Saturday, 15 August 2015 15:59

ብላ ያለው ተጋግሮ ይጠብቀዋል፤ ተሸከም ያለው ታሥሮ ይጠብቀዋል!

Written by 
Rate this item
(22 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን፤ አንድ ሰው ብዙ ከብቶች ወዳሉበት አንድ በረት ገብቶ አንድ ላም ሰርቆ ሲወጣ፤ አንድ መንገደኛ ሰው ያየዋል፡፡ ያም ሌባ ጣቱን አፉ ላይ አድርጐ “ዝም በል አትንገርብኝ ባክህ!” ይለዋል፡፡
ያም መንገደኛ ለማንም እንደማይናገርበት ራሱን በአዎንታ ነቀነቀለት፡፡
ሌላ ጊዜ ሌባውና መንገደኛው አንድ ሆቴል ቤት ተገናኙ፡፡ መንገደኛው ምግቡን በልቶ ሌባውን ክፈልልኝ አለው፡፡
“ለምንድነው የምከፍለው?” አለው ሌባው፡፡
መንገደኛው፤
“ዋ! የላሟን ነገር ለመንደሩ አለቃ እነግርልሃለሁ!” አለው፡፡
ሌባው ተሽቆጥቁጦ ከፈለ፡፡
ሌላ ቀን አንድ የገበያ አዳራሽ ውስጥ ይገናኛሉ፡፡ መንገደኛው የሚችለውን ዕቃ ወስዶ ሲያበቃ ለባለሱቁ፤
“ያ ሰውዬ ይከፍላል” ብሎ ወደ ሌባው ጠቆመ፡፡
ሌባው አሁንም፤
“ለምንድነው የምከፍለው?” አለ፡፡
መንገደኛውም፤
“ዋ! የላሟን ነገር!” አለው፡፡
ሌባው የግዱን ከፈለ፡፡
በሌላ ቦታ መንገደኛው ሌባውን አገኘውና፤
“ገንዘብ ቸግሮኛልና ስጠኝ?” አለው፡፡
ሌባው፤ “ለምንድን ነው የምሰጥህ?” አለ፡፡
“ዋ! የላሟን ነገር!” ሲል ገና፤ ገንዘብ አውጥቶ ሰጠው፡፡
ሆኖም አሁን ቆም ብሎ ማሰብ ጀመረ፡፡
“ለምን ሄጄ ለመንደሩ አለቃ ላም መስረቄን ነግሬ፣ ይቀጣኝም እንደሆን አልቀጣም?” ብሎ አሰበ፡፡ ወሰነ፡፡
ቀጥ ብሎ ወደ መንደሩ አለቃ ሄደና፤
“ጌታዬ፤ ቸግሮኝ ከመንደሩ በረት አንድ ላም ሰርቄያለሁ፡፡ በህጉ መሠረት የምትቀጣኝን ቅጣኝ” ሲል ጠየቀው፡፡ (“የምታፋፍምብኝን አፋፍምብኝና ልሂድ!” እንዳለው ሰው በቀይ ሽብር ዘመን)
አለቅየውም፤ አውጥቶ አውርዶ፤ “ዋናው ይቅርታ መጠየቅህ ነው” ብሎ በምህረት ሸኘው፡፡
ሌባው በደስታ እየፈነጠዘ ሄደ፡፡
ሌላ ቀን መንገደኛው እንደልማዱ “ገንዘብ አምጣ” አለው፤ ሌባውን፡፡ “አልሰጥም” አለ ሌባው።
“ዋ! የላሟን ነገር!” ሲለው፤
“የፈለከው ቦታ ድረስ!” ብሎት ሄደ፡፡
መንገደኛው ተናዶ፤ ወደ መንደሩ አለቃ እየበረረ ሄደና፤ “እገሌ ላም ሰርቋል” ሲል ተናገረ፡፡
አለቃውም “እሱስ ይቅርታ ጠይቋል፡፡ አንተ ነህ ሌባ!”
“ለምን?” አለ መንገደኛው፡፡
“እስካሁን በልብህ ላሟን ይዘህ የምትዞር አንተ ነህ!” አለው፡፡
*   *   *
በአካል የሠረቀው ሌባ ሲባንን ይኖራል፡፡ በልቡ ስርቆቱን የያዘው የባሰ ሌባ፣ ከሌባ እየተሻረከ ሳይነቃበት ይኖራል፡፡ ይህ የሚሆንበት አገር ለከፍተኛ ጥፋት የተጋለጠ ነው፡፡ ቀና የሚመስለው መንገድ ሁሉ ዕውን ቀና ነወይ? ብሎ መጠየቅ ያባት ነው፡፡ የምንገለገልባቸውን ቃላት እንመርምር።
እንደ “ነፃነት”፣ “አማራጭ” እና “ዕድሎች” ያሉ ቃላት ከሚሰጡት ዕሙናዊ ጥቅም የበለጠ ቀስቃሽ ኃይል አላቸው፡፡ በተግባር ግን ገበያ ቦታ፣ በምርጫ ጊዜ እና በሥራ ቦታ አማራጭ ያለን የሚመስሉን “ሀ” እና “ለ”፤ ሌሎቹን ሆህያት ተትተው የተሰጡን ናቸው፤” ይላል ሮበርት ግሪን፡፡
አንድ መሠረታዊ የገዢዎች መርህ አለ፡-
“የመጨረሻው ምርጥ የማጭበርበሪያ ዘዴ፤ ለባላንጣህ አማራጭ የሰጠኸው ማስመሰል ነው። ያኔ ያንተ ሰለባዎች ጉዳዩን የተቆጣጠሩ እየመሰላቸው አሻንጉሊትህ ይሆናሉ፡፡ ከሁለት እኩይ ነገሮች አንዱን እንዲመርጡ አድርጋቸው፡፡ (Choosing between two evils) ሆኖም ሁለቱም አንተን የሚጠቅሙ እንዲሆኑ ማድረግ ነው ዋናው ጥበብ፡፡” (ሮበርት ግሪን)
አማራጮችን አስፍቶ ያለማየት ድህነት፣ አንዱ የድህነታችን ምንጭ ነው፡፡ ይሄ አንድም ከዕውቀትና አቅም ማነስ፣ አንድም አርቆ የማስተዋል ባህል ከማጣት፣ አንድም ደግሞ በአፍንጫ ሥር ዕይታ ከመወጠር ሊከሰት ይችላል፡፡ ከታጠርንበት አጥር ባሻገር ማየት መልካም ነገር ነው። “ይቺን ያቀድኳትን በስኬት ከተወጣሁ” አመቱን እሰየው ብዬ ጨረስኩ፤” ማለት ሌላ እንዳናይ ሊገድበን የሚችል አካሄድ መሆኑን ልብ እንበል፡፡ በአጭር ርዕይ ታቅበን ጊዜ ያመልጣል፡፡ በጀማ ጉዞ ከጀማው ጋር ከማዝገም በላቀ ንቃተ ህሊና መፈትለክ የሚያሻበት ጊዜ ነው፡፡
አንድ ህፃን ልጅ፤ “ወደፊት ምን ለመሆን ታስባለህ?” ተባለ አሉ ዘንድሮ፡፡
ልጁም፤ “ዲያስፖራ!” አለ፡፡ (ስለዲያስፖራ ስንናገር ትውልድን እናስብ!)
ዳያስፖራ ማለት፤ አንድ ተሰብስቦ፣ በአንድ ቦታ ተቀምጦ የነበረ ህዝብ ወይም ቋንቋ አሊያም ባህል፤ ሲበተን ወይም ወደሌላ ሲሰራጭ የሚሰጠው መጠሪያ ነው፡፡ አይሁዳውያን ከእሥራኤል ውጪ የተበተኑበትንም ሁኔታ የሚያመላክት ነውም ይላሉ፡፡ እንግዲህ ለኢትዮጵያውያንም እንደዚያው ነው፡፡
ኢትዮጵያ የውጪውን ዓለም ኢትዮጵያውያን መሰብሰቧ ደግ ነገር ነው፡፡ አያያዟ ምን ያህል ከኢኮኖሚዋ፣ ከፖለቲካዋ፣ ከዲፕሎማሲዋና ከባህሏ ጋር መስተጋብር ይኖረዋል? ዳያስፖራውያኑስ ምን ያህል ከልባቸው መጥተዋል? ተስፋቸው፣ ምኞታቸው፣ የሀገር ፍቅር ስሜታቸው ምን ያህል የጠለቀ፣ ምን ያህልስ ከጥቅም ባሻገር አገርና ህዝብን ያግዛል? የሚለው የነገ ጥያቄ ነው፡፡ እግረ መንገዳችንን፤ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን፤ “ሰው ሆኖ ካሹት (ከፈተጉት) ጥቅም የማይሰጥ የለም” ያለውን ልብ ማለት ይጠቅማል፡፡
እንግዲህ መንገዱ ረጅም ነው፡፡ ከካሬ ሜትር እስከ ልብ ሜትር የሚያለካካ ነው! ማናቸውም ነገር አልጋ በአልጋ አለመሆኑን መገንዘብ ደግ ነው፡፡ ህጋዊውን፣ ቢሮክራሲያዊውንና ሰዋዊውን መንገድ በቀቢፀ - ተስፋ ለማያይ ሰው፣ ሁነኛና ቀና ብርሃን ሊያስተውልበት የሚችል ሁኔታ አለ። በተወሰነ ደረጃ ግን ሂደቱን ሊያሰናክሉ፣ ሊያቀጭጩና ሊያሟሽሹ የሚችሉ እንከኖች ይኖራሉ? ብሎ አለመጠበቅ ቢያንስ የዋህነት ነው፡፡ “ብላ ያለው ተጋግሮ ይጠብቀዋል፤ ተሸከም ያለው ታሥሮ ይጠብቀዋል” የሚለው ተረት መሠረታዊ፣ አገራዊ ፋይዳ የሚኖረው እዚህ ላይ ነው!  

Read 6235 times