት - ኤክስፖርት ባንክ በተገኘው 123 ሚሊዮን ዶላርና ከመንግሥት በሚወጣ 700 ሚሊዮን ብር ገደማ አዲስ ፋብሪካ ይቋቋማል፡፡

የፋብሪካው ሥራ በአሁኑ ወቅት 60 በመቶ ያህል መጠናቀቁን አቶ መካሻ ገልፀዋል፡፡ የዚህ ፋብሪካ ተከላ በዚህ ዓመት ተጠናቅቆ የሙከራ ምርት በግንቦት ወይም ሰኔ ወር የሚጀምር ሲሆን በመጪው ዓመት ጥቅምት ወር ሥራ ይጀምራል ብለዋል - ሥራ አስኪያጁ፡፡ አዲሱ ፋብሪካ የሁለቱን አሮጌ ፋብሪካዎች አቅም አጥፍ አለው - አንድ ሚሊዮን ተኩል (150 ሺ ቶንስ) ኩንታል ስኳር የማምረት አቅም አለው፡፡

ወንጂ ሸፋ ፋብሪካ በአሁኑ ወቅት 3ሺ 200 ቋሚ ሠራተኞች ሲኖሩት እንደሥራው ሁኔታ ከ3-4ሺ ጊዜያዊና የወራት ሠራተኞች ይኖሩታል፡፡ አንደኛው ምዕራፍ የ650 ሚሊዮን ፕሮጄክት ሲሆን ሁለተኛው ምዕራፍ የወለንጪቲ ደግሞ የ1.4 ቢሊዮን ፕሮጀክት ነው፡፡

በግንባታ ላይ ባለው የወንጂ ሸዋ ማስፋፊያ ፋብሪካ ቀለም ሲቀባ ያገኘነው ያሬድ አሰፋ የ24 ዓመት ወጣት ነው፡፡ ከጓደኞቹ ጋር በማኅበር ተደራጅቶ እየሰራ ነው፡፡ የቀለም ቅቡን ኮንትራት የወሰደው አንድ ጓደኛቸው ሲሆን፤ እነሱን ቀጥሮ እያሠራ ነው፡፡ በቀን 150 ብር ይከፍላቸዋል፡፡ እነ ያሬድ፣ እሁድ - ቅዳሜ አይሉም፤ ወሩን ሙሉ ይሠራሉ፡፡ በሚያገኘው ክፍያም ደስተኛ ነው፡፡ ያሬድ ብቻ ሳይሆን ቀጣሪ ጓደኛቸውም ደስተኛ ሲሆን በቅርቡ ግምገማ አድርጐ ክፍያው አዋጪ በመሆኑ በስራው እንደቀጠለበት ይናገራል፡፡

ወለንጪቲ ላይ የሚሠራው ማስፋፊያ የአዋሽን ወንዝ ውሃ አገዳው ወደሚተከልበት ስፍራ በቦይ መጥለፍ ሲሆን፣ ሥራው በአብዛኛው መጠናቀቁን አቶ ታምሩ ገልፀዋል፡፡ ከወንዙ የሚጠለፈው ውሃ 15 ሜ ኪዩብ ውሃ ሲሆን 14.5 ኪ.ሜ ተጉዞ ነው ሸንኮራ አገዳ የሚያለማው፡፡ ከ2-3 ኪ.ሜ ተጉዞ ሁላጋ ላይ 350 ሄክታር መሬት፣ 6 ኪ.ሜ ላይ ደግሞ ጠደቻ በተባለው ስፍራ 500 ሄክታር፣ 10 ኪ.ሜ ላይ 700 ሄክታር ያለማል፡፡ በመጀመሪያው ምዕራፍ 7000 ሄክታር፣ በቀጣይ ዙር ደግሞ 6000 ሄክታር፣ በአጠቃላይ፣ ከ13ሺ ሄክታር በላይ መሬት እንደሚለማና አገዳ ተከላው ከወር በኋላ እንደሚጀመር ተናግረዋል፡፡

ለመስኖ ቦይ ግንባታው ወጪ የተደረገው 790 ሚሊዮን ብር ሲሆን፤ የእርሻ መሳሪያዎች ግዢ የመሬት ዝግጅትና የአገዳ ተከላ አጠቃላይ ወጪ 1.4 ቢሊዮን ብር መሆኑን ኃላፊው ገልፀዋል፡፡

የመተሃራ ስኳር ፋብሪካ፣ በቀን 17ሺ ኩንታል አገዳ የመፍጨት አቅም ይዞ በ1962 መቋቋሙን የጠቀሱት የፋብሪካው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ብዙነህ አሰፋ ሦስት የተለያዩ ማስፋፊያዎች ከተደረጉለት በኋላ፣ በአሁኑ ወቅት በቀን ከ50ሺ ኩንታል በላይ አገዳ እየፈጨ፣ ከ5ሺ ኩንታል በላይ ስኳር እንደሚያመርት ገልፀዋል፡፡

የመተሃራ ስኳር ፋብሪካ ማስፋፊያ ሁለት መልክ አለው፡፡ አንደኛው ያልተጀመረና በሐሳብ ደረጃ ያለ ነው፡፡ እሱም አሁን ያለውን ፋብሪካ፣ በቀን 65ሺ ኩንታል እንዲፈጭ የማሳደግ ዕቅድ አለ፡፡ አሁን በአምስት ዓመቱ ዕቅድ እየተሠራ ያለው ከሰም ላይ በቀን 65ሺ ኩንታል አገዳ የሚፈጭ ፋብሪካ ለማቋቋም ነው፡፡ ሥራው ግን እንደተቀሩት ፕሮጄክቶች ሁሉ ተጓቷል፡፡ የማስፋፋቱ ሥራ ሲጠናቀቅ፣ መተሐራ ስኳር ፋብሪካ አሁን በዓመት ከሚያመርተው 1.3 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ወደ 2.6 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ያድጋል፡፡

“ፋብሪካው፣ ከ8.500 በላይ ሠራተኞች ሲኖሩት 10ሺ 200 ሄክታር አገዳ የሚያለማበት መሬት አለው፡፡ አብዛኞቹ ሠራተኞች ጊዜያዊ ሲሆኑ በሠሩት ልክ ነው የሚከፈላቸው፡፡ በአገዳ ቆረጣ ወቅት በቀን ከ40-50 ብር ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ የቀን ሠራተኞች ደግሞ 23 ብር ነው የሚከፈላቸው - በቀን፡፡ ሠራተኞቹ፣ ቤት በነፃ ይሰጣቸዋል፤ መብራት፣ ውሃ፣ ሕክምናም በነፃ ነው፡፡”

የመተሃራ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞች በአስተዳደሩ ላይ ከፍተኛ ምሬት እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ አስተዳደሩ፣ በዝምድና፣ በጐሳ፣ በጥቅም… አሠራር የተሞላ ነው፡፡

የሠራተኛ ማኅበሩም ለሠራተኛው ጥቅም የሚሟገት ሳይሆን፣ ከአመራሩ ጋር ተሳስሮ ለራሱ ጥቅም የቆመ ነው፡፡ ቋሚ ሳንሆን ጡረታ እንወጣለን፤ በየጊዜው እንጮሃለን፤ ጩኸታችን ግን ሰሚ የለውም፤ አቤት የምንልበት አጥተን ግራ ገብቶናል፡፡ ከኢንፎርሜሽን ርቀናል፤ አናገኝም አናነብም፡፡ ብሶታችንን ለጋዜጠኛ እንዳንናገር፣ አንድም ጋዜጠኛ ወደ ግቢው ዝር እንዲል አይፈቀድለትም፤ ከድልድይ ነው የሚመለሰው፡፡ ዛሬ ይህን ያህል በርካታ ጋዜጠኛ በማየታችን በጣም ገርሞናል፡፡ ዛሬ እንኳ ብሶታችንን እንተንፍስ፡፡ ፋብሪካችን፣ የሰዎችን ሕይወት እያጣፈጠ የእኛን በጣም አምርሮብናል፡፡ ለምንሰራው ሥራ ተመጣጣኝ ክፍያ አናገኝም፡፡ የላባችን ዋጋ ይከፈለን፡፡

ጥቅማጥቅም ቀርቶ ቀደም ሲል የነበረውን ሕክምና እንኳ አቋርጠውብናል፡፡…ይላሉ፡፡

የአምስት ቤተሰብ አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ መለሰ በየነ 17 ዓመት በጊዜያዊነት ከሠሩ በኋላ ቋሚ ሆነሃል መባላቸውን ይናገራሉ፡፡ አሁን ስኳር ተሸካሚ ናቸው፡፡ በ1984 ሥራ የጀመሩት በቀን በ4 ብር ከ03 ሳንቲም ነበር፡፡ ከዚያም 8 ብር ሆነላቸው፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት 15 ብር ገቡ፡፡ በቀን 23 ብር ማግኘት ከጀመሩ ዓመት እንዳልሞላቸው ተናግረዋል፡፡

የስድስት ቤተሰብ አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ በቀለ ከበደ በፋብሪካው ሥራ የጀመሩት በ1976 ዓ.ም ነበር - በ2,14 ብር፡፡ ከዚያም እየተንፏቀቁ 8,45 ደርሰው ቆሙ፡፡ ከ1995 ዓ.ም አንስቶ 15 ብር ይከፈላቸው ጀመር፣ በቅርቡ ደግሞ 23 ብር እየተከፈላቸውን መሆኑን ተናግረዋል፡፡ “ኑሮ ጣሪያ በነካበት ጊዜ በዚች ገቢ ቤተሰባችንን ማስተዳደር አቅቶናል፡፡ ችግራችንን መንግስት ይወቅልን” በማለት ተማጽነዋል፡፡

የፋብሪካው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ብዙነህ ግን በሠራተኞቹ ቅሬታ አይስማሙም፡፡ የስኳር ፋብሪካን ሥራ በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል ይላሉ አቶ ብዙነህ፤ አንደኛው ጊዜያዊና ወቅታዊ ነው፤ ቋሚና ከዓመት እስከ ዓመት የሚሠራ ሥራ አለ፡፡ ወቅትን ጠብቀው የሚሠሩ ሥራዎች አሉ፤ ለዚያ ጊዜያዊ ሠራተኞች ይቀጠራሉ፤ ሥራው ሲያበቃ ያቆማሉ፡፡ ለምሳሌ የአገዳ ተከላና ቆረጣን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በድርጅቱ ውስጥ ለረዥም ዓመት ያገለገለ ሠራተኛ እንደ ችሎታውና የትምህርት ደረጃው በሚጠየቀው መስፈርት መሠረት ፣ በድርጅቱ ውስጥ ባለ ክፍት ቦታ እንዲቀጠር ቅድሚያ ይሰጠዋል፡፡

ነገር ግን የሚያጋጥሙ ችግሮች አሉ፡፡ ሁለትና ሦስት ዓመት ሠርቶ ወደ አገሩ ይሄዳል፡፡ ከአምስትና ስድስት ዓመት በኋላ ይመጣና ሁለትና ሦስት ዓመት ሠርቶ ይሄዳል፡፡ ከዚያም መጀመሪያ ሥራ የጀመረበትን ጊዜ ቆጥሮ 20 ወይም 30 ዓመት ሠራሁ ሊል ይችላል፡፡ ከዚህ ውጭ ረዥም ጊዜ የሠራ ሰው እያለ የውጭ ማስታወቂያ አይወጣም ይላሉ፡፡

ሠራተኛው፣ በቀን ማግኘት የሚገባው ዝቅተኛ ጆርናታ 23 ብር ነው፡፡ ሠራተኛው፣ ቤት በነፃ ይሰጠዋል፡፡ መብራት፣ ውሃ፣ ሕክምና፣ ለሁሉም ሠራተኛ በነፃ ነው፡፡ አንድ ሠራተኛ ለማሳከም ከ60-70ሺ ብር ሊከፈል ይችላል፡፡ ማንኛውም ሠራተኛ በአገር ውስጥ እስከሚቻለው ድረስ ይታከማል፡፡ ሕክምና ላይ እያለ የኮንትራት ጊዜው ቢያልቅ፣ ኮንትራቱ ታድሶለት ይታከማል፡፡

የመተሃራ ስኳር ፋብሪካ ዓመታዊ የሕክምና ወጪ 12 ሚሊዮን ብር ይደርሳል፡፡ የሕክናውን ሥነ ምግባር የሚያበላሹ ሠራተኞችም እንዳሉ መዘንጋት የለበትም፡፡ ሕክምናን ከሥራ መሸሸጊያ አድርገው የሚጠቀሙ ሠራተኞችም አሉ፡፡

የዘመድ ቤት ነው፣ ቅጥር በዘመድ ነው የሚባለው የሲስተሙ፣ የሰው ኃይል አደረጃጀት… የስኳር ፋብሪካ ችግሮች ናቸው፡፡ አሠራሩን አየፈተሹ ማሻሻል ነው፡፡ ብዙ ዓመት ሠርተን ልንባረር ነው የሚባለው አግባብ አይደለም፡፡ በፋብሪካው ቦታ የሌላቸው ሰዎች ምን ይሁኑ? ቋሚ ሠራተኞች የጡረታ መብት ይከበርላቸዋል፡፡ የሕክምና ችግር ያለባቸውም በሐኪም ሲወሰን የጡረታ መብታቸው ይከበራል፡፡ ምደባ በብሔር በዝምድና ነው… የሚባለው ከመመሪያና ከአግባብ ውጭ የተመደበ ሰው ካለ ቅሬታ ማቅረብ ይችላል፡፡ ጥቅማጥቅም መስጠት አልቀረም፡፡ እንደየሥራው ባህርይ ከ6-7ሺ ብር የሚያወጡ ቱታዎች ከውጭ እየገዛን እንሰጣለን፡፡ እንደ ጫማ ያሉ ጥቅማጥቅሞችም በዓመት ሁለት ጊዜ ይሰጣሉ፡፡ አንድ መታወቅ ያለበት ነገር አለ፡፡ ይኼውም የሴፍቲ ሥራ ብዙ ይቀረናል፤ በዚህ ላይ እየሠራን ነው፡፡ 40 ሳንቲም ተጨመረልኝ የሚለው ቅሬታ፣ የሁለትና የሦስት ዓመት ጭማሪ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ጭማሪ በሠራው መጠን ለሚከፈል የቁርጥ ሥራ ጭማሪ ነው፡፡ ቋሚ ሠራተኛ በደሞዙ ስኬል መሠረት የአንድ እርከን ጭማሪ ይደረግለታል በዓመት፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፣ እንደየክፍሉና እንደየግለሰቡ ታታሪነት እስከ ሁለት ወር ቦነስ ሊያገኝ ይችላል በማለት ለሠራተኞቹ ቅሬታ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

 

 

 

Read 2469 times Last modified on Saturday, 11 February 2012 11:00