Saturday, 17 October 2015 08:51

ኖር በይው ልብሱን፣ ሰውዬውስ የቅድሙ ነው

Written by 
Rate this item
(18 votes)

ኖር በዪ የኹጅር የጋኸምን ምስ) - የቤተ ጉራጌ ተረት

ከዕለታት አንድ ቀን ሁለት ጓደኛሞች፤ ገንዘብ በጣም ይቸግራቸውና በምን መንገድ ራታቸውን እንደሚበሉ ያስባሉ፡፡
አንደኛው -  ከሱቅ ገንዘብ እንበደርና የፈለግነውን ምግብ እንብላ
ሁለተኛው - ለባለሱቁ ባለፈው ያለብንን ዕዳ ስላልከፈልነው ምርር ብሎታል፡፡ “ያንን
ካልመለሳችሁልኝ ሁለተኛ ዐይናችሁን አላይም” ብሎኛል፡፡
አንደኛው -  እሺ ሌላ ዘዴ አንተ አምጣ
ሁለተኛው - አጐቴን ሄጄ ላስቸግረዋ?
አንደኛው -  የእራት ስጠን ልትለው ነው? የሆነ ሰበብ ያስፈልግሃልኮ?
ሁለተኛው - የቤት ኪራይ አነሰኝ ሙላልኝ ልበለው?
አንደኛው - አሞሃል? ነገ የሚጣራ ነገር ዛሬ ዋሽተህ የወደፊት እንጀራ ገመድህን በትንሽ ነገር ልትበጥስ ነው?
ሁለተኛው - ታዲያ ምን ማድረግ ይሻለናል?
አንደኛው - አንድ ዘዴ ታየኝ
ሁለተኛው - ምን?
አንደኛው - እዚህ ሠፈር አንድ ድንኳን ተጥሏል፡፡ የሆነ ሰውዬ ሞቷል፡፡ ለምን ራት ሰዓት
አካባቢ እዛ ሄደን፤ መቼም እራት ማቅረባቸው አይቀርምና፤ ቁጭ ብለን   
አንጠብቅም?
ሁለተኛው - አሁን አሪፍ ዘዴ ዘየድክ
አንደኛው - በቃ እዛ እንሄዳለን!
ተያይዘው ወደ ልቅሶው ድንኳን ሄዱ፡፡ ገቡ፡፡
ጠበቁ፡፡ ጠበቁ፡፡ ጠበቁ፡፡ ራት አልመጣም፡፡
12 ሰዓት ተኩል፡፡ አንድ ሰዓት፡፡ ሁለት ሰዓት፡፡ ራት፤ የለም፡፡ ግራ ገባቸው፡፡
አንደኛው - ራት ይቀርባል? አይቀርብም? ለምን አንጠይቅም?
ሁለተኛው - ይሻላል፡፡ ግን ማንን እንጠይቅ?
አንደኛው - እዛ ጋ ወዲህ ወዲያ የሚሉትን ሰውዬ እንጠይቃቸው፡፡
ሁለተኛው - እሺ
አንደኛው ፤ ወደተባሉት ሰው ጠጋ ይልና፤
“እንዴት ነው፣ ራት አይቀርብም እንዴ?”
ሰውዬው - አይ ልጆቼ! ሟቹ ሰውዬ ራሱ የሞተው ርቦት ነው!  
***
ድህነታችንን መጋራት እንጂ መታገል ካቃተን መንገዳችን በእንቅፋት የተሞላ እንደሚሆን ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ከሥሩ ለመንቀል ሥር-ነቀል እርምጃ ያስፈልጋል፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ሥር - ነቀል አስተሳሰብ ማዳበር ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ የምሁራንና ባለሙያዎች አስተሳሰብ መዳበርና የፈቃደ ልቦናቸው መኖር ወሳኝ ነው! በሀገራችን ለምሁራንና ለባለሙያዎች የምንሰጠው ትኩረትና ክብር አናሳ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ድህነትን ለመቀነስ መወሰድ ካለባቸው ዓይነተኛ እርምጃዎች አንዱ ይኸው ለምሁርና ለባለሙያ የምንሰጠው ትኩረት ነው! ምሁራኑም ለሀገራቸው የሚሰጡት ትኩረት ከጥቅም የዘለለ መሆን ይኖርበታል፡፡ የጊዜው ነገር ሆኖ ነው እንጂ ይሄን አይስቱትም! ሹማምንት የህዝብ ፍቅር ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ከህዝብ ጋር መኖር፣ ህዝብ መሀል መኖር አለባቸው፡-
“ዓለም አደገኛ ናት ጠላቶችም በየቦታው አሉ፡፡ ሁሉሰው ራሱን መጠበቅ አለበት፡፡ ምሽግ የመጨረሻ መጠበቂያ ቦታ ይመስለናል፡፡ ከሰው ተነጥሎ መቀመጥ ግን ለበለጠ አደጋ ያጋልጣል፡፡ ከአስፈላጊ መረጃ ያናጥባል፡፡ በግልፅ እንድንታይና ቀላል ኢላማ ያደርገናል፡፡ ስለዚህ ከህዝብ መካከል ሆኖ፣ ወዳጅ እየፈጠሩ መዋሃዱ ይመረጣል፡፡ ከጠላቶች ጥቃት ጋሻ የሚሆንህ ጀማው ነው” ይላል ሮበርት ግሪን፡፡ በተግባር የመፈተኛው ሰዓት አሁን ነው፡፡ ለራስ ጥቅም ከማሰብ ለሀገር ማሰብ ልዩነቱ የሚረጋገጠው ልባችን፣ አፋችንና ተግባራችን አንድ ሲሆኑ ነው፡፡ መለኪያው ከህዝብ ጋር መሆን ነው፡፡ እንደህዝብ ማሰብ ነው፡፡ “ሸክላ ሲሰበር ገል ይሆናል፡፡ መኳንንትም ሲሻሩ ህዝብ ናቸው” የሚለውን ማስተዋል ዋና ነገር ነው፡፡ አዲስ የተሾሙ ሰዎቻችንን ልቦና ህዝባዊነት አይንሳቸው፡፡ ሀገራዊነት አይንሳቸው!
የተሻለ፣ ከትላንት የተለየ ነገር እንዲኖር እንመኝ፡፡ የምናውቃቸው ሰዎች የምናውቀውን ነገር የሚደግሙልን ከሆነ መቀየራቸው ትርጉም ያጣል! አብረን እናስብ! ምሁራንን እናማክር! ለሀገር አሳቢዎች እኛ ብቻ ስላልሆንን ከማህበረሰቡ የረባ አዕምሮና አብራሄ ህሊና (Enlightenment) ያላቸውን ሰዎች የመቀላቀል የተባና ሩህሩህ ልቦና ይኑረን! ይህን ተሐድሶ ያልተላበሱ ሰዎች ይዘን ብዙ አንጓዝም! ይህ ካልሆነ “ኖር በይው ልብሱን፣ ሰውዬውስ የቅድሙ ነው” የሚለው ተረት ዕውን ይሆናልና እንጠንቀቅ!  

Read 5598 times