Saturday, 05 September 2015 08:42

ከ500 በላይ የሰበታ ከተማ አባወራዎች በመብራት እጦት ተሰቃየን አሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

   ከአዲስ አበባ 17 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የሰበታ ከተማ ነዋሪ የሆኑ ከ500 በላይ አባወራዎች፤ ከ7 አመታት በላይ በመብራትና ውሃ እጦት መሰቃየታቸውን በምሬት ተናገሩ፡፡
በሰበታ ከተማ ቀበሌ 08 ጐጥ 9 በሚባል አካባቢ ነዋሪ እንደሆኑ የገለፁት አቤቱታ አቅራቢዎቹ፤ ዋና ችግራቸው የመብራት፣ የውሃና የመንገድ መሠረተ ልማት አቅርቦት መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ከ4 አመት በፊት ከመንግስት ጋር በመተባበር መብራት፣ ውሃና መንገድ ለማሠራት እያንዳንዱ አባወራ 2500 ብር ማዋጣቱን ያስታወሱት አባወራዎቹ፤ አሁንም ድረስ ግን ምንም የተሟላላቸው ነገር እንደሌለ ገልፀዋል፡፡
“መንግስት በተቻለው አቅም በተለይ ለመብራት መሠረተ ልማት የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችንና ሠራተኞችን እየላከልን ነው” የሚሉት ነዋሪዎቹ፤ ችግሩ ያለው የከተማ አስተዳደሮቹ ጋ ነው ብለዋል፡፡ “የከተማ አስተዳደሩ እኛን እንደተቀረው የከተማ ነዋሪ አይመለከተንም፤ አጠገባችን ባሉ መንደሮች መብራትና ውሃ እያለ እኛ ጋ ግን የለም” ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ በተደጋጋሚ ለሚያቀርቡት የልማት ጥያቄ ቀና ምላሽ እንደማይሠጣቸውም ይናገራሉ፡፡
በመንግሥት ገንዘብ በውድ ዋጋ ተገዝተው ለአገልግሎት እንዲውሉ የተላኩ የኤሌክትሪክ ገመዶችና ቋሚ ምሰሶዎች በከንቱ ሜዳ ላይ እየባከኑ ነው ሲሉም ተናግረዋል፤ ነዋሪዎቹ፡፡
የኤሌክትሪክ ኃይል ዝርጋታው ለምን ዘገየ የሚል ጥያቄ ስናቀርብ ሁሌም የትራንስፎርመር አቅርቦት ችግር በምክንያትነት ይጠቀሳል ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ሶስት ትራንስፎርመር ለዚሁ ተብሎ ተገዝቶ እንደተቀመጠ ግን እናውቃለን ይላሉ፡፡
ከትናንት በስቲያ ከሰበታ ተነስተው አዲስ አበባ ወደሚገኘው የኦሮሚያ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ተሠባስበው በመሄድ አቤቱታ ማቅረባቸውን ለአዲስ አድማስ የተናገሩት አባወራዎቹ፤ የቢሮው ተወካይ ሃላፊም ወደ ከተማ አስተዳደሩ ባለስልጣናትና የሚመለከታቸው አካላት ዘንድ ስልክ በመደወል፣ በተለይ የመብራት አገልግሎቱ እስከመቼ እንደሚጠናቀቅ ጠይቀው፣ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል የሚል ምላሽ ማግኘታቸውን ነግረውናል ብለዋል፡፡  የውሃ ጥያቄያቸውም በከተማ አስተዳደሩ በኩል ምላሽ እንደሚያገኝ ተገልፆላቸዋል፡፡

Read 1245 times