Saturday, 17 October 2015 09:42

ኢህአዴግ፤“አዝማሪ ሚዲያ አልፈልግም” ያለው ከልቡ ነው?

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(13 votes)

• እንኳንስ ለ“አድርባይ ሚዲያ” ለራሱም አልተመለሰም!
• ዋናው ችግራችን የኮሙኒኬሽን ነው ተባለ (መግባባት ድሮ ቀረ!)
• “ልማታዊ ጋዜጠኝነት” እና “የመንግሥት ልሳንነት” ለየቅል ናቸው!

   ከጥቂት ሳምንታት በፊት እዚሁ አዲስ አድማስ ጋዜጣ፣ የጤና አምድ ላይ ያነበብኩት ነገር በእጅጉ አስደንጋጭ ነው፡፡ ብዙዎቹ የመድሃኒት ቤት ባለሙያዎች፣ የሃኪም የእጅ ፅሁፍ አንብበው እንደማይረዱ የጋዜጣው ፅሁፍ ያስነብባል (ቻይንኛ ሆነባቸው እንዴ?!) ምን ማለት መሰላችሁ? በአሁኑ ሰዓት ሃኪምና የፋርማሲ ባለሙያ እየተግባቡ አይደለም ማለት ነው፡፡ (“ሌሎቻችንስ ስንግባባ አይደል” እንዳትሉኝ?!) የዚህኛው ክፋቱ ጊዜ የሚሰጥ አይደለም… የሰው ህይወት ነው፡፡
 አንድ ሃኪም እንደተናገሩት፤ መድሃኒቶች በየፋርማሲው ሲጠየቅ፣ የለም የሚባለው… እውነት ጠፍቶ ሳይሆን፤የፋርማሲ ባለሙያዎቹ የሃኪሞቹን የእጅ ፅሁፍ አንብበው ለመረዳት ስለሚያዳግታቸው ነው፡፡ እንደኔ እንደኔ፤ሃኪም የፃፈው ትዕዛዝ አልገባ ሲላቸው… “መድሃኒቱ የለም” የሚሉ ባለሙያዎች ሺ ጊዜ ይሻሉናል፡፡ የተፃፈው ሳይገባቸው በአጉል ይሉኝታ ወይም ድፍረት (በመኃይምነት በሉት!) የመሰላቸውን ብልቃጥ ወይም እሽግ ክኒና አንስተው የሚሰጡን እኮ ፈርደውብናል (ከአሸባሪዎች አይለዩም!)
ሰሞኑን የካቲት 12 ሆስፒታል፣ልዩ የህክምና ክትትል በማድረግ ላይ ላለች የእህቴ ልጅ (ጨቅላ ህፃን ናት) ሃኪም መድሃኒት ያዝላትና አባቴ ለመግዛት ፋርማሲ ይሄዳል፡፡ ባለሙያው ትእዛዙን አንብቦ ወይም ያነበበ መስሎ አንድ መድሃኒት ለአባቴ አንስቶ ይሰጠዋል፡፡ አባቴ መድሃኒቱን ይዞ የካቲት 12 መጣና ላዘዘው ሃኪም ሰጠው፡፡ ሃኪሙ መድሃኒቱን እንዳየ  ነው በንዴት ጨሶ አባቴ ወዲያውኑ እንዲመልሰው ያዘዘው፡፡
ፋርማሲስቱ “የተሳሳተ መድሃኒት ነበር የላከው ÷እናም አባቴ ወደ ፋርማሲው ተመልሶ በመሄድ ሃኪሙ፤መድሃኒቱ የተሳሳተ ነው እንዳለው፤ ለፋርማሲ ባለሙያው ይነግረዋል፡፡ ባለሙያው ሁለተኛ የግምት ሙከራ ያደረገ መሰለኝ፡፡ ደንገጥም ሳይል መድሃኒቱን ለአባቴ ለወጠለት፡፡ (መሳሳት በእኔ አልተጀመረ ብሎ ይሆን?)
ሃኪሙ ሁለተኛውን መድሃኒት ሲያይ፤ “መጀመርያውኑ አንብቦ አይሰጥህም ነበር!” አለ፤ ከቀድሞ ንዴቱ በረድ ብሎ፡፡ እስቲ አስቡት… መድሃኒቱ በቀጥታ (ሃኪሙ ሳያየው!) ለጨቅላ ህፃኗ ተሰጥቶ ቢሆን ኖሮ ------- ሊከሰት የሚችለውን የከፋ አደጋ! (አያድርስ እኮ ነው!)
እኔ የምለው… የሃኪሞች የእጅ ፅሁፍ ይሄን ያህል ሮኬት ሳይንስ ሆኖ ነው እንዴ ፋርማሲስቶች ማንበብ ያዳገታቸው? (ትምህርቱን ወስደዋል ብዬ እኮ!)
ለማንኛውም ግን ፈጣን መፍትሄ የሚፈልግ አደገኛ ችግራችን መሆኑን እንዳትዘነጉብኝ፡፡ ወዳጆቼ… ይሄ እኮ 5 ዓመት እንደታገስነው የታክሲ ወረፋ፤(ቢያንስ ከከንቲባ ምስጋናና ይቅርታ አግኝተንበታል!) ወይም የመብራትና የውሃ መጥፋት አሊያም የኢንተርኔት መንቀራፈፍ--- የምንታገሰው አይነት አይደለም፡፡ የተሳሳተ መድሃኒት ለህልፈት አሊያም ለከፋ የጤና እክል ሊዳርገን ይችላል፡፡ (እስካሁንም የደረሰውን ጉዳት የየሰው ጓዳ ችሎት ነው!)
 በነገራችን ላይ ------ በአገራችን ከ5 ህሙማን አንዱ መድሃኒቶችን በስህተት እንደሚወስድ በጋዜጣው ላይ የተጠቀሰ አንድ ጥናት ጠቁሟል፡፡ (“አደጋ አለው” ይሏል ይሄ ነው!)
እናንተዬ… እንደው አትግባቡ ሲለን ነው እንጂ፣ ቻይና እንኳን ቻይንኛ ከማይናገሩ የሃበሻ ልጆች ጋር (ያውም ሥራ ከማይወዱ!) እንደ ምንም ተግባብታ፣የከተማ ቀላል የኤሌክትሪክ ባቡር ፕሮጀክትን በፍጥነት ሰርታ አስረክባን የለ!
አያችሁልኝ ግን ---- የኮሙኒኬሽን ችግር የሚፈጥረውን አደጋ! (ሃኪምና ፋርማሲስት መግባባት ባለመቻላቸው ህይወት ይጠፋል!) በፖለቲካውም ተመሳሳይ ነው፡፡ ገዢው ፓርቲና ተቃዋሚዎች መግባባት አቅቷቸው በሚከሰት የፖለቲካ ቀውስ፣ ዜጐች ለሞት፣ለእስርና ስደት ይዳረጋሉ (የኮሙኒኬሽን ችግር!)
እዚህ ጋ ግና አንድ ብዥታ አጥርተን ማለፍ አለብን፡፡ ይሄውላችሁ -- በአንድ ቋንቋ ስላወራንና የኮሙኒኬሽን ሚኒስቴር ስላለን ብቻ ተግባብተናል ማለት አይደለም፡፡ ልብ በሉልኝ! ይሄ ከአገራዊ መግባባት (Consensus) ጋር ፈፅሞ አይገናኝም፡፡ እናላችሁ ----- ገዢ ፓርቲና ተቃዋሚ… አስተማሪና ተማሪ… ሃኪምና ፋርማሲስት ---- ነጋዴና ሸማቹ… ገዢው መንግስትና ተገዢው ህዝብ… ተመራማሪውና ገበሬው… ደራሲውና ተደራሲው… ከያኒውና የኪነጥበብ አፍቃሪው… አገልግሎት ሰጪውና ደንበኛው… እውን እየተግባቡ እንደሆኑ እስቲ እንፈትሽ? (በርግጠኝነት የኮሙኒኬሽን ችግር በሽ ነው!)
እስቲ አንድ ለኮሙኒኬሽን ችግር ቀረብ የሚል “አገር በቀል” የወዳጄን ገጠመኝ ላጋራችሁ፡፡ መርካቶ ነው አሉ፡፡ አንድ የነጋዴ ሱቅ ግድግዳ ላይ “ደንበኛ ንጉስ ነው!” የሚል ምርጥ ጥቅስ (መርህ ቢባል ይቀላል!) ተለጥፏል፡፡ አንዱ ደንበኛ፤ እቃ ሊገዛ ወደ ሱቁ ሲገባ አይኑ በአጋጣሚ ጥቅሱ ላይ ያርፋል፡፡ በብዙ ሱቆች ያላየውን ጥቅስ በዚህ ሱቅ በማየቱ ደንበኛው ተደስቶ፤ “ያቺ ነገር አሪፍ ናት!” ይለዋል ለነጋዴው፡፡ ነጋዴው ምን አለ መሰላችሁ? “ሰው እኮ የእውነት ይመስለዋል!” (እንዴት እየተግባባን እንዳልሆነ አያችሁልኝ!) የኮሙኒኬሽን ችግራችንን ማየት እንቀጥል------ (ኮሙኒኬሽን መ/ቤት ቅር እንዳይለው!)
በመንግስት ኮሙኒኬሽን ፅ/ቤት በሚመሩት ወይም በሚተዳደሩት የመንግስት ሚዲያዎችና የግል ሚዲያዎች ላይ የተካሄደ አንድ ጥናት፣ ከሁለት ሳምንት በፊት ይፋ ተደርጐ ነበር፡፡ (ከEBC መርዶ ነጋሪ ዶክመንታሪ ተገላገለን!!!) ለነገሩ … ጥናቱ ሁለቱንም ሚዲያዎች አፈር ድሜ የሚያስገባ እንጂ የሚያሞግስ አይደለም፡፡ በተለይ የመንግስት ሚዲያውንማ----ቀላል ያብጠለጥለዋል መሰላችሁ! (ልማታዊ ጋዜጠኝነት አልተሳካለትም!)
የሆነስ ሆነና ጥናቱ ምን ይላል? በመጀመሪያ ደረጃ ሁለቱም ሚዲያዎች (ልማታዊውም ሲቪሉም!) የአመለካከት… የክህሎትና የአደረጃጀት ችግሮች እንዳሉባቸው ተጠቁሟል፡፡ (“የአመለካከት”… ሲባል እንዴት?) ጥናቱ እንደሚለው፤ በመንግስት ሚዲያ አድርባይነትና የመንግሥት ልሳንነት ጐልቶ የሚታይ ሲሆን የህዝብ ወገንተኝነት ችግር እንዳለበትም ተጠቁሟል፡፡ (አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች -----የህዝብ ወገንተኝነትን አይጠቁሙም?!) ትችቱ ገና አላበቃም፡፡ የህዝብ ብሶት የመቀበል አቅሙ ደካማ እንደሆነና የመልካም አስተዳደር ችግርን ፈትሾ በማቅረብ ረገድ የአቅም ውስንነት እንዳለበትም ጥናቱ ገልጿል፡፡ (ኢህአዴግ “አዝማሪ ሚዲያ አልፈልግም” ያለው ከምሩ ነው?)
 ለመንግስት ሚዲያዎች፣ በተለይ ለEBC ጥናቱ ዱብእዳ ሊሆንበት እንደሚችል አትጠራጠሩ፡፡ (በዶክመንታሪ የግሉን ሚዲያ ሲያሳጣ ነዋ የከረመው!)
ለካስ እስከዛሬ ዶክትመንታሪ የሚሰራው ---- ካሜራና ስቱዲዮ ስላለው ብቻ ነው (ሌላማ ምን አቅም አለው?!) በእርግጥ EBC ልማታዊ ጋዜጠኝነትን ሲያራምድ እንደከረመ ሽንጡን ገትሮ ሊከራከር ይችላል፡፡ ግን አያዋጣውም፡፡ ልማታዊ ጋዜጠኝነትና የመንግስት “ልሳንነት” ለየቅል ናቸው፡፡ (አድርባይነትስ?) ለነገሩ የጥናቱ ውጤት ቢያስደነግጠውም (በተለይ የልማት አጋር ነኝ ለሚል ሚዲያ!) “የጠራ መስመር” ለመያዝ በእጅጉ ይጠቅመዋል፡፡ (ኢህአዴግ እንደሆነ እንኳንስ ለEBC ለራሱም አልተመለሰም!) በመቀሌው የኢህአዴግ 10ኛ ጉባኤ መዝጊያ ላይ በራሱ ላይ ያልሰነዘረው ትችት አለ እንዴ?  ወደ ነጥባችን ስንመለስ፣በጥናቱ ትችት የወረደባቸው የመንግስት ሚዲያዎች በሙሉ በመንግስት ኮሙኒኬሽን ፅ/ቤት ሥር የነበሩ ናቸው፡፡ እናላችሁ… መ/ቤቱ ቢያንስ እንዴት በሥሩ ለሚተዳደሩ ሚዲያዎች ተገቢ አቅጣጫና አመራር መስጠት አቃተው? (እዚያም የኮሙኒኬሽን ችግር አለ ማለት ነው!)
በነገራችን ላይ መንግስት በትክክል የሚፈልገውን ቢናገር እኮ ብዙ ነገሮች ይቃለላሉ፡፡ (የኮሙኒኬሽን ጋፕም አይፈጥርም!) ከምሁሩ… ከነጋዴው.. ከመንግስት ሰራተኛው… ከሲቪል ማህበረሰቡ… ከዲሞክራቲክ ተቋማት… ከተቃዋሚ ፓርቲዎች… በአጠቃላይ ከዜጐች…ወዘተ የሚጠብቀው ወይም የሚሻው ምንድን ነው? (መቼም 95 ሚሊዮናችሁም ልማታዊ መሆን አለባችሁ… አይለንም!)
እናላችሁ------ለምሳሌ ላለፉት በርካታ ዓመታት ስሙ አንዴም በበጐ ተነስቶ ከማያውቀው የፈረደበት የግል ሚዲያ፣ መንግስት ምንድን ነው የሚፈልገው? (“ታማኝ ሚዲያ” የሚባል ነገር አለ እንዴ?) በነገራችን ላይ ዛሬ ይሄን ሁሉ የምንጠያየቀው ለሽሙጥ ወይም ለሽርደዳ እንዳይመስላችሁ፡፡ የኮሙኒኬሽን ችግራችን ለማስወገድ ብቻ ነው፡፡ አያችሁ---ሳንግባባ ኪራይ ሰብሳቢነትን በሉት… ብልሹ አስተዳደርን… ወይም አድርባይነትን ፈጽሞ ልንዋጋ አንችልም፡፡  (ስኬታማ ኮሙኒኬሽን መቅደም አለበት!)
እናም ሁሉም በቀጥተኛና… በቀላል ቋንቋ ፍላጐቱን፣ ዓላማውን፣ ርእዩን፣ ምኞቱን፣ ህልሙን፣ ቅዠቱን (ካለው ማለቴ ነው!) ፍርሃቱን፣ ድፍረቱን፣ አቅሙን፣ ብቃቱን፣ ጉድለቱን፣ ጥንካሬውን፣ ድክመቱን፣ (ስስ ብልቱን እንደማለት!) በግልጽ አውጥቶ መናገር ይኖርበታል (አገራዊ መግባባት ከዚህ ይጀምራል!!)
በመጨረሻ ቅድም ሃሳቤን ላለማናጠብ ስል…የዘለልኩትን የግል ሚዲያዎችን የተመለከተ   የጥናት ውጤት ልጥቀስና ወጌን ልጠቅልል፡፡ የግል ሚዲያን ጥናቱ በሁለት ይከፍላቸዋል - ለዘብተኝነትና ፅንፈኝነት የሚታይባቸው በሚል፡፡ (አሁን እኔ እንደ ጋዜጠኛ ከየትኛው እመደብ ይሆን?) ለማንኛውም ግን ለዘብተኛ የሚላቸው… ሚዛናዊ የመሆን ሙከራ የሚያደርጉትን ነው (ገና ሙከራ እኮ ነው?!) ፅንፈኛ የሚላቸው ደግሞ፤ ግባቸው መንግስትን መለወጥ የሆነ፣ ለፖለቲካዊ ተልእኮ ማስፈፀሚያነት የተመሰረቱ ------ እንደሆኑ ይገልፃል፡፡ (የምናወራው ስለ አማፂያን ነው ስለ ሚዲያ?)
(በጥናቱ አካሄድም ላይ የኮሙኒኬሽን ችግር አለ!)

Read 4615 times