Saturday, 10 October 2015 16:00

ሹመትና ቁመት በምኞት አይገኝም!

Written by 
Rate this item
(19 votes)

  ከእለታት አንድ ቀን አንድ ሽማግሌ ሹም የተቋሙን ሠራተኛ ሁሉ የሚያጣላ፣ የሚያጋጭና የሚበጠብጥ ወሬ እያወራ ሰውን እያተራመሰ አስቸገረ፡፡ ሰው ተሰበሰበና መምከር ጀመረ፡፡
አንደኛው - “ይሄ ሰው የባለቤቱ ዘመድ ነው፡፡ ለዚህ ነው እንደልቡ የፈለገውን እያወራ ዘራፍ የሚልብን!” አለ፡፡
ሁለተኛው - “ታዲያ ባለቤቱም ቢሆኑ‘ኮ ውሸት አይፈቅዱም!”
ሦስተኛው - “እሱን እንኳ እሳቸው ካልተናገሩ ማንም አያውቅም”
ይሄ ሙግት እየተካሄደ ሳለ ባለቤትየው መጡ፡፡
“ምንድን ነው የሚያጯጩሃችሁ?” አለ፡፡
ከተሰበሰቡት መካከል አንዱ፤
“ጌታዬ ይሄ የርስዎ ልጅ በጣም አስቸገረን”
“ምንድ አድርጐ?”
“እየዋሸን”
“ታዲያ ውሸት ለእናንተ አዲስ ነው እንዴ? ታገሱታ!”
“እንዴት ጌታዬ፤ እሱኮ ውሸት አያልቀበትም”
“እንዴት አያልቅበትም?”
“በጣሊያን ጊዜ የሰማውን ውሸት እስከዛሬ ስለሚያስታውስ ነዋ!!”
“ያ ከሆነማ ከዛሬ ጀምሮ ተሰናብቶላችኋል!” አሉ ባለቤቱ!
***
ውሸት ሁሌም ውሸት ነው! የጣሊያን ጊዜ ውሸትና የዛሬ ውሸት ብሎ ልዩነት መፍጠር የለም! ዕውነት ያልሆነ ሁሉ ውሸት ነው ብሎ ማመን እንጂ ለውሸት ጊዜ መለየትም ሆነ፣ ቦቃ መለየት የትም አያደርስም! ማናቸውም አሉታዊ ነገር ያለው ውሸት ነው፡፡ ውሸትን ለማራመድ ሥልጣን ተጠቀምን ማለት ሹመት ለውሸት ተግባር ዋለ ማለት ነው!
“ደንጊያና ቅል ተላግቶ
ዜጋና ሹም ተጣልቶ”
አይሆንም፤ የሚለውን አባባል፤ የማንሽር ከሆነ፣ አዲስ ሹመት አዲስ ሽረት እንደማለት ነው፡፡ የጊዜ ጉዳይ ነውና!
“ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል”ን ምን ያህል ረስተናል?
ሙስናን ተገላግለነዋል ወይ? የጣሊያን ጊዜን ውሸት ተፋትተናል ወይ? መልካም አስተዳደር ዜማ ነው ተግባር ነው? ፍትሕ እዚያው ፍርድ ቤት ነው ወይስ እኛ ውስጥ አለ? ስለ አንደኛውና ስለ ሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ስንቶቻችን በዕውን እናውቃለን?
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች መከፈላቸው መቼም ሳይጠና እንዳልሆነ እንገምታለን፡፡ ለጠቅላይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በርካታ አማካሪ ሲሾም (ሲመራ) ያለጥናት እንዳልሆነ እንዳልገመትን ሁሉ “ጠርጥር ጉድ አለ በሰኔ” የሚለውም ሆነ፤ “የፊት ወዳጅሽን በምን ሸኘሽው?”
    በሻሽ፡፡
ለምን?
የኋለኛው እንዳይሸሽ!”
የሚለው፤ እንደጊዜው የሚፈረጁ ናቸው!!
“ግፋው እንጂ አታርቀው” የሚለውም ያው ነው!” እዚህ ቦታ ያልረባ እዚያ ይገባ!” ማለትም ያጠያይቃል፡፡ “ጉልቻ ቢቀያየር ወጥ አያጣፍጥም!” የሚለው፤ የኃይለሥላሴ ዘመን ሲያበቃና እንዳልካቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሆን የተሰነዘረ መፈክር ዛሬም ቢነሳ አያስቀይምም!
ዋናው ጉዳይ፤ “ወገናዊነትን ሳይሆን ሙያችንን እንሥራበት” የሚለው ነው፡፡
አፈረስነው ያልነው ኢዲሞክራሲያዊነት፣ ኢፍትሐዊነትና ሙስና፤ መልሶ እኛኑ የሚያፈርሰን ታሪክን ከደገምን ነው፡፡ “የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳ” የሚለው ተረት የማይረሳንን ያህል፤
“የተወጋ በቅቶት ቢረኛ፣ የወጋ ምን እንቅልፍ አለው፤
የጅምሩን ካልጨረሰው!” የሚለውንም የማንዘነጋ መሆን አለብን!
ሀገርን በሀቀኛ ተግባር እንሞላ ዘንድ ከሆነ የተሾምነው፤ ሹመት በመቀባት ሳይሆን፣ በመመኘትም ሳይሆን፣ ለሀገር አሳቢ በመሆን ብቻ ተገኘ ማለት ነው!
ሙስናን በተመለከተ አንዲት ገጠመኝ ጠቅሰን እንደምድም፡፡ ሰውዬው መንገድ ላይ ተኝቶ ቁስሉን ዝንብ ወሮታል፡፡ ሌላ መንገደኛ መጥቶ “እሽ!” ብሎ ዝምቦቹን አባረረለት፡፡
ያ ቁስለኛም፤
“ምነው ወዳጄ ጠግበው የተኙትን ዝንቦች አባረህ አዲሶቹን ጋበዝክብኝ!” አለው፡፡

Read 7019 times