Saturday, 04 February 2012 13:03

ዓለምን እየመገበች የራሷን ሕዝቦች ችግር ላይ የጣለች አገር

Written by  ጥላሁን አክሊሉ
Rate this item
(0 votes)

አሜሪካ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የዓለምን የኃያልነት መንበር ከቀድሞ ሶቭየት ሕብረት ጋር በጋራ በመያዝ፣ ከቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት በኋላ ደግሞ ብቻዋን ልዕለ ኃያል በመሆን ዘልቃለች፡፡ ላለፉት 60 ዓመታት ዓለምአቀፍ ሰላምን ለማስጠበቅ በመንቀሳቀስ፣ የጠብ ጫሪነት መንፈስ ያላቸውን መሪዎች በማስወገድ፣ የተፈጥሮ አደጋና ድርቅ በተከሰተባቸው ቦታዎች ፈጥኖ በመድረስ የሰብዓዊ ድጋፍ በማድረግና በተለያዩ አገሮች ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲሰፍን በማድረግ የላቀ ሚና ተጫውታለች፡፡ በአሜሪካ የበላይነት የተቋቋመው የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም ቢሆንም፣ በአገራት መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለመፍታት የሰላም አስከባሪዎችን ከመላክ አንስቶ በእርስ በርስ ጦርነት፣ በረሃብ እና በተፈጥሮ አደጋ ቀያቸውን ጥለው ለሚሰደዱ ሕዝቦች ከፍተኛ የሰብአዊ ድጋፍ አድርጓል፡፡

በተጨማሪም የመንግስታቱ  ድርጅት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሕዝቦችን ኑሮ በማሻሻል ረገድ ብዙ ጥረት አድርጓል፡፡ በአጠቃላይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተለያዩ በጐ ተግባራትን ለመፈፀም በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ያወጣል፡፡

የመንግስታቱ ድርጅት ከ190 በላይ አባል አገራት ቢኖሩትም አብዛኛውን የድርጅቱን ወጪ የምትሸፍነው አሜሪካ ነች፡፡ ከተባበሩት መንግስታት ዓመታዊ በጀት 22 በመቶ ያህሉን ትሰጣለች፡፡ ድሀ አገራት ለድርጅቱ በየዓመቱ የሚሰጡት 0.001% ሲሆን በማደግ ላይ ያሉ አገራት ደግሞ 0.01% ነው፡፡ ሃብታም አገራትም ቢሆኑ ከ2-5% በላይ አያዋጡም፡፡

በገንዘብ ሲቀመጥ በ2009 ዓ.ም አሜሪካ 6.37 ቢሊዮን ዶላር የሰጠች ሲሆን፣ በ2010 ደግሞ 7.692 ቢሊዮን ዶላር ለተባበሩት መንግስታት ተሰጥቷል፡፡ አሜሪካ ለሰላም ማስከበር በ2010/11 ወደ 7.2 ቢሊዮን ዶላር ለድርጅቱ ለግሳለች፡፡ በሌላ በኩል በመንግስታቱ ድርጅት ሥር የሚገኙት ከ20 በላይ ድርጅቶች የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኙት ከአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት በጀት ውጪ ባሉ የአሜሪካ ተቋማት ሲሆኑ የአለም የምግብ ፕሮግራም (FAO) የሚደገፈው በአሜሪካ ዲፓርትመንት አፍ አግሪካልቸር ነው፡፡ የአለም አቀፍ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ (IAEA) ደግሞ በአሜሪካ የኢነርጂ ዲፓርትመንት ይደገፋል፡፡ ዩኒሴፍ (UNICEF) የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኘው ከአሜሪካ የጤናና የሰብዓዊ አገልግሎት ዲፓርትመንት ነው፡፡ የሰብዓዊ መብት ተቋማትና ሌሎች ድርጅቶችም ከተለያዩ የአሜሪካ ተቋማትና ከግለሰብ ባለሀብቶች የገንዘብ ድጋፍ በማግኘት የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ ዩ ኤስ ኤድን (USAID) ጨምሮ በርካታ የእርዳታ ድርጅቶችም በአሜሪካ በሚደረግላቸው የገንዘብ ድጋፍ የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡

ከላይ ከተጠቀሱት ውጪ አሜሪካ ለጦርነትና ለሰላም ማስከበር የምታወጣው ወጪ አላት፡፡ ለምሣሌ በኢራቅና በአፍጋኒስታን ጦርነት ወደ 1 ትሪሊዮን ዶላር አውጥታለች፡፡ አሜሪካ በስቴት ዲፓርትመንት በኩል ለተባበሩት መንግስታት አመታዊ በጀት የምትለግሰውን ጨምሮ ከግብር ከፋይ ዜጐቿ የምትሰበስበው ነው፡፡ የተባበሩት መንግስታትም ሆነ በስሩ ያሉት የተለያዩ ድርጅቶች ያለ አሜሪካ ድጋፍ የትም ሊደርሱ አይችሉም፡፡ ይሁን እንጂ በአሜሪካ በተፈጠረው የበጀት ቀውስ ምክንያት የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሃፊ ባንኪሙን በ2012/13 የድርጅቱ በጀት በ3% እንደሚቀንስ ገልፀዋል፡፡

 

ድህነት በአሜሪካ

በመላው ዓለም ላይ ያለውን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ እንዲሁም የጦርነትና የተፈጥሮ አደጋ ለመታደግ በየዓመቱ በቢሊዮን ዶላር ገንዘብ ከካዝናዋ እያወጣች የምትሰጠው አሜሪካ፤ አብዛኞቹ ዜጐቿ በችግር ውስጥ ተዘፍቀዋል ቢባል ለማመን ያስቸግራል፡፡ ነገር ግን እውነት ነው፡ ፡ሰሞኑን ለንባብ የበቃው News week መጽሔት Rich America, poor America በሚል ርዕስ ባስነበበው ጽሑፍ አያሌ አሜሪካዊያን በስራ ማጣትና በኑሮ ውድነት አሳራቸውን እየበሉ እንደሆነ ገልጿል፡፡ ይህም በሃብታም አሜሪካዊያን እና በድሃ አሜሪካዊያን መካከል ከፍተኛ ልዩነት አስከትሏል ብሏል፡፡

ሃብታሞቹ አሜሪካዊያን የሚበሉትን ምግብ ድሆች እንኳን ሊበሉት አይተውትም አያውቁም፡፡ የሀብታሞች መኖሪያና የድሆች መኖሪያ የተለያየ ነው፡፡ የአመለካከትና የግንዛቤ ልዩነትም በሁለቱም ጽንፍ ያሉትን ሰዎች አራርቋል፡፡ የሀብታሞች መዝናኛና የድሆች መዝናኛ ለየቅል ነው፡፡ ይሁንና ወደ 300 ሚሊዮን የሚጠጉት ዜጐችን ያቀፈችው አሜሪካ፤ በአንድ መንግስት ትመራለች፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ ልዩነቱ በጣም እየሰፋ በመምጣቱ በርካታ አሜሪካዊያን የድሆችን ጐራ ተቀላቅለዋል፡፡

በ19ኛው ክ/ዘመን የታሪክና የማህበረሰባዊ ጉዳዮች ፀሐፊ የነበሩት በኋላም የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት ቤንጃሚን ዲስራሊ ጠቅላይ ሚኒስትር ከመሆናቸው በፊት እ.ኤ.አ በ1845 The Rich and the poor በሚለው መጽሐፋቸው ላይ፣ በወቅቱ በእንግሊዝ ማህበረሰብ ውስጥ የቡርዣው ሥርዓት የወለዳቸው ከበርቴዎችንና ብዙሃኑን ምስኪን ዜጐች አነጻጽረው ባቀረቡት ጽሑፍ፣ “ሃብታሞች ድሆችን ረስተዋቸዋል፤ ድሆችም ሃብታሞችን ረስተዋል፡፡ አንድ ማዕከላዊ መንግስት ቢኖርም ድሆችን የሚያስተዳድርበትና ሃብታሞችን የሚያስተዳድርበት መንገድ የተለያየ ነው፡፡ የሀብታሞች ባህርይ እና የድሆች ባህርይ በጭራሽ አይገናኝም፡፡ የሃብታም ልጆች ትምህርት ቤትና የድሀ ልጆች ትምህርት ቤት የተለያየ ነው…” በማለት ገልፀው ነበር፡፡ ቤንጃሚን ዲስራሊ ከዛሬ 150 ዓመት በፊት ለእንግሊዝ ማህበረሰብ የፃፉት መጽሐፍ ዛሬም በአሜሪካዊያን ይሠራል፡፡

በስራ ማጣትና በኑሮ ወድነት የተማረሩ አሜሪካዊያን ባለፈው ጥቅምት ወር በነቂስ  አደባባይ በመውጣት ተቃውሞ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ በተለይም በኒውዮርክ ዎል ስትሪት የተባለውን ትልቁን የገበያ ማዕከል ለቀናት በቁጥጥር ስር በማድረግ በአሜሪካ መንግስትና የአገሪቷን ሀብት በገፍ የሚቀራመቱት ባሉዋቸው የግዙፎቹ ኩባንያዎች ባለቤቶች ላይ ቁጣቸውን ማሰማታቸው አይዘነጋም፡፡

ዋነኛ መፈክራቸውም “99% የምንሆን ብዙሃን አሜሪካዊያን ተገልለን 1% የሚሆኑት የትላልቅ ኩባንያ ባለሀብቶች የአገሪቷን ሃብት ይጠቀማሉ” የሚል ነው፡፡ ከዎልስትሪት ተነስተው እስከኒውዮርክ አደባባይ ድረስ ባደረጉት ሰልፍ ባለሀብቶችን ክፉኛ ተቃውመዋል፡፡ ይሄንን ተቃውሞ ተከትሎም ዋሽንግተን፣ ቺካጐ፣ ኦሃዮ፣ አትላንታ፣ ቦስተን፣ ኦክላንድ እና ካሊፎርኒያን ጨምሮ በ70 ከተሞች ተመሳሳይ ተቃውሞ መካሄዱ ይታወቃል፡፡

በተጨማሪም አብዛኛውን የአገሪቱን ግብር የሚከፍሉት 99% የሚሆኑት ሆነው ሳለ መንግስት ለግል ባንኮችና የፋይናንስ ተቋማት የሚያደርገውን ድጐማ ተቃውመዋል፡፡ በዋሽንግተን Freedom Plaza አካባቢን በመቆጣጠር ያሰሙት መፈክር “Banks are cancer”, “We” are “The 99 percent,“ therefore conservatives must necessarily apologies for the 1 percent” የሚል ነበር፡፡

የአሜሪካ የኢኮኖሚ ቀውስና የሥራአጥ ቁጥር ማሻቀብ ባየለበት በዚህ ጊዜ የፕሬዚዳንታዊ ምርጫም በአገሪቱ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ የሪፐብሊካንን ፓርቲ ወክለው የሚወዳደሩት እጩዎች በአሜሪካ የተከሰተውን የሃብት ክፍፍል አንስተው የመፍትሔ ሃሳብ ከማቅረብ ይልቅ፣ በቀጥታ ለችግሩ ተጠያቂ ያደረጉት ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማን ነው፡፡ በተለያዩ መድረኮችም አሜሪካ ለገባችበት ቀውስ ተጠያቂው ኦባማ ናቸው በማለት ክፉኛ ተችተዋቸዋል፡፡

ምናልባትም የሃብት ክፍፍሉ ውስጥ የላይኛውን ቦታ ከያዙት አብዛኞቹ የሪፐብሊካኖች ወዳጅ ከመሆናቸው ሌላ ሪፐብሊካን እጩዎችም ራሳቸው ባለሀብቶች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ሚት ሮሚኒ እጅግ የናጠጡ ባለሀብት ናቸው፡፡ በወር ከትላልቅ ድርጅቶቻቸው ከ2 ሚሊዮን በላይ የተጣራ ገቢ አላቸው፡፡ ኒውት ጊንግሪትም ቢሆኑ ባለሀብት ናቸው፡፡ በመሆኑም የሀብት ክፍፍሉን ማንሳት በራሳቸው ላይ ጣት መቀሰር መሆኑን በመረዳት ጣታቸውን በኦባማ ላይ አነጣጥረዋል፡፡

እንግሊዛዊው ፀሐፊ ቤንጃማን ዲስራሊ በመጽሐፋቸው ላይ፣ እውነተኛ ባለሀብቶች በማህበረሰቡ ውስጥ በሚፈጠረው የሃብት ልዩነት ደስተኞች እንዳልሆኑ ጠቅሰዋል፡፡ በተጨማሪም በካፒታሊዝም ኢኮኖሚ ውስጥ ሀብት በጥቂቶች ብቻ የሚሰበሰብ ከሆነ የካፒታሊዝም ሥርዓት ሕጋዊ ሊሆን አይችልም በማለት ዲስራሊ በመጽሐፋቸው ላይ አብራርተዋል፡፡

የበርክሌ ዩኒቨርስቲ ኢኮኖሚስቱ ኢማኑኤል ሴዝ፣ እ.ኤ.አ ከ1970 ዓ.ም ጀምሮ በአማካይ የአሜሪካዊያን ወንዶች ገቢ እንዳሽቆለቆለ ይናገራሉ፡፡ በተመሳሳይም ዝቅተኛ ኑሮ ውስጥ ከሚገኙት 75 በመቶ ያህሉ ቤተሰቦች ገቢያቸው ወርዷል፡፡ በተቃራኒው እ.ኤ.አ ከ1979 ዓ.ም ወዲህ ደግሞ 1 በመቶ የሚጠጉት ሃብታሞች ገቢያቸው በእጥፍ አድጓል፡፡ እጅግ በጣም ሃብታም (Supper rich) የሚባሉት 0.01 በመቶ የሚደርሱት ደግሞ በተመሳሳይ ዓመት በሰባት እጥፍ ገቢያቸው ጨምሯል በማለት ገልፀዋል፡፡

አሜሪካዊያን ከዚህ በፊት በአገራቸው ታላቅነት ኩራት የሚሰማቸው ቢሆንም፣ አሁን ግን ከደረሰባቸው ከባድ ችግር የተነሳ በአገራቸው ላይ ተስፋ ወደ መቁረጥ ተቃርበዋል፡፡

ዛሬ በአሜሪካ ለተፈጠረው የሃብት ልዩነት መስፋት መንስኤው የኒዮ ሊበራሊዝም ኢኮኖሚስቶች ያመጡት ጣጣ ነው በማለት የኒዮሊበራሊዝምን ኢኮኖሚ ይተቻሉ፡፡

የሊበራሊዝም ኢኮኖሚ በ19ኛው ክ/ዘመን በአሜሪካ ሰፊ ተቀባይነት አግኝቶ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ በኋላ እ.ኤ.አ በ1930 ዓ.ም በአለም ላይ ታላቁ የኢኮኖሚ ቀውስ (The Great depression) ሲከሰት የሊበራሊዝም ኢኮኖሚ የሚከተሉ አገራትን ጠቅላላ ይዞ ገደል ገባ፡፡

በአሜሪካ የፈጠረው የሃብት ክፍፍል በአንድ ትውልድ ውስጥ ከፍተኛ ልዩነትን አስከትሏል፡፡ ለምሣሌ በጣም ሃብታም የሚባሉት አሜሪካዊያን የሚኖሩት የሃብታሞች መኖሪያ ብቻ በሆኑት በማንሃተን፣ በሳንታ ሞኒካ፣ በማሊቡ፣ በቦስተን እና በቢቨርሊ ሂል አካባቢ ሲሆን፣ እነዚህ አሜሪካዊያን አብዛኞቹ ድሆች አሜሪካዊያን እንዴት እንደሚኖሩ እንኳን አያውቁም፡፡ በሌላ በኩል በሃብታሞች መኖሪያ የሚወለዱ ልጆች ከህጋዊ ጋብቻ የሚወለዱ ሲሆን፣ በድሆች መኖሪያ የሚወለዱት የተወሰኑት በጋብቻ ቢሆንም አብዛኛዎቹ ግን ከጋብቻ ውጭ የሚወለዱ ናቸው፡፡

ይሁን እንጂ በአሜሪካ ለተፈጠረው ችግር ተጠያቂው የኒዮ ሊበራሊዝም ኢኮኖሚ መስፋፋቱ አይደለም በማለት የሚከራከሩም አሉ፡፡ በኢኮኖሚ ሥርዓቱ ሰዎች ሁሉ ያለምንም ገደብ እና ተጽእኖ እኩል ተጠቃሚ የሚሆኑበት እንጂ አንዱን ነፃ አድርጐ ሌላውን የሚያግድበት ሥርዓት አልተዘረጋም ባይ ናቸው፡፡ ችግሩ በአሜሪካ ከ1970ዎቹ ወዲህ የስራ ባህል እየቀነሰ መምጣትና ሰዎች በመዝናኛ እና በአልባሌ ተግባራት በስፋት መሰማራታቸው ነው ይላሉ፡፡ በአሜሪካ ዋነኛው ችግር የስራ መጥፋት አይደለም፡፡ ነገር ግን የሕብረተሰቡ የስራ ዝንባሌ መቀነሱ ነው በማለትም እነዚህ ወገኖች ይከራከራሉ፡፡ በተጨማሪም በአገሪቱ ቀን ቀን የሚለቀቁት ስፍር ቁጥር የሌላቸው የቴሌቪዥን ቻናሎች የአሜሪካዊያንን ቀልብ በመውሰድ ስራ ፈት አድርጓቸዋል በማለት ያብራራሉ - በብዙ ቦታዎች በሳምንት ከ40 ሰዓት በታች እንደሚሰሩ በመግለፅ፡፡

በሌላ በኩል የወንጀል እና ሕገወጥነት መስፋፋት ለስራ ባህል መቀዛቀዝ ምክንያት እንደሆነ ይነገራል፡፡ አሁን አሜሪካ ለገባችበት ቀውስ በኢኮኖሚ ስርዓቱ ላይ ማሳበብ ብቻውን መፍትሔ የለውም የሚሉ ተንታኞች፤ በአሜሪካ የዜጐች የስነ ምግባር መውረድ፣ የሃይማኖተኝነት መላላት፣ የትዳር መፍረስና የቤተሰብ አንድነት መናጋት እንዲሁም ሌሎች ተመሳሳይ ችግሮችን እንደምክንያት ያስቀምጣሉ፡፡

በአሜሪካ ከጆርጅ ዋሽንግተን አንስቶ እስከ ጆን ኦፍ ኬኔዲ ድረስ የነበሩ መሪዎች ጠንካራ እምነትና የአገር ፍቅር ነበራቸው፡፡

በቤተሰብ ደረጃም ሆነ በማህበረሰብ ውስጥ አንድነት ነበር፡፡ ይሁንና በአሁኑ ወቅት እነዚያ ማህበራዊ እሴቶች መናዳቸው በአጠቃላይ የኅብረተሰቡን ህልውና እንዳናጋው ይገልፃሉ፡፡ በሃብታሞችና በድሆች መካከል የተፈጠረው ሰፊ ልዩነትም የኅብረተሰቡ አኗኗር ያመጣው ውጤት ነው ባይ ናቸው፡፡ በመሆኑም አሜሪካ አሁን ከገባችበት ቀውስ እንድትወጣ ጠንክሮ መስራት፣ የተደራጀ ቤተሰብ መመስረት፣ የማህበረሰብን አንድነት ማጠናከር እና እምነትን ማጐልበት ያስፈልጋል በማለት ያብራራሉ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የምርጫ ክርክር ላይ ያሉት ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በበኩላቸው በሃብታምና በድሃው መካከል ያለው ሰፊ ልዩነት መፍትሄ እንደሚበጅለት ለአሜሪካ ህዝብ ቃል ገብተዋል፡፡

 

 

Read 3701 times Last modified on Saturday, 04 February 2012 13:08