Saturday, 10 October 2015 15:52

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት: ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ የሕንጻ ኪራይ አልሰበሰበም

Written by 
Rate this item
(3 votes)
  •         የገቢ አሰባሰቡ የአስተዳደር ጉባኤ አባላቱን አወቃቅሷል
  •         ከዕድሳት ዕጦት የሕንጻው ደኅንነት አደጋ ላይ ወድቋል

   በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት፣ ለተለያዩ አገልግሎቶች ከአከራያቸው የሕንጻው ክፍሎች ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ የኪራይ ክፍያ አለመሰብሰቡ ተገለጸ፤ ተከራዮች ውዝፍ ዕዳቸውን ከነመቀጫው አጠናቀው እንዲከፍሉ ጽ/ቤቱ አስጠነቀቀ፡፡
የሀገረ ስብከቱን ሕንጻ ለቢሮ፣ ለሕክምና እና ለሱቅ አገልግሎቶች ከተከራዩ ስድስት ተከራዮች ያልተሰበሰበው አጠቃላይ ክፍያ ብር 675 ሺሕ 244 ከ31 ሳንቲም ያህል እንደኾነ ጽ/ቤቱ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ከጻፈው የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ማስጠንቀቂያው ከደረሳቸው  መካከል፣ ከሰኔ ወር 2005 ዓ.ም. ወዲህ ኪራያቸውን ሳይከፍሉ የቆዩና እስከ 360 ሺሕ ብር ከፍተኛ ውዝፍ ያለባቸው ተከራዮች እንደሚገኙበት ታውቋል፡፡ተከራዮች ደብዳቤው በደረሳቸው በሦስት ቀናት ውስጥ ውዝፍ ዕዳቸውን ከነመቀጫው ከፍለው ለጽ/ቤቱ ካላሳወቁ፣ ቢሮዎቻቸውና ሱቆቻቸው እንደሚታሸጉ የተሰጠው ማስጠንቀቂያም የሚገባውን ያህል ተግባራዊ ሳይሆን ከወር በላይ ማስቆጠሩ ተገልጧል፡፡
ኪራዩ በወቅቱ ቢሰበሰብ፣ ገንዘቡ በወቅቱ የነበረውን ዋጋ ያህል ቤተ ክርስቲያኒቱን ተጠቃሚ ያደርግ እንደነበር የሚገልጹ የሀገረ ስብከቱ ምንጮች፣ የፋይናንስና በጀት ዋና ክፍሉን ቀዳሚ ተጠያቂ አድርገዋል፡፡
ዋና ክፍሉ ከኪራዩ የሚሰበሰበውንና የቀረውን ገቢ በየጊዜው ለአስተዳደር ጉባኤው በሪፖርት በማሳወቅ፣ ክፍያው እንዳይወዘፍ ማድረግ የሚገባው ቢሆንም አለማቅረቡ ድክመቱን እንደሚያሳይ ምንጮቹ አስረድተዋል፡፡
በከፍተኛ የክፍያ ዕዳ ከሚታወቁ ተከራዮች መካከል ከአንዳንድ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ጋር ግንኙነት ያላቸው እንደሚገኙበት ምንጮቹ ጠቁመው፤ አጀንዳው በአስተዳደር ጉባኤው ስብሰባ ላይ ቀርቦ በታየበት ወቅትም “የገቢ አሰባሰቡ በዝምድና የተሸፋፈነ ነው” በሚል ሓላፊዎቹን እርስ በርስ አወቃቅሶ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
በ2001 ዓ.ም. በወቅቱ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል አስተዳደር፣ በከፍተኛ ወጪ ተሠርቶና በቀድሞው ፓትርያርክ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ሕንጻ፣ ባለቤት አልባ እስኪሰኝ ድረስ እያፈሰሰ እንደሚገኝና አስቸኳይ ዕድሳት ካልተደረገለትም ደኅንነቱን አስጊ እንደሚያደርገው ምንጮቹ ይገልጻሉ::

Read 1147 times