Saturday, 14 November 2015 08:59

“ለጌሾው ወቀጣ ማንም ሰው አልመጣ፤የመጠጡ ጊዜ ከየጎሬው ወጣ!”

Written by 
Rate this item
(15 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን ሁለት ጓደኛሞች ረዥም መንገድ ሊሄዱ ይነሳሉ፡፡ ምክክር ይጀምራሉ፡፡
አንደኛው - እንዲያው ለነገሩ እንዲህ ያለ ረዥም መንገድ ስንጀምር ብዙ ስንቅ መያዝ ነበረብን’ኮ፡፡
ሁለተኛው - ያንተን አላቅም እንጂ እኔ ከቤት የተዘጋጀልኝን ስንቅ ይዣለሁ፡፡
አንደኛው - ምን ምን ይዘሃል?
ሁለተኛው - በሶ፣ ጭኮ
አንደኛው - ሌላስ?
ሁለተኛው - አንድ አገልግል አላቂ ምግብ፣ ለአንድ ቀን የሚሆነን፡፡
አንደኛው - የሚጠጣስ?
ሁለተኛው - የሚጠጣስ ከኮዳዬ ውሃ ሌላ ምንም አልያዝኩም!
አንደኛው - መንገድ ላይ አውሬም፣ ሽፍታም ሊያጋጥመን ይችላል፡፡ ምን መሳሪያ ይዘሃል?
ሁለተኛው - ኧረ መሣሪያስ ምንም አልያዝኩ፡፡ እንዲያው አምላካችንን ተማምኜ ነው የወጣሁ፡፡፡ ለመሆኑ አንተስ ምን ይዘህ ነው የመጣህ?
አንደኛው - እኔ ምግብ፣ መጠጥ፣ መሳሪያ… አንዱንም አልያዝኩም፡፡ የሁለታችንን ልባዊ ፍቅር፣ አብሮ አደግነትና ዝምድናችንን ተማምኜ ነው የመጣሁት፡፡
ሁለተኛው - ይሄንንም ካሰነበተልን ምን እንፈልጋለን፡፡ በዚሁ ተማምነን መንገዳችንን መቀጠል ነው ያለብን፡፡
አንደኛው - በጣም ጥሩ እንግዲህ፤ ልባችንን አንድና ንፁህ አድርገን እንገስግስ፡፡
ሁለቱ ጓደኛሞች ተስማምተው መንገዳቸውን ተያያዙት፡፡ ከተማውን ዘልቀው ገጠር ደረሱ፡፡ ጫካ ጫካውን ሲያቋርጡ በድንገት አንድ ድብ ከፊታቸው ከች አለ፡፡ ይሄኔ አንደኛው በከፍተኛ ፍጥነት ተስፈንጥሮ ዛፍ ላይ ወጣ፡፡ ሁለተኛው የሚያደርገው ጨነቀው፡፡ አንድ ዘዴ ትዝ አለው፡፡ ድብ በተፈጥሮው ሬሣ አይበላም፡፡ ስለዚህ ሰውዬው ድምፁን አጥፍቶ ቢጋደም ድቡ ምንም ላያደርገው ይችላል፡፡
መሬት ላይ ተጋደመ፡፡
ድቡ ወደተኛው ሰው ቀረበና ወደፊቱ ጠጋ አለ፡፡ ከዚያም አሸተተውና ሞቷል ብሎ ጥሎ ሄደ፡፡ ድቡ መሄዱን ያየው ዛፉ ላይ ያለው ሰውዬ፣ ፈጥኖ ወረደና ወደተኛው ጓደኛው በመምጣት እንዲህ ሲል ጠየቀው፤
“ድቡ ወደ ጆሮህ ጠጋ ብሎ ሹክ ያለህ ነገር ምንድነው?”
የተጋደመው ጓደኛውም እንዲህ ሲል መለሰለት፡-
“ወዳጄ ሆይ! ከእንዲህ ከማያስተማምን ከሀዲ ጓደኛ ጋር አብረህ ረዥም መንገድ አትጀምር! ብሎ ነው የመከረኝ!”
*         *         *
ረዥም ጉዞ የሚጠብቀን መንገደኞች መተማመን ይገባናል፡፡ በአንድ ልብ የማይጓዙ መንገደኞች አገር አይገነቡም፡፡ ይልቁንም ቶሎ የመፈራረስ፣ እርስ በርስ የመጠራጠር፣ አንዱ አንዱን ለመጣል የመጣር፣ የመተነኳኮስና የመካካድ ባህሪ ያነግሳሉ፡፡ ተቋማዊ
አደረጃጀታቸውን ጥያቄ ላይ የሚጥለው ይህን ዓይነት ባህሪ ሲኖር ነው፡፡ ቡድናዊነትና ወገናዊነት ከበዛ መንገዶች እንቅፋት ይበዛባቸዋል፡፡ ይህ በፈንታው አገሬውን ይበድላል፡፡
መልካም አስተዳደርን ለማምጣት አስተዳዳሪዎቹ መልካም መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ መልካምነት በድንገት የሚከሰት ነገር አይደለም፡፡
የልብ ንፅህናን ይፈልጋል፡፡ የእጅ ንፅህናንም ይፈልጋል፡፡ ብስለትን ይፈልጋል፡፡ የሙሰኞች ፀር መሆንን ይጠይቃል፡፡ ከስህተት ተምሮ በየጊዜው ራስን ማሻሻልን ይጠይቃል፡፡ ባለጉዳይን ማክበርን ይጠይቃል፡፡ ምዝበራን መከላከልን ይጠይቃል፡፡ ፍትሐዊነትን ይጠይቃል፡፡

እነዚህ ባህርያት ሂደታዊ ናቸው፡፡ እያደር ራስን በመለወጥ የሚመጡ ናቸው፡፡ አብዛኛውን የለውጥ ጉዞ አዲስ አበባ ላይ ማየት የዋና ከተማችን እምብርትነትና ከተሜነት (ሜትሮፖሊታን መሆን) አመላካች ነው፡፡ ብዙ ጥፋቶችም ልማቶችም የሚታዩት ዋና ከተማ ላይ
መሆኑ ቁልፍ ቁልፍ ተቋማትም፣ ሹማንንትም እዚችው ከተማ ላይ መከማቸታቸውን ይነግረናል፡፡ ከየክልሉ ወደ ዋና ከተማይቱ የሚፈልሰው ህዝብ፣ የነዋሪውን ህዝብ ቁጥር መጨመሩ ብቻ ሳይሆን ባለጉዳዩን ያበረክተዋል፡፡ ባለጉዳዩ የመሬት ጉዳይ አለው፡፡
የመኖሪያ ቤት ጉዳይ አለው፡፡ የፍትህ ጉዳይ አለው፡፡ የከፋ የኢኮኖሚ ጉዳይ አለው፡፡ ይህንን ጉዳይ የሚፈታለት፣ የሚያስተናግድለት መልካም አስተዳደር ይሻል፡፡፡ በንፁህ መሰረት ላይ የተቋቋሙ መሥሪያ ቤቶች ከሌሉ፣ ባለጉዳይ አስፈፃሚ ጋር እየተሞዳሞዱ ሥራ
በሚያንቀሳቅሱበት ከተማ፣ መልካም አስተዳደርን መመኘት ቢያንስ የዋህነት ነው፡፡ ብርቱ ቁጥጥርና ብርቱ እርምጃን ይጠይቃል፡፡ እርምጃው እውነተኛ እርምጃ እንዲሆን የተሿሚዎች እከክልኝ ልከክልህ ሰንኮፍ መነቀል አለበት፡፡ ዘረፋና ምዝበራ መቆም አለበት፡፡
ከቢሮ ውጪ የሚደረጉ ውሎችና ድርድሮች መወገድ አለባቸው፡፡ ይህ ትግል ከባድ ቁርጠኝነትን ይጠይቃል፡፡
ተግባሩ ላይ ሳይሳተፉ ወይም ተግባሩን እያደናቀፉ፣ የአደባባይ ስብሰባ ላይ አንደበት ቢያሳምሩና ቢያስጨበጭቡ “ለጌሾው ወቀጣ
ማንም ሰው አልመጣ የመጠጡ ጊዜ ከየጎሬው ወጣ!” እንደሚባለው ነው እሚሆነው፡፡ ተግባሪ ሳይኖር፣ ስለመልካም አስተዳደር ዘማሪው በዛ እንደማለት ነው፡፡ ተግባሪ አመራር ይኖር ዘንድ ውስጡ መፈተሽ ይኖርበታል!

Read 7504 times