Saturday, 10 October 2015 15:58

መድረክ፤ አዲሱ የኢህአዴግ መንግሥት ለሀገሪቱ ችግሮች መፍትሄ አይሠጥም አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(18 votes)

    የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ፤ ሰሞኑን የተቋቋመው አዲሱ የኢህአዴግ መንግስት፣ ለኢትዮጵያ መሠረታዊ ችግሮች መፍትሔ ሊሰጥ አይችልም አለ፡፡ “የህዝብን ይሁንታ አግኝቶ ውክልና ያለው መንግስት አይደለም” ሲልም መድረክ ተቃውሟል፡፡ ከትናንት በስቲያ በጽ/ቤቱ ለሀገር ውስጥና ለውጭ መገናኛ ብዙሃን መግለጫ የሰጠው መድረክ፤ ኢህአዴግ ለአዲሱ መንግስት አመራር እንዲሰጥ ያሰባሰበው የሰው ሃይል ስብጥር፣ ብቃት ያለው አይደለም ብሏል፡፡
“የአዲሱ መንግስት የሰው ሃይል ስብጥር ‘የፍራሽ አዳሽ’ ዓይነት እንጂ ለአዲሱ መንግሥት ሕይወት የሚሰጥ አይደለም” ያለው መድረኩ፤ ኢህአዴግ በየመግለጫዎቹ የሕብረተሰቡን መጠነ ሠፊ ችግሮች እንደሚፈታና ሀገሪቱን እንደሚያለማ ቢገልፅም ባለበት መሠረታዊ ችግር የተነሳ አይሳካለትም ብሏል፡፡
 አዲሱ መንግስት ለሀገሪቱ ችግሮች መፍትሔ ሰጪ አይሆንም ሲል ከጠቀሳቸው ምክንያቶች መካከል ድርጅቱ የሚከተለው የፖለቲካ መስመር ፀረ ዲሞክራሲ መሆኑና አሣታፊ አለመሆን የሚሉት ይገኙበታል፡፡
የአሜሪካ መንግስት “ሽብርተኝነትን በመከላከል ስም” ለገዥው ፓርቲ ድጋፍ መስጠቱ የሌሎች ለጋሽ ሀገሮችንም አቋም አስለውጧል ያለው መድረኩ፤ ሀገራቱ ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን ዲሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶች ጥያቄ ችላ ማለታቸው ለገዥው ፓርቲ አደፋፋሪ አለማቀፍ ሁኔታን እንደፈጠረለት ገልጿል፡፡ መድረኩ በምርጫ 2007 ማግስት ምርጫውን አስመልክቶ “ምላሽ የሚሹ ባለ 5 ነጥብ ጥያቄዎች” አቅርቦ እንደነበር አስታውሶ፤ እስካሁን ምላሽ እንዳልተሰጠውና በአባላቶቹና ደጋፊዎቹ ላይ የሚፈፀሙ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶችም ተጠናክረው እንደቀጠሉ አስታውቋል፡
ኢህአዴግ በአንድ ፓርቲ ሥርዓት የሚመሩ የቻይናና የሩቅ ምስራቅ ሀገሮችን አርአያነት መከተሉን አጥብቆ የተቸው መድረኩ፤ “እንደ ወረደ የተኮረጀው አሠራር፣ የብዙሃዊነት ተምሣሌት በሆነችው ኢትዮጵያ ላይ ሊሠራ እንደማይችል አለመጤኑ አደገኛ ነው” ብሏል፡፡ ይህ ዓይነቱ የመንግሥት አካሄድ በሀገሪቱና በህዝቡ ሉአላዊነትና ሠላም ላይ ሊያስከትል የሚችለው አደጋ እንደሚያሳስበውም አክሎ ገልጿል፡፡

Read 2959 times