Saturday, 10 October 2015 16:34

“የቅባት እህሎች” እና “የዳያስፖራ” ሚኒስቴሮች ያስፈልጉናል!!

Written by 
Rate this item
(8 votes)

ለፓርላማ እንቅልፍ መድሃኒቱ፣ ብርቱ “ተቃዋሚ ፓርቲ; ነው!
            ሙሴቬኒም ፓርላማ ውስጥ እንቅልፋቸውን ሲለጥጡ ተይዘዋል!
            አዲስ መንግስት ተቋቋመ ወይስ የሚኒስቴር መ/ቤቶች ተፐወዙ?
   ሰሞኑን ከፓርላማው መከፈትና አዲስ መንግስት መቋቋም ጋር ተያይዞ ሲናፈስ የሰነበተው ወሬ  የአንድ ም/ቤት አባል ማንቀላፋት (ሸለብታ!) ነው፡፡ እኔ የምለው… በፓርላማ ወይም በስብሰባ ላይ መተኛት ያን ያህል ብርቃችን ነው እንዴ? (ደርሰን ንቁ ስንመስል ገርሞኝ እኮ ነው?!) የአገራቸው የፓርላማ አባላት በጅምላ እያንቀላፉ ያስቸገሯቸው የምዕራብ አፍሪካ ጋዜጠኞች ምን አሉ መሰላችሁ? “በቲቪ የቀጥታ ስርጭት ለህዝብ በሚደርስ የፓርላማ ጉባኤ ላይ ያንቀላፉ ፖለቲከኞች፤በየግል ቢሮአቸው ሲሆኑ ምን ሊያደርጉ ነው?!” (እዚያማ አልጋ ከእነፍራሹ ይኖራቸዋል!!)
ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ--- ከጥቂት ዓመታት በፊት የሰማኋት አንዲት የፓርላማ ቀልድ ትዝ አለችኝ፡- አንድ የፓርላማ አባል በጉባኤ ላይ፣ ትኩስ ቡና ሲቀርብላቸው ምን አሉ መሰላችሁ? “አይ እኔ አልጠጣም፤እንቅልፍ ይረብሸኛል!” (የፓርላማ እንቅልፍ ለምደዋል ማለት ነው!) ዝም ብዬ ሳስበው---የሰሞኑ የፓርላማ “ማንቀላፋት” ከሌላው ጊዜ ለየት ሳይል  እንደማይቀር ገመትኩ፡፡ እርግጠኛ መሆን ቢያስቸግርም እስቲ የሚለይበትን ጥቂት መላ ምቶች ለማስቀመጥ እንሞክር፡፡  (ከማማት መላ መምታት ይሻላል!)
ምናልባት… የፓርላማው አባል ማሸለብ ትኩረት የተሰጣቸው አዲስ መንግስት በሚመሰረትበት ታሪካዊ ወቅት ላይ በመሆኑ ይሆን? ወይስ 2ኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን  ዕቅድ ይፋ በተደረገበት ማግስት ስለሆነ ይሆን? ወይስ ደግሞ የአዲስ አበባ ቀላል የኤሌክትሪክ ባቡር አገልግሎት መስጠት በጀመረበት ሰሞን በመሆኑ ይሆን? ያለዚያ እኮ የአንድ የምክር ቤት አባል ድንገት በእንቅልፍ መወሰድ እንደ ጉድ አይወራም ነበር፡፡ በተለይ እኮ ማህበራዊ ሚዲያው ቀላል ቀወጠው መሰላችሁ!! ይታያችሁ----ከ500 በላይ ከሚሆኑ የምክር ቤቱ አባላት ውስጥ አሸለቡ ወይም አንቀላፉ ተብለው ምስላቸው የተለቀቀው እኮ የአንድ ም/ቤት አባል ብቻ ነው (ከደከማቸው ደሞስ ቢተኙ!?)
አንዳንድ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም ጠበኞች ምን ቢሉ ጥሩ ነው? “ተቀምጠው ምንም ከማይፈይዱ አባላት የተኙት ይሻላሉ!” (አሽሙር ሳይሆን አይቀርም!) ወደ ቁም ነገሩ ስንመጣ ግን ወደፊትም ተመሳሳይ የማንቀላፋት ወይም የማፋሸግ ወይም የድብርት ስሜት በፓርላማ አባላት ዘንድ እንዳይፈጠር መከላከያ እርምጃዎች መውሰድ የግድ ይላል፡፡ (ልብ አድርጉልኝ!! እንቅልፍ በግለ-ሂስ አይሻሻልም!) እናላችሁ ---- ዛሬ አንድ ሰው ብቻ ነው የደበተው ተብሎ ችላ ከተባለ፣ ነገ በተረጋጋ ስብሰባ በሉት በተጋጋለ ክርክር ውስጥ እንቅልፋቸውን የሚለጥጡ የፓርላማ አባላት ቁጥር መጨመሩ የማይቀር ነው፡፡
መፍትሄው ታዲያ ምንድን ነው?… ቀላልና ብዙ ወጪ የማይጠይቅ ነው፡፡ ምን መሰላችሁ? አላስተኛ የሚሉ ብርቱ ተቃዋሚዎች፣ አልፎ አልፎ ቀልድና ተረብ እንዲሁም ትኩስ ቡና ናቸው፡፡ (ፓርላማ ውስጥ ቡና ቢፈላ----- ችግር አለው?) የሆኖ ሆኖ እኒህ በሌሉበት ሁሌም  ቢሆን ፓርላማ ውስጥ “ማሸለብ” የሚጠበቅ ነው፡፡ (ስጋትና ጉጉት የለማ!)
ፓርላማ ውስጥ የማንቀላፋት ችግር ያለው በእኛ አገር ብቻ እንዳይመስላችሁ፡፡ በሌሎች የዓለም አገራትም የተለመደ ነው፡፡ ዓምና በኡጋንዳ ፓርላማ ምን እንደተከሰተ ታውቃላችሁ? ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ንግግር ሲያደርጉ፣የ74 ዓመቱ ሁለተኛ ምክትል ጠ/ሚኒስትር ሞስስ አሊ፤ ፊታቸውን በጥቁር መነጽር ጋርደው እንቅልፋቸውን ሲለጥጡ፣ ጋዜጠኞች በካሜራ ቀርፀው ጉድ አድርገዋቸው ነበር፡፡ ከዚያ 4 ዓመት ቀደም ብሎ ደግሞ በዚያው ፓርላማ በርካታ የተኙ ሚኒስትሮችንና የምክር ቤት አባላትን በካሜራው ያስቀረ አንድ የአገሪቱ ጋዜጣ፣ በፊት ገፁ ላይ ደርድሯቸው፣  “Sleeping Nation” (“የምታንቀላፋ አገር” እንደማለት!) በሚል ርዕስ አወጣቸው፡፡ (ተራ በተራ መተኛት እኮ የአባት ነው!)
ሙሴቪኒ እ.ኤ.አ በ1986 የፕሬዚዳንትነት ሥልጣን ሲይዙ፣ከመጀመሪያዎቹ ሚኒስትሮች አንዱ በመሆን ያገለገሉት ፕሮፌሰር ኤድዋርድ ካኮንጌ በወቅቱ ስለነበረው ፓርላማ ሲያስታውሱ፤ “እኔ በሙሴቪኒ መንግስት ውስጥ ሳገለግል ነገሮች አጓጊና በስሜት የሚያጥለቀልቁ ስለነበሩ፣ ማንም በፓርላማ ውስጥ የሚተኛበት ምክንያት አልነበረውም” ብለዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ምን ተፈጠረ? “አሁን ያለው ሁኔታ በፓርላማ ውስጥ አጓጊ ነገር አለመኖሩን በግልጽ አመላካች ነው” ሲሉ ፕሮፌሰሩ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡ (የእኛስ የእንቅልፍ ሰበብ?)
አንዳንዴ ደግሞ የፓርላማ አባላት ብቻ ሳይሆኑ ዋናዎቹም ሊያንቀላፉ እንደሚችሉ ጠርጥሩ፡፡ በኡጋንዳ እንዲህ አጋጥሟል፡፡ ራሳቸው ፕሬዚዳንት ሙሴቪኒ፤ፓርላማ ውስጥ በበጀት ጉዳይ ላይ የሚደረገውን ንግግር የሚሰሙ መስለው እንቅልፋቸውን ሲለጥጡ፣ በካሜራ ተቀርጸው በአንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ተሰራጭቶ ነበር፡፡ (እዚያስ ጋ አልደረስንም!) ወዲያው ታዲያ  የኡጋንዳ መንግስት ቃል አቀባይ ምን ብሎ ቢያስተባብል ጥሩ ነው? “ጥሞና ውስጥ ገብተው ሲያሰላስሉ እንጂ አልተኙም” ብሏል ከተፎው ቃል አቀባይ፡፡ ለነገሩ የኛዎቹም የማስተባበል ዕድል ቢያገኙ እኮ ማስተባበል አያቅታቸውም ነበር፡፡
በበርማ አንድ የፓርላማ አባል በስብሰባ ውስጥ ሲያንቀላፉ በካሜራ ተቀርፆ ምስላቸው በማህበራዊ ሚዲያ በመሰራጨቱ፣የአገሪቱ ጋዜጠኞች ላይ የነፃነት ገደብ ለማበጀት ሰበብ ሆኖ እንደነበር ተዘግቧል፡፡ ጋዜጠኞች እንደ ቀድሞ አዳራሽ ውስጥ ገብተው ሳይሆን ኮሪደር ላይ ሆነው የፓርላማውን ሂደት ከቴሌቪዥን ላይ እንዲከታተሉ ተወስኖባቸው ነበር፡፡ (ማንቀላፋታቸው ሳያንስ ነፃነት ማፈናቸው!?)
የህንድ ጎምቱ ፖለቲከኞችም በፓርላማ የሞቀ ክርክር በሚካሄድበት ወቅት በተደጋጋሚ ተኝተው ለካሜራ ተዳርገዋል፡፡ በቅርቡ በህንድ ፓርላማ ውስጥ በዋጋ ንረት ላይ የሞቀ ክርክር ሲደረግ የም/ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ራሁል ጋንዲ፤ እንቅልፋቸውን ሲለጥጡ በካሜራ ተቀርፀው ምስላቸው በማህበራዊ ሚዲያዎች በመሰራጨቱ፣ የተቃዋሚዎች መዘባበቻ ሆነው ነበር፡፡  
በነገራችን ላይ የየአገራቱን ተሞክሮ ያመጣነውን በፓርላማ ውስጥ መተኛትና ማንቀላፋት የተለመደና በመሆኑ ተገቢ ነው ለማለት አይደለም፡፡ ይልቁንም የኢህአዴግን ፈለግ በመከተል፣ የዓለም አገራትን ተሞክሮ ለመፈተሽና ልምዱን ለመቀመር ነው፡፡  
የማታ ማታ ግን መፍትሄው በእጃችን መሆኑን እንዳትዘነጉት፡፡ አላስተኛ የሚሉ ብርቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣በየመሃሉ ቀልድና ተረብ እንዲሁም ትኩስ ቡና ለፓርላማው መነቃቃትና እንቅልፍ አልባ መሆን ወሳኝ ናቸው፡፡ እንዲህ እንዳሁኑ ገዢው ፓርቲ ፓርላማውን መቶ በመቶ ሲሞላውስ? ቀናነቱ ካለ በየጊዜው የተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በእንግድነት መጋበዝ ይቻላል፡፡ (ያልተመረጡ ተቃዋሚዎች ፓርላማ ድርሽ እንዳይሉ የሚል ህግ እንደሆነ አልፀደቀም?!)
እናላችሁ----ዋናው ነገር ምን መሰላችሁ? ፓርላማው የተነቃቃና የተሟሟቀ (እንቅልፍና ድብርት አልባ!) ይሆን ዘንድ ከፀሐይ በታች የሚቻለውን ሁሉ ማድረግ ግድ ይለናል፡፡ ያለዚያ ግን በቀጥታ በሚተላለፍ የቴሌቪዥን ስርጭት የሚያንቀላፉ የም/ቤት አባላት ቁጥር እንደ ህንድ፣ በርማና ኡጋንዳ ማሻቀቡ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ (እንደ ኢኮኖሚያችን በሁለት ዲጂት እንዳይመነደግ ፍሩልኝ!)
አሁን ደግሞ እስቲ ወደ አዲሱ የመንግስት ምስረታ ጉዳይ ልውሰዳችሁ፡፡ አዲስ ስለተመሰረተው መንግስት ተቃዋሚዎች
ቢጠየቁ ምን እንደሚሉ መገመት አያቅተኝም፡፡ ኢህአዴግንና ተቃዋሚዎችን እኮ እኩል ነው የምናውቃቸው፡፡ እናም መልሳቸው፤ “ፌዝ ነው” የሚል ነው የሚሆነው፡፡ ተቃዋሚዎች፤#ፌዝ ነው” ማለታቸውን ጠቅሰን ኢህአዴግን መልሰን ብንጠይቀውስ? እሱ ደግሞ “ይሄ ለህዝብ ያላቸውን ንቀት ያሳያል; ይለን ነበር፡፡ እኛ ገዢዎቻችንን የምናውቀውን ያህል እነሱም ቢያውቁን፣ በቀላሉ እንግባባ ነበር፡፡ (አወይ አለመተዋወቅ!)
እኔ የምለው ---- እኔና እናንተስ ስለ አዲሱ መንግስት አቋማችን ምንድነው? እውነት አዲስ መንግስት ተቋቋመ ወይስ የአራዳ ልጆች እንደሚሉት፤“ለበዓሉ ድምቀት” ዓይነት ነገር ነው የሆነው? ኢህአዴግ ብዙ ሰዎች ከመቀያየር ይልቅ ብዙ መ/ቤቶች መቀያየር ሳይቀለው አልቀረም፡፡ (ሚኒስቴር መ/ቤቶች እንደጉድ ተፐውዘዋል!)
በነገራችን ላይ አንዳንድ መዋቅራዊ ማስተካከያ የተደረገባቸው የሚኒስቴር መ/ቤቶች ክፉኛ ተተችተዋል፡፡ (እቺ ተገኝታ ነው!) ሆኖም ልማቱን እስካላደናቀፈ ድረስ ማንም መተቸትም ሆነ መቃወም ህገመንግስቱ ያጐናፀፈው መብቱ ነው፡፡ ስለዚህ ይበረታታል፡፡ እንግዲህ የትችት ኢላማ ከሆኑት አዳዲስ የሚኒስቴር መ/ቤቶች መካከል በዋናነት የእንስሳትና የዓሳ ሃብት ልማት ሚ/ር፣ የነዳጅ፣ የማዕድንና የተፈጥሮ ጋዝ ሚ/ር፣ (በምኞት ---የተቋቋመ መ/ቤት ብለውታል!) ይልቅስ አንድ ሃሳብ ብልጭ አለለልኝ (ለምን የምኞት ሚኒስቴር አይቋቋምም?)
ወደ ዋናው ጉዳይ ስንገባ፣በእኔ በኩል የሚኒስቴር መ/ቤቶቹን ለመተቸት ከመጣደፍ ይልቅ ሃሳቡን ለማብላላት፤ለማንሸራሸር ቅድምያ ሰጥቻለሁ፡፡ (ባይሆን “የሃሳብ ማንሸራሸሪያ ሚኒስቴር” እንዲቋቋም ሃሳብ ማቅረብ ይሻላል!) እናላችሁ…በሚኒስቴር ደረጃ መቋቋም ሲገባቸው ተዘንግተው ወይም በአንዳንድ ኪራይ ሰብሳቢ ወገኖች ሴራ ሆን ተብለው እንዳይቋቋሙ የተደረጉ መ/ቤቶችን ለመጠቆም ወይም ለማጋለጥ እወዳለሁ፡፡ (የዜግነት ግዴታዬ ነዋ!)
ለምሳሌ በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ፣ በ10 እና 8 እጥፍ እያደገ የቀጠለው የቅባት እህሎችና ጫት ምርት እንዴት ይዘነጋል?! ይታያችሁ… በ2014 እ.ኤ.አ ከሁለቱ ምርቶች የተገኘው የውጭ ምንዛሪ 940 ሚ. ዶላር ነበር፡፡ (ለችግራችን ደራሽ እኮ ነው!) ታዲያ ለእነዚህ ከፍተኛ ገቢ ላስመዘገቡ የግብርና ምርቶች የሚኒስቴር መ/ቤት መቋቋም ይበዛባቸዋል? እናም ---- “የቅባት እህሎችና የጫት ሚኒስቴር” እንዲቋቋም ኃሳብ ቀርእናቀርባለን፡፡ (ሃባ ዶላር አስገኝቶ የማያውቀው ዓሳ እንኳን የሚ/ር መስሪያ ቤት ተቋቁሞለታል!) ምናልባት “ጫት” የሚለው አጠራር ደስ የማይል ከሆነ “አረንጓዴው አልማዝ” ልንለው እንችላለን፡፡
ሌላው የተረሳው አካል ማን መሰላችሁ? ዳያስፖራ ነው፡፡ እናላችሁ----በተለያዩ የዓለም አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የዳያስፖራ አባላት ለዘመዶቻቸው የሚልኩት ገንዘብ ከጠቅላላው የኤክስፖርት ገቢ በእጅጉ እንደሚልቅ መንግስት ደጋግሞ አስታውቋል፡፡ እ.ኤ.አ በ2011 በቀረበው ሪፖርት፤ በዓመቱ የመጀመሪያ 7 ወራት ከዳያስፖራ የተላከው የውጭ ምንዛሪ መጠን 1.74 ቢ. ዶላር ሲሆን ይሄም ከቀደመው ዓመት የ19.6 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ተጠቁሟል፡፡ ይሄን የኢኮኖሚ ዋልታችንን እንዴት በሚኒስቴር ደረጃ ማዋቀር ተዘነጋን? (በውለታ ቢስነት ያስወቅሰናል!) እናም “የዳያስፖራ ሚኒስቴር” ዛሬ ነገ ሳይባል እንዲቋቋም ልማታዊ መንግስታችንን እንጠይቃለን (ፒቲሽን እናሰባስባለን አልወጣንም!) በነገራችን ላይ የአቅም ግንባታ ሚኒስቴር ምን ገንብቶ እንደፈረሰ የሚያስረዳን ቢኖር ደግ ነበር፡፡ ተጠያቂነትና ግልጽነት ከዚህ ይጀምራል! (አንዳንዶች “አቅም የሌለው የአቅም ግንባታ ሚ/ር” ይሉት ነበር!)
ይሄኛው ለብዙዎቹ ግር ሊል ይችላል፡፡ አዎ--- “የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሚኒስቴር” ማቋቋም ----ያስፈልጋል፡፡ (የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ለመገንባት እታትራለሁ ለሚል ገዢ ፓርቲ ወሳኝ ጉዳይ ይመስለኛል!) ሌላው የኪነጥበብ ጉዳይ ነው፡፡
አርቲስትና ገጣሚ በሞላባት አገር ሲሆን “የግጥም (ቅኔ) ሚኒስቴር” ካልሆነ ደግሞ “የኪነጥበብ ሚኒስቴር” (Ministry of Arts) ቢቋቋም ቢያንሰው እንጂ አይበዛበትም፡፡
 ሃቁን እንነጋገር ከተባለ እኮ ----- ከተፈጥሮ ጋዝ ሃብታችን ይልቅ የግጥምና የእስክስታ ሃብታችን በብዙ እጥፍ ይበልጣል፡፡ አንድም ባህላዊ እሴት ነው - ማንነታችን የተገነባበት፡፡ አንድም ለቱሪስት እየሸጥን ገቢ የምናገኝበት ምጭ የውጭ ምንዛሪ ምንጫችን ነው (“በእጅ የያዙት ወርቅ” ሆኖብን እንጂ!!) የሚኒስቴር መ/ቤት ማዋቀሩን በነካ እጃችን እንጨርሰው ካልን “የግምገማ ሚኒስቴር” (የግምገማ ባህልን ለአፍሪካ ፓርቲዎች ለማጋራት!) “የሰላምና ማረጋጋት ሚኒስቴር” (ለጐረቤት አገራት ለምናደርገው አስተዋጽኦ!) “የፕሮፓጋንዳ ሚኒስቴር” (ፀረ - ሰላምና ፀረ - ልማት ሃይሎችን የሚመክትና የሚያከሽፍ!) “የዕዳዎች ሚኒስቴር” (IMF የውጭ ዕዳ ክምችታችሁ አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርትን 50 በመቶ ያህላል በማለቱ!) የሚሉት አዳዲስ የሚኒስቴር መ/ቤቶች ይቋቋሙ ዘንድ እንጠይቃለን፡፡
 ሃሳብ ብልጭ ሲልልን ወይም ደግሞ በህልማችን ከታየንም ሊቋቋሙ ይገባል የምንላቸውን የሚኒስቴር መ/ቤቶች መጠቆማችንን እንቀጥላለን፡፡ (ለጊዜው #የባቡር ሚኒስቴር” እንዴት ነው?)
 እናንተ ----- ስለ ሚኒስቴር መ/ቤቶች በመጻፍ ብቻ ሚኒስትር የሆንኩ መሰለኝ!!

Read 4097 times