Saturday, 05 December 2015 09:10

“የግሉን ፕሬስ “የደፈሩ” የመጀመሪያው መሪ!!”

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(15 votes)

• ሚኒስትሮች ቃለምልልስ መስጠት ሥራቸው መስሎኝ?
• አገር በጋዜጣ ብቻ የምትፈርሰው ከምን ብትሰራ ነው?
• “ከእናንተ በላይ ኢትዮጵያዊ ነኝ” ለማለት የሚዳዳው አለ!

ባለፈው ሳምንት በመረጃ ነፃነት ህጉ ዙሪያ በተካሄደው ውይይት ላይ የተለያዩ አነጋጋሪ ጉዳዮች ተነስተው ነበር፡፡ (ባይነሱ ነበር የሚገርመው!) ከእነሱም መካከል ----- “መንግስት ህጉን ለመተግበር ቁርጠኝነት ይጐድለዋል”፣ “የህዝብ ግንኙነት ሃላፊዎች ምደባ ብቃት ላይ ሳይሆን ካድሬነት ላይ ያተኮረ ነው”፣ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጽ/ቤት ራሱ የአደረጃጀት ችግር አለበት፣ መረጃ መስጠትን እንደውለታ የሚቆጥሩ ኃላፊዎች አሉ ---- እና ሌሎችም ሃሳቦች ተነስተዋል፡፡
አዲሱ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ሃላፊ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ፣ በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ቀደም ሲል የተተቸባቸው ጽ/ቤታቸው የአደረጃጀት ችግር እንደሌለበት ጠቁመው፤ “ከመረጃ ነጻነት ህጉ ጋር በተገናኘ የመንግስት ከፍተኛ ሃላፊዎች (ሚኒስትሮች) ለጋዜጠኞች ቃለምልልስ የመስጠት ግዴታ የለባቸውም” ሲሉ በአራት ነጥብ ዘጉ፡፡  (“እየመጣሽ…” ማለት አሁን ነው!) እነሱ  የመጠየቅ ግዴታ ከሌለባቸው የመረጃ ነፃነት ህጉ እንዴት ነው የሚተገበረው? (በአስማት!)
እናም ---- ሚኒስትሩ የሃላፊዎች ግዴታ በመንግስት የተዘጋጀ ሰነድ መስጠት ብቻ ነው አሉ፡፡ (እኔማ ሚኒስትሮች ቃለ ምልልስ መስጠት ሥራቸው መስሎኝ ነበር?!) ግን ቁርጤን ነገሩኝ ---- ግዴታ እንደሌለባቸው! (ግዴታቸው ምን ይሆን?) በዚህ አጋጣሚ … ኢንተርቪው የመስጠት ግዴታ ያለባቸው ሃላፊዎች ቢነገሩን ጥሩ ነበር (ማንም ግዴታ የለበትም ከተባለም ችግር የለም!)
ዝም ብዬ ነገሩን ሳስበው ግን ገረመኝ፡፡ ትልቁን የህዝብ ሥልጣን ሰጥቶ፣ አይናገሩም አይጋገሩም----ብሎ ነገር ምንድን ነው? ቀድመን ብናውቅ እኮ መላ እንዘይድ ነበር፡፡ (አንመርጣቸውማ!) በነገራችን ላይ ጋዜጠኛ እኮ የህዝብ ጥያቄ---ቅሬታ---ሃሜት---ስሞታ--መረጃ--ይዞ ነው ለቃለምልልስ የሚሄደው፡፡ በሌላ አነጋገር መልስ የሚሰጡት ግብር ለሚከፍለውና ድምጽ ለሚሰጣቸው፣ የሥልጣን ባለቤት ለሆነው ሰፊው ህዝብ ነው፡፡ (ጋዜጠኛ የህዝብ ወኪል ነው ለካ!) በእርግጥ እኛም አንዳንዴ እንደ ቢቢሲ Hard Talk ምናምን ሲያምረን ብናፋጥጣቸው ደስ ይለናል፡፡ ግን አልሆነም በቃ፡፡
እኔ የምለው ግን ሚኒስትሩ፤ ለምን ይሆን ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ከቃለ ምልልስ ግዴታ ነፃ ሊያወጧቸው (ሊከላከሏቸው) የፈቀዱት? (ባውቀው ደስ ይለኝ ነበር!) ለነገሩ እስከ ዛሬም እኮ ሚኒስትሮች ቃለ ምልልስ የመስጠት ግዴታ ኖሮባቸው አያውቅም፡፡ (የአሁኑን ለየት የሚያደርገው በመረጃ ነፃነት ህጉ ላይ ውይይት በተደረገበት ዕለት መሆኑ ብቻ ነው!)
የሚገርመው ግን ምን መሰላችሁ? እንዲህ በተባለ በጥቂት ቀናት ልዩነት ውስጥ አንድ ያልተጠበቀ ታሪካዊ አጋጣሚ ተከሰተ፡፡ (ተዓምር በሉት!) “ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ቃለምልልስ የመስጠት ግዴታ የለባቸውም” የሚለውን አባባል የሚፈታተን ክስተት እኮ ነው፡፡  እናላችሁ --- በኢህአዴግ የ25 ዓመት የስልጣን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ ሰሞኑን ለግል ሚዲያ ቃለምልልስ ሰጥተዋል፡፡ በእርግጥ እሳቸው ስለሰጡ የቀሩት ሚኒስትሮች ለቃለምልልስ ወረፋ ይይዛሉ እያልኩ አይደለም፡፡ (ዓይነጥላቸው ይገፈፍላቸዋል ለማለት ነው!!)
በነገራችን ላይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ (መሬት ይቅለላቸውና!) “አባይን የደፈሩ የመጀመሪያው መሪ” እንደተባሉት ሁሉ ---- ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝም፤ “የግል ፕሬሱን የደፈሩ የመጀመሪያው መሪ” ሊባሉ ይችላሉ፡፡ (ተቃዋሚ ካለ ----) -ሰሞኑን ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ። ኢህአዴግ ቡድን እንጂ ግለሰቦች ሲወደሱ ሰለሚከፋው፣ “የግል ሚዲያን የደፈረው ጠ/ሚኒስትሩ ሳይሆን ፓርቲው ነው” የሚል ነገር ብትሰሙ እንዳይገርማችሁ። (ባህሉ ነዋ!) ምናልባት አንጋፋው ታጋይና የህወኃት መስራች አቦይ ስብሃትም (አንዳንዶች “አነጋጋሪው” ይሏቸዋል!) በበኩላቸው፤ “የግል ሚዲያውን የደፈረው ኃይለማርያም ሳይሆን ህዝቡ ነው” ሊሉ ይችላሉ፡፡ (“አባይን የደፈረው ኢህአዴግም መለስም አይደሉም፤ ህዝቡ ነው” እንዳሉት!!) ለማንኛውም ግን እውነቱ ይሄ ነው። (አውጎቾ ተረፈ “እያስመዘገብኩ ነው” ብሎ የጻፈው ታሪክ ትውስ አለኝ!)  
ለማንኛውም ግን ጠ/ሚኒስትሩ ለግል ጋዜጣ ቃለምልልስ ሲሰጡ የነጻውን ፕሬስ አባላት “ሰርፕራይዝ” ማድረግ አምሯቸው አይመስለኝም። አስፈላጊነቱን መዝነውና መርምረው ነው። ሚኒስትሮቻቸው ደግሞ ከዚህ የሚማሩት ይኖራል፡፡ (አንማር ካሉ ግምገማ ላይ ይማሩታል!) ከዚህ አጀንዳ ከመውጣቴ በፊት አንድ ጉዳይ ላንሳ፡፡ ቀደም ሲል በጠቀስኩት የመረጃ ነፃነት ህጉ ላይ በተካሄደ ውይይት ከተሰነዘሩት አስተያየቶች መካከል፣ “መረጃ ለመስጠት የቤት ልጅና የውጭ ልጅ እየተባለ አድልዎ ይደረጋል” የሚል ቅሬታ ይገኝበታል፡፡ እውነቱን ልንገራችሁ አይደል….ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በየጊዜው ለኢቢሲ ወይም ለአዲስ ቲቪ አሊያም ለፋና ቃለምልልስ ሲሰጡ ባየሁ ቁጥር ተመሳሳይ ስሜት ይወረኝ ነበር፡፡ (የውጭ ልጅ የመሆን ስሜት!) አሁን ግን አከተመ፤ ሁሉም እኩል ልጅ ነው፡፡ (ልጅና የእንጀራ ልጅ ብሎ ልዩነት የለም!)
አንዳንዴ ምን ይገርመኛል መሰላችሁ? የሆነ አካል፣ ፓርቲ፣ ሚዲያ፣ የመንግስት ተቋም ወዘተ --- “ለአገሪቱ ከአንተ የበለጠ…አስባለሁ…እቆረቆራለሁ---ምናምን” ለማለት ሲዳዳው! (አንዳንዱማ ከአንተ በላይ “ኢትዮጵያዊ ነኝ!” ሊል ሁሉ ምንም አይቀረው!) በዚህ ቢበቃው ደግሞ ጥሩ ነበር፡፡ ዝም ካላችሁት…ኢትዮጵያዊነታችሁን ከመቀማት በመለስ በፍረጃ ያሽራችኋል፡፡ ፀረ - ልማት፣ ፀረ - ሰላም፣ ፀረ- ዕድገት፣ ፀረ - አገር፣ ወዘተ እያለ፡፡ (ኢትዮጵያዊነትን ከመቀማት እኩል እኮ ነው!) ይሄ ጉዳይ በምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ? የ100 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ ለመሆን ጥቂት ዓመታት ብቻ የቀረው አንጋፋው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት፣ ከአሳታሚዎች ጋር ለመፈራረም ባሰናዳው ውል ላይ ባነበብኩት አንቀፅ የተነሳ ነው። እንዲህ ይላል አስገራሚው አንቀጽ፡- “አታሚው በአሳታሚው እንዲታተም የቀረበለት የጽሑፍ ስክሪፕት ህግን የሚተላለፍ ስለመሆኑ ለማመን በቂ ምክንያት ካለው አላትምም የማለት መብት አለው” (ኢህአዴግ “የድሮ ሥርዓት ናፋቂዎች” አለ!) ትክክለኛው ቦታው እኮ እዚህ ጋ ነው! ብርሃንና ሰላም፤የደርግ ዘመን ሳንሱር ናፍቆታል መሰለኝ፡፡
ከምሬ እኮ ነው----አቃቤ ህግ እንኳን ጋዜጣው ህግ ሲተላለፍ የሚከሰው ታትሞ ከወጣ በኋላ ነው፡፡ ለምን? ሳንሱር ወይም ቅድመ - ምርመራ ክልክል ነዋ! ማተሚያ ቤቱ ግን “አዳሜ ልታሳትሚ ስትመጪ በአጉሊ መነፅር እየመረመርኩ ከህትመት ውጭ አደርግሻለሁ” ያለ ነው የሚመስለው፡፡
ይሄ የውሉ አንቀፅ ከሳንሱር ክልከላ ህግ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም በማለት የሚከራከሩት የማተሚያ ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ተካ አባዲ፤ “አንቀፁ፤ አገርን የሚያፈርስ ዘገባ ካለ አላትምም” የሚል ነው ይላሉ፡፡ (አገር በጋዜጣ ትፈርሳለች እንዴ?)
 ሥራ አስኪያጁ አክለውም፤ “እንደ አንድ የመንግስት ተቋም፣ የህዝብንና የአገርን ደህንነት የመጠበቅ ሃላፊነት ስላለብን ውሉን ለማስፈረም እንገደዳለን” ብለዋል፡፡ (የት አገር ነው የአገር ደህንነት በማተሚያ ቤት ተጠብቆ የሚያውቀው!) ይኼውላችሁ…ቅድም ያልኩት ይሄንን ነው፡፡ የግሉ ሚዲያ ለምንድን ነው አገርን እንደሚያፈርስ ተደርጐ የታሰበው? (ኢትዮጵያዊ እኮ ነው?!) እንደሳቸው መ/ቤት የመንግስት ተቋም ባይሆንም… የአገርን ደህንነት በመጠበቅ ረገድ  ፈጽሞ ከማተሚያ ቤቱ ያነሰ ሃላፊነት ሊኖረው አይችልም፡፡ ቅድም እንደተባባልነው----- “ለአገሪቱ እንደኔ አሳቢና ተቆርቋሪ የለም” ብለን ስንጀምር ነው ነገር የሚበላሸው፡፡  
“ሁሉም ለአገሩ ያስባል፤ ሁሉም አገሩን ይወዳል፤ ሁሉም ለአገሩ ይቆረቆራል፤ሁሉም ዕድገቷን  ይመኛል፤ ሁሉም ብልጽግናዋን ያልማል” ብለን መነሳት ነው ያለብን። ያኔ ብቻ ነው እኩል የኢትዮጵያዊነት ስሜት፣ባለቤትነት፣ሃላፊነት----- በሁላችንም ዘንድ የሚሰርጸው፡፡ (ሳላውቀው ብሄራዊ መግባባት የሚፈጥር ነገር ተናገርኩ እንዴ!) አድርጎት ነው!!

Read 5904 times