Saturday, 07 November 2015 09:17

ለሉሲዎች ከ2016 የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ውጭ መሆን ፌዴሬሽኑ ተጠያቂ ነው ተባለ

Written by 
Rate this item
(8 votes)

ቡድኑ በቀጣዩ ኦሎምፒክ ማጣሪያም አይሳተፍም

    የኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን ሉሲ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለሚመለከተው አካል መላክ የነበረበትን የተሳትፎ ማረጋገጫ ደብዳቤ ባለመላኩ በሰራው ጥፋት ሳቢያ፣ በካሜሩን አስተናጋጅነት ከሚካሄደው የ2016 የአፍሪካ ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ ውድድር ውጭ ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ የውድድር ተሳትፎ ማረጋገጫ ደብዳቤውን ባለመላኩ ሳቢያ ብሄራዊ ቡድኑ
ከቅድመ ማጣሪያ የምድብ ድልድል ውጭ መደረጉን የተነገረ ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪም ቡድኑ በዚሁ የፌዴሬሽኑ ጥፋት ምክንያት ከ2016ቱ የሪዮ ዴ ጄኔሮ ኦሎምፒክ ማጣሪያ ውጭ መሆኑንም ምንጮቻችን ገልጸዋል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ ካይሮ በሚገኘው የካፍ ዋና ጽህፈት ቤት በተከናወነው የቅድመ ማጣሪያ ውድድር የምድብ ድልድል እጣ አወጣጥ ስነስርዓት ውስጥ ሉሲዎቹ አለመካተታቸውን ያስታወሱት ምንጮች፣ ፌዴሬሽኑ ከሚመለከተው አካል ጋር ተጻጽፎ ቡድኑን ወደ ውድድር ለመመለስ ማቀዱንና የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ ትናንት ወደ ግብፅ በማቅናት፣ በበጀት ምክንያት በውድድሩ
በማይሳተፉ አገራት ቡድኖች ምትክ ብሄራዊ ቡድኑ መሳተፍ የሚችልበትን ዕድል ለማመቻቸት እንዳሰቡም ጠቁመዋል፡፡ፌዴሬሽኑ ባለፈው የአለም ዋንጫ ማጣሪያ ውድድር ተሳትፎ በነበረው የወንዶች ብሄራዊ ቡድን መመዝገብ የነበረበትን የምንያህል ተሾመ ቢጫ ካርዶች ችላ በማለቱ ሳቢያ በተፈጠረ ችግር ከፍተኛ የህዝብ ተቃውሞ ገጥሞት እንደነበር ይታወሳል፡፡

Read 4324 times