Saturday, 31 October 2015 09:23

ሁሉ ፈረስ ላይ ከወጣ ማን መንገድ ያሳያል?

Written by 
Rate this item
(16 votes)

አንዳንድ ዕውነተኛ ክስተቶች ሲቆዩ ተረት ይመስላሉ፡፡ የሚከተለው እንደዚያ ዓይነቱ ነው፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን፣ ከዓመታት በፊት፣ እዚሁ እኛ አገር የቀበሌና የከፍተኛ የሶስት ወር የሂሳብ ሪፖርት፣ ይሰማ ነበር ይባላል፡፡ በዚህ ስብሰባ ምክንያት የታሠሩ አንድ ሰው ለእሥር መዝጋቢው የነገሩት ነው፡፡ እንዲህ አሉ፤ “ሪፖርቱን ይሰማ ዘንድ የቀበሌው ነዋሪ ግዴታ አለበት፡፡”
በዚሁ መሰረት የዚያን ዕለት የቀበሌው ህዝብ ግልብጥ ብሎ ወደቀበሌው አዳራሽ መጥቷል፡፡
ሰብሳቢው -
“እንደለመደው የቀበሌያችንን የፋይናንስ ሪፖርት እናዳምጣለን” አሉ፡፡
ይሄኔ እኔ፤
“ከዚያ በፊት እኔ አንድ አስተያየት አለኝ” አልኩ፡፡
ዕድል ተሰጠኝ፡፡
(በዚያን ዘመን ገዢ የነበረው መንግሥት - “የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ” ነበር የሚባለው፡፡ የሽማግሌው አስተያየት ይህን ስም በተመለከተ ነበር)
“በተሰጠኝ ዕድል በመጠቀም የመንግሥታችን ስም “ጊዜያዊ” የሚለው ልክ አይደለም፡፡ ይሄን ሁሉ ዓመት አስተዳድሮን ዘላቂ የማይሆንበት ምክንያት አይታየኝም፡፡ ስለዚህ ከዛሬ ጀምሮ “ጊዜያዊ” የሚለውን እንሰርዝና ዘላቂ እናድርገው” አልኩ፡፡
ህዝቡ በሁለት ተከፍሎ ሙግት ገጠመ፡፡ የጠዋቱ ስብሰባ እስከ ከሰዓት ዘለቀ፡፡ ሰብሳቢው ተናደዱና፤
“ስብሰባው ለሌላ ቀን ተዛውሯል” አሉና በተኑት፡፡
ከዚያ እኔም እንደሌላው ሰው ወደ ቤቴ እየሄድኩ ሳለሁ
“ትፈለጋለህ” ብለው ወደ እሥር ቤት አመጡኝ፡፡ ምን አጠፋሁ? ብል፤ “የፋይናንስ ስብሰባ አደናቅፈሃል!” አሉኝ… ካሉ በኋላ ወደ መዝጋቢው ፍርጥም ብለው ዞረው፤ “ይሄውልህ ወዳጄ፤ ይሄ መንግሥት ለምን ዕድሜ ጨመርክልኝ ብሎ አሠረኝ፡፡ ባጭሩ መቀጨት ነው እንዴ የሚፈልገው?” አሉ፡፡
***
ብዙ መንግሥታት የሚበጃቸውን አያውቁም፡፡ የሚጠቅማቸውን ሲመከሩ፣ በግድ ምክሩ ከራሴ ወገን ካልመጣ በሚል ይመስላል፤ አሻፈረኝ፣ አልሰማም ይላሉ፡፡ አንድ የትምህርት ሚኒስቴር ሹም እንዳሉት ነው፡፡ አንድ ጊዜ አንድ ወጣት የዩኒቨርሲቲ ምሩቅ ኃላፊው አልሰማ እያሉ ሲያስቸግሩት፤
“ይሆናል ሲሉዎት አይሆንም
አይሆንም ሲሉዎት ይሆናል፤
የርሶ ነገር ምን ይሻላል?”
ሲል ፃፈላቸው፡፡
ኃላፊው የመለሱለት፤
“ተጣጥሮ መሾም ነው!” የሚል ነበር፡፡
ይህ ዕውነታ ዛሬም የሚከሰት ነው፡፡ ልዩነቱ ዛሬ በግልፅ ሹሞቹ እንቢታቸውን አለመግለፃቸው ነው፡፡ አለመሰማማት ክፉ አባዜ ነው፡፡
የምክሩን ምንነት እንጂ የመካሪውን ማንነት ብቻ ማየት ከጥንት ጀምሮ ጐጂ ባህል ነው፡፡ ምክሩን አውቆና መርምሮ፣ ጠቃሚውንና ጐጂውን መለየትም ያባት ነው፡፡ ሁሉም ነገር ሂደት መሆኑን አለመርሳት ብልህነት ነው፡፡
አዲስ ሃሳብን እንደጠላት ማየት የዋህነት ነው፡፡ ሁሌ በአንድ ሀዲድ ላይ መሄድ ለውጥን ያርቃል እንጂ አያቀርብም፡፡ ፕሮጄክቶች ሥራ ከመጀመራቸው በፊት፣ ዕቅዶች ከመተግበራቸው በፊት፣ የሚቀርቡ የሥጋት አስተያየቶችን ለእንቅፋትነት የተሰነዘሩ አድርጐ ማየት በተለይ ከተለመደ፤ አደገኛ ነው፡፡ የሚያመላክተውም የአሉታዊነት ኃይልን (Negative Energy) ነው፡፡
አለመቀበልን “እኔ ያልኩት ብቻ ነው ልክ” ማለትን፣ አልፎ ተርፎም ፍርደ ገምድልነትን ነው የሚያመጣው፡፡ ያ ደሞ ፀረ - ዲሞክራሲ ነው፡፡ ሥራዎች ከተሠሩ በኋላ “ይፍረሱ”፣ “እንደገና ይስተካከሉ”፣ “መጀመሪያም ፕላኑ ችግር ነበረበት” ማለት ጊዜን፣ የሰው ኃይልን፣ ገንዘብና ንብረትን ማባከን መሆኑን መቼም ማንም ጅል አይስተውም፡፡  ብዙ ተብሏል፡፡ አልተሰማም፡፡ ሆኖም መንግሥት ባይሰማስ እኛ ምን እናድርግ? ብሎ ማሰብም ደግ ነው፡፡ ሁሌ መንግሥትን በመጠበቅ ህዝብ ተባብሮ መሥራት የሚችለውን ተሳትፏዊ ተግባር አለመፈፀምም ደካማነት ነው፡፡ ለምሳሌ በ1966 ዓ.ም ድርቅ ወቅት የዩኒቨርሲቲ መምህራንና ተማሪዎች፤ ወሎና ትግራይ ድረስ በራሳቸው ወጪ ሄደው ህዝቡን ለመታደግ ጥረዋል፡፡ ዛሬም እንደዚያ ማሰብ ጠቃሚ ነው፡፡ ህዝብ በረሃብ ሲጐዳ እጅን አጣምሮ መቀመጥ፤ “ያንተ ቤት ሲንኳኳ ይሰማል እኔ ቤት” የሚለውን መዘንጋት ነው፡፡ ችግሩ ያገር ነውና አገር መረባረብ አለበት፡፡ ህዝብ የሚቻለውን ማድረግ አለበት፡፡ አለበለዚያ “ሁሉ ፈረስ ላይ ከወጣ ማን መንገድ ያሳያል” ይሆናል፡፡

Read 5811 times