Saturday, 07 November 2015 09:07

በአቃቂ ቃሊቲ ለ52 ዓመታት ባሕረ ጥምቀት ሆኖ ያገለገለው ቦታ እያወዛገበ ነው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(8 votes)
  •  ምእመናን ቦታው ለሌላ ዓላማ መዋሉ እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል
  • • ክ/ከተማው ልማቱ በዓለ ጥምቀቱን ታሳቢ ያደረገ ነው ብሏል

   ላለፉት 52 ዓመታት በበዓለ ጥምቀት ማክበርያነትና በታቦት ማደርያነት ሲያገለግል የነበረው ቦታ ለሌላ አገልግሎት መዋሉ እንዳሳዘናቸው የአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ የዘጠኙ አድባራት አስተዳዳሪዎችና ምዕመናን ገለፁ፡፡ ቦታውን በዘመናዊ መንገድ አልምተው፣ ለምዕመናን ማንበቢያና ለአረጋውያን ማረፊያ ለማድረግ ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ ቤተ ክርስቲያኗ የፕሮጀክት ምክር ሐሳብ ለክፍለ ከተማው አስገብታ ስትጠይቅ መቆየቷን የወረዳዎቹ አስተዳዳሪዎችና የምዕመናን ተወካይ ኮሚቴ ተናግረዋል፡፡
የኮሚቴዎቹ ሰብሳቢ መልአከ ፀሐይ አባ ኃይለ መለኮት ይሄይስ እንደተናገሩት፤ ይህ ጉዳይ እልባት አግኝቶ ቦታው ለባህረ ጥምቀቱ አገልግሎት እንዲውል በየደረጃው ደብዳቤ ቢያስገቡም ሰሚ ማጣታቸውን ገልፀዋል፡፡ የአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሙሉነህ ፈይሳ በበኩላቸው፤ አሁን ቦታውን እያለማ ያለው የአዲስ አበባ ውበት መናፈሻና ዘላቂ ማረፊያ ኤጀንሲ እንደሆነ ገልፀው፣በሚከናወነው ልማት ቦታው ባሕረ ጥምቀትና የታቦት ማደርያ መሆኑን ታሳቢ ያደረገ ዲዛይን ተዘጋጅቶ የመናፈሻ አገልግሎት ለመስጠት
እየተሠራበት መሆኑን ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ “ላለፉት 52 ዓመታት የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች የተከሏቸውና ያለሟቸው ዛፎች እየተገነደሱ ቦታው ወደ በረሃማነት ሊቀየር ነው” ያሉት
የኮሚቴው አባላት፤ እየተሰራ ያለው ስራ ከኦርቶዶክስ እምነት ጋር ፍጹም የሚቃረን በመሆኑ እንቃወማለን ብለዋል፡፡ ለክፍለ ከተማው ያስገቡት ምክረ ሐሳብ ወደሚመለከተው አካል መምራቱን አስታውሰው፣ ከ50 ሺሕ እስከ 100 ሺህ ብር የሥራ መጀመሪያ ገንዘብ እንዲያሳዩ ተጠይቀው፤ 2.1 ሚሊዮን ብር የልማት በጀት እንዳላቸው ቢያሳዩም ልማቱ ሳይፈቀድ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ “ቦታውን
ማንም አይነካባችሁም፤ ይህን ለምዕመናንም አሳውቁ” በማለትም ክፍለ ከተማው አዘናግቶናል፤ ይላሉ፡፡
የክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አስፈጻሚ በበኩላቸው፤ ቦታው የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ይዞታ እንደሆነ ጠቁመው፣ ቤተ ክርስቲያኗ በቦታው ላይ የይዞታ መብት ሳይኖራት እንዴት ቦታውን ላልማ ትላለች፤ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በ27/11/2002 ዓ.ም ለወቅቱ የከተማዋ ከንቲባ አቶ ኩማ ደመቅሳ በፃፈው ደብዳቤ፤ የከተማዋን ልማት ቤተክርስቲያን እንደምትደግፍ ገልፆ፣ በአቃቂ ቃሊቲ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ከ41
ዓመታት በላይ ለባሕረ ጥምቀት እየተገለገሉ ያቆዩት ቦታ ለሌላ አገልግሎት ከመዋሉ በፊት አብያተ ክርስቲያናቱ በቦታው ላይ ሊሠሩት ያቀዱትን የልማት ሥራ ማከናወን እንዲችሉ አመራር እንዲሰጥላቸው አሳስቧል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶሱን የማሳሰቢያ ደብዳቤ ከፕሮጀክት ምክረ ሐሳቡ ጋር አያይዘው መላካቸውን የኮሚቴው ተወካዮች ገልጸዋል፡፡
ባለፈው ኅሙስ በቦታው ተገኝተን እንደታዘብነው፣ ቦታው እየተቆፈረ የግንባታ ሠራተኞች ሥራቸውን እየሠሩ ሲሆን በርካታ የግራር ዛፎችም ተቆርጠው ተከምረዋል፡፡ በሥፍራው በርካታ የፌደራል ፖሊሶች ከኮሚቴ አባላት ጋር በመነጋገር፣ የተሰበሰበው ሰው እንዲበተን ያዘዙ ሲሆን አባቶች በጸሎት አሳርገው ሕዝቡን አረጋግተው ወደየመጣበት መልሰዋል፡፡
“እኛ ፀብና ግርግር አንፈልግም፤ መንግሥት ችግራችንን ያውቀዋል ብለንም አንገምትም” ያሉት የኮሚቴው አባላት፣ “እስከ አሁን መልስ ለማግኘት ያንኳኳናቸው በሮች ስላልተከፈቱን ጉዳዩን በመገናኛ ብዙኃን በኩል ለከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ለማሰማት ተገድደናል፤” ብለዋል፡፡
የክፍለ ከተማው ሥራ አስፈፃሚ በበኩላቸው፤ “ቦታው በታቦት መግቢያነቱና መውጫነቱ ይቀጥላል፤ ይህን የከለከለ የለም፤ የመናፈሻው ዲዛይንም ይህን ታሳቢ ያደረገ ነው፤” ሲሉ ተቃውሞውን አስተባብለዋል፡፡ የክ/ከተማው ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅ መልአከ ምሕረት አምኃ መኳንንትን ለማነጋገር በተደጋጋሚ ስልካቸው ላይ ብንደውልም ዝግ በመኾኑ ሐሳባቸውን ለማካተት አልቻልንም፡፡   

Read 3928 times