Saturday, 26 September 2015 08:18

“ልማቱን ላለማደናቀፍ” ሲባል … አገር እንዳይደናቀፍ!

Written by 
Rate this item
(27 votes)

“ከ100% በላይ ተጠናቋል” … ምን ማለት ነው?

    አንድ ወዳጄ ሰሞኑን ስልክ ደወለልኝና፤ “ፋብሪካው ከ100% በላይ ተጠናቋል ይባላል ወይ?” አለኝ፤ የመገረም ቅላፄ በሚያስተጋባ ድምፅ፡፡
“ምን ማለት ነው? እንዴት?” አልኩት፤ በመገረም ሳይሆን ግራ በመጋባት፡፡
“የሆነ ዜና ላይ ሰምቼው እኮ ነው … የሶላር ማምረቻ ምናምን መሰለኝ”
እኔ ከመናገሬ በፊት ሌላ አስገራሚ መረጃ አከለልኝ፡፡
“ደሞ እኮ ገና ሥራ አልጀመረም!”
“ምኑ ነው ታዲያ ከ100% በላይ ተጠናቋል የተባለው?”
ለአፍታ ያህል በጥልቅ ሀሳብ ውስጥ ሰጠምኩ፡፡
“ግን የት ነው የሰማኸው…. ከየትኛው ሚዲያ?” ከጥልቅ ሃሳብ ውስጥ መንጥቆ ያወጣኝ ከአንደበቴ ያፈተለከው የራሴ ጥያቄ ነበር፡፡ ወዳጄ መለሰልኝ፡፡
“ከመንግስት ሚዲያ ነው … ኢዜአ ወይም ኤፍ ኤም …” (ያው የመንግስት ሚዲያ የመንግስት ነው ብሎ መለሰኝ!)
እኔ የምላችሁ ግን …  “ፋብሪካው ከ100% በላይ ተጠናቋል” ሲባል… እውነት ምን ማለት ነው? ኢህአዴግ ስንት በታማበት የግንቦቱ ምርጫ እንኳን ከ100 ፐርሰንት በላይ ውጤት አምጥቷል አልተባለም! (ቦርዱማ 100% የተባለውንም አስተባብሏል!)
አሁን እኔ ለማወቅ የጓጓሁት ምን መሰላችሁ? ፋብሪካ ወይም ኮሌጅ አሊያም ሆስፒታል… ከ100% በላይ ተጠናቋል ሲባል… ምን እንደሚመስል ነው፡፡
እውነቴን እኮ ነው የምላችሁ … ከ100% በላይ የተጠናቀቀ ምንም ነገር ገጥሞኝ አያውቅም፡፡ ቆይ ግን? በምርጫስ ቢሆን … እገሌ ፓርቲ ከ100% በላይ በሆነ ድምፅ (ከየት መጥቶ?) አሸነፈ ይባላል እንዴ? (እዚህም ባይሆን እነ ሰሜን ኮሪጠ አካባቢ!) እኔ እንግዲህ ከወዳጄ መረጃ የተረዳሁት ምን መሰላችሁ? ከ100% በላይ ተጠናቋል ከተባለ፣ (ጦቢያ ምድር ማለቴ ነው!) “ሥራ አልጀመረም” ማለት ነው፡፡ (በምን ቋንቋ እንዳትሉኝ!)
መቼም ይሄን ዜና ያጠናቀረው ጋዜጠኛ፣ ቢያንስ “ቅጥ አምባሩ የጠፋ ዘገባ” በሚል ዘርፍ ዕውቅና ሊሰጠው ይገባል፡፡ ለነገሩ እንዲህ አይነት ልማታዊ ጋዜጠኞች በሽበሽ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የEBC ጋዜጠኞች፤ የመንግስትን የልማት ስራዎች ወይም ስኬቶች ያለ ቅጥ በማጋነን፣ በመለጠጥና በማስፋት … ማንም የሚያህላቸው እንደሌለ በአስር ጣቴ ልፈርምላችሁ እችላለሁ፡፡ (ኧረ ኢህአዴግም ይፈርምላቸዋል!) እኔ የምለው ግን… “የግነት ጋዜጠኝነት” የሚባል ኮርስ አለ እንዴ? የኢህአዴግ ካድሬዎች እንዲህ ያለውን የ“ልማታዊ ጋዜጠኞች” ግነት፣ ለልማት ካላቸው ውስጣዊ መነሳሳትና መቆርቆር የመነጨ ነው … በሚል ሊገመግሙት ይችላሉ፡፡ ግምገማቸው ትክክል ነው … አይደለም የሚለውን ለመወሰን ግን አስቸጋሪ ነው፡፡ (“ውስጣዊ መነሳሳት” እና “መቆርቆር” የሚሉት ሃሳቦች መለኪያቸው ምንድን ነው?)
በነገራችን ላይ በየዓመቱ መስቀል ሲመጣ ትዝ የሚለኝ ... EBC ለበዓሉ ከመጡ የውጭ ቱሪስቶች ጋር የሚያደርገው ኢንተርቪውና ከዚያ ውስጥ የሚሰራው ግነት የበዛበት ዜና ነው፡፡ ይሄ እንኳን ዓላማው የአገር ገፅ ግንባታ በመሆኑ ችግር የለውም፡፡ ግን እኮ ዓላማው እንደተባለው ከሆነ፣ መቅረብ ያለበት ለኛ ሳይሆን ለውጭ ሰዎች ወይም ለኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች ነበር፡፡ (እኛማ አረረም መረረም እየኖርነው ነው!)
ወደ “ልማታዊነት” ጉዳይ ልመልሳችሁ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በየሚዲያው ተከታትላችሁልኝ ከሆነ … ከመንግስት ባለስልጣናት እስከ ወረዳ አስተዳደር፣ ከከፍተኛ ባለሀብት እስከ ጥቃቅንና አነስተኛ ነጋዴዎች … ወዘተ ድረስ ምንም ሲናገሩ “… ልማታዊነት” የምትለዋን ቃል በግድ መደንገር አለባችሁ የተባሉ ይመስላሉ፡፡ “ልማታዊነት” ቃሉን ደጋግሞ በመጥራት ብቻ የሚመጣ ከመሰላቸው ቀለጡ፡፡ (አስማት እኮ አይደለም!)
እውነቱን ለመናገር ይሄ አካሄድ ግን ጤናማ አይደለም፡፡ ልማታዊ የመንግስት አመራሮችንም ሆነ ልማታዊ ባለሀብቶችን ፈፅሞ አይፈጥርልንም (ልማታዊ ደስኳሪዎችን እንጂ!)
ከዚያ ዘለል ካለም እንደ EBC ጋዜጠኞች ያሉ “የልማት ተቆርቋሪዎችን” ይፈጥርልን ይሆናል፡፡ ችግሩ ግን በአሁኑ ዘመን ጦቢያ የሚያስፈልጋት … በተግባር የሚሰራላት እንጂ የሚደሰኩርላት አሊያም የሚቆረቆርላት አይደለም፡፡ ልማታዊ ለመሆን ካድሬ መሆን አያስፈልግም (ለነገሩ ካድሬ ልማታዊ ሆኖ አያውቅም!) ልማታዊነት እኮ በተሰማራንበት ዘርፍ ውጤታማ ስራ ማከናወን ነው፡፡ ኪሳራ ሳይሆን ትርፍ ማስመዝገብ፡፡ ከመንግስትም ሆነ ከህዝብ የተሰጠንን ኃላፊነት በብቃት መወጣት ነው - ልማታዊነት!!
የተሰጣቸውን ትልቅ ኃላፊነት ሳይወጡ ቀርተው፤ “ልማቱ ወደፊት እንዲገሰግስ አስበን፣ ልማቱ እንዳይደናቀፍ ሰግተን፣ ልማቱ እንዳይቋረጥ ጓጉተን … ወዘተ” ሰበብ ድርደራ አያዋጣም፡፡
እንደውም ከተቻለ ከካድሬ በቀር ሌላው የመንግስት አገልጋይና ሹመኛ ሁሉ “ልማታዊ” የሚለውን ቃል ያለቦታው እንዳይደነጉር መመሪያ ቢጤ ቢወጣ ሸጋ ነበር፡፡ (በልማታዊነት ስም ሆድ አባብቶ ኃላፊነትን መሸሽ ተለምዷል!)
እናላችሁ … ሁሉም በተሰማራበት ሙያና በተሰጠው ኃላፊነት ቢለካ ነው የሚበጀው  “ልማታዊ …” የሚለውን ቃል በየንግግሩ መሃል በመሸጎጥ፣ እርስ በርስ መሸዋወድ ይብቃን! “ልማታዊ ነኝ” ያለ ሁሉ፤ ልማታዊነቱን በስራው ፍሬ፣ በውጤቱ ያስመዝን፡፡ ያኔ “ሀቀኛው ልማታዊ” እና “ሃሳዊው ልማታዊ” በግልፅ ይለያል፡፡ (ልማታዊነትን በመደስኮር የለማ አገር አላየንም!)
 ፖለቲካዊ ወጌን ከመቋጨቴ በፊት ሰሞኑን ለተለያዩ ሚዲያዎች ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የፀረሙስና ኮሚሽነሩ አቶ ዓሊ ሱሌይማን፤ ለአንድ ጥያቄ የሰጡትን ምላሽ እስቲ እንቆዝምበት፡፡
ከጋዜጠኛ የቀረበላቸው ጥያቄ እንዲህ ይላል፡- “ፀረሙስና ኮሚሽን፤ በከፍተኛ ባለስልጣናትና ባለሀብቶች ከሚፈፀሙ ሙስናዎች ይልቅ በትንንሽ ሙስናዎች ላይ የሚያተኩረው በፍራቻ የተነሳ ነው እንዴ?”
እሳቸውም እንዲህ ሲሉ መለሱ፤ “ሰው ይፈራል ባይባልም፣ የምንፈራበትም የማንፈራበትም ጉዳይ አለ፡፡ ትልቁ ነገር ግን ፍርሃቱ የግል ጉዳይ አይደለም፡፡ ልማት እንዳይደናቀፍ በመስጋት ነው፡፡ ልማቱን ላለማደናቀፍ በማለት ትንሹን ነገር አስበን፣ ትልቁ ነገር እንዳይሰናከል የምናደርገው ነገር ሊኖር ይችላል፡፡ በተረፈ ግን በራሳችን እንዲህ ብናደርግ እንዲህ ይመጣብናል የምንለው ነገር የለም፡፡”
እንዴ… ከዚህ በላይ ምን ይምጣ?! በትልቅ ስጋት … በከባድ ፍርሃት … እንዳሉ ያስታውቃሉ እኮ (ግን ያው ለልማቱ ሲሉ ነው!) “ልማቱ እንዳይደናቀፍ…” እየተባለ በሚደረገውም በማይደረገውም የተነሳ … አገሪቷ እንዳትደናቀፍ ሰጋሁ፡፡ (እንዴት አልሰጋ?!)
እኔ የምላችሁ… ቆይ ግን ልማት ምንድን ነው? ልማትና ሙስናስ? ትላልቆቹ ሙሰኞች በህግ ሲጠየቁ እንዴት ነው ልማቱ የሚደናቀፈው? ቁንጮዎቹ ሙሰኞች ይሄን ያህል አስፈሪ ሆነዋል ማለት ነው? በቁጥርስ ስንት ይሆናሉ? በመቶኛ ሲሰሉስ? ግን ግን እንዲህ የሚያስፈሩ እስኪሆኑ ድረስ ለምን ተጠበቁ? መቼ ነው “ልማቱ እንዳይደናቀፍ …” ከሚል ስጋት የምንወጣው?
ምናልባት እንዲህ ጉዳዩን እየበታተንን ስንፈትሸው አንዳች መላ፣ አንዳች ዘዴ ብልጭ ይልልን ይሆናል፡፡
በዚህ አንገብጋቢ ጉዳይ ላይ ጭንቅ ጥብብ ለማለት፣ የግድ የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር መሆን አይጠበቅብንም፡፡ ኢትዮጵያዊ መሆን ብቻ በቂ ነው፡፡ እናም እሳቸውንም ቢሆን ከሸክሙን እናግዛቸው (ለብቻቸውማ እዳ የለባቸውም!) መልካም ደመራ! መልካም መስቀል!

Read 4286 times