Monday, 31 August 2015 08:55

ብትናገር ያምናውን፣ ብትፈትል አንድ ልቃቂት

Written by 
Rate this item
(13 votes)

      አንዳንድ ታሪክ ካልተደጋገመ ሰሚ አያገኝም፡፡ የሚከተለው እንደዚያ ነው፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ጋብሮቮ ወደ ሩቅ መንደር ሄዶ ሲመለስ ብርቱካን ይዞ መጣ፡፡ የመንደሩ ሰዎች “ብርቱካን ስጠን”፣ “ስጠን” እያሉ አስቸገሩት፡፡
ጋብሮቮው እንዲህ አላቸው፡-
“የሰፈሬ ህዝብ ሆይ! የእኔን በጣት የምትቆጠር ብርቱካን ከምትለምኑ ለምን ከዋናው ቦታ ሄዳችሁ እንደ እኔ ፋንታችሁን አትወስዱም?”
የሰፈሩ ሰዎችም፤
“ዋናው ቦታ ወዴት ነው?” አሉት፡፡
ጋብሮቮውም፤
“ማዶ ያለው መንደር ብርቱካን በነፃ እየታደለ‘ኮ ነው!”
“አትጠራጠሩ ይልቅ ቶሎ ብላችሁ ሩጡ፡፡ በገፍ እየተሰጠ ነው!”
ህዝቡ ጋብሮቮው ያለውን በማመን ወደተባለው መንደር መሮጥ ጀመሩ፡፡
መንገድ ላይ ያሉ ሌሎች ሰዎች የሚሮጡትን ሰዎች ይጠይቋቸዋል፡፡
“ወዴት ነው የምትሮጡት?”
“እማዶ ካለው መንደር ብርቱካን እንደጉድ በነፃ ይታደላል”
እነዚህኞቹም የተባለውን አምነው መሮጥ ጀመሩ፡፡ ቀስ በቀስ የመንደሩ ህዝብ በጠቅላላ መሮጥ ቀጠሉ፡፡
ጋብሮቮው ዘወር ብሎ ሲመለከት አገር በሙሉ በአንድ አቅጣጫ ሲሮጥ አየ፡፡
ይሄኔ ጋብሮቮ ሆዬ፤
“እንዴ! ይሄ ነገር እውነት ይሆን እንዴ?” ብሎ ወደ ህዝቡ ሩጫውን ቀጠለ፡፡
***
ራሳችን በፈጠርነው ህልም ራሳችን ከመወናበድ ይሰውረን፡፡ ራሳችን የወለድነውን ልጅ የእኛ አይደለም ከማለትም ያድነን፡፡ የራሳችን ውሸት እውነት መስሎን ዳግመኛ ከመሳሳት አምላክ መልካሙን ያሳየን፡፡
“ዕድለ ቢስ ወፍ ማሽላ ሲያሸት ትታወራለች” ይባላል፡፡ አንዳንድ ታጋይ በሚበላበት ሰዓት ከቦታው ይሰናበታል፡፡ አንዳንድ የተማረ ሰው የሱ ሙያ ሲያብብ እሱ ይጠወልጋል፡፡
“ያውና እዛ ማዶ ብርሃን ያድላል
አሁን እኔ ብሄድ አለቀ ይላሉ” እንዳለው ነው ዐይነ ስውሩ ለማኝ፡፡
የተነገረውን ሁሉ በደፈናው የሚያምኑ የዋሃን፤ አሳዛኝ ናቸው! ህዝብ፤ ማንም ሹመኛ፣ ምሁር፣ ጊዜያዊ አለቃ፣ አውቃለሁ ባይ አፈ-ቀላጤ ወዘተ ተናገረ በሚል ሙሉ እምነቱን ዋና ማተብ አድርጐ እንዳፈተተ መጓዝ የለበትም፡፡ ቀልቡን ገዝቶ፣ ነፍሱን አግዝፎ መንቀሳቀስ ይኖርበታል፡፡ ግዙፉን ነገር፣ ማቴሪያሉን ብቻ ሳይሆን መንፈሱን ማሰብ ቁልፍ ነገር ነው፡፡
ስለ ሹመትና ስለ ሃላፊነትም ስናስብ፤
“በግራም ወጣ ወደ ኮርቻ፣ በቀኝም ወጣ ወደ ኮርቻ”፤ እንደተባለው ተረት ውስጠቱን ማስተዋል ይገባናል፡፡
እንደ ጋብሮቮው፤ እኛው በፈጠርነው የጥንቃቄ ኢኮኖሚ ተገዝተን፣ እኛው መልሰን ተታልለን፣ “ለካ ልክ ነበርን፣ ህዝብ ከእኛ ጋር ነው” ብለን መሞኘት የለብንም፡፡
የእኛን የፖለቲካ ወዳጆች፣ አባሎች፣ አጋሮች፣ እንከንና ስህተት፣ ጥበት እና ትምክህተኝነት፣ በቅጡ አስተውለን፣ እነሱም መክረው፣ ዘክረውና አምነው ነው ወደፊት ተጉዘናል ማለት ያለብን፡፡ “እከክልኝ ልከክልህ” እንደማይሰራ ሁሉ፤ “ወገኔ ነው በዚህ እንኳ ይጠቀም” ማለትም በፍፁም አይሰራም!
አገራችንን ጉድ ያደረጋት የመዓት ዝምድና ገመድ ትብትብ ነው፡፡
የማህበረሰብ ግንዛቤያችንን ከፖለቲካና ኢኮኖሚ ግንዛቤ ይልቅ በባህል ዙሪያ ማሰብ ትልቅ ፍሬ አለው፡፡ ለዚህ በዓለም ላይ ያለውን ባህልና የሃይማኖት ጦርነት ስራዬ ብሎ ማስተዋል አንዳች ዋጋ አለው፡፡ ባህል ምን ያህል ዋጋ ቢኖረው ነው ዓለም በጠቅላላው ባህል ያላቸውን ሀገሮች ጦርነት ውስጥ እየዘፈቀች ለጥፋትም እየዳረገቻቸው ያለው፡፡ (ሶርያ፣ ኢራቅ፣ ግብፅ፣ የመን፣ ወዘተ ልብ ይሏል) ብሎ መጠየቅ የአባት ነው! ሃይማኖትስ ምን ያህል የጠብ ጫሪነት ነዳጅ ቢኖረው ነው ሃይማኖት ያላቸው ሀገሮች ለጦርነት እንዲዳረጉ ማገዶ የሚሆነው? ብሎ ማሰብ ብልህነት ነው፡፡
ዘመን እየተለወጠ ሲመጣ ሰዓሊው አዲስ ምስል፣ ገጣሚው አዲስ ምንባብ፣ ደራሲው አዲስ መጽሀፍ፣ ፖለቲከኛው አዲስ ግንዛቤ፣ መንግስት ደግሞ አዲስ ዕቅድ ሊያመጣ ይጠበቃል፡፡ የትላንቱን ካነበብን፣ የትላንቱን መንገድ ከደረትን፣ ሌላው ቀርቶ የትላንቱን ሳቅ ከሳቅን አዲስ ሳቅ ነጠፍን ማለት ነው፡፡ “ብትናገር ያምናውን፣ ብትፈትል አንድ ልቃቂት” የሚለው ተረት የሚነግረን ይሄንኑ ነው፡፡

Read 6269 times