Saturday, 07 November 2015 09:02

“እስቲ ቲያትር እንይ” ፌስቲቫል የፊታችን አርብ ይጀምራል

Written by  ማህሌት ኪዳነወልድ
Rate this item
(0 votes)

ኦቴሎ ከ30 ዓመት በኋላ ወደ መድረክ ይመለሳል

   አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለ2ኛ ጊዜ ያዘጋጀውን “እስቲ ቲያትር እንይ” የተሰኘ አመታዊ የቴአትር ፊስቲቫል የፊታችን አርብ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ተገለፀ፡፡ በመክፈቻው ዕለት የትያትር ተመልካችን ፈጥረዋል ተብለው ከሚወደሱ ዘመን ተሻጋሪ ትያትሮች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሰው “ኦቴሎ” ከ30 ዓመት በኋላዳ መድረክ እንደሚመለስ አዘጋጆቹ ጠቁመዋል፡፡ እስከ ህዳር 11 ለስምንት ቀናት በሚቆየው ፌስቲቫል፤ በመክፈቻው ዘመናዊ ትያትር ከተጀመረበት ከ1909 አንስቶ እስከ አሁን ድረስ የተሰሩና የተመረጡ በፌስቲቫሉ ከ20 በላይ ከቅንጭብ እስከ የሙሉ ጊዜ ትያትሮች በባህል ማዕከል በ5ኪሎና በ6 ኪሎ ይታያሉ ተብሏል፤ ቲያትሮቹ በጐዳና ላይ ይቀርባሉ፡፡
በተጨማሪም የተማሪዎች የቲያትር ውጤቶች፣ ድምጽ አልባ ቲያትሮች (ማይም ወይም ፓንቶ)፣ የትያትር የቤተሙከራ ውጤቶች፣ ለኮርስ መሟያነት የቀረቡና በለልማት ዘርፍ የሚመደቡ ቲያትሮች፣ በፌስቲቫሉ ላይ እንደሚቀርቡ ታውቋል፡፡
የቴያትር ትምህርት በዲፓርትመንት ደረጃ የሚሰጡ እንደ መቀሌ፣ ወሎ፣ አክሱምና ደሴ ያሉ የክልል ዩኒቨርሲቲዎች ያዘጋጇቸውን ቲያትሮችም ለተመልካች ይቀርባሉ፡፡
አላማችን ያለፈውን ዓመት ፌስቲቫል መድገም አይደለም ያሉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቲያትርና ጥበባት ትምህርት ክፍል ሐላፊ አቶ ተስፋዬ እሸቱ፤ ዘንድሮ በይዘትም፣ በአቀራረብም በተሻለ መልኩ ብዙ ነገሮችን ጨምረን ነው የመጣነው፤ በቀጣይ ዓመት ፌስቲቫሉን አለምአቀፍ ለማድረግ አቅደናል ብለዋል፡፡
የቃቄ ዋርዶ፣ ኦቴሎና እንግዳን ጨምሮ በርካታ ቴአትሮች በሚታዩበት ፌስቲቫል፤ በጠዋቱ ክፍለ ጊዜ በ5 ኪሎ ግቢ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች የሚቀርቡ ሲሆን ማንኛውም የቲያትር አፍቃሪ በሁሉም ፕሮግራሞች ላይ በነፃ መታደም እንደሚችል ተገልጿል፡፡
ከዓምናው ፌስቲቫል “ቲያትር ተመልካች የለውም” እየተባለ የሚወራው ሐሰት መሆኑን አረጋግጠናል ያሉት ሐላፊው፤ “እስኪ ኑ ቲያትር እንይ” በማለት መግለጫቸውን ቋጭተዋል፡፡
ፌስቲቫሉ የሚካሄድበት እያንዳንዱ ቀን በቴአትር ዘርፍ ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረከቱና ለወጣቱ አርአያ መሆን በሚችሉ 8 የቴአትር ጠቢባን የሚታወሱ ሲሆን አርቲስት አውላቸው ደጀኑ፣ እዩኤል ዮሐንስ፣ ፊሊፕ ካፕላን፣ መላኩ አሻግሬ፣ አስናቀች ወርቁ፣ ወጋየሁ ንጋቱ፣ ደበበ እሸቱና ደበበ ሰይፉ ቀናቱ በመስማቸው ይሰየማል ተብሏል፡፡

Read 1227 times