Saturday, 12 December 2015 11:14

“ዕብድ እህል ገዝቼ ሚስቴን አሳበድኳት!”

Written by 
Rate this item
(40 votes)

   ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ባል ወደ ሩቅ አገር ሲሄድ መንገድ ላይ ይመሽበታል፡፡
ወደ አንድ ቤት ጎራ ብሎ፤
“የመሸበት መንገደኛ እባካችሁ አሳድሩኝ?” ሲል ይለምናል፡፡
አባወራውም፤
“ቤታችን የእግዚአብሔር ቤት ነው፡፡ ግባ፡፡ የበላነውን በልተህ፣ የጠጣነውን ጠጥተህ፤ መደብ ላይ እናነጥፍልህና ትተኛለህ፡፡” አለው፡፡
ባለቤቲቱም፤
“እኛም ወደናንተ አገር ብንመጣ ይሄንኑ እንደምታደርጉልን እናውቃለን፡፡ ተቀመጥ” አለችው፡፡ እንግዳው ገብቶ እየተቀመጠ፤ “እግዚአብሔር ይስጥልኝ፡፡ ብድር ከፋይ፣ ውለታ መላሽ እንዲያደርገን እመኛለሁ፡፡”
ውሃ አሙቀው እግሩን እንዲታጠብ አደረጉ፡፡ እራት ቀረበ፡፡ ከጎን ምድጃው ላይ ቡና ይቆላል፡፡ እራት እየተበላ፤
“ከእኛ ብዙ ርቀህ ለመሄድ አስበህ ነው?”
“ብዙም አይርቅም፡፡ ከእንግዲህ ግማሽ ቀን ቢያስጉዘኝ ነው”
“እንግዲያው ቡናህን ትጠጣና በጊዜ እንድትተኛ እናደርግሃለን፡፡ ቀኑን ሙሉ መንገድ መትቶህ ደግሞ ነገም ሌላ መንገድ ያደክምሃል፡፡” እራት አብቅቶ ቡና ቀረበ፡፡ ፈንዲሻ ተቆላ፤ ተበላና ወደ ተነጠፈለት መኝታ ሄደ፡፡
ጠዋት ቁርስ አብልተውት ሲወጣ ወደ ሴትዮዋ ጠጋ ብሎ፤
“እሜቴ አንድ ነገር ላስቸግርሽ?”
“ምን ልርዳህ?”
“ይሄ ማታ የቆሉትና ያበሉን ምን ነበር?”
“ፈንዲሻ፤ ፈንዲሻ ነው!”
“ገበያ ላይ ይገኛል?”
“ኧረ የትም ይገኛል!”
“እግዚአብሔር ይስጥልኝ” ብሎ አመስግኖ ተሰናበተ፡፡
ወደሚሄድበት ከተማ ደርሶ ሲመለስ ያን ፈንዲሻ እህሉን ገዝቶ ወደ ቤቱ አመራ፡፡
“ዛሬ ተዓምር የሆነ ነገር ይዠልሽ መጥቻለሁ” አላት ለሚስቱ
“ምን?”
“ፈንዲሻ የሚባል የሚፈካ እህል፡፡ ቡና ስታፈይ ትቆይውና እንበላለን”
ቡናው ከፈላ በኋላ ሚስትየው፣ የፈንዲሻውን በቆሎ ክዳን በሌላው ብረት ድስት አድርጋ ስታራግበው ከፊሉ በግራ፣ ከፊሉ፣ በቀኝ የቀረው ወደላይ እንደርችት መፈነጣጠር ጀመረ፡፡ ሚስት የቱን ትያዘው? አንዴ ወደቀኝ የሄደውን ልትይዝ ስትዘል፣ አንዴ ወደ ግራ የሄደውን ልትቀልብ ስትወራጭ፤ ባልም መላው ጠፍቶት ግራ እንደተጋባ ቆሞ፤
“አዬ ጉድ! አዬ ጉድ! ሳይቸግረኝ ዕብድ እህል ገዝቼ ሚስቴን አሳበድኳት!” አለ፡፡
*         *       *
ዕብድ እህል ገዝተን አገር እንዳናሳብድ መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡ ዕብድ ዕቅድ አቅደን አገሬውን እንዳናሳብድ ተረጋግተን ማቀድ ይገባናል፡፡ ዕብድ ሲስተም ዘርግተን በየቀኑ እየተቋረጠ “ሲስተም የለም” እንዳንል ማስተዋል አለብን፡፡ ብቃት የሌለው የሰው ኃይል ቀጥረን ግራ ተጋብቶ ባለጉዳይ እንዳያሳብድ ከመነሻው በጥራት ላይ የተመሰረተ አሰራርና ሰራተኛ ማዘጋጀት ግድ መሆኑን መገንዘብ ዋና ነገር ነው! ጥናቶች ሁሉ ጥናት እያስፈለጋቸው ከመጣ፤ ድካማችን ሁሉ ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ነው፡፡
“ቀድሞ ነበር እንጂ፣ መጥኖ መደቆስ
አሁን ምን ያደርጋል፣ ድስት ጥዶ ማልቀስ”
የሚለውን አገርኛ አነጋገር በቅጡ መረዳት፤ ምን ጊዜም ወቅታዊነት ያለው መሆኑን መገንዘብ ከአያሌ አባዜ ያድነናል!
ዕብድ የሲስተም እህል ባልተከደነ ብረት - ድስት እንደሚፈነዳዳው፣ ፈንዲሻ አላዋቂ ቆይውን እንደሚያደነባብር፣ ብልጣ ብልጥ ባለሙያም እንዳሻው እንደሚጮልልበት ማጤን አያዳግትም፡፡ ሙስናችን ለያዥ ለገራዥ ባስቸገረበት በአሁኑ ሰዓት፤ አንድ የጥንት ታሪካዊ ምሳሌ ማየት ደግ ነው!
አንድ መምህር አንድ ጥንታዊ ደብር እንደኃላፊ ይሾማሉ፡፡ አዲሱ ኃላፊ የማያስበሉና የማይሞዳሞዱ ናቸው! ቀድሞ በደብሩ ሹመኛ የነበሩትና በሙስና ይታሙ የነበሩት ሁሉ አኮረፉ፡፡ ስለዚህም ንጉሱ መጥተው አቤቱታ እናሰማ ሲሉ ጠየቁና ንጉሱ መጡ፡፡ እንዲህ ሲሉ ሹማምንቱ ከሰሱ፡-
“ንጉሥ ሆይ! ለመሆኑ ምን አጥፍተን ነው እንዲህ ያለ አህያ የሾሙብን?”
ንጉሡ፤ “እህ ምን ትላለህ? አዲሱ ተሿሚ?” አሉና ጠየቁት፡፡
አዲሱ ተሿሚም፤
“ይሁን ጃንሆይ! እኔስ አህያ ልሁን፡፡ ግን ጃንሆይ፤
እኔ አንድ አህያ ለስንት ጅብ እሆናለሁ?!” ሲል መለሰ፡፡
ንጉሱ፤ “ሥልጣንህ የፀና ይሁን፡፡ ነገሩ ገብቶኛል!” አሉና ወሰኑ፡፡ እንዲህ ያለ ንጉሥ ሊኖረን ይገባል፡፡ ከዚህ የምንገነዘበው ነገር እንግዲህ ስለመልካም አስተዳደርና ስለሙስና ታሪክ የሚያስተምር ሪኮርድም አለን እንደማለት ነው፡፡ ታሪካችንን በመረመርን ቁጥር ጥፋታችንን ፍንትው አድርጐ የማያሳይ መስተዋት አገኘን ማለት ነው፡፡
ስለነባሮቹ ጅቦች ይሄን ያህል ካልን፣ ስለአዳዲስ ጅቦችም የምናውቀውን እንል ዘንድ ወቅቱ ግድ ይለናል፡-
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ መንደር ውስጥ ሌብነትና ዘረፋ እጅግ እየናጠጠ ሲመጣ የሰፈሩ ሰው ሁሉ አውጫጪኝ ተቀመጠ! (በዚያ መንደር ተጠርጣሪ ሌቦች አቶ ለማ፣ አቶ ቢተውና አቶ ጀንበር ናቸው እየተባለ ይወራል፡፡)
ሰው በየፊናው እያጉተመተመ ድፍረቱን አጥቶ ሳለ፣ አንድ ባለቅኔ አዛውንት ተነሱና በወኔ፡-
“ጐበዝ!
ሌባው ለማ!
ቢተው ይተው!
ባይተው ግን፤ ጀንበር በሠረቀ ቁጥር፤ ህዝቡ የሚሰቃይበት፤ ከቶ አንድም ምክንያት አይኖርም!” ሲሉ ደመደሙ!
ህዝቡ ዋናውን ነቀርሳ ስለሚያውቅ፣ ግብረ - ገባዊ ባህሪውን ጥሶ “ዕውነትክን ነው! ይገባሃል!” ማለቱን ቀጠለ፡፡ ትልቁ ነጥብም እዚሁ ላይ ነው! ሌቦቻችንን እኛው እያወቅን አንሸሽማ! እቺ ባቄላ ያደረች እንፈሁ እንበል፡፡
የሀገራችንን ፖለቲካዊ - ኢኮኖሚ፣ ትላንትም፣ ዛሬም፣ ነገም፣ ውሉ የማይታወቅ ከማስመሰል ይልቅ፤ ፈር ቀዳጅ፣ አመርቂ፣ ዘላቂ፤ ሰው ለሰው አጠያያቂ፣ እንዲሆነ የቱን ብንገዛ፣ የቱን ብንሸጥ፣ የቱን ውሉን ብንሰርዝ፣ የቱን ከኃያላን ውጪ ብናደርግ… የሚለውን ሃሳብ ያለምንምና ያለ ማንም ተፅዕኖ ልንከውነው እንችል ይሆን ብሎ ከአገር ጋር መክሮ፣ ዘክሮ መራመድ የጥበብ መጀመሪያ ነው፡፡ ይህን ያሠመረና ሁሉን ያስተዋለ መንገድ መጓዝ፤ “ዕብድ እህል ገዝቼ ሚስቴን አሳበድኳት” ከማለት ያድነናል!!

Read 12730 times