Saturday, 03 October 2015 09:55

የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት በቀረበባቸው አቤቱታ ላይ የሰጡት ምላሽ

Written by 
Rate this item
(10 votes)

“በአመራር ችግር ከ200 በላይ መምህራን ለቀዋል;
የተሳሳተ ገፅታ ለመፍጠር የሚደረግ ጥረት ነው”

ባለ 10 ገጽ አቤቱታ ለትምህርት ሚኒስትሩ ቀርቧል

  ሰሞኑን በኢሜይል የደረሰን ደብዳቤ “ግልፅ አቤቱታ - ይድረስ ለክቡር የትምህርት ሚኒስትር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ” ይላል፡፡ አቤቱታ አቅራቢዎች፤“የዲላ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክና አስተዳደር ሰራተኞች” መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ መረር ያለ አቤቱታቸውና ትችታቸው ያነጣጠረው በዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት በዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ ኮሬ ላይ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም ለትምህርት ሚኒስቴር ቢሮ፣ ሁለት ጊዜ የድረሱልን ጥሪ አቤቱታ አስገብተው ምላሽ እንዳልተሰጣቸው አቤቱታ አቅራቢዎቹ በደብዳቤያቸው ላይ አስታውሰዋል፡፡ ይህንን ግልፅ አቤቱታ ለክቡር የትምህርት ሚኒስትሩ ለማቅረብ በሁለት ምክንያቶች መገደዳቸውንም ይጠቅሳሉ፡፡ “አንደኛው ምክንያታችን፤ በአምባገነኑ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ ኮሬ አማካኝነት ተቋም ብቻ ሳይሆን አገር ጭምር እየፈረሰ ስለሆነ የዜግነት ግዴታችንን ለመወጣት ነው” ይላሉ፡፡ ሁለተኛውን ምክንያታቸውን ሲገልጹም፤“ከዚህ ቀደም በፃፍናቸው አቤቱታዎች ላይ አጥጋቢ ምላሽ የማይሰጠን ከሆነና አምባገነኑ መሪ ከእኩይ ሥራቸውና ሀገር ከማፍረስ ተግባራቸው የማይታቀቡ ከሆነ ወደ ሚዲያው እንደምናወጣውና እስከመጨረሻ ድረስ ሄደን እንደምንታገል አስቀድመን በመናገራችን እንዲሁም የአምባገነኑ መሪ የመብት ረገጣ፣ ዛቻ፣ ጥላቻ፣ ስድብና የመብት ጥሰት በየቀኑ እየተባባሰ በመሄዱ ነው” ብለዋል - አቤቱታ አቅራቢዎቹ፡፡
በ10 ገፆች የቀረበው “የዲላ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክና አስተዳደር ሰራተኞች” አቤቱታ፤ በዋናነት በብልሹ የዩኒቨርሲቲው አመራር የተነሳ ሶስተኛ ድግሪ ያላቸው ነባር መምህራን ዩኒቨርሲቲውን ጥለው እየተሰደዱ መሆናቸውን ይገልጻል - በአንድ ዓመት ብቻ ከ200 በላይ ሠራተኞች መውጣታቸውን በመጥቀስ፡፡ አቤቱታ አቅራቢዎቹ ሌሎች በዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ይፈጸማል ያሏቸውን፣ ሥልጣንን ያለ አግባብ በመጠቀም…ቤተዘመድን ሥራ መቅጠር----የዘረኝነትና ጠባብነት አስተሳሰብ እና ሌሎችንም ጠቅሰዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ በ16 ነጥቦች የተዘረዘሩትን አቤቱታዎች በተመለከተ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ ኮሬን በስልክ አነጋግሮ ተከታዩን ምላሽ ሰጥተውታል፡፡ (ፕሬዚዳንቱ ለሰጡን ፈጣን ምላሽና ማብራሪያ የዝግጅት ክፍላችን ምስጋናውን ይገልጻል፡፡)
አቤቱታ አቅራቢዎቹ ለትምህርት ሚኒስትሩ በፃፉት ደብዳቤ ተራ ቁጥር 1 ላይ የሰፈረው ቅሬታ በከፊል እንዲህ ይላል፡-
“…በአንድ እስክሪብቶ ጫፍ ስልጣንን ሁሉ ከህግ፣ መመሪያና አዋጅ ውጭ ተቆናጠው ይዘው በዩኒቨርስቲው ውስጥ 229 ሠራተኞችን ያለምንም ደንብና ሥርዓት፣ ያለመመሪያ፣ ያለ ውድድር ወይም በይስሙላ ውድድር ለካምፓስ ሆስፒታል ቀጥረውና አስቀጥረው ምንም እርምጃ ሳይወሰድባቸው መቅረቱ ወይም ደግሞ እርስዎ እንዲያጣራ ልከው መጥቶ ሄደ የተባለው ቡድን ሪፖርት የውሃ ሽታ ሆኖ መቅረቱ አሳዝኖናል…”
የፕሬዚዳንቱ ምላሽ፡-
በቅጥር ጉዳይ እኔ የምሰጠው ትዕዛዝ የለም፡፡ በተለይ የቀረበው ቅሬታ ከጽዳትና ከጥበቃ ሠራተኞች ጋር የተገናኘ ነው፡፡ ይሄን የሚመለከተው ራሱን የቻለ ኮሚቴ ነው፡፡ ተወዳድሬ ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ እድል አላገኘሁም ብሎ ቅሬታ ያቀረበ የለም፡፡ በኔ ደረጃ ምንም ውሣኔ የተሠጠበት አይደለም፡፡ ትክክለኛ አሠራርን ተከትሎ የተተገበረ ነው፡፡ እኔ ጋ በዚህ ጉዳይ የቀረበ አንድም ቅሬታ የለም፡፡ በነገራችን ላይ ይሄን ቅሬታ የሚያቀርቡ ግለሰቦች አይታወቁም፡፡ በአካል ቀርበውም ቅሬታ አላቀረቡም፡፡ የሠራተኛ ዝውውር ስርአታችንን አድሏዊ ለማስመሰል ሁሉ ሲጥሩ ተመልክተናል፡፡ የአካባቢው ልጆች ብቻ የተለየ እድል ተጠቃሚ ለማስመሰል የሌሎችን ዝርዝር አውጥተው ነው እንደ ማስረጃ የሚያቀርቡት፡፡ እውነታው ግን ሌላ ነው፡፡ ማንም ቢሮ መጥቶ ቢመለከት፣ አድሏዊነት በሌለው ሁኔታ ነው የዝውውር ስራዎች የሚሠሩት፡፡ የሌላ አካባቢ ሰዎችም ዝውውር ሲጠይቁ ይዘዋወራሉ፡፡ ተቀጠሩ የተባሉ ግለሰቦች ጉዳይም በሰው ሃብት አስተዳደር በኩል የሚያልቅ ነው፤ እኔ ጋ የሚመጣ አይደለም፡፡
 በብልሹ አመራርና በተለያዩ ጫናዎች የተነሳ፣ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች እየተሰደዱ ነው፡፡ በአንድ ዓመት ብቻ ከ200 በላይ የሚሆኑ ሌክቸረሮች ዩኒቨርሲቲውን ለቀዋል፡፡ በስም ከጠቀሷቸው መካከል ዶ/ር አህመድ ሁሴን (ወደ አ.አ.ዩ በዝውውር ሂደት ላይ ያሉ) ዶ/ር ወንዳወቅ አበበ (ወደ ሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከ3 ወራት በፊት የለቀቁ) ይገኙባቸዋል፡፡ የሠራተኞች ስደቱ እውነት ነው?
እንግዲህ ከዩኒቨርሲቲው ለቀዋል ከተባሉት መካከል ለምሣሌ ዶ/ር አህመድ አብረን፣ ማናጅመንት ውስጥ የምንሠራ፣ የምንግባባ ሰው ነን፡፡ ጊዜውንም በምርምር ስራ የሚያጠፋ፣ በዚህም የምርምር ስራዎችን እንዲሠራ የተደረገ ምሁር ነው፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የማስተማር እድል አግኝቶ ሲሄድም በሠላም የሸኘነው ሰው ነው፡፡ በግል አንድም ቀን በሃሳብ እንኳ ተጋጭተን አናውቅም፡፡ ዶ/ር ወንዳወቅም ቢሆን በጣም የምንግባባ ሰዎች ነን፡፡ አዋሣ ቤተሰቦቹ ስላሉ እድሉን ሲያገኝ፣ ከቤተሰቤ ጋር አንድ ላይ መሆን አለብኝ ብሎ የኮንትራት ውል ጊዜውን ከጨረሰ በኋላ ነው የሄደው፡፡
በአጠቃላይ ለቀዋል የሚባሉት መምህራን እየሄዱ ያሉት ወደ ቤተሰባቸውና ወደተሻለ ስራ እንጂ “ዲላ ዩኒቨርሲቲ አልተመቸንም” በሚል አይደለም፡፡ በእርግጥ በጣም ልምድ ያላቸው መምህራን የኮንትራት ጊዜያቸውን እየጨረሱ መሄዳቸው አንዱ ስጋታችን እንደሆነና ትምህርት ሚኒስቴርም በዚህ በኩል ሊረዳን እንደሚገባ እያሳወቅን ነው፡፡
መምህራን የሚለቁት በአመራር ችግር አይደለም እያሉኝ ነው?
እኛ ለአንድም አስተማሪ ማስጠንቀቂያ እንኳ ሰጥተን አናውቅም፡፡ የስንብት ደብዳቤም ለአንድም መምህር ሰጥተን አናውቅም፡፡ በአሠራር ስርአታችንም ቢሆን ከአመራር ጋር እንጂ ከመምህራን ጋር ብዙም አንደራረስም፡፡ እኛ የምንወያየው ከአመራሮች ጋር ነው፡፡ በመምህር ደረጃ ከኛ ጋር የተነጋገሩት አንድ መምህር ብቻ ናቸው፡፡ የጂኦሎጂ ዲፓርትመንት መምህር የነበሩ ግለሰብን አንድ ተማሪ ስለከሰሳቸው፣በዚያ ጉዳይ አነጋግረናቸዋል፡፡ ከዚያ ውጪ የመምህራን ጉዳይ በኮሌጅ ዲኖች ደረጃ የሚያልቅ ነው፡፡
በአንድ አመት ብቻ 200 ሠራተኞች  ለቀዋል የሚለው ትክክለኛ መረጃ አይደለም፡፡ አዎ! ሰዎች የተሻለ ነገር ሲያገኙ የስራ ዝውውር ማድረጋቸው አይቀርም፡፡ እኛ ሠራተኞቻችን የተሻለ ስራ አግኝተው መልቀቂያ ሲጠይቁ፣ አስፈላጊውን ክሊራንስ አድርገን የሽኝት ስነስርዓት አዘጋጅተን ነው የምንሸኘው፡፡ እነሱም ምስጋና አቅርበውልን ነው የሚሄዱት፡፡ አሁንም ቢሆን “ዝውውር ፍቀዱልን፤ ወደ ቤተሰባችን እንጠጋ” የሚል ማመልከቻ ያስገቡ አሉ፡፡ ይሄ ያለና የሚኖር ጉዳይ ነው፡፡
ለምሣሌ ከኢነጂነሪንግ ዲፓርትመንት ብዙ ሰው ነው የሚለቀው፡፡ ወደ ስኳር ፕሮጀክቶች፣ ወደ ሜቴክ የተሻለ ስራ አግኝተው ይለቃሉ፡፡ ኢንጂነሪንግ አካባቢ በእርግጥም ሰው ብዙ አይቆይልንም፤ ይሄ ደግሞ ገበያው የፈጠረው ነው፡፡ በአመራሩ ምክንያት ሠራተኛ እየለቀቀ ነው የሚለው ስሞታ የተሳሳተ ገፅታ ለመፍጠር የሚደረግ ጥረት ነው፡፡
እርስዎ ለአንድም  መምህር ማስጠንቀቂያ ጽፈን አናውቅም፤የስንብት ደብዳቤም ለአንድም መምህር ሰጥተን አናውቅም፡፡ ብለዋል፡፡ ቅሬታ አቅራቢዎቹ በደብዳቤያቸው ላይ እርስዎን የሚገልፁት “አምባገነን” እያሉ ነው፡፡ ይሄ በምን ምክንያት ይመስልዎታል? ቁጡ ባህሪ አለዎት እንዴ? ከአስተዳደር ሠራተኞች ጋር ያለዎት ግንኙነትስ?
ምናልባት እኔ ወደ ዲላ ስመደብ፣በደንብ ያልተያዙ ስራዎች ከመኖራቸው አንፃር በእልህና በቁጭት የሚሠሩ ትጉህ ሰራተኞችን ነው የምይዘው፡፡ ትክክል ነው አይደለም የሚሉ ውሣኔዎችን እየሠጠሁ ነው የምሄደው፡፡ ይሄ ደግሞ አልተለመደም መሠለኝ፡፡ ስራዎችን ጫን አድርጌ የመሄድ ነገር ነበር፤ ይሄ ደግሞ ከእልህ ጋር የተያያዘ እንስራ በሚል መንፈስ የማደርገው ነው፡፡ ጫና ፈጥሬ ስራ እንዲሠራ ስለማደርግ ነው፡፡ ለምን ቀስ አትልምም… ይሉኛል፡፡ የመንግስት መመሪያን ለመፈፀም ጫን ብለን እንሄዳለን፤ ከዚያ አንፃር ይመስለኛል፡፡ ግን ስራን ማዕከል ያደረገ ጫና ነው እንጂ ከስራ ውጪ ምንም ነገር የለም፡፡
ከስራ የለቀቁት መምህራን ምን ያህል ይሆናሉ?
በዝርዝር የተዘጋጀ ነገር የለም፡፡ ግን ብዙዎቹ በ2007 ብቻ አይደለም የለቀቁት፤ ከዚያ በፊትም ብዙ ለቀዋል፡፡ በስም ከተጠቀሱት መካከልም ከ2007 ዓ.ም በፊት የለቀቁ አሉ፡፡
  ፕሬዚዳንቱ ከዩኒቨርስቲው እንዲለቁ የሚፈልጓቸውን የአስተዳደር ሠራተኞችና ምሁራንን ያስደበድባሉ በማለት አቤቱታ ቀርቧል፡፡ ለምሳሌ የሶሻል ሳይንስ ዲን ዶ/ር፤ በመኪና ቁልፍ ተወርውሮ ተመቷል፡፡ የባዮሎጂ ትምህርት ክፍል ኃላፊ፤ስድብና ዛቻ በተደጋጋሚ ደርሶባቸዋል የሚል ተጠቅሷል፡፡  
ይሄ ጉዳይ በቀጥታ እኔ ላይ መለጠፉ ነው እንጂ ስነምግባር የጐደላቸው ሹፌሮች እንዳሉ አይተናል፡፡ ዶ/ር ቦጋለ በጣም ጥሩ ሰው፣ ተግባቢ ነበረ፡፡ ሹፌሮች ይሄን ድርጊት መፈፀም አልነበረባቸውም፡፡ በዚህ ምክንያት የዩኒቨርሲቲው ትራንስፖርትና ስምሪት ክፍል ሃላፊዎች ሹፌሩን ከስራ አግደውታል፡፡ የሌሎች ሹፌሮችን የስነ ምግባር ጉድለት በማረቅ ረገድ በትክክል አልመራችሁም በሚል ከሚመለከታቸው የስራ ሃላፊዎች ጋር በጥብቅ ተነጋግረናል፡፡ ችግሩ አለ ግን አመራሩ ላይ በቀጥታ መለጠፉ ተገቢ አልነበረም፡፡ እኛም እርምጃ እየወሰድን ነው፡፡
ስልጣንን አላግባብ በመጠቀም ያለ ደንብና ስርአት ሠራተኛ መቅጠር፣ በሃላፊ ላይ ሃላፊ ደርቦ መሾም የሚል አቤቱታም ቀርቧል፡፡ ለ3ኛ ድግሪ ትምህርት ወደ አዲስ አበባ የሄዱ ሰው፤ እዚያው በሚገኝ ቢሮ በዳይሬክተርነት ተመድበዋል - በሌላ ሃላፊ ላይ ተደርበው፡፡ ስለዚህስ የሚያውቁት ነገር አለ?
በደብዳቤው ላይ በስም የተጠቀሰችው መስከረም ጃራ ማለት በዩኒቨርሲቲው ፀሐፊ የነበረች ናት፡፡ አዲስ አበባ ሽሮ ሜዳ ላይ የአገናኝ ቢሮ አለን፡፡ እሷ የዚያ ቢሮ ፀሐፊና አስተባባሪ ናት፡፡ አሁንም እዚያው አዲስ አበባ ሩዋንዳ አካባቢ በ10 ሚሊዮን ብር አዲስ ህንፃ ገዝተናል፡፡ እሱን ህንፃ ለማስተባበር አንድ ሠራተኛ ልከናል፡፡ በሌላ በኩል ብቻውን ጫና እንዳይበዛበት በደብዳቤው የተጠቀሰችውን ምስራቅ ጠና (የፒኤችዲ ተማሪ በአ.አ.ዩ) እገዛ እንድታደርግለት አድርገናል፡፡
ሌላው አቤቱታ፤የዶክትሬት ድግሪያቸውን ሳያገኙ “ዶክተር በሉኝ፣ ዶክተር ሆኛለሁ” በማለት ለ 1 አመት የዶክተር ደሞዝ በልተዋል የሚለው ነው
ይሄ ፍፁም ሃሰት ነው፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ትምህርቴን መጨረሴን የሚያረጋግጥ ደብዳቤ የፃፈልኝ በህዳር ወር ነው፡፡ ግን ምረቃው በአመቱ መጨረሻ ነበር፡፡ በዚህ መነሻ ዩኒቨርስቲው ፒኤችዲ መጨረሴን ጠቅሶ ነው ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ደብዳቤ የፃፈው፡፡ እኔም ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ጋር ውል ከገባሁ በኋላ ነው ወደዚህ ተመድቤ የመጣሁት፡፡ ደሞዜ የተስተካከለውም በዚያ መሠረት ነው፡፡
የ3ኛ ድግሪ ተማሪዎች የምርምር ገንዘብ ድጋፍ ሲሰጥ፣ ለኔም ይገባኛል ብለው ወስደዋል የሚል ወቀሳም አቅርበዋል፡፡ ይሄስ እንዴት ነው?
እኔም በወቅቱ እየተማርኩ ነበር፡፡ የ3ኛ ድግሪ ተማሪዎች ሲሄዱ፣በማናጅመንት ደረጃ የወሰነው የሚያገኙት ጥቅማጥቅም አለ፡፡ መጀመሪያ የሚሄድ ሰው ቤተሰቡንም ይዞ ሊሄድ ስለሚችል 10ሺህ ብር እንሠጣለን፡፡ ሁለተኛ ላይ ደግሞ ቶሎ ጨርሶ እንዲመጣ ለማበረታታት 10ሺህ ብር እንደገና ይሠጣል፡፡ እኔም ይሄን መብቴን ተጠቅሜ እንደ አንድ የ3ኛ ዲግሪውን እንደሚጨርስ ተማሪ፣በማመልከቻ ጠይቄ፣ይገባሃል ተብዬ፣ በመመሪያ መሠረት ነው የተሰጠኝ፡፡
በዩኒቨርሲቲው ወጪ ጀርመን፣ ኦስትሪያና ቻይናን ጐብኝተዋል፤ እንዲሁም እሣቸውን ውጪ የጋበዟቸውን ሁለት ግለሰቦች እንደገና በዩኒቨርስቲው ወጪ ወደ ኢትዮጵያ ጋብዘዋል---- የተባለው አቤቱታስ?
የሄድኩት ለዩኒቨርስቲው ስራ ነው፡፡ ግንኙነት የምንፈጥርባቸው ጉዳዮች ነበሩ፡፡ ት/ት ሚኒስቴር በደብዳቤ ተጠይቆ፣ ቦርድም አውቆት ተፈቅዶ ነው ወደ ኦስትሪያና ጀርመን የሄድኩት፡፡ ቻይና ደግሞ 13 ዩኒቨርስቲዎች ናቸው የጉብኝት ግብዣ ቀርቦላቸው የሄዱት፡፡ ከነዚያ አንዱ የኛ ዩኒቨርስቲ ስለነበር ሄጃለሁ፡፡ ለልምድ ልውውጥ ነው የተሄደው፡፡ በአጠቃላይ ወደ ሃገራቱ የሄድኩት ለግል ጉዳይ ሳይሆን ለዩኒቨርሲቲው የስራ ጉዳይ ነበር፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ወጪያቸው ተሸፍኖ እንዲመጡ የተደረጉት የውጭ ሀገር ዜጐችም መልካም ግንኙነት ለመፍጠር፣ ለአጋርነትና የተሻለ ፈንድ ለማምጣት እንዲሁም የአካባቢውን ተጨባጭ ሁኔታ ለማሳየት የሚያስፈልገውን ወጪ ሸፍነን አምጥተናቸዋል፡፡ ሌሎችም እንዲህ ይመጣሉ፡፡ ለኮንፈረንስ እንኳን የሚመጡና ወጪያቸውን የምንሸፍንላቸው ሰዎች አሉ፡፡
በዩኒቨርስቲው ከፍተኛ የገንዘብ ብክነት እንዳለ … በሆነ ባልሆነ በጀቱ ቶሎ እንደሚያልቅ… በዚህም የተነሳ በዩኒቨርስቲው የሚተገበሩ የመስክ ትምህርቶችና ሌሎችም ወጪ የሚጠይቁ ትምህርት ነክ ጉዳዮች እንደቆሙ ተጠቅሷል፡፡ ለመሆኑ የወጪ ቁጥጥራችሁ ምን ይመስላል?
የገንዘብ ቁጥጥራችን ጠንካራ ነው፡፡ ገንዘብ ወጥቶ ለታለመለት አላማ መዋል አለመዋሉን በጥብቅ ነው የምንቆጣጠረው፡፡ ሰዎችን ለስልጠና ስንልክም በበቂ ጥናት ላይ ተመስርተን ሰዎቹ ተመልሰው የሚኖራቸውን አስተዋጽኦ ከግምት በማስገባት ነው፡፡ በዚህ በኩል ውስን በጀት ነው የምንጠቀመው፤ የሚባክን ገንዘብ የለም፡፡ የወጣው ብር ምን ላይ ዋለ? ምን አስገኘ የሚለውን በየጊዜው እንገመግማለን፡፡ እጥረት እንዳለብንም እንረዳለን፡፡ በየጊዜውም እያስተካከልን እንሄዳለን፡፡
“ማንኛውም የተቃውሞ ሃሳብ ሲነሳባቸው፣ቶሎ ብለው ድካማቸውንና የራሳቸውን ጠባብነት ከጌዴኦ ማህበረሰብ ጋር ለማገናኘት ይሞክራሉ፡፡ የጌዴኦ ጠላት ነው አጥፉት የሚል ዘመቻ በዩኒቨርሲቲውና ከግቢው ውጭ እንዲከፈትበት ይደረጋል፡፡ ለምሳሌ አንድ መምህር ቤቱ በወረበሎች ተቃጥሎበታል-----” የሚል አቤቱታም በደብዳቤው ቀርቧል ------
 ሰው እኔ ላይ ተቃውሞውን ስላቀረበ አልፈርጅም፡፡ የራሱን ሃሳብ በፈለገው ልክ ማራመድ ይችላል፡፡ አንድ ግለሰብ ከተማ ውስጥ ችግር አጋጥሞኛል፣ የሆኑ ሙከራዎች ተደርገውብኛል ብሏል፡፡ ይሄን እንግዲህ በደንብ ማጣራት ይጠይቃል፡፡ እሱም ፍ/ቤት ከሶ ምርመራ እንዲካሄድ ማድረግ ይችላል፡፡ በህግ አግባብ ተጣርቶ ምላሽ ያግኝ በሚል ተወስኗል፡፡  
እኔ የአካባቢው ተወላጅ ስለሆንኩ፣ “ለአካባቢው ህዝብ ይሳሳል፤ ይራራል” የሚሉ ነገሮች ቢኖሩ አይደንቅም፤በእውነትም የአካባቢው ህብረተሰብ እንዲለወጥ እፈልጋለሁ፡፡ ግን በጠባብነት አይደለም፡፡ ዩኒቨርስቲው የብሔር ብሔረሰቦች ማዕከል ነው፡፡ በአካባቢው ያለውን ልማት እንደግፋለን፤ ብሔራዊ ፖሊሲውንም እንተገብራለን፡፡
በቅጥረኛ ሰዎች ስለላ ይደረግብናል፣ ዛቻና ማስፈራራት ይደርስብናል፣--- በሚል ስለቀረበው  አቤቱታስ-----?
እንደዚህ ያለ ነገር ተደርጐ አያውቅም፡፡ ምናልባት አስተዳደራዊ ውሣኔ በሚሹ ጉዳዮች ላይ መረጃ እናሰባስባለን፡፡ ጆሮ ጠቢ ሊኖረኝም አይችልም፤ አያስፈልገኝም፡፡ የተማሪዎች አገልግሎት መሟላት አለመሟላቱን ለማወቅ ግን መረጃ የግድ ያስፈልገናል፡፡ በአካባቢው ላይ ሺሻ ቤት እንዳለና እንደሌለ፣ በሴቶች ላይ ጥቃት የሚፈጽሙ ስለመኖር አለመኖራቸው በየጊዜው የማጣራት ስራ እንሠራለን፡፡ ከዚህ በተረፈ ግን ሰዎችን አደራጅቼ አላሠልልም፡፡
በክልሉ መንግስት ስር ያሉ የተለያዩ ሴክተር መ/ቤቶችና ሌሎችም ተጠቃሚዎች በማስተርስ ድግሪ ደረጃ አማርኛ ቋንቋና ቅርስ ጥበቃ ጥናት ይከፈትልን ብለው ጠይቀው፣ አስፈላጊነቱም በዳሰሳ ጥናት ተረጋግጦ እያለ እሳቸው፤ “እኔ የዲላ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ሆኜ በህይወት እስካለሁ አማርኛና ታሪክ አይከፈትም” ብለዋል የሚል ስሞታ በደብዳቤው ቀርቧል…
አማርኛና ታሪክ መደበኛ የዲግሪ ፕሮግራም አለን፡፡ አሁን ጥያቄው የማስተርስ ፕሮግራምን በተመለከተ ነው፡፡ የማስተርስ ጥያቄዎች በብዛት ሲመጡ እንከፍታለን የሚል ሃሳብ ነው ያለን፡፡ አሁን በትምህርት አከፋፈት ላይ ያስቀመጥነው ስርአት አለ፡፡
በእሱ አሠራር ላይ በየደረጃው ተነጋግረን፣ ይሄኛው ፕሮግራም በኛ ተቋም ተጨባጭ ሁኔታ ወይም በሀገሪቱ ለማፍራት ከታቀደው የሰው ሃይል ቁጥር ጋር ይጣጣማል ወይ? ይሄ የትምህርት ክፍል ሌላ ቦታ የለም ወይ? የሚል ጥያቄና ውይይት አድርገናል፡፡ “ሰው እየተመረቀ ስራ ላይ የማይውል ከሆነ” በሚለው ጉዳይ ላይም በስፋት ተነጋግረናል፡፡ በአሁን ወቅት ኮሚቴዎች እንዲያጠኑት እያደረግን ነው፤ እነሱ በሚያመጡት ውጤት ላይ ተንተርሰን ወደ ቀጣይ ሂደት እንገባለን፡፡ ግን በዚህ ደረጃ የሚገለፅ ጉዳይ አልነበረም፡፡ ቃል በቃል ተናግሯል ተብዬ የተጠቀሰብኝ ንግግርም አግባብ አይደለም፡፡ እኔ እንደዛ አይነት ነገር አልተናገርኩም፡፡  

Read 6074 times Last modified on Saturday, 03 October 2015 14:38