Saturday, 26 September 2015 08:18

የዩኒቨርስቲው በር ተሰብሯል! ዐምዶቹም ተነቃንቀዋል!

Written by  ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ (የቀድሞው የአ.አ ዩ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(15 votes)

         በዚህ ጽሑፍ የማነሣቸው ርእሰ ጉዳዮች በአራት የተከፈሉ ናቸው፡፡ አንደኛው፡-  ስለ ዩኒቨርስቲ አጠር ያለ መሠረታዊ ሐሳብ እና የአካዳሚያዊ ነጻነት መርሖዎች፤ ኹለተኛ፡- የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመንግሥት መዳፍ ሥር ስለ መውደቅ፤ ሦስተኛው፡- የፕሬዝዳንት ዶ/ር አድማሱ ጸጋዬን ገጸ ሰብእና (persona) በኹለት ወጎች ሥር ማብራራት ሲኾን፣ አራተኛው፡- የርእሰ ጉዳዮቹ ማጠቃለያ ነው፡፡

(ሀ) ዩኒቨርስቲ እና አካዳሚያዊ ነጻነት
ከኹሉ አስቀድሞ አንባቢ ልብ እንዲልልኝ የምፈልገው፣ በዚህ ጽሑፍ የቀረቡት አስተያየቶች እና ምልከታዎች እንደ አንድ በፍልስፍና መስክ የተሰማራ ሰው መጠየቅ ያለባቸውን ነገሮች ለመጠየቅ ያለሙ ናቸው፡፡ ይህም ሐሳቦቹ እና ምልከታዎቹ በአጠቃላይ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ከመከጀል ብቻ ሳይኾን ሳንጠይቃቸው ብናልፍ ትክክል አይኾንም ከሚል እምነት በመነሣት ነው፡፡
የዚህ ጽሑፍ አንደኛው ዓላማ የሚያጠነጥነው፣በዩኒቨርስቲ ምንነት ዙሪያ በመኾኑ ስለ ዩኒቨርስቲ ጠቅለል ያለ ዕሳቤ እና በተጨማሪም ዩኒቨርስቲን፣ “ዩኒቨርስቲ” የሚያሰኙትን ርእይ፣ ተልእኮ እና ግብ ማሳየት ነው፡፡
የዩኒቨርስቲ  ዋነኛው ርእይ እና ተልእኮ፣ ዕውቀት ማፍለቅ ሲኾን፣ ያፈለቀውንም  ለተማሪዎች ማስተላለፍ እና መተግበር ነው፡፡ ይህም ማለት የዩኒቨርስቲ ዋነኛው ተግባር ከዘመን ዘመን እየተሸጋገረ አኹን ላይ የደረሰውን ዕውቀት መጠበቅ እና መከባከብ እንዲኹም በተሟላ መልኩ ለትውልዱ ማሳወቅ እና ማስተላለፍ ነው፤ በተጨማሪም ከዚህ በፊት ያልነበረውን ሐሳብ እና ዕውቀት መፍጠርም ነው፡፡
ዩኒቨርስቲ የአንድ ሀገር ምሁራዊ ህልውና እና የሥልጣኔ ዕድገት መገለጫ በመኾኑ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ከሌሎች ተቋማት በተሻለ የሕግ እና የነጻነት መብት ሊሰጠው ይገባል፡፡ እዚህ ላይ ትልቁ የጀርመን ፈላስፋ ካርል ያስፐርስ ስለ ዩኒቨርስቲ ምንነት ሲገልጹ፤ ዩኒቨርስቲ በመንግሥት ቁሳዊ እና ፋይናንሳዊ ድጎማ የሚተዳደር ቢኾንም ከሌሎች ተቋማት ለየት የሚያደርገው የራሱን ርእይ እና ተልእኮ ቀርጾ የሚተገብር እና የሚንቀሳቀስ አንጻራዊ ነጻነት ያለው በመኾኑ ነው፡፡ ለዚህም ነው፣ የዩኒቨርስቲ መምህራን የመንግሥት ደመወዝተኛ ቢኾኑም እንደ ሌሎቹ የመንግሥት ተቋማት ሠራተኞች (civil servants) የመንግሥትን ፖሊሲ ለማስፈጸም የተቀጠሩ አገልጋዮች የማይኾኑት፡፡
በተጨማሪም የዩኒቨርስቲ ዐቢይ ተልእኮ የምንለው፣ ተቋሙ እውነት ላይ ለመድረስ ማንኛውም ጉዳይ የሚጠየቅበት እና የሚመረመርበት ማእከል መኾኑ ነው፡፡ ይህንንም ተልእኮ በአግባቡ ለመወጣት ዩኒቨርስቲ በልዩ ልዩ ተቋማት ሥር ለሚያካሒደው ጥናት እና ምርምር ያልተገደበ ነጻነት እና  መብት ይኖር ዘንድ ግድ ይላል፡፡ ዩኒቨርስቲ ነጻነቱን በማስቀደም ነው፣ የዕውቀት መዲና እና መፍለቂያ ኾኖ  ከዘመን ዘመን እየተሸጋገረ የመጣው፡፡ የዩኒቨርስቲ ነጻነትን ባነሣን ቁጥር የአካዳሚያዊ ነጻነት ጥያቄ ቁልፍ የኾነ ድርሻ ያለው መሠረታዊ ሐሳብ እንደ ኾነ ግልጽ ነው፡፡
(ለ) አካዳሚያዊ ነጻነት
አካዳሚያዊ ነጻነት ማለት ማንኛውም መምህር በሥራ ገበታው ላይ ሊኖረው የሚገባውን ነጻነት እና መብት የሚደነግግ  የሕግ መርሕ ነው፡፡ አኹን በዓለም ላይ በሰፊው ተቀባይነት ያገኙት የአካዳሚያዊ ነጻነት መርሖዎች፣ የዛሬ አንድ መቶ ዓመት ገደማ በአሜሪካን ሀገር በጉዳዩ ዙሪያ የጥናት ስብሰባ ከተደረገ በኋላ ተሳታፊዎቹ የሚከተሉትን አራት ነጥቦች አቅርበው፣ ሕጋዊ ከለላ ለማሰጠት በመቻላቸው እነሆ እስከ አኹን ድረስ ወሳኝ የኾኑ የአካዳሚያዊ ነጻነት መርሖዎች እና አዕማድ ኾነዋል፤ ፍሬ ሐሳቦቹም እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡
1. የመመራመር እና የማሳተም ነጻነት
ማንኛውም መምህር በፈለገው እና በመረጠው ርእስ ምርምር እና ጥናት የማካሔድ ሙሉ መብት አለው፡፡ በተጨማሪም በምርምር ያገኘውን ውጤት ያለምንም ዕንቅፋት እና ገደብ የማሳተም መብት አለው፡፡
2. መምህር በክፍል ውስጥ ስለሚኖረው ነጻነት
ማንኛውም መምህር ለሚያስተምረው ትምህርት ይኾናል የሚለውንና የሚበጀውን የማስተማርያ ጽሑፎችን የማካፈል እንዲኹም ማንኛውንም ትምህርት ነክ የኾኑ ጉዳዮችን በውይይት እና በጥያቄ ያለምንም ጫና ለተማሪዎቹ ሊያቀርብ ይችላል፡፡
3. በትምህርት ተቋም ቅጽር ውስጥ የሚኖር መብት/Intramural Right)  
ማንኛውም መምህር አቅሙና ችሎታው እስከ ፈቀደ ድረስ የአንድን የዩኒቨርስቲ አስተዳደር እና አመራር ሳይፈራ እና ሳይሸማቀቅ የማሔስ እና የመተቸት ሙሉ መብት አለው፡፡
4. ከትምህርት ተቋሙ ቅጽር ውጭ ስላሉ ጉዳዮች የሚኖር መብት(Extramural Right)
ማንኛውም መምህር በሥራ ገበታው ላይ እያለ የሀገሩን የአስተዳደር፣ የፖለቲካ እና የማኅበራዊ ጉዳዮችን የመተቸት ሙሉ መብት አለው፡፡
እነዚህ ከላይ የተገለጹት መርሖዎች በሕግ ማህቀፍ ሥር መካተታቸው፣ በአካዳሚው ዓለም ውስጥ ለተሰማሩ መምህራን ሥራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑና እንዲኹም ለወከባና ለእንግልት እንዳይዳረጉ መከታ ይኾናቸዋል፡፡
፪.
 አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን ለመቆጣጠር የተደረገው ሒደት
ኢሕአዴግ ስለ ፖለቲካ ስትራቴጅና አቅጣጫ  በ1997 ዓ.ም. ባወጣው ሰነድ ላይ፤ ስለ ሀገሪቱ ምሁራን የሚከተለውን ግምጋሜ አቅርቧል፡፡ ግምጋሜው የታየበትን መነጽር፣ ከዚህ በታች ስለምናቀርበው የዩኒቨርስቲው በመንግሥት ቁጥጥር ሥር መዋል መንደርደሪያ ይኾነናል፡፡
እንደ ኢሕአዴግ አመለካከት፣ምሁሩ ምንጊዜም ወደ ሥልጣን ማማተሩ ስለማይቀር በተቻለ መጠን የሥልጣን  መወጣጫ መንገዱ ተዘግቶ መያዝ አለበት፡፡ ይህን ለማሳካት ምሁሩ የንዋይ ፍላጎቱ በተቻለ መጠን እንዲሟላለት ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ በመኾኑም በሙያው ዙሪያ ባሉ ሳንካዎችና ጥቅማጥቅሞች ተጠምዶ ወደ ሀገራዊ ጥያቄዎች ሳይሻገር በእዚያው ማጥ እየዳከረ እንዲኖር ማድረግ ይኖርበታል፡፡
ከዛሬ ስድስት መቶ ዓመት በፊት፣ ታላቁ ኢትዮጵያዊ ሊቅ፣ ቅዱስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ፣ ከደረሷቸው መጻሕፍት መካከል ‘መጽሐፈ ምስጢር’ ብለው በሰየሙት ድርሳናቸው ውስጥ፣ ሳይማሩ እናስተምራለን ብለው ስለተነሡ የቤተ መንግሥት ባለሟሎች የሚከተለውን ብለው ነበር፡፡ ከአባ ጊዮርጊስ የወሰድነው ጥቅስ ሊቁ ለሌላ ጉዳይ የተናገሩት ቢኾንም ለያዝነው ርእስ የመንፈስ ቅርበት አለው ብለን ስለምናምን በዚሁ አገባብ የጠቀስነው መኾኑን ለአንባብያን እያስታወስን ጥቅሱን ያጎረሱንን መሪጌታ ሳናመሰግን አናልፍም፡፡
“እሉ እሙንቱ [መነኮሳት] እለ ቀዲሙ የዐየሉ ገዳመ አድባረ ወበዐታተ ወድኅረ ይትዋሐውሑ በአዕጻዳተ ነገሥት፡፡ ቀዲሙ  ከመ ኢይትመሀሩ መጻሕፍተ ነቢያት ወሐዋርያት በንኡሶሙ ወጽኡ ገዳመ ወተግኅሡ እምዐጸደ ቤተ ክርስቲያን እንተ ይእቲ  እመ ኩልነ ዘኢይነጽፍ ሐሊበ አጥባቲሃ፡፡ ወድኅረኒ  ኢይፈጽም ገድሎሙ በጽማዌ ውስተ ገዳም  ቦኡ ውስተ አብያተ ነገሥት ወበዊኦሙ ከመ ኢያርምሙ መሀሩ ዘኢትምህሩ ወሰበኩ ዘኢያእመሩ፡፡ ይልህቅኑ ሕፃን ዘእንበለ ሐሊበ አጥባተ እሙ ይሌቡኒ መነኮስ ዘኢተምህረ መጻሕፍተ ነቢያት ወሐዋርያት ከመ ይኩን መመህረ ለሰማዕያን ፡፡ ለሀወት ገዳም በኃጢአቶሙ ወለሀዋ አድባረ ምኔታት ወኢረኪቦቶሙ፡፡
“ለሀወት ቤተ ክርስቲያን በእንተ ዘነሠቱ አናቅጺሃ ነቢያተ ወነክነኩ አዕማዲሃ ሐዋርያተ፡፡ ወሠርዑ ሎሙ ሕገ ወሥርዓተ ዘኢይወጽአ እምእስትንፋሰ አፉሁ ለእግዚአብሔር ፡፡”
ትርጉም፡-
“እነዚህ [መነኮሳትም] ቀድሞ በበርሀ በተራሮችና በዋሻዎች የሚዘዋወሩ በኋላ ግን በነገሥታት ዐፀዶች  ውስጥ የሚመላለሱ ናቸው፡፡ ቀድሞ በታናሽነታቸው ጊዜ የነቢያትና የሐዋርያትን መጻሕፍት እንዳይማሩ የጡቶቿ ወተት የማይደርቅ የኹላችን እናት ከኾነች ከቤተክርስቲያን ዐፀድ ርቀው ወደ ገዳም ወጡ፡፡ ኋላም ገድላቸውን በገዳም ውስጥ ኾነው በጭምትነት እንዳይፈጽሙ ወደ ነገሥታት ቤት ይገባሉ፤ገብተውም ዝም እንዳይሉ ለራሳቸው ያልተማሩትን ያስተምራሉ፤የማያውቁትንም ይሰብካሉ፣ሕጻን ያለ እናት ጡት ያድጋልን? መነኩሴስ ለሚሰሙ ሰዎች አስተማሪ ይኾን ዘንድ ያልተማረውን የነቢያትና የሐዋርያትን መጻሕፍት ያስተውላልን?
“ቤተ ክርስቲያን ስለ ኃጢአታቸው አለቀሰች፡፡ የገዳማት ተራሮችም እነርሱን ባለማግኘታቸው አለቀሱ፤ቤተ ክርስቲያን ነቢያት በሮቿን ስላፈረሱ፣ ምሰሶዎቿ ሐዋርያትንም ስለነቀነቁ አለቀሰች፡፡ ከእግዚአብሔር አንደበት ያልወጣውንም ሕግና ሥርዓት ለራሳቸው ሠሩ፡፡”
ከላይ በጥቅስ ከተቀመጠው የአባ ጊዮርጊስ ትዝብት የሚከተሉትን ፍሬ ነገሮች ነቅሰን ማውጣት እንችላለን፡፡ የአመራረጣችን መሠረት፣ ባለንበት ወቅት አንጋፋው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እንዴት ሙሉ በሙሉ በመንግሥት መዳፍ ሥር እንደ ወደቀ  የጥቅሱ መንፈስ ማሳያ ኾኖ ስላገኘነው ነው፡፡ አኹን በሥልጣን ላይ ያለው ሥርዓት፣ ከገጠር ወደ ከተማ እንደ መጣው ኹሉ፣ የአባ ጊዮርጊስም ‘ምሁራን’ ከበረሓ ወደ ቤተ መንግሥት የመጡ በመኾናቸው ተመሳሳይነታቸው ከፍ ያለ ነው፡፡
የቅዱሱን ተግሣጽ በኹለት ምድብ በመክፈል በመጀመሪያ፣ የትዝብታቸውን መነሻ ቀጥለን ደግሞ፤ ድርጊቱ ያስከተለውን አሉታዊ ዉጤት እናያለን፡፡
ሀ. የትዝብታቸው መነሻ፡-
የተወሰኑ ምእመናን መንፈሳዊ ሕይወት በመፈለግ ወደ ዋሻ፣ አድባራት እና በረሓ ገቡ፡፡ መንፈሳዊ ተጋድሎ አልኾንላቸው ሲል በረሓውንና ዋሻውን ለቀው ወደ ቤተ መንግሥት ጠጋ አሉ፤ ወደ ቤተ መንግሥቱም አዘውትረው መመላለስ ጀመሩ፡፡ ከማዘውተራቸው ብዛት የቤተ መንግሥቱን አመኔታና ይኹንታ ተቀዳጁ፡፡ የሹማምንቱን ቅቡልነት ቢያገኙም በየበረሓው ወጣትነታቸውን በከንቱ አባክነው በዘመኑ ከቤተ ክርስቲያን ብቻ ይገኝ የነበረውን ትምህርት ሳያገኙ ስለቀሩ፣ የቤተ መንግሥት ባለሟልነታቸውን ተጠቅመው፣ ያልተማረውን ምእመን እናስተምራለን ብለው ተነሡ፡፡   
ለ. ድርጊቱ ያስከተለው አሉታዊ ውጤት፡-
አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ፤ኹኔታው ያስከተለውን አሉታዊ ውጤት በኹለት ዘይቤ (Metaphor) ያስረዳሉ፡፡ እነዚህም፡- “በሮቿ ተሰበሩ” እና “አዕማዷ ተነቃነቁ” የሚሉት ናቸው፡፡
በሮቿ ተሰበሩ፡-
“በሮቿ ተሰበሩ” ከሚለው ዘይቤ ውስጥ በዛ ያሉ ምልከታዎችን መንቀስ ይቻላል፡፡ በር ስንል የሚፈለገው የሚገባበት፣ መግባት የሌለበትን ደግሞ  መቆጣጠሪያ ሥርዓት መኾኑን ነው የሚያመለክተው፡፡ በመኾኑም የተናጋና የተሰበረ በር ያለው ተቋም፤ ማንም እንዳሻው የሚገባበትና የሚወጣበት፣ ሥርዓት አልባ ጎዳና ኾኗል ማለት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የራሷን ልዕልና አስጠብቃ መዝለቅ ተስኗታል እንደማለትም ነው፡፡
አዕማዷ ተነቃነቁ፡-
የአንድ ቤት ዐምዱ ወይም ምሶሶው ከተነቃነቀ፣ጨርሶ የመፈራረሱ ጉዳይ ተቃርቧል ማለት ነው፡፡ በአባ ጊዮርጊስ ዕይታ፤ የቤተ ክርስቲያኒቷ ዶግማ፣ ቀኖና፣ ትውፊት በአጠቃላይ አስተምህሮዋ ተናግቷል ማለታቸውን ያሳያል፡፡ በተፈጠረው አግባብ የለሽ አካሔድና ቀውስ የቤተ ክርስቲያኒቷ አበው አዘኑ፤ አለቀሱም፡፡
ወደ ጥንተ ነገራችን ስንመለስ፤የአባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ አቀራረብ፣ አኹን በዩኒቨርስቲው ቅጥር ውስጥ የሚካሔደውን ኹኔታ በሚገባ ለመረዳት እንደ መነጽር ይኾነናል፡፡ ከኹሉ አስቀድሞ፣ የአባ ጊዮርጊስ ‘መምህራን’ እናስተምራለን ብለው የተነሡት ራሳቸው ሳይማሩ ያልተማሩትን ሰዎች ለማስተማር ነው፡፡ በእኒህ ኹለት ዓመታት ውስጥ፣ በዩኒቨርስቲው ግቢ ውስጥ እናሠልጥን ብለው የተነሡት የመንግሥት ሹመኞች ራሳቸው በሚገባ ሳይማሩ፣ አልተማሩም የሚሏቸውን ሳይኾን፣ የተማሩትን ክፍል ለማስተማር መነሣታቸው ነው፡፡ ከዚኽ አንጻር አባ ጊዮርጊስ የታዘቧቸው መምህራን ከአኹኖቹ እናስተምር ባዮች በእጅጉ የተሻሉ ኾነው እናገኛቸዋለን፡፡ ይኸውም የቀድሞዎቹ፣ ራሳቸው ባይማሩም እናስተምር ያሉት ያልተማሩትን ሲኾን የእኛዎቹ ግን እናስተምር ብለው የተነሡት የተማሩትን በመኾኑ ነው፡፡ አባ ጊዮርጊስ በዚህ ዘመን ቢኖሩ ኀዘናቸው ምን ያኽል በበረታ ነበር!!
አባ ጊዮርጊስን በእጅጉ ያሳዘናቸውና ያስገረማቸው፣ ቤተ መንግሥት በፍጥረቷ የአስተዳደር መንገድ መቀየስ እንጂ የዕውቀት ምንጭ ወይም የምሁርነት ምኩራብ ሳትኾን፣ ዐዋቂዎች ነንና እናስተምር እያሉ የሚነሡባት ማእከል ኾና ስላገኟት ነው፡፡ አኹን ወዳለንበትም ጊዜ ስንመጣ፣ ብዙዎችን እያሳሰበ ያለው በየዩኒቨርስቲው እናሠልጥን እያሉ የሚመጡት ሰዎች አኳኋን ነው፡፡ ልክ እንደ አባ ጊዮርጊስ ‘ምሁራን’ አስቀድመው ወደ በረሓ ከወጡ በኋላ ተመልሰው ቤተ መንግሥቱን በቁጥጥራቸው ሥር አዋሉ፡፡ ከዚያም ቤተ መንግሥቱም ዩኒቨርስቲውም አይቅርብን ብለው የዩኒቨርስቲውን መምህራን እናስተምራለን ብለው ብቅ አሉ፡፡
የአባ ጊዮርጊስ ኀዘን የበረታው፣ እኒኽ ‘ምሁራን’ ቤተ ክርስቲያን እንደ በሮቿ የምታያቸውን የነቢያት አስተምህሮ ስለሰበሩና በምሰሶ የተመሰሉትን የሐዋርያትን ዶግማና ቀኖና ስላነቃነቁ ነው፡፡ ብዙዎችን ታዛቢዎች በእጅጉ እያሳሰባቸው ያለው በአስተማሪነትና በአሠልጣኝነት ስም፤ ዩኒቨርስቲው የዕውቀት፣ የጥበብ፣ የምርምርና የመሳሰሉት ዕሴቶች ገዳም ኾኖ ሳለ፤ ሊቃነ ማእምራኑ (ፕሮፌሰሮቹ) ያስቀመጧቸውን ሚዛኖች (በሮች) በመስበር አዕማዷን ስላነቃነቁት ነው፡፡የቤተ ክህነቱ በር እንደተሰበረው ኹሉ፣ የየኒቨርሲቲውም በር ተሰብሯል ስንል ዩኒቨርስቲው ተማሪዎቹንም ኾነ መምህራኑን  መርጦ የመቀበል መብቱ ተገፍፎ፣ በፖለቲካ ትእዛዝ እንዲሞላ በመደረጉ፣ ማንም እንዳሻው የሚገባበትና የሚወጣበት ኾኗል ማለታችን ነው፡፡ የአዕማዷን መነቃነቅ በምናነሣበት ጊዜ በዋናነት የምናቀርበው፣ ዩኒቨርስቲው የነበረው የማስተማር ሥነ ዘዴ ተሽሮ፣ ከፖለቲካ ኃይሉ በመጣ ማዘዣ፣ እነርሱ ይበጃል የሚሉትን አካሔድ ተግባራዊ እንዲያደርግ መገደዱን ነው፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚኾነው፣ ከቢፒአር እስከ ቢኤስሲ እና አንድ ለአምስት አደረጃጀትን መምህራኑ ሳይመክሩና ሳይዘክሩበት፣ ዩኒቨርስቲው እንዲከተል መደረጉ ነው፡፡  የአባ ጊዮርጊስ ‘ምሁራን’፣ የመንግሥትን ኃይልና ቤተ ክርስቲያንን ገና በሚገባ ያልተቆጣጠሩ ሲኾን፣ የአኹኖቹ ምሁሮች ግን ሥልጣንን ሙሉ በሙሉ ለያዙ ኃይሎች ተጠሪዎች ናቸው፡፡ በመኾኑም ከንኡሳን (ደቃቂን) ሓላፊዎች  እስከ ዐቢይ አለቃው - ፕሬዝዳንቱ፣ ድረስ ለቤተ መንግሥቱ የፖለቲካ ቀኖና ተገዥና  ተኣማኒ በኾኑ እሺ ባዮች እንዲያዝ ተደርጓል፡፡  
እውነተኛ ዩኒቨርስቲያዊ ይትበሃል ተሽሮ፣ የበረሓ ጀግኖች እንዳፈተታቸው የሚናኙበት ኾነ፡፡ የመማር ማስተማር ሒደቱንም፣ ዩኒቨርስቲያዊ ልዕልናው ስለ ተገፈፈ ሳይንሳዊና ሞያዊ አሠራሩ ተሻረ፡፡ በቦታውም ከፖለቲካው ጽሕፈት ቤት በሚመነጭ ኢሕአዴጋዊ ትእዛዝ በሩን አፈረሱት፤ ዐምዱንም አነቃነቁት፡፡ ካርል ያስፐርስ የገለጹት ‘አማናዊው ዩኒቨርስቲ’ እና እውነተኞቹ ምሁሮቿ ስለ እነዚህ ሰዎች አድራጎት አብዝተው ያዝናሉ፡፡ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ሲቋቋም፣ ሊቁ ዶክተር እጓለ ገብረ ዮሐንስ፣ የበሩን ኹለት አዕማድ ‘በዕውቀት’ እና ‘በሠናይ’ (Virtue) በመመሰል የዘመሩለት፣ ማንም ሰው ሊያየው በሚችለው መልኩ መሠረቱ ተናጋ፤ ውድቀቱም ተቃረበ፡፡



Read 4698 times Last modified on Saturday, 26 September 2015 08:49