Saturday, 07 November 2015 09:15

ኩባንያዎችና ነጋዴዎች በውጭ ምንዛሪ እጥረት ተቸግረናል አሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

ቴክኖ ሞባይል ላለፉት 3 ወራት አላመረተም

    በሀገሪቱ በተከሰተው የውጭ ምንዛሪ እጥረት የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች ምርት ማምረት እስከማቆም የደረሱ ሲሆን በአስመጪና ላኪነት የንግድ ስራ ላይ የተሠማሩ ነጋዴዎችም መቸገራቸውን ገልፀዋል፡፡
ከ900 በላይ ሠራተኞችን ይዞ ተንቀሳቃሽ ስልኮችን በማምረት ሥራ ላይ የተሠማራው የቴክኖ ሞባይል አምራቹ ዊጉዩ ኩባንያ፤ በውጭ ምንዛሪ እጥረቱ የተነሳ ላለፉት 3 ወራት ምርት ማምረት ማቆሙን አስታውቋል፡፡
ኩባንያው የውጭ ምንዛሪ ከባንክ ቢጠይቅም “ትንሽ ጊዜ ታገሱ” የሚል መልስ እንደተሰጠው የቴክኖ የአስተዳደር ክፍል ሃላፊ አቶ ገነነ አዘነ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
ሃላፊው እንዳሉት፤ ኩባንያው ጠንካራ የገንዘብ አቅም ያለው በመሆኑ ለኪሣራ ባይዳረግም ስራ ባቆመባቸው ወራት በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ አጥቷል፡፡
“ችግራችንን ለመንግስት አሳውቀናል፤  በቅርብ ጊዜ ችግሩ ይፈታል የሚል ተስፋ አለን” ብለዋል፤ ሃላፊው፡፡
ኩባንያው በቀን ከ10ሺህ በላይ ተንቀሳቃሽ ስልኮችን አምርቶ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገራት ያቀርብ እንደነበርና በአሁን ሰአት በምንዛሪ እጥረቱ የተነሣ ሙሉ ለሙሉ ምርት ማቆሙን ጠቁመው፣ ያጋጠማቸው ችግር ጠንከር ያለ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በተመሳሳይ በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው በአስመጪነትና ላኪነት ስራ ላይ የተሠማሩ ነጋዴ በበኩላቸው፤ የዶላር እጥረቱ ከአንድ አመት በላይ እንደሆነው፤ ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እጥረቱ እየተባባሰ እንደመጣና በንግድ ስራቸው ላይ ከፍተኛ ፈተና እንደጋረጠባቸው ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡   
“ከ5ሺ ዶላር ጀምሮ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ለባንክ ፕሮፎርማ ካስገባን በኋላ እድል ከቀናን ከ3 እና 4 ወር በኋላ ነው የምናገኘው” የሚሉት ባለሃብቱ፤ በችግሩ የተነሳ ሠራተኛ በትነው ስራ ፈተው እስከመቀመጥ መድረሣቸውን ገልፀዋል፡፡
የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ስራ አስኪያጅ የሆኑ ግለሰብም ፋብሪካቸው በውጭ ምንዛሪ እጥረት የተነሳ ከውጭ ጥሬ እቃ ማስገባት መቸገሩን ጠቅሰው ባለፉት 4 ወራት ኢንዱስትሪያቸው ለከፍተኛ ኪሣራ እየተዳረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ “መንግስት በተደጋጋሚ ችግሩ በአጭር ጊዜ ይቀረፋል” የሚል ምላሽ ሲሰጠን ቆይቷል ያሉት ስራ አስኪያጁ፤ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን ችግሩ ይበልጥ እየተባባሰ መጥቷል ብለዋል፡፡
በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ችግሩ ካልተቃለለላቸው ሠራተኛ እስከመቀነስ የሚደርስ እርምጃ ሊወስዱ እንደሚችሉ የጠቀሱት ስራ አስኪያጁ፤ በቅርብ የሚያውቋቸው ፋብሪካዎችም ተመሳሳይ እርምጃ መውሰዳቸውን እንደታዘቡ ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡ በአስመጪነትና ላኪነት የንግድ ስራ ላይ የተሠማሩ ሌላው አስተያየት ሰጪ፤ የዶላር እጥረቱ ስራቸውን ሙሉ ለሙሉ እንዳስተጓጐለባቸው ጠቁመው፤ መንግስት በአጭር ጊዜ ውስጥ እልባት ካላበጀለት የስራ ዘርፋቸውን ለመቀየር እንደሚገደዱ ተናግረዋል፡፡
“የምንዛሬ ጥያቄ ስናቀርብ በአሁን ሰአት መንግስት ከውጭ ስንዴ እያስገባ ስለሆነ ትንሽ ታገሱ የሚል ቀጥተኛ ያልሆነ የቃል መልስ እየተሰጠን ነው ብለዋል - ባለሀብቶቹ፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ሃጂ ኢብሣ ተጠይቀው ሲመልሱ፤ “ይሄ የኛም
ጥያቄ ነው ትክክለኛ ምላሽ የሚገኘው ከብሔራዊ ባንክ ነው” የሚል ምላሽ የሰጡን ሲሆን የብሔራዊ ባንክ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ መስፍን ደምሴ ጋር ደውለን መረጃ ለማግኘት ብንሞክርም በደብዳቤ መጠየቅ እንዳለብን ተገልፆልናል፡፡  

Read 4502 times